አቶ ተስፋዬ አለና ውልደታቸው ወላይታ ውስጥ ሁንቦ ወረዳ ቦሳ ዋንቼ የተባለች መንደር ውስጥ ነው። በ1957 ዓ.ም የተወለዱት እንግዳችን ለቤተሰባቸው አራተኛ ልጅ ናቸው። እናም ከብቶችን በማገድ እና ቤተሰባቸውን በማገዝ ነበር የልጅነት ጊዜያቸውን በአብዛኛው የሚያሳልፉት። እድሜያቸው ከፍ ሲል ደግሞ በወቅቱ ትምህርት ቤት ባልነበረባት ገጠራማ መንደራቸው አስኳላ ለመግባት ያላቸውን ፍላጎት የተመለከቱ ቤተሰቦቻቸው በአካባቢያቸው ወደሚገኘው የፕሮቴስታንቶች ፀሎት ቤት ያስገቧቸዋል።
አቶ ተስፋዬም ምንም ወንበር ባልነበረው ክፍል ከጓደኞቻቸው ጋር ከቤታቸው በርጩማ እየያዙ በመመላለስ እስከ ሶስተኛ ክፍል ድረስ ተምረዋል። ከሶስተኛ ክፍል በኋላ ግን በፀሎት ቤቱም ቢሆን የሚያስተምር ባለመኖሩ የአንድ ሰዓት ተኩል የእግር መንገድ ተጉዘው በሚያገኙት ኦፓ ዋንቼ የተባለው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምረዋል። በትምህርት ቤት አካባቢ አንድም ሻይ ቤት በወቅቱ ስላልነበረ ጠዋት ቁርስ ተመግበው አመሻሽ ላይ ቤታቸው ሲደርሱ ነበር ተጨማሪ ምግብ የሚያገኙት።
ከስድስተኛ ክፍል በኋላ ግን የበለጠ አስቸጋሪ የሆነው ጊዜ መጣ። ከሰባተኛ ክፍል ጀምሮ ትምህርት ቤት ያለው ወላይታ ሶዶ ከተማ ላይ በመሆኑ ከቤታቸው በየቀኑ የሁለት ሰዓት ተኩል ጉዞ አድርገው ጠዋት በመጀመሪያው ክፍለ ጊዜ መድረስ ከክፍል ሲወጡም እንደዚያው ተመሳሳይ ጉዞ የማድረጋቸው ጉዳይ ግዴታ ሆነ። እናም ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ ተነስተው ከጓደኞቻቸው ጋር ሶዶ ድረስ በመመላለስ ትምህርታቸውን ቀጠሉ።
አቶ ተስፋዬ በወቅቱ እንደሚያስ ታውሱት፤ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ከብዙ ድካም በኋላ ቢሆንም በመንደራቸው ደግሞ መብራት ባለመኖሩ ለጥናት ፈታኝ ነበር። ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በተራ የባህር ዛፍ ቅጠል እየሰበሰቡ በማቃጠል በሚያገኙት ብርሃን ታግዘው ያጠኑ ነበር። 9ኛ እና 10ኛ ክፍሎችን ደግሞ ወላይታ ሶዶ ሊጋባ በየነ ትምህርት ቤት ከቀድሞው መንገድ በተጨማሪነት 20 ደቂቃ እየተጓዙ ተምረዋል።
ይህ ሁሉ የልጅነት ጥንካሬ ትምህርትን ፍለጋ ነበር። ዕውቀት ለመሸመት የተጀመረው ጉዞ ግን 10ኛ ክፍልን ሳያገባድዱ አቋረጡ። የፖሊስነት ሙያ ለመጀመር ማስታወቂያ አይተው የተመዘገቡ የክፍል ጓደኞቻቸውን አይተው እርሳቸውም ፖሊስ ለመሆን ቆርጠው ተነሱ። በ1976 ዓ.ም ከወላይታ ሶዶ ለፖሊስነት ተመዝግበው ወደ ሀዋሳ ከተማ ተላኩ።
ሀዋሳ ላይ አስፈላጊው ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ ደግሞ ለገዳዲ ፖሊስ ማሰልጠኛ ገብተው ለ12 ወራት ስልጠና ወሰዱ። ወዲያውም አዲስ አበባ ተመድበው የትራፊክ ፖሊስ እንዲሆኑ ተመረጡ። በወቅቱ የወር ደመወዛቸው ደግሞ 112 ብር እንደነበር ያስታውሳሉ።
በትራፊክ ፖሊስነት መዲናዋ ላይ ተሽከርካሪዎችን ሲያስተናብሩ ለሁለት አመት የሰሩት አቶ ተስፋዬ፤ በወቅቱ አስመራ ላይ ጦርነት ሲደረግ በግዳጅ እንዲሄዱ ቢጠየቁም አልሄድም አሉ። አልሄድም በማለታቸው በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በሚስጥራዊ ህትመት ውስጥ ተመድበው ጥብቅ ቁጥጥር የሚፈልገው ስራ ላይ በፖሊስነት ተመደቡ። ሚስጥራዊ ህትመት ላይ እየሰሩ ግን ማታ ማታ ያቋረጡትን ትምህርት ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት በመቀጠል እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ተምረዋል።
በወቅቱ ለዩኒቨርሲቲ የሚያበቃ ውጤት ባለማም ጣታቸው ቢያዝኑም ለሁለት ዓመት የቆዩበትን የህትመት ክፍል የፖሊስ ጥበቃ ስራ ለቀው ወደ አዋሽ መልካ ቁንጡሬ ዝውውር ጠይቀው አመሩ። በዚያም ገጃ ዴራ በተባለ ቦታ ከፖሊስነት ሙያቸው በተጨማሪ ለማስታወቂያ ሚኒስቴር የመረብ ኳስ ቡድንን በመቀላቀል በርካታ ጨዋታዎች ላይ ተወዳድረዋል።
ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር የአዋሽ ቆይታ በኋላ ግን የ12ኛ ክፍል ውጤታቸውን ዳግም ለማሻሻል በማሰብ በድጋሚ ወደ አዲስ አበባ ቢመለሱም ውጤቱ አስደሳች አልሆነላቸውም። በጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ እና በተለያዩ ቦታዎች በፖሊስነት ሙያቸው ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ተስፋዬ በወቅቱ ቤተሰብ መስርተው ልጆችም ወልደዋል፡፡
ጊዜ ጊዜን እየወለደ 1989 ዓ.ም ላይ በፖሊስነት ሙያ የደረሱት የዛሬው የሲራራ እንግዳችን ደመወዛቸው 1ሺ300 ብር ቢደርስም ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር አልበቃ አላቸው። እናም በስም ብቻ ወደሚያውቋት ኬንያ አምርተው እጣፈንታቸውን ለመወሰን ቆርጠው ተነሱ። በሞያሌ አድርገው በተሽከርካሪ ከተጓዙ በኋላ ኬንያ ድንበርን ተሻገሩ። ኬንያ ገብተውም በቀጥታ ወደ ናይሮቢ ከተማ ነበር ያመሩት። በወቅቱ አንድም የሚያውቁት ሰው እና ስለከተማዋ አኗኗር ግንዛቤ ስላልነበራቸው ለስምንት ቀናት የተበላሸ የጋራዥ መኪና ውስጥ ለማደር ተገደው እንደነበር አይዘነጉትም።
ሳይደግስ አይጣላም ነውና ነገሩ፤ በፈተና የተጀመረው የናይሮቢው ህይወት በጥቂቱም ቢሆን የሚያስረሳ አጋጣሚ ተፈጠረ። ከአንድ ኢትዮጵያዊ ጋር ተገናኝተው እራሱ ምግብ ቤት ውስጥ እያስተናገዱ አንድ ሺ የኬንያ ሽልንግ ማለትም በወቅቱ መቶ የኢትዮጵያ ብር ሊከፍላቸው ተስማማ። ምግብ እያቀረቡ እና ሰዎችን እያስተናገዱ 15 ቀናት እንደሰሩ ግን ቀጣሪያቸው የደመወዛቸው ጉዳይ ላይ ስምምነት እንዳልተደረገ በማስመሰል የሰሩበትን ሊከለክላቸው ሲዳዳው አለመግባባት ተፈጠረ።
ስለ ሁኔታውን የተረዱ ሌላ ሰው ግን በእጥፍ ደመወዝ ወስደው በምግብ ቤታቸው ቀጠሯቸው። እዚያም ሁለት ወር ሲቆዩ ማታ ማታ መጽሃፍ ቅዱስ ሲያነቡ ቀጣሪያቸው መብራት ይቆጥርብኛል በማለታቸው ሊለያዩ ግድ ሆነ። አሁንም ሌላ ቤት ቀይረው በአጠቃላይ ለስድስት ወራት እንደሰሩ ግን ያተረፉት ገንዘብ እና ድካማቸውን ሲያስተያዩት የማያዋጣ ሆነባቸው። በዚህ ወቅት ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ያገኙትን እየሰሩ ለመኖር ወስነው ሲነሱ አንድ ኢትዮጵያዊ ወዳጃቸው ወደ ኬንያ ምርቶችን እያመላለሱ ቢሰሩ እና በኬንያም እቃዎችን በጥቂቱ ይዘው ቢሄዱ መልካም እንደሆነ ምክር ይሰጣቸዋል።
በጉዳዩ የተስማሙት አቶ ተስፋዬ በኬንያ የበርበሬ እና ሽሮ ምርቶች ተፈላጊ መሆናቸውን በማጤን ከኢትዮጵያ ይዘው ለመመለስ ጉዞ ጀመሩ። 3 ሺ ብር ብቻ ይዘው ወደ ሻሸመኔ ሲያቀኑ የበርበሬ እና የሽሮ ምርቶች ረክሰው አገኟቸው። 250 ኪሎ ግራም በርበሬ እና 50 ኪሎ የተፈጨ ሽሮ በያዙት ገንዘብ ገዝተው ሊመለሱ ሲሉ ግን ለመጓጓዣ የሚሆን ገንዘብ አጠራቸው። አንዲት ኬንያ ውስጥ የሚያውቋቸው ኢትዮጵያዊት ጉዳዩን ሲሰሙ የማስጫኛ እና የትራንስፖርት ወጪውን በብድር ለመሸፈን በመስማማታቸው አቶ ተስፋዬ ምርቱን ይዘው ወደ ናይሮቢ አመሩ።
ከኢትዮጵያ ያስጫኑት ምግብ ናይሮቢ ሲደርስ በ17ሺ ብር ተሸጠ። አቶ ተስፋዬም ብድራቸውን ከፍለው በመጀመሪያ 10ሺ ብር አተረፉ። ሸጠው እንደጨረሱ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ተጨማሪ ምርት ለማምጣት ሲያስቡ ከናይሮቢ ጌጣጌጦችን እና በእንጨት የተሰሩ ቅርጻቅርጾችን ገዝተው ወደ አዲስ አበባ አቀኑ።
በመዲናዋ ዋናው ፖስታ ቤት አካባቢ ጌጣጌጦችን አስረክበው በርበሬ እና የተለያዩ ቅመማቅመሞችን አስጭነው በድጋሚ ወደ ኬንያ አመሩ። እንዲህ እንዲህ እያለ የተጀመረው ንግድ በዓመት እስከ 300 ሺ ብር የሚደርስ ትርፍ የሚያስገኝ ለመሆን በቃ። በአግባቡ የተደራጁት ነጋዴው በጥቂት ወራት ውስጥ እህታቸውን፣ የእህታቸውን ልጅ እና ልጃቸውን ወደ ናይሮቢ በመውሰድ ሁለት የምርት ማቅረቢያ ሱቆችን ከፍተው መስራት ጀመሩ። በአንደኛው ሱቅ የኬንያ ምርቶችን ሲሸጡ በሌላኛው ደግሞ የኢትዮጵያን ምርቶች ይነግዱባቸው ነበር።
ስምንት ቀን መኪና ውስጥ ባደሩባት ናይሮቢም ታዋቂ ነጋዴ በመሆን ስራቸውን ማጧጧፉን ተያያዙት። አለፍ ሲልም ቀበቶ የቆዳ ውጤቶች እና የጸጉር ቅባት እየወሰዱ ይሸጡ ነበር። በሌላ በኩል ወደ አዲስ አበባ የሚመጣው የቅርጻቅርጽ እና ጌጣጌጥ ንግዱ ከፍ እያለ ሲሄድ ደግሞ ፖስታ ቤት አካባቢ አንድ ሱቅ ተከራይተው ሰው ቀጥረው ማሰራት ጀመሩ።
የአዲስ አበባውን ሱቃቸውን ወደ ሁለት አሻገሩ። ከኬንያ እና ኢትዮጵያ ከተሞች የተዘረጋውን የንግድ ስራቸውን እየተመላለሱ በመምራታቸው ብዙ ትርፍ አስገኘላቸው። በአዲስ አበባ ከተከራዩዋቸው ሱቆች መካከል ደግሞ መንግስት የአከራይ ተከራይ አዋጅ ሲያወጣ አንዱን ወደራሳቸው አዙረው መስራት ቀጠሉ።
ከሱቅ ንግዱ በተጓዳኝነት ደግሞ ዶሮ በማርባት፣ ሙዝ ከአርባምንጭ በማስመጣት እና በተለያዩ ንግዶች ላይ በመሰማራት ሲሳተፉ ቆይተዋል። አሁን ላይ ከባለቤታቸው ጋር በመሆን አንድ ሰራተኛ ቀጥረው በአዲስ አበባ ቁርስ ቤት ከፍተው እየሰሩ ይገኛል። በፖስታ ቤት አካባቢውም ቁርስ እና ቡና ለደንበኞቻቸው ያቀርባሉ።
በጎረቤት አገር ያላቸውን ንግድ ደግሞ ወደ ተሻለ ደረጃ አሸጋግረውታል። የኢትዮጵያ ገንዘብ ምንዛሬ አቅም መዳከሙን የተረዱት አቶ ተስፋዬ የኬንያውን ሱቃቸውን ወደ ሆቴልነት በመቀየር አንደ ሙሉ ግቢ ተከራይተው ምግብ ቤት ከፈቱ። በናይሮቢ እንጀራ እና ክትፎ እንዲሁም የተለያዩ የኬንያ ምግቦችን በማቅረብ በየእለቱ ገቢ በመሰበሰብ ላይ ናቸው።
በናይሮቢው የባህል ምግብ ቤት ስድስት ኬንያውያንን እና ስምንት ቤተሰቦቻቸውን እያሰሩ ይገኛል። ለኢትዮጵያውኑ ቤተሰ ቦቻቸው ልዩ ክፍያ ያመቻቹት አቶ ተስፋዬ ለኬንያውያኑ ሰራተኞች ብቻ 40 ሺ ብር ደመወዝ በየወሩ ይከፍላሉ። ቅድስት የባህል ምግብ ቤት ብለው በልጃቸው ስም የሰየሙት የንግድ ቤት በወር 12 ሺ ብር ኪራይ ይከፍሉበታል። ክትፎ እና የተለያዩ ጣፋጭ የኢትዮጵያ ምግቦችም ለታዳሚው በየቀኑ የሚቀርብበት ምግብ ቤት መሆኑን አቶ ተስፋዬ ያስረዳሉ።
አቶ ተስፋዬ አራት ሺ ዶላር በመክፈል ልጃቸውን እና ቀድሞ ወደናይሮቢ የወሰዷ ቸውን ሁለት ዘመዶቻቸውን ወደአሜሪካ ልከዋል። ይህ ለእኔ ትልቅ ሃብት ነው የሚሉት እኚህ የንግድ ሰው ያገኘሁት ይበቃኛል ሳይሉ አሁን ደግሞ ያደጉበት መንደር ላይ ደግሞ 500 የቡና ችግኞችን እያለሙ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ እና ኬንያ ላይ ያላቸው ሃብት ደግሞ በአጠቃላይ 1ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር እንደሚገመት ይገልፃሉ።
ንግድ ማለት ለእርሳቸው አንድ ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ አትርፎ መሸጥ ብቻ ሳይሆን ትርፉንም በተለያዩ መስኮች ላይ አውሎ መገኘት ጭምር ነው። በህይወት ዘመናቸው ከደረሱባቸው ችግሮች ከመሸነፍ ይልቅ ይበልጥ እየበረቱ ማደግን በመልመዳቸው ለዚህ ደርሰዋል። ማንኛውም ሰው ነገውን ብሩህ ለማድረግ ዛሬ ላይ ጠንክሮ ቢሰራ ውጤታማ መሆኑ አይቀርም የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው። እኛም በስራቸው የበለጠ ውጤት እንዲገጥማቸው እየተመኘን ቸር እንሰንብት እንላለን።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2012
ጌትነት ተስፋማርያም