ለመሠረተ ልማት ባይተዋር የሆኑ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ጉዳይ

መንግሥት የከተሞችን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመፍታት የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ቀርፆ እየሠራ ይገኛል። በተለይም የሀገሪቱም ሆነ የአፍሪካ መዲና ብሎም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ያስችል ዘንዳ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በስፋት በመገንባት ለተጠቃሚዎች ማቅረቡ ለብዙዎች እፎይታን ሰጥቷል።

ሆኖም እድል ቀንቷቸው የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን የበቁ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉ ሁሉ አሁንም የመኖሪያ ቤት በተስፋና በጉጉት እየጠበቀ ያለው ነዋሪ ቁጥር በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም። በርካቶች ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ባላገኙበት ሁኔታ የመኖሪያ ቤት ፈላጊው ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።

ለጽሁፌ መግቢያ ያህል ይህን አነሳሁ እንጂ የዛሬው ዋነኛ አጀንዳዬ ግንባታቸው ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች በተላለፉት የጋራ መኖሪያ ቤቶች መንደሮች ያለው ስር የሰደደ የመሠረተ ልማት ችግር ጉዳይ ነው። እርግጥ ነው በተለይም በመሃል አዲስ አበባ የተገነቡት አብዛኞቹ በሚባል ደረጃ ውሃ፤ መብራት፤ መንገድና መሰል ለኑሮ ወሳኝና አንገብጋቢ የሆኑ መሠረተ ልማቶች ተሟልቶላቸው ለነዋሪዎች የተላለፉ ናቸው።

አንዳንዶቹም ነዋሪዎቹ ከገቡ በኋላ በሂደት እየተሟላላቸው የሕዝቡም ጥያቄዎች ምላሽ ያገኙባቸው እንዳሉ እረዳለሁ። ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ ግን በተለይ በከተማዋ ዳርቻዎች የተገነቡና በቅርቡ ወደ ኦሮሚያ ክልል በተከለሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መንደሮች የማስተውለው የመሠረተ ልማት ችግር ነዋሪውን ለከፍተኛ እንግልት እያደረገ ያለበት ሁኔታ ነው።

ለዚህ አብነት አድርጌ የማነሳውም ከስድስት ዓመት በፊት ለተጠቃሚዎች በእጣ የተላለፉትን የኮዬ ፈጬ ሁለት የጋራ መኖሪያ ቤቶችን መንደር ነው። እንደሚታወቀው በወቅቱ በተፈጠረው የፖለቲካ ችግር ምክንያት እጣው ቢወጣም ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በትዕግስት ጠብቆና ከሌለው ጉርሱ ቀንሶ ቆጥቦ ቤት የተሰጠው ባለእድለኛ ቤቱን እጁ ማስገባት የቻለው ከረጅም ጊዜ ቆይታ በኋላ ነው።

ከ50 ሺ በላይ ቤቶችን ባካተተው በዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት ታዲያ ነዋሪዎች ቁልፋቸውን ተረክበው ወደ ቤታቸው ሲገቡ ከነበረባቸው የቤት ኪራይ ጫና ተላቀን እንደማንኛውም ዜጋ በጊዜ ሂደት አስፈላጊ መሠረተ ልማት ተሟልተው የተመቻቸ ኑሮ እንኖራለን በሚል ተስፋ ነበር።

ሆኖም ጊዜ ጊዜን እየወለደ ቢሄድም በዚህ መንደር ውሃ፣ መብራት፣ መንገድ፣ ጤና ጣቢያና ትምህርት ቤት እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎት ሳያገኙ በመቅረታቸው ነዋሪው በብዙ የኑሮ ቀውስ ውስጥ እንዲኖር ተገዷል። እርግጥ ነው ከ50 ለሚልቁት ነዋሪዎች ቁጥር ባይመጥንም አንድ መለስተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገንብቶ በቅርቡ ሥራ ጀምሯል፤ መብራትም ለአንድ ህንፃ ማለትም ከ40 እስከ 60 ለሚደርሱ ቤቶች አንድ ቆጣሪ ተሰጥቶ የሃይል ጥያቄ በጥቂቱ ተመልሷል።

ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነዋሪው ሙሉ ለሙሉ ወደ መኖሪያ ቤቱ እየገባ መሆኑን ተከትሎ የተሰጠው የሃይል መጠን ከተጠቃሚው ብዛት ጋር የማይመጣጠን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አብዛኛውን ጊዜ በጨለማ ለማደርና እንደ ከሰል ባሉ የሃይል አማራጮች ለመጠቀም ተገዷል።

ከሁሉም በላይ ግን አንገብጋቢ የሆነውና ነዋሪውን ያማረረው የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ጉዳይ ነው። በአካባቢው ሰፊ የሆነ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት እንዳለ የሚነገር ቢሆንም፤ በተጨባጭም በአቅራቢያ ባሉ አካባቢዎች ላይ ውሃው ወጥቶ ጥቅም ላይ እንደዋለ ቢታወቅም በእነዚህ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች ግን ውሃ የማግኘት ተስፋቸው የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቶባቸዋል።

ከካሳ ጥያቄና ከሌሎችም ምክንያቶች ጋር ተያይዞ ከሁሉም መሠረተ ልማቶች በባሰ ሁኔታ የውሃ መስመር ዝርጋታው እንዲዘገይ ተደርጎ ነበር፤ እሺ ይህስ ይሁን። ዝርጋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ቤቶቹን ተረክቦ እያስተዳደረ ያለው የመንግሥት አካል መስመሩ እንዲገናኝ አስደርጎ ውሃውን ማስለቀቅ ሲገባው ይህን አለማድረጉ ሕዝቡ በየእለቱ ከፍተኛ ወጪ እንዲያወጣ አስገድዶታል። አንድ ጄሪካን ውሃ (ሊያውም ለመጠጥ አገልግሎት የማይውል) ከ15 እስከ 30 ብር በመግዛት የውሃ ቸርቻሪዎች ሲሳይ ሆኗል።

በሌላ በኩል የኮሪደር ልማቱንና መልሶ ልማቱን ተከትሎ በአካባቢው የነዋሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ይገኛል። ይህንን የሕዝብ ብዛት በሚመጥን ደረጃ የመንገድ መሠረተ ልማት የተገነባበት ሁኔታም የለም። በዚህ የተነሳ ከቱሊዲምቱና ቀድሞ ከተገነባውና ከለማው ኮዬ አንድ ሞልተው ከሚነሱ አውቶብሶችና ታክሲዎች ውጪ መነሻቸው ኮዬ ሁለት የሆነ ምንም አይነት ትራንስፖርት አገልግሎቶች አለመኖራቸውም ሌላው የነዋሪዎቹን ችግር ከድጡ ወደ ማጡ ያደረገባቸው ብል ማገናን አይሆንብኝም። አልፎ አልፎ ውር ውር የሚሉት ታክሲዎችም ቢሆኑ ተቆጣጣሪ የሌላቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንዳሻቸው ታሪፍ የሚጨምሩበት ሁኔታ የሕዝቡን የኢኮኖሚ አቅም እየተፈታተነው ይገኛል።

የሚገርመው ነገር ደግሞ ይህ ፕሮጀክት ግዙፍና ወደፊት የድሬዳዋ ያህል በርካታ የሕዝብ ቁጥር ይሸከማል ተብሎ የተሠራ የመሆኑን ያህል ምንም አይነት መሠረተ ልማት ያለመዘርጋቱ ነው። እንደሚታወቀው ደግሞ እነዚህ ቤቶች የተገነቡት ከከተማ እጅግ ርቀው በመሆናቸው የህክምና አገልግሎት ለማግኘት (በሽታው የቱንም ያህል አጣዳፊ ቢሆን) ረጅም ርቀት መጓዝ የግድ ሆኗል።

እርግጥ ነው ኮዬ አንድ አነስተኛ የመንግሥት ጤና ጣቢያ አለ፤ እሱም ቢሆን ለግዙፉ የኮዬ ሁለት ሕዝብ ቀርቶ ቀድመው ኑሮ ላጣጣሙት የኮዬ አንድ ነዋሪዎች እንኳን በተደራሽነትም፤ በባለሙያና በአቅምም የማይመጥን ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ይህ ግብር ከፋይ የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪ እንደማንኛውም ዜጋ እነዚህን የመሠረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙለት በተደጋጋሚ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አቅርቧል። ይሁንና በየጊዜው የተለያዩ ምክንያቶችን ከመደርደርና ያልተጨበጠ ተስፋ ከመስጠት ባለፈ ወደ ተግባር የተለወጠ ልማት ማየት አልቻለም።

በአንፃሩ ደግሞ ለልማትም ሆነ ለሌሎች መንግሥታዊ ሥራዎች ሕዝቡ በተጠየቀ ቁጥር የቱንም ያህል የኑሮ ጫና ውስጥ ቢሆን የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። በመሆኑም መንግሥት በመሃል ከተሞች ላይ እያከናወነ እንዳለው ሰፊና አበረታች የልማት ሥራ ሁሉ ለመሠረተ ልማት ባይተዋር በሆኑና ከተማ ዳርቻ ለሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪዎች መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ሊገባ ይገባል የሚል እምነት አለኝ!። በተለይ ደግሞ የውሃ ጉዳይ ጊዜ የማይሰጥና አንገብጋቢ ከመሆኑ አንፃር ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ባይ ነኝ!፡

ሜሎዲ ከኳስ ሜዳ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You