አዲስ አበባ፡- መንግስት በ2009 በጀት ዓመት የወጪ ንግዱን ለማበረታት ባወጣው መመሪያ መሰረት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድር አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸውን ቡና አምርተው ወደ ውጭ የሚልኩ የህብረት ስራ ማህበራት፣ አርሶ አደሮችና ላኪዎች አስታወቁ፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ አብዛኞቹ ላኪዎች እዳ ያለባቸው በመሆኑ ተጨማሪ ብድር ለመስጠት አሰራሩ የማይፈቅድለት መሆኑን አመልክቷል፡፡
በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሲዳማ ዞን ሸንበዲኖ ወረዳ ውስጥ ቡና የሚያመርቱና የሚልኩ አርሶ አደሮች፣ የህብረት ስራ ማህበራትና ላኪዎች ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ በተያዘው በጀት ዓመት ከፍተኛ መጠን ያለው የቡና ምርት ቢመረትም በተመረተው ልክ ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችል የብድር አቅርቦት ባለማግኘታቸው ተቸግረዋል፡፡
አርሶ አደር ጉጃ ቤቴራ እንደሚሉት፤ የዘንድሮ ምርት ደግሞ ከወትሮ በተለየ መልኩ ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ምርታቸውን በስፋት ለመሸጥ ቢጓጉም ምርቱን ሰብስበው ወደ ገበያ እስከሚልኩበት ጊዜ ድረስ ለስራ ማስኬጃ የሚሆን ገንዘብ እጥረት ያጋጠማቸው በመሆኑ ምርቱን በጥራት ለመላክ በሚያደርጉት ጥረት እንቅፋት ፈጥሮባቸዋል፡፡ በተለይ ለጉልበት ሰራተኞቻቸው የሚከፍሉት በየሳምንቱ በመሆኑ የገንዘብ እጥረቱ አቅማቸውን እየፈተነ ይገኛል፡፡ የቴላሞና አካባቢው የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር የሂሳብ ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ሆላና በበኩላቸው ማህበራቸው በ2011 ዓ.ም ምርቱ ከፍተኛ በመሆኑ ሦስት ሚሊዮን 250ሺ ኪሎ ግራም ለመሰብሰብ ማቀዱን አመልክተው፤ ይሁንና በዓለም ገበያ መቀዛቀዝ ጋር ተያይዞ የቡና መሸጫ ዋጋ ዝቅተኛ በመሆኑ የማህበሩን አባላት ተስፋ እያስቆረጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለምርት ከሚወጣው ከፍተኛ ወጪ አንፃር ዋጋው የማይመጣጠን በመሆኑ ምርቱን ወደ ገበያ ይዞ ለመውጣት ስጋት ያደረባቸው የገለጹት አቶ ተስፋዬ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ምርቱ ከፍተኛ በመሆኑ በዚያ ልክ አጥቦ ቀሽሮ ለገበያ ለማቅረብ ያስችለው ዘንድ የብድር አቅርቦት ከባንክ ማግኘት አለመቻሉ ተጨማሪ ተግዳሮት የፈጠረበት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቃሬ ካውቻም «የምርቱ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች ውስጥ ያሉ የማጠቢያ ማሽኖች ከወትሮው በተለየ ከሚጠበቀው ሰዓትም በላይ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ማህበራቱም ሆነ ዩኒየኖቹ ያለውን ምርት በሙሉ ማጠብና ማበጠር የሚያስችል መሳሪያ በብቃትና በስፋት የሌላቸው በመሆኑ ምርቱ በወቅቱ ሳይሸጥ እንዳይቀር ስጋት ፈጥሯል» ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚያስፈልጉትን ማሽኖችን ለመግዛት የብድር አቅርቦት ማግኘት አደጋች እንደሆነባቸውም ጠቁመዋል፡፡
የብድር አቅርቦት እጦት ጉዳይ ከአርሶ አደሩ ጀምሮ እስከ ላኪው ድረስ ማነቆ ሆኖ መቆየቱን አቶ ቃሬ ተናግረው፤ በዚህ ረገድ ከዚህ ቀደም የፌዴራል መንግስት ባለሀብቱ ያለበትን ችግር በመገንዘብ የመፍትሄ አቅጣጫ አስቀምጦ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ተፈፃሚ አለመሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
«ከዚህ ቀደም ብሄራዊ ባንክ ከአርሶ አደሩ ጀምሮ ሁሉም የቡና ላኪዎች ብድር እንዲያገኙ የሚያደርግ በአሰራር የፖሊሲ ማሻሻያም ጭምር አድርጎ መፍትሄ አስቀምጧል፡፡ በዚያ መፍትሄ መሰረት የገንዘብ አቅርቦቱ በሚፈለገው ጊዜ ባለመሰጠቱ ከፍተኛ ቅሬታ ፈጥሯል፡፡ ይህ ችግር እንዲፈታ ተደጋገሚ መፃጻፎችና ምልልሶች ተደርገዋል፡፡ እስካሁን ግን ምላሽ ሊሰጥ አልቻለም» በማለት አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮርፖሬት ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ በልሁ ታከለ ባንካቸው ላይ የቀረበውን ቅሬታ አስመልክተው «ባንኩ በመንግስት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ዘርፎች በተለይም ለወጪ ንግድ የብድር አቅርቦት ያመቻቻል፡፡ ይሁንና ሲዳማ ዞን ያሉ አብዛኞቹ የቡና ላኪዎች በ2008 ዓ.ም ከግል ባንኮች የተበደሩትን ገንዘብ ባለመክፈላቸው ምክንያትና ያስያዙት ሀብት እንዳይወረስና ልማቱ እንዳይቋረጥ በሚል በመንግስት በተሰጠ አቅጣጫ ባንካችን እዳቸውን ከፍሏል፤ ይህም እዳ ለባንካችን ሳይከፍሉ ተጨማሪ ብድር ሊሰጣቸው ባለመቻሉ ነው» ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ይህ ማለት ግን ሁሉንም ላኪዎችና አርሶ አደሮች ይመለከታል ማለት እንዳልሆነ አቶ በልሁ አመልክተው፤ በተለይም በቀጥታ ቡና ለመላክ ፈልገው ፈቃድ አውጥተው የመጡ አርሶ አደሮች እንደሌሉ እስካሁንም በዚህ ደረጃ ባንኩ ብድር ተጠይቆ የከለከለበት አግባብ አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡ ከላኪዎቹ ጋር በተያያዘ ግን ከዞኑም ሆነ ከክልሉ መስተዳድር ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች መደረጋቸውን አምነው በቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫ ይሰጣል የሚል እምነት እንዳላቸው አስገንዝበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 19/2011
በማህሌት አብዱል