ቅድመ -ታሪክ
በትምህርት የሚያምኑት ወላጆች የልጆቻቸውን መልካምነት ሲመኙ ኖረዋል:: እነሱ የንግድ ሰዎች ናቸው፡፡ ህይወታቸውን ለመምራት የሚያዋጣቸውን ሲሞክሩ ቆይተዋል፡፡ ሁሌም ልጆቻቸው ከእነሱ በተሻለ እንዲገኙ ይሻሉ፡: ይህ ይሆን ዘንድም የአቅማቸውን ሲያደርጉላቸው ኖረዋል፡፡ የዘወትር ምኞታቸው የልጆቻቸው ተምሮ መለወጥ ነውና የፍላጎታቸውን ለመሙላት ወደ ኋላ ብለው አያውቁም፡፡
መሀመድ ኑሩ ከበርካታዎቹ የቤቱ ልጆች መሀል አንደኛው ነው፡፡ እንደ እድሜ እኩዮቹ ትምህርት ቤት ውሎ ሲመለስ ወላጆቹ በፍቅር ይቀበሉታል፡፡ስለነገው እያሰቡም የፍላጎቱን ያሟላሉ፡፡ በየአመቱ ከክፍል ተዘዋውሮ ለውጥ ባሳየ ጊዜም የተስፋና ምኞታቸውን ስኬት እያለሙ ስለወደፊት ማንነቱ ያለመታከት ይመክሩታል፡፡ ይህ ልጅ ማለት ለእነሱ አብሮ የኖረ ፍላጎታቸውን የሚያሳካና ለታናናሾቹ መልካም ማሳያ የሚሆን ነው፡፡
መሀመድ የቤተሰቦቹን የተለየ ፍላጎትና በእሱ ላይ ያሳደሩትን እምነት የሚውቀው ገና የልጅነት ዕድሜው ላይ ሆኖ ነው፡፡ ትምህርቱን በአግባቡ ተምሮ እስከ ስምንተኛ ክፍል ሲደርስም በተለየ ጥረትና ፍላጎት ነበር፡፡የአስራ ሁለተኛ ክፍልን የማትሪክ ፈተና ሲወስድ ደግሞ የወላጆቹን ሀሳብ እንደሚሞላ እርግጠኛ ሆነ፡፡
ጊዜው ደርሶ የፈተና ውጤቱ ከእጁ ሲገባ ግን እውነታውን እንኳን ለሌላው ለራሱ የሚነግረው አልሆነም፡፡በጉጉት ሲጠብቀው የቆየው ውጤት እንደታሰበው አልተገኘም፡፡ ይህኔ የነበረው ተስፋ የመከነ ያህል ተሰማው:: ሌሎች አማራጮችን ከመሞከርም በዝምታ መቆዘምን መረጠ፡፡
ሰፈር መዋል ሲጀምር አይምሮው ብዙ ማሰብ ያዘ፡፡ከመማር ይልቅ ሰርቶ ማደር ላይ አተኩሮም ይበጀኛል ያለውን ሞከረ:: ሰርቶ መግባቱ ግን እንደቀድሞው የሚመች አልነበረም፡፡የትናንትናው ተማሪ ዛሬ በስራ ላይ ሲገኝ መሰላቸትን አበዛ፡፡ይህ ስሜት ደግሞ እምብዛም የሚያራምደው አልሆነም፡፡ የጀመረውን አቋርጦ ሰፈር ለመዋል ወሰነ፡፡
ጥቂት ቆይቶ የልጃቸውን ከመንደር ተቀምጦ መዋል ያጤኑት አባት ከእሳቸው የንግድ ሱቅ እንዲውል ዕድል ሰጡት፡፡ መሀመድ ለጊዜው መንፈሱ ተረጋግቶ የስራ ትጋቱን አሳየ፡፡ ከባህል ልብስ መሸጫው የሚመጡ ደንበኞችን እያስተናገደም ገበያውን ለመምራት ሞከረ፡፡ ይህ ጉዞ ግን ረጅም አላራመደውም፡፡የራሱን ለመስራት እንደሚፈልግ ሰበብ ፈጥሮ ከአባቱ እይታ ራቀ::
ከቀናት በኋላ የነጋዴው ልጅ መሀመድ እንዳሰበው ሆኖ የራሱን ንግድ ስለመጀመሩ ተሰማ፡፡የልደት ሻማዎችን እያቀለጠ የጀመረው ሽያጭም ትርፍ እንዳስገኘለት በራሱ አንደበት መሰከረ፡፡ የንግድ ስራው ለጥቂት ጊዜያት እንዳዋጣው ሆኖ ዘለቀ፡፡ የየእለቱን እየሸጠም ለነገው ጥሪት ለመያዝ ጥረቱን ቀጠለ፡፡
እያደር ግን የታሰበው ሁሉ ባልሆነ አቅጣጫ መጓዝ ጀመረ፡፡‹‹ያዋጣኛል›› ሲል የጀመረው የሻማ ንግድም ከኪሳራ ጥሎት ኪሱ ባዶ ሆነ፡፡ይህኔ የመሀመድ የአፍላነት ዕድሜ ፈተና ሆነበት፡፡ ከትዕግስት ይልቅ ንዴትን የመረጠው ወጣት በብስጭት ውሎ ማደርን ልምዱ አደረገ፡፡
ተመልሶ ከመንደር መዋል የጀመረው መሀመድ ገንዘብ መያዝ የለመደ እጁ ባዶ ቢሆንበት ተጨነቀ፡፡ለዚህ መፍትሄም ጉልበቱን ተጠቅሞ ኪሱን ጦም ላለማሳደር ወሰነ፡፡ለዚህ ሀሳቡ ብቸኛ አማራጭ ተሸክሞ ማደር ሆነና ከሌሎች ሰርቶ አዳሪዎች ጋር እየተጋፋ መንደሩ ካለ መጋዘን መዋልን ለመደ ፡፡ይህኛው ስራ ከሌሎች ሁሉ ተሽሎ ለወራት እንዳዋጣው ዘለቀ፡፡
አሁን የመሀመድ ውሎ ከብዙዎች ያገናኘዋል፡፡ከመንደር መገኘቱም ወጪ ወራጁን ጠንቅቆ እንዲያውቅና ማንነታቸውን እንዲለይ እያስቻለው ነው፡፡በአካባቢው እነማን ሰርተው እንደሚገቡ የትኞቹ ተቀምጠው እንደሚውሉ ካወቀ ቆይቷል፡፡ ይህ እውነታ ደግሞ በቀጣይ ላቀደው ዓላማ አስፈላጊና ወሳኝ የሚባል እየሆነ ነው፡፡
የመሀመድ ባልንጀሮች
ውሎው በመንደር ከሆነ ወዲህ በርካታ ባልንጀሮችን ያፈራው መሀመድ የብዙዎቹን ማንነትና የገቢ ምንጫቸውን ሚስጥር ተረድቷል ፡፡ይህን ካወቀ ወዲህም ራሱን በእነሱ ቦታ ተክቶ በምኞት ሲብሰለሰል ከርሟል፡ ፡ገንዘብን ለማግኘት ዘዴው ቀላል መሆኑን ሲያውቅም በሀሳባቸው ተስማምቶ ከተገኘው ሊካፈል ከወሰነ ቆይቷል፡፡
መሀመድ የሚያስበውን ለመፈጸም ከራሱ ተስማምቶ የባልንጀሮቹን ይሁንታ መጠበቅ ይዟል፡፡ በእሱ ዕምነት ያለምንም ውጣውረድ መንገደኞችን ጠብቆ ዝርፊያ መፈጸም ቀላል የሚባል ነው፡፡ይህን ማድረግ ከለመደም እንደሌሎች ሁሉ ኪሱ ባዶ አይሆንም፡፡ያሻውን መንዝሮ የፈለገውን ማድረግ ይቻለዋል፡፡
አንድ ቀን መሀመድ ከጓደኛው ጋር ስታድየም አካባቢ ተገኘ፡፡ የዛንቀን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከናይጄሪያ አቻው ጋር ኳስ የሚገጥምበት በመሆኑ ስፍራው ተጨናንቆ ነበር፡፡ይህን ግርግር ያስተዋለው የመሀመድ ጓደኛ ዓይኖቹን ባሻገር ልኮ ከአንድ ሰው ላይ አተኮረ፡፡
ሰውዬው ወደ ታክሲ ለመግባት እየተጋፋ ስለነበር ኪሱን መጠበቅ አልቻለም:: ይህን ያስተዋለው ወጣት እንደምንም ተሽሎክልኮ አጠገቡ ደረሰና ሞባይሉን ከኪሱ አወጣ፡፡ ወዲያው ግን ድርጊቱን ባስተዋሉ ብርቱዎች ተይዞ ወከባና ዱላ ይወርድበት ጀመር:: በዚህ ልምዱ የነበረው መንታፊ ግን እንደምንም ዱላውን ተቋቁሞ ስልኩን እንደያዘ ከእጃቸው አመለጠ፡፡አባራሪዎቹ መንታፊው ቢያመልጣቸው አብሮት የነበረውን መሀመድን ይዘው ለጣቢያ አስረከቡ፡፡
በዝርፊያ ትብብር ከፖሊስ ጣቢያ ውሎ ያደረው መሀመድ በዋስ ተለቆ እስኪወጣ ከአዲስ ባልንጀሮች ጋር ተግባባ፡፡ ትውውቃቸው ስር ሰዶም ከተፈታ በኋላ ሊፈጽሙት ስላቀዱት ጉዳይ እየነገሩ አማከሩት፡፡ቀድሞም ይፈልገው የነበረ ሀሳብ ነበርና በሚሉት ሁሉ ተስማምቶ ከእነሱ ጋር ሊያብር ወሰነ ፡፡
ከእስር መፈታት
መሀመድ ከቀናት በኋላ በዋስ ተለቆ ወደ ቀድሞ ህይወቱ ተመልሷል፡፡አሁን ቆየት ብለው ከተቀላቀሉትና እስር ቤት ካወቃቸው ባልንጀሮቹ ተገናኝቶ ያሰቡትን ለመተግበር እየተወያዩ ነው፡፡ዕቅዳቸውን ለመፈጸም አብሯቸው በተጓዘበት የመጀመሪያው ቀንም በለስ ቀንቶት ከጥቅሙ ተጋርቷል፡፡ ይህ ብቻ ግን አልበቃውም፡፡ሲነጋጋ ከቤት እየወጣና ከመንገድ ያገኛቸውን እግረኞች አንገት እያነቀ የያዙትን መንጠቅ ልምዱ አድርጓል፡፡
መሀመድና ጓደኞቹ ወፍ ሳይንጫጫ ከቤት ወጥተው በአሳቻ ቦታ ላይ መቆምን የዘወትር ተግባራቸው አድርገዋል፡፡በዚህ ስፍራ በድንገት የደረሰ መንገደኛ ቢኖር ከእጃቸው አያመልጥም:: ዝርፊውን ጠርጥሮ ሊታገላቸው ከሞከረ ደግሞ በያዙት ጩቤ ካሻቸው ቦታ ወግተው የያዘውን ይዘርፉታል፡፡
ልደታ ክፍለ ከተማ የሞላ ማሩ አካባቢ ነዋሪዎች በእነዚህ ዘራፊዎች ድርጊት ስጋት ከገባው ቆይቷል፡፡ማልደው ወደ መናሀሪያ መንገድ የጀመሩና ጉዳይ ኖሯቸው ሳይነጋ የወጡ በርካቶች በነመሀመድ ወጥመድ ተጠልፈው ወድቀዋል፡፡አብዛኞቹ ህይወታቸው ስለተረፈ ብቻ ነገሩን ትተውታል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ከህግ ፊት ቀርበው ‹‹አቤት›› ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
ጨለማ ለባሾቹ ዘራፊዎች ከድርጊታቸው አልታቀቡም ፡፡ወፍ ሳይንጫጫ ከቤት ወጥተው ካሰቡት ስፍራ ያደባሉ፡፡እግር የጣለውን ይዘው፣ ከኪስ ከጉያው ይገባሉ:: ሁሌም ማንነታቸው እንዳይለይ በእጅጉ መጠንቀቅ ልምዳቸው ነው፡፡መረጃ ተገኝቶ ምስክር እንዳይጠቁምም እንደሁኔታው ፊታቸውን ይሸፍናሉ፡፡
ከዝርፊያው በኋላ ገንዘቡን እኩል ተካፍለው የሚሸጠውን ለደንበኞቻቸው ያስረክባሉ፡፡ ሁሌም ሞባይል የሚገዛቸው አንድ ነጋዴ ደግሞ በየቀኑ ከእነሱ እየተረከበ የድርሻውን ይወስዳል፡፡ሁሌም ከማለዳው ጉዳይ በኋላ የያዙትን ይዘው ከጫት ቤት ሲቅሙ ይውላሉ፡፡ ተከታዩን ዕቅድ እየነደፉም ከመሸታ ቤት ያመሻሉ፡፡
ሲነጋጋ በስልክ ተቀጣጥረው፣ በፉጨት ተጠራርተው ይገናኛሉ፡፡ ከመንገዱ የቀደመውን እንደ ከብት ዘርጥጠው የታገላቸውን በጅዶ ዘርረው ሁለመናውን ይረከባሉ፡፡በሌላ ቀን ቦታ ቀይረውና ጥቂት አዘናግተው ከድርጊታቸው ይገኛሉ፡፡
አንድ ቀን ምሽት በጊዜ ተገናኝተው ስለነገው ውሏቸው ሲመክሩ አመሹ፡፡የዛን ቀን በድንገት የተቀላቀላቸው የሰፈራቸው ልጅ አብሯቸው ሲዝናና ቆይቷል፡፡ምሽቱ ገፍቶ ሌቱ ሲጋመስ ግን ከእሱ ጋር መቀጠሉን ያልፈለጉት ሶስቱ በዘዴ እንግዳውን ሸኝተው ዕቅዳቸውን መንደፍ ያዙ፡፡ ካስቀዱት መጠጥ እየተጎነጩም ውድቅቱን አጋምሰው ከንጋት ዳርቻ ተቃረቡ፡፡
የካቲት 27 ቀን 2006 ዓ.ም ንጋት
ሽማግሌው አባት ከእኩለሌሊት በኋላ ዕንቅልፍ በዓይናቸው አልዞረም፡፡ በነጋ አልነጋ ጉጉት ሰዓታቸውን ሲያዩ ቆይተዋል:: አስር ተኩል ሲሆን ግን ፊታቸውን ታጥበው ልብሳቸውን መልበስ ጀመሩ፡፡ ሁሌም ማልደው ቤተክርሰቲያን መሳለም ልምዳቸው ቢሆንም ዛሬ ከወትሮው በተለየ መቅደም የፈለጉ ይመስላል፡፡ ዕለተ መድሀኒአለም ነውና ከመቅደሱ ገብተው፣ ከቅዳሴው ተካፍለው ለመመለስ ጋቢያቸውን ለብሰው ተዘጋጅተዋል::
ከቤታቸው ወጥተው በእግራቸው መንገድ ሲጀምሩ ከጎናቸው ማንም አልነበረም:: የአካባቢው ጭርታ ቢያይልባቸውም ከዚህ ቀድሞ የሚወጣ አለመኖሩን ገምተው ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡ አሁንም መንገዱን እያቋረጡ ይብሰለሰላሉ፡፡ ከቅዳሴ መልስ የሚከውኑትን እያቀዱም በሀሳብ ይባዝናሉ፡፡
ጥቂት እርምጃዎችን እንዳለፉ ካሰቡት እንደሚገኙ አውቀዋል፡፡ ቅዳሴ ሳይጀመር ለመድረስ ደግሞ ያለዕረፍት መራመድ ይኖርባቸዋል፡፡ይህ ይሆን ዘንድ ከእግራቸው ነጠቅ እያሉ መንገዳቸውን ቀጥለዋል፡፡‹አሁንም ከቤት ይዘውት የወጡት ሀሳብ ከእሳቸው ጋር ነው፡፡ ለሁሉም ከቤት ሲመለሱ እንዳሰቡት ይሆናሉ፡፡ አሁን ግን ከቤተክርሰቲያኑ አጸድ ለመድረስ መፍጠን አለባቸው፡፡
ሽማግሌው አባት ከመንደራቸው ርቀው ወደ መሀል ሲቃረቡ ከንጋቱ አስራ አንድ ሰዓት እየሆነ ነበር፡፡ ዋናውን መንገድ አልፈው አቋራጩን ያዙ፡፡ይህ ቦታ ጭር ያለና ጨለማ የሚባል ነው፡፡ እሳቸው ግን በመንገዱ ለአመታት ተመላልሰውበታል፡፡ጥቂት አለፍ ብለው ደግሞ ከቤተክርስቲያኑ ግቢ ይደርሳሉ::
ይህ ከመሆኑ በፊት ሶስት ሰዎች ወደ እሳቸው ሲመጡ አስተዋሉ፡፡ጊዜው እየነጋ መሆኑን ገምተውም ወደ ጉዳያቸው የሚሄዱ መንገደኞች መሆናቸውን አሰቡ፡፡ ሰዎቹ ሽማግሌውን መከተል ከጀመሩ ቆይተዋል:: አጠገባቸው ሲደርሱ ግን አልፈዋቸው እንደ ሚሄድ አዘናግተው መለስ ብለው አንገታ ቸውን በማነቅ ከመሬት ጣሏቸው፡፡ሽማግሌው በድንጋጤ እንደመንገዳገድ ብለው በቁማቸው ተዘረሩ፡፡
እነ መሀመድ የሽማግሌውን መውደቅ እንዳዩ ለሁለት መሬት ለመሬት እየጎተቱ ከአንድ ጥግ ወሰዷቸው፡፡ከኪስ ከጉያቸው ገብተውም ገንዘብና ሞባይላቸውን ወሰዱ፡፡ኪሳቸውን በርብረው ባዶ መሆኑን ሲያውቁ ከወደቁበት ትተዋቸው ከአካባቢው ተሰወሩ፡፡
የማለዳዋ ጸሀይ ደምቃ መውጣት ስትጀምር ለመንገዱ የቀደሙ ሰዎች የሽማግሌውን መውደቅ አስተውለው ቀረቧቸው፡፡ ተጠግተውም በግልጽ የሚስተዋል ቁስልና ጉዳት ያለመኖሩን አረጋገጡ፡፡ሽማግሌው በልማደኞቹ ዘራፊዎች ‹‹ሀንግ›› በሚባለው ስልት መጎዳታቸውን ሲያውቁም ትንፋሻቸውን አዳምጠው በፍጥነት ወደ ህክምና አደረሷቸው::
ከዝርፊያው መልስ
እነ መሀመድ ከሽማግሌው በዝርፊያ ያገኙትን ሞባይልና 575 ብር ጥሬ ገንዘብ በእጃቸው አስገብተዋል፡፡ እንደተለመደው ሞባይሉን ለደንበኛቸው አድርሰውም በተካ ፈሉት ገንዘብ ቁርስ እየበሉ በቀጣዩ የዝርፊያ እቅድ ላይ መነጋገር ጀምረዋል:: ሁሌም ቢሆን እንደሽማግሌው በቀላሉ የሚረታ ተዘራፊ ሲገጥማቸው ይደሰታሉ፡፡በለመዱት ዘዴ አንገቱን አንቀው ያሻቸውን ለመፈጸም ስራው ይቀልላቸዋል፡፡
የፖሊስ ምርመራ
ስለተፈጸመው የዝርፊያ ወንጀል ጥቆማ ደርሶት ከሆስፒታል የተገኘው ፖሊስ ሽማግሌውን በህይወት አግኝቶ ቃላቸውን ተቀብሏል፡፡በወቅቱ በከፋ ጉዳት መሀል ሆነው አጥቂዎቹን በህግ ለመፋረድ የተማጸኑት ተጎጂ ውሎ አድሮ አቅማቸው ተዳከመ፡፡ከቀናት በኋላም ህመማቸው ጠንቶ ህይወታቸው ማለፉ ታወቀ፡፡ፖሊስ ይህን ካረጋገጠ በኋላ የድርጊቱን ፈጻሚዎች በቁጥጥር ስር ለማዋል ሌት ተቀን ባዘነ፡፡በመርማሪ ሳጂን መስፍን ሀይለሚካኤል የሚመራው ቡድንም ጥቆማና መረጃዎች በደረሱት አካባቢዎች እየተገኘ የወንጀለኞቹን ዱካ ማሰስና ማስረጃዎቹን ማነፍነፍ ያዘ፡፡
ከቀናት ያለሰለሰ ጥረት በኋላ ፖሊስ ከተፈላጊዎቹ መሀል መሀመድን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራውን ቀጠለ፡፡ በፋይል ቁጥር 705/06 በተከፈተው የምርመራ መዝገብ ከተጠርጣሪው የተወሰደው ቃል ተዘጋጀ፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2012
መልካምስራ አፈወርቅ