ተወልደው ያደጉት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሰላሌ አካባቢ ነው፡፡ ከገብረ ጉራች አምስት ኪሎ ሜትር ወጣ ብላ በምትገኘው ቄሴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ተምረዋል፡፡ ስዩም ደምሰው በሚባል አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 7ኛ እና 8ኛ እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ገብረ ጉራች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል:: የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪውን በሶሲዮሎጂ ትምህርት መስክ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀብለዋል፡፡ ኔዘርላንድ አገር ከሚገኘው ዩኒቨርሲቲ በዚያው በሶሲዮሎጂ የትምህርት መስክ የዶክትሬት ዲግሪያውን አግኝተዋል፡
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ለስድስት ዓመታት በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን በዓለም አቀፉ የእንሳሰት ልማት ጥናት ተቋም በተመራማሪነትና በዕጩ ዶክተርነት ተቀጥረውም ሰርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የምሥራቅ አፍሪካ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት የሆኑት እኚሁ ግለሰብ ታዲያ ከለውጡ ወዲህ በአገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ በሚሰጧቸው ገንቢ ሃሳቦች ዕውቅናን አግኝተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከዛሬው እንግዳችን ከዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ ጋር በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረገውን ቃለምልልስ እንደሚከተለው ይዞ ቀርቧል፡፡መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ዶክትሬት ድረስ ያጠኑት ማህበራዊ ሳይንስ ጥናት ዘርፍ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከፖለቲከኞች እኩል ሃሳብ ሲሰጡ እንመለከታልን:: ዕድሉን ስላገኙ ነው? ወይስ የተለየ ምክንያት ስላለዎት ነው?
ዶክተር ብርሃኑ፡- እኔ ያጠናሁት ማህበራዊ ሳይንስ ከፖለቲካ ጉዳይ የወጣ አይደለም፡፡ የማህበረሰብ ጥናት በአጠቃላይ ማህበረሰብን የምንረዳበት መንገድን የምናጠናበት ሳይንስ ነው፡፡ የእኛ ሕዝብ ደግሞ ኑሮው የተመሰረተው በግብርና ላይ እንደመሆኑ ሁሉም ነገር የሚቃኘው በፖለቲካ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በፖለቲካ ላይ ሃሳብ ለመስጠት የፓርቲ ውግንና የግድ ያስፈልጋል ብዬ አላምንም፡፡ በሃሳብ ደረጃ የምረዳውንና የሚገባኝን ነገር ከመናገር ወደኋላ አልልም:: በእርግጥ የሰራሁት በአብዛኛው በመምህርነትና ምርምር ዘርፍ ነው፡፡ ግን እኛ አገር ላይ ያለው የፖለቲካ ትኩሳት፥ መካረሩ በእኛም ሙያ የሚገለፅ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚያ የተለየ ብዙም የወጣ የፖለቲካ ተሳትፎ የለኝም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ፖለቲካውን በንቃት የሚከታተሉ ከመሆንዎት አንፃር ለውጡ ምን ጥሩ ጎኖችን ይዞ መጥቷል ይላሉ? እንደስጋት የሚያዩት ነገር ካለም ይጥቀሱልን?
ዶክተር ብርሃኑ፡- እኛ አገር ውስጥ የመጣው ለውጥ መሠረታዊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህንንም ስል ከዚህ ቀደም ለውጥ ስላልነበረ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በለውጥ ነው የምትታወቀው፡፡ የነበሩት መንግሥታት ሁሉም በሚባል ደረጃ በጉልበት ወይም በተፈጥሮ የተነቀሉ ናቸው፡፡ አብዮት የተለመደበት አገር ነው፡፡ ታሪኩን ማየት ካስፈለገም እንደምታውቂው ልጅ እያሱም ወደ ሥልጣን የመጣው አፄ ምኒልክ ስለሞቱ ነው፤ አፄ ኃይለሥላሴም የነገሱት ልጅ እያሱን አስወግደው ነው፤ መንግሥቱም ወደ ሥልጣን የመጣው ንጉሱን ገድሎ ነው፤ በተመሳሳይ መለስ መንግሥቱን በጦር ኃይል ነቅሎ ሥልጣን ያዘ፤ እሱ ደግሞ በተፈጥሮ ሞት ሥልጣኑን ለኃይለማርያም አስረከበ፡፡ የአሁኑ ለውጥ ግን የተለየ ነው፤ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉንም መንቀል ሳይሆን በተቻለ መጠን ያለውን ጥሩ ነገር አስጠብቆ ወደፊት ለመሄድ የተሞከረበት ነው ባይ ነኝ፡፡
ስለዚህ በተፈጥሮም ሆነ በሰው መንቀል አለ ማለት ነው፡፡ በታሪካችን የመጀመሪያው በሚባል ደረጃ ትክክለኛ ተሃድሶ እንደመጣም አምናለሁ፡፡ የቀደሙት መሪዎች አለመታደል ሆኖ ሳይጨባበጡ ነው ሥልጣን የተለዋወጡት፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ግን በታሪካችን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ተጨባብጠው ነው ሥልጣን የተረካከቡት፡፡ ይህም በፖለቲካ ጉዞ ውስጥ ወሳኝ የሆነ መሠረተ ድንጋይ እንደማስቀመጥ ነው፡፡ የዚህ ለውጥ መሠረት የፈለገ ቢሆንም በሕዝብ እይታ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ ነው፡፡
ይህ ማለት ግን ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ነው ማለት አይደለም፡፡ በአብዮት ሥልጣን ስትይዢ ነቅለሽ ሞሉ ለሙሉ አዲስ ሥርዓት ነው የምታመጪው፡፡ አገሪቷንም ዜሮ ላይ አውርደሽ ከዜሮ ትጀምሪያለሽ ማለት ነው፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ በሀገር ደረጃ ሁሉም ነገር ከዜሮ ስለሚጀመር ኪሳራ ነው የሚሆነው:: በመሪዎች ዓይን ግን ካየሽ የመጣውን መሪ ተግዳሮት የሚሆንበት ነገር አይኖርም መንገዱ አልጋ በአልጋ ነው የሚሆንለት፡፡ በተሃድሶ መልኩ ሥልጣን ስትይዢ የሚሻኮቱት ኃይሎች ጎን ለጎን ሆነው ሥልጣን የሚቀባበሉ በመሆኑ ሀገሪቷን ከዜሮ ሳይሆን ካለበት ነው የምታስቀጥይው:: ስለዚህ የሚሻኮቱት ኃይሎች አንዱ ሌላው የመጎተት፥ በሌላኛው ላይ እንቅፋት የመፍጠር ሁኔታ አብሮ ይመጣል ማለት ነው፡፡
አሁን ኢትዮጵያን እያጋጠማት ያለው ችግር እነዚህ ሁለት ቡድኖች ጎን ለጎን እየተፎካከሩ መሆናቸው ነው፡፡ የቀድሞው አመራር ወደሥልጣን ተመልሶ የመምጣት ዕድል ባይኖረው አሻጥር ለመስራት ወይም የተካውን መሪ ደካማ መስሎ እንዲታይ ጥረት ያደርጋል፡፡ ለውጡ ሲመጣም የተከመረና ያደረ የቤት ሥራ ነበር፡፡ ዕዳውን ዜሮ አድርጎ ሰርዞ አይደለም ሥልጣኑን የተረከበው፡፡ ከፍተኛ ውጥረትን የወረሰ አመራር ነው፡፡ ስለዚህ ካለፈው መሪ የወረሳቸው ችግሮችን ለመፍታት ጥረት የሚያደርገበት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ እናም ይሄ አመራር አሁንም ከምንም በላይ ፈተና የሚያጋጥምበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው፡፡ ሕዝቡ እንደዚያ በሆይታና በደስታ ቢቀበለውም እነዚህ ችግሮች ተመልሰው እንደሚመጡ ግን መረሳት አልነበረበትም፡፡ ምክንያቱም የተወረሰው ችግር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ አልፎ አልፎ አሁንም የሚያስፈሩ የሚያስደነገጡ ነገሮች አሉ፡፡
ስለዚህ ሕዝቡ አሁንም ካለው አመራር ጋር መቆም አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ አመራሮች የወረሱት ችግር ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ መረዳት ይገባዋል፡፡ መረዳት ብቻ ሳይሆን መርዳትም ከሕዝቡ ይጠበቃል:: ችግሩ እንዲፈታ መረባረብ አለበት፡፡ አለዚያ በአንድ ጀምበር ሁሉ ነገር ይፈታል ብሎ የሚጠብቅ ከሆነ አንዳንድ ጊዜ መንገራገጮች ሲታዩ ልንወድቅ ነው የሚል ነገር ይሰማል:: ግን እንደዚያ መሆን የለበትም፡፡ እናም በአጠቃላይ እኔ ስለለውጡ ቀና አስተሳሰብ ነው ያለኝ፡፡
አዲስዘመን፡- ኢህአዴግ በአሁኑ ወቅት ከግንባርነት ወደ ውህደት ለመምጣት ዝግጅት እያደረገ ነው፤ ይህንን ጉዳይ እንዴት ያዩታል?
ዶክተር ብርሃኑ፡- ኢህአዴግ አራቱ ድርጅቶች አንድ ላይ መጥተው የፈጠሩት ግንባር ነው፡፡ አሁን ደግሞ ሊመሰርቱት የፈለጉት ፓርቲ ነው፡፡ በእኔ እምነት ይሄ አደረጃጀት ከግንባር የተሻለ ጥንቅር አለው ተብሎ የታመነ ይመስለኛል፡፡ እኔ ግን አንዳንድ ጊዜ ውህደት የሚለውን ቃል መጠቀም ላይ እቆጠባለሁ፡፡ እንደሚመስለኝ ውህደት የሚለው ነገር እዚህ አገር ውስጥ የሚፈጥረው ስዕል ጥሩ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ የሆነ ፌዴራሊዝም የምትከተል አገር ነች፡፡ ይሄ ማለት እያንዳንዱ ብሔር የራሱን ማንነት ይዞ የጋራ አገር ለመፍጠር የተስማሙበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን ችለው የራሳቸው ቋንቋ አላቸው፡፡ ያ መብት ተከብሮላቸው ከዚያ ደግሞ ይሰማሙና አንድ አገር ይመሰርታሉ፡፡
አሁን ግን ውህደት ስትፈጥሪ ከዚያ መዋቅር ጋር የመሄድ ዕድሉ በጣም ዝቅተኛ ነው የሚሆነው፡፡ ምንም እንኳ ኢትዮጵያን ለማዋሃድ የተደረገው ጥረት ተሳክቶ ባያውቅም አንዳንድ ጊዜ ሕዝብ ላይ ወይም ግለሰቦች ላይ የሚፈጥረው ነገር ወደ ድሮ ኢትዮጵያ እንመለሳለን የሚል ስጋት ነው፡፡ በእኔ እምነት ዳግመኛ ወደዚያ ሥርዓት መሄድ ይቻላል ብዬ ባላምንም ግን ውህደት ሲባል ሰው አዕምሮ የሚመጣው ይሄ ነው:: ስለዚህ ለእኔ አሁን ኢህአዴግ እያደረገ ያለው ውህደት አይመስለኝም፡፡ግን የተሻለ አደረጃጀት ለመፍጠር ጥረት እያደረገ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር ኢህአዴግ አገሪቱ
ዘጠኝ ክልሎች ቢኖሯትም ከዘጠኙ ውስጥ አራቱን ብቻ ነው አቅፎ የያዘው፤ አምስቱን በር ላይ አስቀምጧቸዋል፤ ይሄ ፍትሃዊ አይደለም:: የአሁኑ አደረጃጀት ብርድ ውስጥ የነበሩ ፓርቲዎችንም ያቅፋል:: ስለዚህ ለእኔ የተሻለ አደረጃጀት ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በእርግጥ ግንባርም ሆኖ ማቀፍ የሚችልበት ዕድል አለ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ውህደት ለሚለው ቃል ምን ምትክ ቃል ሊኖረው ይችላል? ግንባርም ሆኖ ማቀፍ ይችላል ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
ዶክተር ብርሃኑ፡- በእኔ እምነት ኢህአዴግ ግንባርም ሆኖ ውጭ ያሉትን ፓርቲዎች ማቀፍ ይችላል፤ ከግንባርም የተሻለ አደረጃጀት ካለ ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን ከግንባር ወደ ፓርቲ በሚኬድበት ጊዜ ግን ፓርቲ ውስጥ ደግሞ የተለያዩ አደረጃጀቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ሲባልም ሁሉንም ክልል የሚወክል አካል ያለበትና ብዝሃነት ያለው መዋቅር መዘርጋት ይቻላል:: የማይቻልበት ሁኔታ የለም፤ ዋናው መስማማት መቻላቸው ነው፡፡ ነገር ግን ውህደት ሲባል ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን የሚደፈጥጥ የሚመስልበት ሁኔታ አለ፡፡ እንዴት ነው በክልል ደረጃ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር የሚችሉት? የሚለው ጥያቄ ያመጣል፡፡ እናም ግራ መጋባትን እየፈጠረ ነው ያለው፡፡
እኔ እስከገባኝ ድረስ ውህደት አይደለም፤ ይልቁንም ኢህአዴግ አሁን ያለው አደረጃጀት ሕዝባዊነቱን አያሟላም፤ ምክንያቱም ያቀፈው የተወሰኑትን ክልሎች ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ እንደስሙ ዴሞክራሲያዊ አልነበረም፤ ምክንያቱም ኢህአዴግ ውስጥ ውሳኔ የሚወሰንባቸው መንገዶች ዴሞክራሲያዊ አይደሉም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ አገራዊ ውሳኔ ስታስተላልፊ አምስቱን ክልሎች ውጪ ትተሽ ከሆነ ዴሞክራሲያዊ ሊባል አይችልም፡፡ በሌላ በኩል የትግራይንና የኦሮሚያን ሕዝብ በእኩል ቁጥር መወከል ዴሞክራሲያዊ አይደለም፡፡ ስለዚህ በብዙ አቅጣጫዎች ኢህአዴግ ዴሞክራሲያዊ አይደለም፡፡
በመሆኑም በመጀመሪያ ውጪ የቀሩትን ፓርቲዎች ማስገባት ይገባዋል፤ እንዲሁም እዚያ ውስጥ ለሚኖሩትም እንደ ሕዝቡ ቁጥር ልክ ውክልና መስጠት ይገባል:: የኢህአዴግ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የይስሙላ እሳቤ ነው፡፡ ሁሉንም በእኩል ቁጥር ለመተካት የተደረገ ሴራ ነው ባይ ነኝ:: በነገራችን ላይ ውክልና የሚባለው ነገር በጣም ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም የሚባለው ነገር ዋናው ማጠንጠኛ ቁጥር ነው:: ቁጥሩን አዛብተሽ ሁሉም በእኩል ቁጥር ወክለሽ ዴሞክራሲ አለ ማለት አትችይም:: ብዙ ጊዜ ኢህአዴግ ውስጣዊ ዴሞክራሲ አለው ይባላል፤ ነገር ግን አለ ብዬ አላምንም:: እንደሚመስለኝ እነሱ ለማለት የሚፈልጉት እዚያ ውስጥ ከገቡ በኋላ መከራከር መቻላቸውን ነው፡፡ ለመሆኑ መከራከር ምን ዋጋ አለው? ከወጡ በኋላ መተግበር ካልተቻለ፤ የተቃወመ ሰው ድምፁን ማሰማት ካልቻለ::
ስለዚህ በመጀመሪያ እነዚህን መሠረታዊ ችግሮች መፍታት አለበት፡፡ ካልፈታ ግን ኢህአዴግ ወዴትም መሄድ አይችልም:: እንደአጠቃላይ ስለዚህ እንደቁጥራቸው መጠን ነው መወከል አለባቸው የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ ይህን ሲያደርግ ምንዓይነት የተሻለ አደረጃጀት ይዤ እመጣለሁ ብሎ አስቦ ከመጣ ጥሩ ነው:: ስለዚህ ውህደት የሚለው ነገር በሃሳብ ደረጃ ህብረብሔራዊ የሆነውን ፌዴራሊዝም የሚፃረር ይመስላል:: ብዙውን ጊዜ ውዥንብሩ የሚፈጠረው ከዚያ ይመስለኛል፤ ስለዚህ ጠርቶ መገለፅ አለበት ባይ ነኝ:: ውህደት የሚለው ቃል መቀየር አለበት፤ ምንም የሚዋሃድ ነገር የለም! ምክንያቱም ሁሉም ሕዝብ ወክሎ እስከመጣ ድረስ ከሌላው ጋር መዋሃድ አይችልም፡፡ እሱ መረሳት የለበትም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ጋር ተያይዞ በኢህአዴግ ውስጥ በተለይ ደህዴን የወከላቸው 56 ብሔር ብሔረሰቦች በአግባቡ ተወክለው ነበር ለማለት ይቻላል ወይ? በተለይ በአሁኑ ወቅት የክልልነት ጥያቄ ያቀረቡ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ባሉበት ሁኔታ በዚሁ መቀጠሉ አሁንስ ከዚህ ቀደም የነበረው ችግር ላለመቀጠሉ ምን ዋስትና ይኖራል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ብርሃኑ፡- አሁን ለእኔ ትልቁ ጥያቄ የሚስማሙበት ማዕቀፍ አይመስለኝም፤ በግለሰብም ደረጃ እኔ የምፈልገው ነገር በሕጋዊ መንገድ እንዲሟላልኝ እፈልጋለሁ:: ያ ከተሟላልኝ በኋላ ግን ከሌሎች ጋር ያማደርገው ነገር በእኛ ስምምነት የሚወሰን ስለሆነ ችግር ያለው አይመስለኝም:: በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ስትከተለው የነበረው ህብረብሔራዊ ፌዴራሊዝም ደቡብ ክልል ላይ ተግባራዊ ነበር ብዬ አላምንም፤ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ደቡብ ይመራው የነበረው በአቅጣጫ ወይም በቦታ አቀማመጥ (ጂኦግራፊያዊ ፌዴራሊዝም) ነው፡፡ በደቡብ ክልል ስር ያሉት ብሔሮች ሕዝብ ቁጥር ትንንሽ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ምንአልባት ለእያንዳንዳቸው የማስተዳደር ሥልጣን ቢሰጣቸው ሊጠቅማቸው የማይችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡
ለምሳሌ ዘጠኝ አገር ከምንሆን አንድ ኢትዮጵያ ብንሆን ይሻላል የምንለው በኢኮኖሚም ቢሆን ከሌላ ጋር ለመወዳደር ኃይል እንዲኖረን ለማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ በክልልም ደረጃ ይሄ ይሰራል:: ጠንካራ መሆን አለባቸው፡፡ ልማትም ሆነ ምንም ሲሰራ ክብደት የሚያነሳ ሥራ እንዲሰራ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ 56ቱም ብሔር ብሔረሰቦች የራሳቸው ክልል መሆን ይችላሉ ወይ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ብዙ ጉዳዮችን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን በሚጠይቁት ነገር ለምሳሌ የማንነት ጥያቄ ወይም ራሳቸውን የማስተዳደር ጥያቄ ካላቸው ተግባራዊ መሆን የሚችልበት ሁኔታ አለ:: ይህ ሲባልም የአገሪቱ ወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን የሕዝብ ጥያቄ በአግባቡ ታይቶ መልስ ሊሰጠው ይገባል፡፡
በነገራችን ላይ አሁን አሁን ብሔርተኝነት ለአገሪቱ ችግር እንደሆነ ሲነገር አዳምጣለሁ፡፡ ይህንን የሚሉት ሰዎች ከየት እንደሚያመጡት ግን አላውቅም፡፡ እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔርተኝነት ችግር ያለ አይመስለኝም፤ እንዲያውም ችግር የሆነው ብሔርተኝነት አለመኖሩ ነው፡፡ ሕዝቦቹ ራሳቸው መብታቸውን አስጠብቀው ራሳቸውንም ለማሳደግ የሚችሉበት ሁኔታ አሁንም ሙሉ ለሙሉ ተፈጥሯል ማለት አይቻልም፡፡ ይህ ጉዳይ ሲነሳ በትክክል ታይቶ በቅን ሁኔታ ለመቀበል አሁንም ችግር አለ፡፡ የብሔር ጥያቄ ሲመጣ አሁንም አስተሳሰቡ ገና አልተሰበረም::
በአጠቃላይ ጥያቄዎቹ በአግባቡ ታይቶ ባሉበት ሁኔታ ለምን በቀበሌ ደረጃ አይሆንም ራሳቸውን ማስተዳደር እንዲችሉ መፍቀድ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቀና የሆነ አስተሳሰብና ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆንም በኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን ጫና ታሳቢ በማድረግ ቀስ በቀስ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ አሁን የአንተ ጥያቄ አይመለስም የሚባልበት ዘመን ላይ አይደለንም ያለነው፡፡ በግለሰብም ደረጃ የሚጠየቅ ጥያቄ ተፈጥሯዊ ነው:: መንግሥትም ቢሆን የሚጠየቀው ጥያቄ ተፈጥራዊ እንደሆነ ወስዶ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ መመለስ ይገባዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሕዝብ ቁጥር እንደመስፈርት የሚታይ ከሆነ ከዚህ ቀደም በክልልነት ደረጃ ከተሰጣቸው አንደ ሐረሪ ያሉ ክልሎች የላቀ ሕዝብ ያላቸው ብሔሮች አሁንም በደቡብ ክልል ውስጥ ተጠቃለዋል፤ የእነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች ተጠቃሚነት በምን መልኩ ሊመለስ ይገባል ይላሉ?
ዶክተር ብርሃኑ፡- በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው! እንደማስበው እዚህ አገር ውስጥ ክልሎች አወቃቀር ነገር ሲነሳ የማስበው የፖለቲካ ውሳኔ ነው የሚመስለኝ፡፡ አንዳንዶቹ ስለጠየቁና ሌሎቹም ጡንቻ ስላላቸው ብቻ ክልል የሆኑ አሉ፡፡ አንዳንዶቹም ስላልጠየቁ ብቻ ያልሆኑ አሉ፡፡ ለዚያም ነው እዚህ አገር ውስጥ የብሔርተኝነት ችግር ሳይሆን የብሔርተኝነት መጥፋት ችግር ነው ያለው የምለው፡፡ስለዚህ አሁንም ክልል የመሆን ጥያቄ ያነሳ ብሔር ለምን ክልል መሆን እንዳስፈለገው፤ ሕገመንግሥታዊ ሁኔታዎችን ማየት በግልፅ አጥንቶ ለሚመለከተው ማቅረብ ነው፡፡ አሁን ካነሳሽው ሐረሪ ክልል አንፃር በደቡብ ክልል ውስጥ ያሉ በርካታ ብሔሮች ክልል የመሆን ዕድል አላቸው:: ነገር ግን ሁሉንም ክልል ብናደርጋቸው የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ተፅእኖው ምንድን ነው የሚለው ነገር ተደምሮ ጥያቄው አብሮ መነሳት አለበት፡፡
ይህንንም ስል ግን ቢያንስ ቢያንስ እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል:: ክልል የመሆን መስፈርቱን እንደሚያሟሉ፥ የራሳችሁ ክልል ሊኖራችሁ የሚችልበት ሕገመንግሥታዊ መንገዶች እንዳሉ ገልፆ ከእነሱ ጋር ደግሞ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ በነገራችን ላይ ሕዝብ የሚጠይቀውን ነገር ሁልጊዜ ከትልቋ ኢትዮጵያ ጋር የማገናኘት አዝማሚያ ሁሌም አይመቸኝም፡፡ ዞሮ ዞሮ የተሻለ አደረጃጀት በመንግሥት ወይም ደግሞ በፖለቲከኞች ዓይን ብቻ ሳይሆን በሕዝቦች ዓይን ተቀባይነት የሚያገኝ ማዕከላዊ ነገር መፈለግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚያ ደግሞ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ በግልፅነት ማውራት ይገባል ባይ ነኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርሶ ብሔርተኝነት ችግር እንዳልሆነ ያምናሉ፤ ይሁንና አሁን ባለንበት የሉላዊነት(ግሎባላይዜሽን) ዘመን ላይ ብሔርተኝነት ጥቅም የለውም የሚሉ ወገኖች አሉ፤ እንዲያውም የሚያመጣው ጉዳት አስጊ እንደሆነም ይገልፃሉ፤ በዚህ ላይ ምን ሃሳብ አለዎት?
ዶክተር ብርሃኑ፡- በዓለም ታሪክ ፖለቲካና ብሔር ተለያይተው አያውቅም:: ይህንን ሲሉ መሰረታቸው ምን እንደሆነ እኔ አላውቅም፡፡ ትላልቅ የፖለቲካ ምሁራን ሳይቀሩ የብሔር ማንነት ጉዳይ በኃይል ሊከበር እንደሚችል እንጂ ከፖለቲካ ጋር እንደማይገናኝ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ በእኔ እምነት ብሔርና ፖለቲካ ተለያይተው አያውቁም፤ ብሔር መንግሥት ለመመስረት ጥረት ሲደረግ ነበር የቆየው እኮ! ኢትዮጵያ የብሔሮችን ማንነት ጨፍልቃ አህዳዊ መንግሥት ለመፈጠር የሞከረችው ብሔርና ፖለቲካን ፤ ብሔርና አገረ መንግሥቱን አንድ ለማድረግ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ብሔራዊ መንግሥት፥ ብሔራዊ መዝሙር፥ ብሔራዊ ቲያትር ማለት ምን ማለት ነው? በእኔ አረዳድ ብሔርን የሚወክል መንግሥት ወይም ተቋም ማለት ነው፡፡ ምንም የተለየ ነገር አይደለም፡፡ ስለዚህ ብሔርተኝነትንም ከወሰድን ፅንሰሃሳቡ ርዕዮተ ዓለሙን ካየን የሰው ልጅ በተፈጥሮው የተከፋፈለ ነው፡፡ ይህንን የተከፋፈለ የሰው ልጅ ለማስተዳደር ጥሩ የሚሆነው የብሔር መንግሥት ነው፡፡ ብሔርተኝነት እዚህ ላይ ነው የሚመሰረተው:: ብሔርና ፖለቲካ አይገናኝም የሚባለው ነገር ትርጉም አልባ መከራከሪያ ነጥብ ነው የሚመስለኝ፡፡ ከሉላዊነት ጋርም አይገናኝም::
በእርግጥ ያለንበት ዘመን የፖለቲካ ትርክት የብሔርተኝነት ትርክት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ውስጥ እንዲያውም አነስተኛ ነው፡፡ አሜሪካ ውስጥ ለምሳሌ የነጭ ብሔርተኝነት ትርክት ነው የኖረው፡፡ የትም ብትሄጂ ይህንኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ቱርክና ቻይናን ብትወስጂ የሚከተሉት የፖለቲካ ትርክት የብሔርተኝነት ጥያቄ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የመነጨው ከግሎባላይዜሽን (ሉላዊነት) ነው፡፡ ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች የተካሄዱት በብሔርተኞችና በሊበራሊስቶች መካከል እኮ ነው፡፡ እንደመታደል ሆኖ ሊበራሊስቶች በሁለተኛ ዓለምጦርነት ካሸነፉ በኋላ የግለሰቦችን መብት አከብራለሁ ብለው ሲዘንጡ አሁንም የግለሰቦች ጥያቄ መቅረቡ አላቆመም፡፡
አሁን አሁን እኮ በሉላዊነት ሰበብ በሃይማኖትም የተወገዙ ፀያፍ ነገሮች እየተሰራጩ ነው የሚገኙት፡፡ በዚህ ሰበብብ እኮ ነው አንቺ ሰፈር እየመጣ ሥራ የሚቀማሽ የበዛው፡፡ ለዚህም ነው ሰው አሁን ወደ ቡድን የተመለሰው፡፡ በአጠቃላይ የሊበራሊዝም መለጥጥ ሰዎችን ተስፋ ማስቆረጥ ውስጥ አስገብቶ ወደ ናሽናሊዝም መለሳቸው:: አሁን አሁን እየተቀነቀነ ያለው በዓለም ደረጃ ብሔርተኝነት ነው፡፡ እኛ እስካሁን ይህንን ሳንፈታ ወደ ሊበራሊዝም ካልሄድን ስንል ዓለም ደግሞ ከሊበራሊዝም ወደ ብሔርተኝነት እየተመለሰች ነው የምትገኘው:: አንዳንድ ጊዜ የተያያዘውን ነገር በማራገብ እና አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታን ባለመረዳት ሰዎች የተሳሳተ ወይም የተዛባ ሁኔታን አያለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- አንዳንዶች ኢህአዴግ ወደ ውህደት መጣ ሲባል ከዚህ ቀደም ተበትኖ ነበር ወይ? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ በእርግጥ ተበትኖ ነበር ለማለት ይቻላል?
ዶክተር ብርሃኑ፡- እንደሚመስለኝ ኢህአዴግ ተበትኖም፤ ተሰባስቦም አያውቅም:: አንዳንድ ሰዎች ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ተፈቃቅዳ የኖረች አገር ናት ይላሉ፡፡ እኔ በዚህ ሃሳብ አልስማማም፡፡ ኢትዮጵያ የፖሊስ ገዥ አገር ሆና ነው የቆየችው፡፡ በጠመንጃ ነው አንዳንዶቹ ተጣብቀው የኖሩት፡፡ አሁንም ቢሆን አማራም ሆነ ትግሬው፤ ኦሮሞም ሆነ ሱማሌው በያለበት ነው እየኖረ ያለው፡፡ በእነዚህ ሕዝቦች መካከል ያለው የጠነከረ መስተጋብርም የለም፡፡ በእኔ እምነት አገሪቱን የሚመራው መንግሥት ነው ሁሉንም እየጨፈለቀ የሚያስተዳድራቸው:: ኢህአዴግም እንደዚያ ይመስለኛል፤ አራቱን ድርጅቶች እዚያ ውስጥ ይዞ ግን በጉልበት አሰላለፍ ተጣብቀው የቆዩ ይመስለኛል:: እዚያም ሳንደርስ አመሰራረቱን ካየን ኢህአዴግ ታክቲካል ድርጅት ነው፤ በተለይም ህወሓት የራሱን ዓላማ ለማስፈፀም ያቋቋመው ድርጅት ይመስለኛል፡፡
ሌሎቹ ሦስቱ ድርጅቶች እሱ በሚፈልገው መዋቅር ተደራጅተው ነው የኖሩት፡፡ ሲቀጥል ደግሞ 27ቱን ዓመት ህወሓቶች የበላይ ሆነው ሌሎቹ እሺ እንዲሉ የተገደዱበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ አሁን ህወሓት ከነበረበት ቦታና ሥልጣን አኳያ ተገፍቷል፡፡ ስለዚህ እንደድሮ ጠርንፎ አንድ ላይ ይዟቸው ሊቆይ አይችልም፡፡ ስለዚህ አሁን ያለው አመራጭ ነፃ ሁኔታን መፍጠር ብቻ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ውጪ ላሉትም አስበው አንድ ላይ ለመስራት የፈለጉ ይመስለኛል፡፡ ለነገሩ ለኢህአዴግ ከዚህ በተሻለ መደራጀት መገኘት አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የግድ ይለዋል፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ወደ ፊት መሄድ አይችሉም ብዬ አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ ምርጫ ሊያሸንፉ አይችሉም፡፡
አዲስ ዘመን፡-ይህንን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
ዶክተር ብርሃኑ፡- በመጀመሪያ እንዳልኩት አመሰራረቱ ራሱ ታክቲካል ነው:: ድርጅቱን ህወሓት ነው የመሰረተው፤ ስለዚህ ህወሓት እንደሚፈልገው ነው የሚመራው::
አሁን ህወሓት በዚያ ቦታ የለም፤ ስለዚህ የኢህአዴግ መዋቅር በቦታው የለም ማለት ነው፡፡ መስራቹ፣ አዛዡ፣ ባለቤቱ ወደዚያ ተገፍቷል፡፡ ከነበረበት ቦታ ተወስዷል፡፡ የተቀሩት ሦስቱ ደግሞ አንድ ላይ ተይዘው የቆዩት በአንድ ምሰሶ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን እንዴት የተሻለ አደረጃጀት ይዘን ሕዝብ ማገልገል እንችላለን ብለው መጠየቃቸው ትክክለኛም ጥያቄ ነው፡፡ ህወሓትንም ባቀፈ መልኩ አንድ ላይ ተስማምተው እንደፖለቲካ ተቋም መስራት የሚችሉበት ዕድል አለ ብዬ አምናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርሶ ይህንን ቢሉም ህወሓት ሰሞኑን በተከታተይ እያወጣቸው የሚገኙት መግለጫዎች በአንድ ላይ ለመስራት የሚያስችሉ አይመስሉም፤ እንዲያውም መዋሃድ ማለት ፓርቲውን ለመጨፍለቅ የታሰበ እንደሆነ ነው የሚገልፀው፤ ይህ በሆነበት ሁኔታ እንዴት ወደ ጋራ ነገር ሊመጡ ይችላሉ ተብሎ ይታሰባል?
ዶክተር ብርሃኑ፡- በሁለት መንገድ ልናየው እንችላል፡፡ በተወሰነ ደረጃ የምስማማበት ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ እኔም አስቀድሜ እንዳልኩት ውህደት የሚለው ቃል በራሱ አወዛጋቢ ነው፡፡ ስለዚህ እሱ ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ጥሩ ጥያቄ ነው:: ግልፅ መደረግ ይገባዋል፡፡ ግን ከበስተጀርባ ያለው ፍላጎት ምንድን ነው? ብለሽ ካየሽ በተወሰነ መልኩ ላለፉት 27 ዓመታት የብሔር ፌዴራሊዝም የህወሓት ነው፥ ሕገመንግሥቱ የህወሓት ነው፥ ኢህአዴግ የህወሓት ነው ሲባል የኖረው:: ህወሓትም «የኔ ናቸው» ብሎ የሚያምን ከሆነና ከሥልጣናቸው እንደተነሱ አስበው የእኛን ነገር አትንኩ ዓይነት ነገር ከሆነ ከዚህ በኋላ የሚያስኬድ አይደለም፡፡
እነሱም ቢሆኑ ቁጭ ብለው መነጋገር ነው ያለባቸው:: የተሰራው ጥፋት ሕዝቡ ላይ የደረሰው ጫና ቀላል አይደለም፤ ይህን መቀበል አለብን::: ምንም መሸሽ አያስፈልግም፡፡ ወሳኙ ነገር የሚመስለኝ ጥፋቱን አምኖ፤ ይቅርታ ጠይቆ የተሻለ አደረጃጀት ይዞ መምጣት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መነጋገር ነው፡፡
በሌላ በኩል ግን እኔ ምንም እንኳ ውህደት በሚለው ፅንሃሳብ ባልስማማም እንኳ ውህደት ቢያደርጉ እንኳ ተጠቃሚ የሚሆነው ህወሓት ነው ባይ ነኝ፡፡ ምክንያቱም አሁንም ቢሆን የክስ ጨዋታዎች አሉ፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት የደረሰው ጉዳት ቀላል አልነበረም፤ ለዚህ ደግሞ በዋናነት ተጠያቂ ህወሓት ነው የሚለው ነገር ጎልቶ ነው የሚወጣው፡፡ በእርግጥ ሁሉንም ነገር እነሱ ናቸው የሰሩት የሚል እምነት የለኝም:: ሁሉም ድርሻ ይኖረዋል፡፡ በበላይነት ይህንን ድርጅት የመራው፥ ቁልፍ የሥልጣን ቦታዎችን ይይዝ የነበረው ህወሓት ነው፡፡ እንበልና ቢዋሃዱ ጥፋታቸውም አብሮ የሚዋሃድ ነው የሚመስለኝ፡፡ እነሱ ግን ይህንን አቅጣጫ ያዩ አይመስለኝም፡፡ ዞሮ ዞሮ የተሻለ አደረጃጀት መፍጠር መቻል አለባቸው፡፡
በእርግጥ የመደመር እሳቤ ውስጥ ይሄ ነገር ይነሳል፡፡ የመዋሃዱ ዋና ዓላማ ጥሩ ጥሩውን ይዞ መጥፎን እያሻሻሉ ወደፊት መሄድ ነው የሚገባው፡፡ ስለዚህ በኢህአዴግም አንድ ላይ የመስራት ባህል አለ፤ ይህንን ጥሩ ነገር ይዞ ሌሎችንም ጨምሮ በውስጥ ደግሞ ጠርናፊ የሆኑ ሕግጋቶች አሻሽሎ ከዚህ የተሻለ የሕዝቦችን ጥያቄ ሊመልስ የሚችል አደረጃጀት ይዞ መምጣት ይገባዋል፡፡ ይሄ ደግሞ የሚሆነው ሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች በተለይ ላለፉት 27 ዓመታት ክልሎቹን ወክለው የነበሩት ተሳትፈው አብረው መቀጠል አዋጭ ይመስለኛል፡፡
ህወሓትም እዚያ ጫፍ ላይ ቁጭ ብሎ በየቀኑ መግለጫ ከማውጣት ጠጋ ብሎ መነጋገር ነው የሚገባው፡፡ ከዚህ ቀደም ለውህደት ጥናት ተጀምሮ እንደነበር የሚገልፅ ሃሳብ አሁን አሁን እየወጣ ነው፤ ጥናቱን አብረው ከጀመሩ እንዴት እንተግብረው የሚለውን ነገር አብረው መመካከር አለባቸው፡፡ እዚያ ቁጭ ብሎ ድንጋይ ብቻ መወራወር ከዚህ በኋላ የትም እንደማያደርስ መገንዘብ ይገባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዚሁ ጋር አያይዞ ውህደቱ አንዳንድ የህወሓት አመራሮች ፌዴራሊዝምን ይጨፈልቃል የሚል ስጋት አላቸው፤ ይህ ምን ያህል ውሃ የሚያነሳ ሃሳብ ነው?
ዶክተር ብርሃኑ፡- እንደሚመስለኝ ስጋቱ ሊፈጠር ይችላል፤ በመሰረቱ ሕዝቦችን የሚያሰጋ ቃላት መጠቀም አስፈላጊ አይደለም:: ይሁንና ማንም ኃይል ፌዴራሊዝምን ማጥፋት አይችልም፡፡ ውህደትም ለምሳሌ ዞሮ ዞሮ የፖለቲካ ተቋማቱ የሚመረጡት በሕዝብ ነው፡፡ ሕዝቡ ምንዓይነት ነገር ነው የሚቀበለው የሚለውን ጥያቄ መዘንጋት የለባቸውም:: ስለዚህ ፌዴራሊዝምንም ማጥፋት አይቻልም፡፡ ፌዴራሊዝምን ሊያጠፋ የሚፈልግ ማንኛውም ኃይል ይጠፋል:: ምንም ጥያቄ የለውም፤ ማንም ቢሆን፤ ምክንያቱም በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት ሲደረግ የነበረው እንቅስቃሴ ሕዝቡን በጣም አንቅቶታል፡፡
ፌዴራሊዝምን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እሸራርፈዋለሁ የሚል አካል ምንም ቦታ አይኖረውም፡፡ እኔ አካሄዱ መሆን ያለበት አሁን የተጀመረውንና ወረቀት ላይ ያለውን ፌዴራሊዝም ተቀብሎ ከዚህ በላይ ለማጠናከር ነው መሰራት ያለበት:: እናም የፖለቲካ ተቋማትም ኢህአዴግ ለምሳሌ ምንም ቢሆን በመርህ አሁን ያለውን ፌዴራሊዝም ወረቀት ላይ ያሰፈሩት እነሱ ናቸው፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ውስጥ ወደ ኋላ እመልሳለሁ የሚል አንድም ግለሰብ የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ቢኖርም ደግሞ ጤነኛ አይመስለኝም፡፡ እነሱ ለፖለቲካ ታክቲክ ሊጠቀሙበት ይችላሉ:: ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን እንደስጋት ያየዋል ብዬ አላምንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ውህደቱ ከምርጫ በፊት መከናወን አለበት ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ብርሃኑ፡- እሱ ጉዳይ ለእኔ ከባድ ውሳኔ ነው፡፡ የተሻለውን አደረጃጀት ከዚህ የጠራውንና የሕዝብን ጥያቄ ሊመልስ የሚችል አደረጃጀት ከምርጫ በፊት ይዘው ቢመጡ መልካም እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ዞሮ ዞሮ ኢህአዴግ የሚባለው ድርጅት ግልፅ የሆነ አላማ ኖሮት ውክልናው የሕዝቦችን ቁጥር ማዕከል የሚያደርግ መሆን አለበት፡፡ ያንን ለሕዝቡ ይዞ ቢመጣ የተሻለ የመመረጥ ዕድሉን ይጨምራል ብዬ አምናለሁ፡፡ ግን ውህደት የሚለውን ውዥንብር ቃል ይዘው ባይመጡ ደስ ይለኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአዴፓና ኦዴፓ፤ በአዴፓና በህወሓት መካከል ያለው ልዩነት ሳይፈታ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ወደዚህ ነባራዊ ሁኔታ መግባት ይችላሉ ተብሎ ይታመናል?
ዶክተር ብርሃኑ፡- ይህንን ጉዳይ በአንድ ጀምበር መፍታት አለባቸው አልልም፤ እነሱ የፖለቲካ ተቋም እኮ ናቸው፡፡ እነሱም ለራሳቸው ጠቀሜታ ሲሉ ነው ይህንን ችግር የሚፈቱት፡፡ ተወዳድሮ ለማሸነፍ ነው አይደል እንዴ? ስለዚህ ጊዜ ሰጥቶ ይህንን ጉዳይ መፍታት ይጠበቅባቸዋል:: ይህንን ካልፈቱ እንደፖለቲካ ተቋም እንደአባል ድርጅት ያለመቀጠል ዕድላቸው ሰፊ ነው የሚሆነው:: ስለዚህ ይህንን ጉዳይ ከምንም በላይ አስቀድመው መፍታት አለባቸው::
ምንም ጊዜ መፍጀት የለባቸውም፡፡ ድንጋይ የመወራወር ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ምንም የተጋነነ ነገር በመካከላቸው ያለ አይመስለኝም:: ቁጭ ብለው አለመነጋገራቸው ነው ድክመታቸው:: ድክመትን ይዞ ወደፊት መራመድ አይቻልም:: ለተፎካካሪ ፓርቲዎችም ይህንን ድክመታቸውን አይተው ሊጠቀሙበት የሚችሉበት ዕድል ነው የሚከፍቱት:: ምክንያቱም አገሪቱን ኢህአዴግ ብቻ አይደለም ማስተዳደር ያለበት፤ ጠንካራ ፓርቲ ከመጣና ለሕዝቡ ራሱን መሸጥ ከቻለ መመረጥ ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት ከ130 በላይ ፓርቲዎች ተፈጥረዋል፤ እነዚህ ፓርቲዎች በዚሁ መልኩ መቀጠላቸው በአገር ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ምንድን ነው? ምንስ መሰራት አለበት ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ብርሃኑ፡- እኔ እነዚህ ሁሉ ፓርቲዎች ናቸው ወይ? የሚል ጥርጣሬ አለኝ:: እኔ ግለሰቦች ይመስሉኛል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ እዚህ አገር ፓርቲ ለመመስረት ምንም የሚከለክል ነገር የለም ማለት እኮ ነው:: የፈለገ ሰው ተነስቶ ዛሬ ፓርቲ መመስረት ይችላል፡፡ ፓርቲ ለማቋቋም ፍላጎት ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ምርጫ ቦርድም እዚች ጉዳይ ላይ ትንሽ ጠንከር ያለ ነገር ቢያደርግ የተሻለ ነው የሚል ሃሳብ አለኝ:: በእኔ እምነት እነዚህ ፓርቲዎች ለምርጫ ጥሩ ግራ መጋባት ይፈጥራሉ ብዬ አምናለሁ:: እኛ ነን የምንመርጣቸው ወይስ እነሱ ናቸው የሚመርጡን የሚል ጥያቄ አለኝ፡፡ እነዚህ ሰዎች እኮ ነጋዴዎች ሊሆኑ ይችላሉ:: የሚሸጡት ድምፅ ሊኖር ይችላል፡፡ ዞሮ ዞሮ ሕዝቡ ጥያቄውን የሚመልስለትን ፓርቲን እንዲመርጥ ማንቃት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ግንዛቤ የማስጨበጡን ሥራ ምርጫ ቦርድ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ውድድሩ ራሱ ገፍቶ እንዲያወጣቸው ማድረግ ይገባል::
አዲስ ዘመን፡- አሁን በዶክተር አብይ የሚመራው መንግሥት ወገንተኛ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፤ በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች በአፋጣኝ ምላሽ አለመሰጠቱ በብዙዎች ላይ ጥርጣሬ እንደፈጠረ ይገለፃል፡፡ ይህም ህወሓት ያደርገው ወደ ነበረው ሥርዓት እንዳንመለስ የሚል ስጋት ፈጥሯል? በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
ዶክተር ብርሃኑ፡- ይህ ጉዳይ ሰፊና ስሜት ቀስቃሽ ነው፡፡ ሲጀመር የኦሮሞ የበላይነት እየተፈጠረ ነው የሚለው ነገር ካለማወቅ የሚነጭ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ የኦሮሞ የበላይነት ስለመኖሩ ምንድን ነው ማሳያ ሲባል ትግሬዎች ይዘውት የነበረውን ቦታዎች ኦሮሞ ይዟል የሚል ምላሽ ይሰጥሻል:: እዚህ አገር ውስጥ እኮ ከአጠቃላይ ሕዝቡ ኦሮሞ 40 በመቶ ነው:: ስለዚህ የአገሪቱ 40 በመቶ የሚሆነው ቦታ ይገባዋል ማለት ነው:: ይሄ ልክ እንደ ጥቁርና ነጭ ግልፅ መሆን የሚገባው ጉዳይ ነው:: አሁን ባለው ሁኔታ ግን ኦሮሞ 40 በመቶ ድርሻ አልያዘም::
ጠቅላይ ሚኒስትሩም በተደጋጋሚ ገልፀውታል:: ኦሮሞ ከነበረው በላይ ይዞ ከሆነ እኔ ሥልጣኔ እለቃለሁ እስከማለት ደርሰዋል:: በነገራችን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኦሮሞ ሥልጣን መስጠት አይችሉም፡፡ ቁጥራችን ነው የሚሰጠን:: ማንም ሥልጣን ያዘ አልያዘ የሚገባውን ስፍራ ማግኘት አለበት፡፡ ስለዚህ እኔ ኦሮሞ በቁጥሩ ልክ ሥልጣን ይዟል የሚል በማስረጃ ልንከራከር እንችላለን፡፡ ትግራዮች ይዘውት የነበረውን ቦታ ቢይዝ እንኳ የሚመጥነው አይደለም፤ ምክንያቱም የትግራይ ሕዝብ እኮ አምስት በመቶ ነው፡፡ ገና 35 በመቶ ይቀራል ማለት ነው፤ ስለዚህ እንዲህ የሚሉ ሰዎች ተስፋ ይቁረጡ፡፡ ይህንን በድፍረት ነው የምናገረው፡፡
የመታወቂያ ጉዳይ እንውሰድ፤ ለኦሮሞ መታወቂያ ይሰጣል የሚባል ነገር እሰማለሁ፤ ለማን ነው የተሰጠው? እኔ አንድ ማሳያ ልስጥሽ አዲስ አበባ የተስፋፋችው ኦሮሞን በማፈናቀል ነው፡፡ በ1991 ዓ.ም ከነበራት ይዞታ 40 በመቶ ሰፍታለች፡፡ እዚያ መሬት ላይ የነበሩ ሰዎች ተገፍተው ነው የሄዱት:: ለእነዚያ ሰዎች ተመልሰው መታወቂያ ተሰጥቷቸው ከሆነ እሰየው ጥሩ እርምጃ ነው:: ምክንያቱም አዲስ አበባ ስትስፋፋ የነበሩትን ሰዎች ማቀፍ መቻል አለበት:: የተሻለ መሬት፥ የተሻለ ቤት ባይሰጣቸው የነዋሪነት መታወቂያ ግን በነበሩት ቀዬ ላይ ቢሰጣቸው ምንም ችግር የለውም:: ከሌላ አካባቢ የሚመጡ ሰዎች እኮ ዛሬም መታወቂያ እየተሰጠ ነው፡፡
አዲስ አበባ የነዋሪዋ ቁጥር የበዛው እዚህ ብቻ በተወለደው ነው?፡፡ አይደለም!፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ጉዳይ ፖለቲካም አይደለም ሃሜት ነው፡፡ እኔ ለእነዚህ ሰዎች ጠበቃ ሆኜ ብከራከር ሁሉ ደስ ይለኛል፡፡ ለምንድን ነው አዲስ አበባ ወደ ውጭ እየገፋች መሬትን ወደ ውስጥ የምታስገባው?፡፡ አዲስ አበባ እንደከተማ መስፋት ካለባት ሕዝቦቹን እያቀፈች ነው አብራ ማደግ ያለባት:: ከኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየም ጋር በተያያዘ ብዙ የሚነገር ነገር አለ፡፡ እንደሚታወቀው ቦታው ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የነበረ ነው፡፡ ክልሎች ሲዋቀሩ ወሰን ተሰጥቶቸዋል፤ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋር በመነጋገር አንድ ፕሮጀክት ሊገነባ ይችላል፡፡ ነገር ግን ኮዬ ፈጬ በምን ሁኔታ እንደተገነባ ግልፅ አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ አስተዳደሩ ፈፀመ ለተባለው ስህተት ከ15 ዓመት በላይ እየቆጠበ ከነገ ዛሬ ይደርሰኛል እያለ ሲጠብቅ የነበረው የከተማዋ ነዋሪ በምን ጥፋቱ ነው የሚቀጣው?
ዶክተር ብርሃኑ፡- ምንድን ነው መቀጣት ማለት? አሁን አልተሰጠውምና ወደፊት አይሰጠውም ማለት አይደለም:: ዞሮ ዞሮ አዲስ አበባ መስተዳድር ራስ ገዝ ነኝ ብሎ ልዩ ጥቅምን አልተገብርም ማለት አይችልም:: ግን በፅንሰሃሳብ ደረጃ አስተዳደሩ ያለበትን ችግር ፈቶ ለነዋሪዎች ቤት መስጠት አለበት:: ግን ይሄ ጉዳይ በእኔ የሚመለስ አይደለም:: አስተዳደሩ ተገቢውን ምላሽ ይሰጣል የሚል እምነት አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር ብርሃኑ፡- እኔም አክበራችሁ ጠርታችሁ የዘመን እንግዳ ስላደረጋችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2012
ማህሌት አብዱል