አዲስ አበባ:- ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማት ያለመኖር በኢትዮጵያ መልካም አስተዳደር እንዳይሰፍን ማድረጉ ተገለፀ።
የመልካም አስተዳደር ቀንን አስመልክቶ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ከዋፋ ፕሮሞሽን ጋር በመተባበር <<ያልተሸራረፈ መብት ለሁሉም>> በሚል መሪ ቃል ትናንት በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የመነሻ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት የፐብሊክ ፖሊሲና ማኔጅመንት ተመራማሪ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ሄኖክ ስዩም እንደገለጹት፤ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማት ያለመኖር በኢትዮጵያ መልካም አስተዳደር እንዳይሰፍን አድርጓል።
‹‹ጥንታዊ የዴሞክራሲ ስርዓቶች ባለቤት ነን›› በማለት በምሳሌነት እንደገዳ፣ በልሃ ልበልሃ እንዲሁም ጎረቤት ከጎረቤት ጋር ተጠራርቶ ቡና በመጠጣት ውይይቶችን በማካሄድ ችግሮችን የመፍታት ባህል መኖሩን ጠቅሰው፤ ለኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ስርዓት እንግዳ ባይሆንም መልካም አስተዳደር ያልሰፈነ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር ያልሰፈነው ጠያቂ ትውልድ ስለሌለ ነው ማለት እንደማይቻልም ያስረዱት ተመራማሪው፤ የ1966ቱን አመጽ፣ የ17 አመት የኢህአዴግ ትግልን፣ የ1997 ዓ.ም የተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመጽ፤ ከ2007 እስከ 2010 ዓ.ም የነበረው አመጽ ለዴሞክራሲ የተከፈሉ መስዋእትነቶችን አብራርተዋል።
ህገ መንግስታዊ መሰረት ስለሌለው ነው እንዳይባል በኢፌዴሪ ህገመንግስት ከአንቀጽ 10 እስከ 40 ባለው ክፍል ስለ ዴሞክራሲ እና ሰብአዊ መብት የሚያጠነጥን መሆኑን አስታውሰው፤ ያልተማረ እና መረጃ የሌለው ህዝብ እንዳይባል ሰፊ የተማረ የሰው ኃይል ያላት አገር መሆኗንም ጠቁመው፤ መልካም አስተዳደር ያልሰፈነው ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማት አለመኖር ዋነኛ ተግዳሮት መሆኑን አብራርተዋል።
እንደጥናት አቅራቢው ገለፃ፤ የዴሞክራሲ ተቋማት ከመልካም አስተዳደር ስርዓት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያላቸው ሲሆን፤ የዴሞክራሲ ተቋማት የአንድን አገር የዴሞክራሲ ግንባታ ለማሳለጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ።
ስለዚህ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች በመሆናቸው የዴሞክራሲ ስርዓት ሲገነባ የመልካም አስተዳደር ስርዓት እየሰፈነ ይሄዳል። ይሄንን ለማድረግ ደግሞ የዴሞክራሲ ተቋማት ዘርፈ ብዙ አስተዋጽፆ የሚያበረክቱ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የዴሞክራሲ ተቋማቱ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ለዜጎች የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች በአገሪቱ ህግና መመሪያ መሰረት ዜጎች የሚገባቸውን አገልግሎት እንዲያገኙ የመከታተል፣ የማስተካከልና ተገቢውን አገልግሎት ካልሰጡ የማጋለጥ ሚና ይጫወታሉ፤ አስፈጻሚዎችንም ይከታተላሉ ብለዋል።
በአጠቃላይ የዴሞክራሲ ተቋማት በአገሪቱ ውስጥ የሚከሰቱ ጉድለቶችን ነቅሶ በማውጣት፣ በመጠቆም እና በመተቸት ክፍተቶች እንዲሞሉና እንዲስተካከል ይጠቁማሉ። እንዲሁም እነዚህ ተቋማት ዴሞክራሲያዊ ተቋማትና አገር ወዳድ ዜጎች እንዲፈሩ ከማድረግ ባሻገር መልካም አስተዳደርን በማስፈን ህዝብና መንግስት እንዲተማመን እንዲሁም በአንድ አገር ፍትሃዊነት እንዲሰፍን ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ ዶክተር ሄኖክ ተናግረዋል።
አዲሰ ዘመን ጥቅምት 14/2012
ሶሎሞን በየነ