አዲስ አበባ፡- በቅርቡ የህወሓት ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ከትግራይ ሚዲያ ሀውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በአንዳንድ እንቅስቃሴዎች መንገድ መዝጋትን ጨምሮ ትግራይን ለማንበርከክ የሚወሰዱ እርምጃዎች እንዳሉ ሲገልጹ፤“የቀድሞ የህወሓት ጓዶቹ ያበሳጩትና እነሱን ማብሸቅ የሚፈልግ ዶክተር አረጋዊ በርሄ የሚባልን ሰው የትግራይ መሪ ይሆናል ብሎ ለማምጣት አዲስ አበባ የሚያዘጋጅ ኃይል አለ።
ከዚህ ቀደም ዶክተር አረጋዊ በርሄ ትግራይ በመጡበት ወቅት ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመሆን በትግል ነበር ያስወጣናቸው አሁንም እንዳታስቀስፏቸው ብለው” ተናገረው ነበር። ይህንን መነሻ በማድረግ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር የአመራር አባልና የቀድሞ የህወሓት መስራች ዶክተር አረጋዊ በርሄን “አስተያየቱን እንዴት ያዩታል?” ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል።
“ለእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ምላሽ ለመስጠት ፍላጎት የለኝም። ነገር ግን በትግራይ እያለሁ በእኔም ላይ ሆነ በሌሎች ላይ ችግር ሲደርስብን የነበረው በራሱ በህወሓት ባለስልጣናት ነው። ችግር ፈጣሪዎቹን ወጣቶች የላኩብንም እነርሱ ራሳቸው ናቸው። ከ37 ወረዳዎች ከእያንዳንዱ 150 ወጣቶች ሰብስበው፤ ውሎ አበል ከፍለው፤ ትራንስፖርት አዘጋጅተው በቀብር ስነስርዓት ላይ እንዲጨፍሩ አድርገዋል።
አባላችንንም መርዝ እስከማጠጣት ደርሰው ነበር። በቀብር ስነስርዓቱ ላይ አብይ ሌባ፤ አብርሃ ደስታ ሌባ፤ አረጋዊ ሌባ፤ ባንዳ እያሉ ሲጨፍሩ ነበር፡፡ ይሄ ነገር እንደ ስነምግባርም ትክክል አይደለም በትግራይ ባህል እንዲህ አይደረግም።
“አቶ ጌታቸው እንደዚህ ዓይነት ነገር የሚናገሩት በጀመሩት አፈና መቀጠል ስለሚፈልጉ ነው። ትግራይ ለመሄድም ሆነ ከትግራይ ለመውጣት ማንንም አላስፈቅድም። አሁንም እኔን አደጋ ላይ የሚጥሉ ነገሮች ሊሞክሩ ይችላሉ። እኛ ትግል የጀመርነው የትግራይን ህዝብ መታፈንና ሌሎች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመቅረፍ ነው።
ዋናው ነገር ለትግራይ ህዝብ በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲመርጥ ዕድሉ እንዲሰጠው ማድረግ ነው። ከዚያ በኋላ ከፈለገ እነርሱን፤ ከፈለገ እኛን መምረጥ ይችላል። ይህንንም ከትግራይ ህዝብ ጋር በመሆን መሥራቴን እቀጥላለሁ። ይሄ ነገር ተፈጠረ ብዬ ግን ከጀመርኩት እንቅስቃሴ አላፈገፍግም።” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
አዲሰ ዘመን ጥቅምት 14/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ