“ፓርቲዎች አሸንፈው መንግስት በመሆን ብቻ የሚያምኑ ከሆነ የፖለቲካን ሙሉ ቅርጽ አያሳይም፤ መሸነፍንም መለማመድ አለባቸው። በቤተሰብ፣ በጓደኛና በማህበር የፖለቲካ ፓርቲ መመሥረት አያዋጣም። መንግስትንና ፓርቲን፤ እንዲሁም ፓርቲንና ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ማየት ተገቢ አይደለም።”
ይህንን የተናገሩት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሲሆኑ፤ የንግግሩ አውድ ደግሞ ሰሞኑን ከአገሪቱ ፓርላማ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡበት ወቅት ነው። ለመሆኑ የሀሳቡን አንድምታና ምልከታ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እንዴት ያዩታል?
በየካ ክፍለ ከተማ ጃን ሜዳ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ማስተዋል መኮንን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የፖለቲካ ፓርቲዎች አሸንፈው መንግስት በመሆን ብቻ የሚያምኑ ከሆነ የፖለቲካን ሙሉ ቅርጽ አያሳይም። መሸነፍንም መለማመድ ያስፈልጋል›” ማለታቸው አዎንታዊ ሀሳብ ነው። ሀሳቡ ዓለም አቀፋዊና የዴሞክራሲ መርኅ ነው።
የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት በዋናነት መወዳደር ያለበት ለማሸነፍ ቢሆንም፤ ከዚህ ውጭ ግን በተቃራኒ ውጤት ከመጣ መሸነፍንም በጸጋ መቀበል አለበት። ይህ ካልሆነ የአገር ሠላምና የዜጎች ደኅንነት አስተማማኝ አይሆንም። ነገር ግን ይህ እንዲሆን ቅድሚያ መሠራት ያለባቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ።
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ “አሁን ያለው የምርጫ ቦርድ ተዓማኒ ነው ወይ? ገዥው ፓርቲ በምርጫ ቦርዱ ሥራ ጣልቃ አይገባም ወይ?” የሚሉና መሠል ገፊ ምክንያቶች መወገድ አለባቸው። እነዚህ ሀሳቦች ካልተወገዱ ግን መሸነፍን መለማመድ አለባቸው ማለት ከቃል ንግግር የዘለለ ፋይዳ የለውም። በተለይ፤ በአፍሪካ ውስጥ እንዲህ አይነት ችግሮች የሚከሰቱት ሀሳቡን ባለመረዳት አይደለም። የመሸነፍን ጽንሰ ሀሳብ ባለመቀበልና ባለመውደድ ብቻ ሳይሆን ፍትሐዊ አይደለም የሚያስብሉ ነገሮች ስላሉ ነው።
‘ፓርቲዎች በጓደኛ፣ በቤተሰብና በማህበር መመስረት የለባቸውም’ የሚለውም ሀሳብ ትክክል ነው የሚሉት አቶ ማስተዋል፤ ነገር ግን የአገሪቷ ፖለቲካ የሰፈር ፖለቲካ በመሆኑና በሠፈር ፖለቲካ ውስጥ እየተኖረ እንዲህ አይነት የፓርቲ አደረጃጀት ትክክል አይደለም ማለቱ አጠያያቂ መሆኑን ይናገራሉ። ስለዚህ ከሥረ መሠረቱ የፖለቲካ አካሄዱ መቀየር ካልቻለ የፖለቲካ ፓርቲዎች መብዛት አይቀሬ እንደሆነም ይጠቁማሉ።
አቶ ማስተዋል እንደሚሉት፤ “‘ፓርቲና መንግስት መለያየት አለበት’ የሚለውም ሀሳብም ቢሆን የሚደገፍ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለው በዚህ አይነት መንገድ አይደለም። ቀጣይነትም ያለው አይመስልም። ከአንድ መንግስት የሚጠበቀው ፓርቲና መንግስት መለያየት አለበት የሚል ቃል ሳይሆን በእርግጥም ለይቶ ማሳየት ነው።”
በቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ጎሮ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ አንገሶም መዓሾ በበኩላቸው፤ የፖለቲካ ፓርቲን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት ሀሳብ ትክክል ነው በማለት፤ አብዛኛው የፖለቲካ ፓርቲ ለውድድር ሲቀርብ አሸንፋለሁ እንጂ ብሸነፍ በሚቀጥለው የተሻለ ተወዳዳሪ ሆኜ እመጣለሁ የሚል መርኅ ይዞ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
ፓርቲዎች ለህዝቡም ግልጽ አቋማቸውን ማሳየት እንዳለባቸው፤ የህዝቡንም ይሁኝታ ማግኘት የሚችሉት በሀሳብ ልዕልና ሲያምኑ መሆኑን ተናግረዋል። ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ብቻ ሳይሆን ገዥውም ፓርቲ ከአሁን ቀደም ከሰራቸው ስህተቶች ታርሞ በዚህ ቁመና መገኘት አለበት ሲሉም መክረዋል።
እንደ አቶ አንገሶም ገለጻ፤ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስን የማህበረሰብ ክፍሎችን ብቻ ይዘው መንቀሳቀስ የለባቸውም። የአገሪቱ ዜጎች የፓርቲዎቹን አገራዊ ጥቅም በተመለከተ በግልጽ ማወቅም ይጠበቅባቸዋል። ከቤተሰብ፣ ከጓደኛና ከማህበር የዘለለ አባል ያልያዘ ፓርቲ ነገ ላይ ማንን እንደሚመራ አይታወቅም። ፍላጎቱና ጥቅሙም ከማህበር አይዘልም።
ይልቁንም፤ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀራርበው አስተሳሰባቸውን፣ ፕሮግራማቸውንና እቅድቸውን ግልጽ አድረገው ምህዳራቸውን በማስፋትና ብዙ አባላትን በማፍራት ሥራቸውን ማከናወን አለባቸው። ወጥ የሆነ አቋም ያለውን ፓርቲ ለማግኘትም ጊዜው የሚጠይቀውን ጥሩ የሆነ የፖለቲካ መደላደል መኖሩ የግድ ነው።
“የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዙኃኑን አሳታፊ በሆነ መንግድ መደራጀት አለባቸው፤” የምትለው ደግሞ በአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ወጣት የሺእመቤት ቦጋለ ናት። ወጣቷ አክላም፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የማህበረሰቡን የእርስ በርስ ትስሰር ማጎልበት እንዳለባቸው በመጠቆም፤ ሁሉም በየጎራው መሮጡን ትቶ የብዙኃንን ፍላጎትና ጥቅም ማስከበር እንዳለበት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ደግፋ ትናገራለች።
“ፓርቲና አገር አንድ አይደለም። አገር ሁልጊዜም ይኖራል። ህዝብ ለአንድ ፓርቲ ይሁንታ ካልሰጠ ማስተዳደር አይችልም። ስለዚህ እገሌ የሚባል ፓርቲ ከሌለ ልማት የለም፣ አገር የለም፣ መበታተን ይመጣል የሚሉትን አስተሳሰቦች ወደ ጎን በመተው ፓርቲንና መንግስትን ነጣጥሎ ማየት ተገቢ ነው” በማለት ወጣት የሺመቤት አስታውቃለች።
“አሁን በአገሪቷ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ፓርቲዎች ተወዳድረው ሥልጣን ቢያገኙ እንኳን ምን እንደሚሰሩ አያውቁትም።” የሚሉት በጉለሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ፍሮምሳ ታደሰ ናቸው። የፓርቲዎች የአባላቶቻቸው ስብጥር ከጓደኝነትና ከቤተሰብ የዘለለ መሆን እንዳለበትና አሸናፊነትን ብቻ ሳይሆን ተሸንፈውም ለአገር ሊያበረክቱ ስለሚገባቸው ጉዳይ ማወቅና ማሳወቅ እንዳለባቸውም አቶ ፍሮምሳ ይመክራሉ።
አቶ ፍሮምሳ፤ ፓርቲዎች አሁን ላይ አገሪቷ ያለችበትን ሁኔታ ያለገናዘብ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን በመጥቀስ የፓርቲዎቹ እንቅስቃሴ “በእንቀርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው እንዳይሆንም ስጋት እንዳላቸው አስታውቀዋል። በመሆኑም ዴሞክራሲያዊ ሁኔታዎችን ተከትለው የፖለቲካን ቅርጽ ሊያሳይ በሚችል ቁመና ላይ በመገኘት፤ በተለይ በጉርብትናና በመተዋወቅ፤ እንዲሁም መሰል የአደረጃጀት ስልቶች የሚደረገውን አካሄድ ሊከተሉ እንደማይገባ ገልጸዋል።
መንግስትና ፓርቲ መለየት አለበት የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብ የሚደገፈው “ፓርቲ ራሱን የቻለ አገር ባለመሆኑ ነው ያሉት አቶ ፍሮምሳ፤ ወጥ የሆነች ኢትዮጵያ ኖራ በዚህ ውስጥ በማሸነፍም፤ በመሸነፍም የሚያልፉ ፓርቲዎች ሊኖሩ እንደሚችሉና ለዚህም አገርን በማስተዳደር ሂደት ውስጥ የፓርቲን ሚና በመለየት ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ “ከእኔ ሌላ ላሳር” የሚለውን አቋማቸውን መለወጥ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
አዲሰ ዘመን ጥቅምት 14/2012
አዲሱ ገረመው