“ከተወለድኩ እንዲህ ዓይነት ቡቃያ በቀዬው በቅሎ አያውቅም። እንደ ቤተዕምነት ጠዋት እና ማታ ማሳውን እየተሳለምሁ አይኔ ይጠግባል። የፀሐይዋ ጮራ ማሳው ላይ ብትን ሲል ሲያዩት ሰብሉ ያለቅጥ ያስጎመጃል።” የሚሉት በምስራቅ ጎጃም ዞን በጎዛመን ወረዳ የነራታ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አድማሴ ያለው ናቸው።
በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የደብረ ማርቆስ ግብርና ምርምር ማዕከል ከጎዛመን እና ከአነደድ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤቶች ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የአርሶ አደሮች የመስክ ጉብኝት በዓል ላይ ያገኝናቸው የሰባት ቤተሰብ አስተዳዳሪው አርሶ አደር አድማሴ፤ በቀበሌዋ በ33 ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም ከታቀፉ 46 አርሶ አደሮች መካከል አንዱ ናቸው።
የእርሳቸው ድርሻ ሁለቱን ሄክታር የሚሸፍን ሲሆን፤ ቀደም ሲል ደኑ ተመንጥሮ፤ አፈሩ በዝናብ እና በነፋስ ተሸርሽሮና ተጠርጎ መሬቱ እርቃኑን በመቅረቱ አይደለም። ስንዴና ገብስ የመሳሰሉ ሰብሎችን አምርተው የምግብ ፍጆታቸውን ለመሸፈን ቀርቶ፤ መሬቱ እንግዶና ግብጦ ማብቀል ተስኖት ለድህነት ተጋልጠው እንደነበር ይናገራሉ።
መሬቱ አሲዳማ በመሆኑ የፈለጉትን ሰብል ዘርተው፤ አምርተው ተጠቃሚ ሳይሆኑ ዘመናት ማስቆጠራቸውን የሚናገሩት አርሶ አደሩ፤ ዘንድሮ ግን የደብረ ማርቆስ ግብርና ምርምር ማዕከል በዞኑ በሰፋፊ ኩታ ገጠም መሬቶች ላይ በሰራው ቴክኖሎጂ የማስተዋወቅና የማስፋፋት ስራ ተጠቃሚ ሆነዋል።
ከምርምር ማዕከሉ በተግባር የተደገፈ የቴክኖሎጂ ድጋፍ አግኝተው መሬቱን በኖራ በማከምና የቀረበላቸውን ምርጥ ዘር በኩታ ገጠም በመዝራት ገና በቡቃያው ሲያዩት የሚያጠግብ የስንዴ አዝመራ ሊበቅልላቸው መቻሉን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የደብረ ማርቆስ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ያለው ማዘንጊያ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ ከተቋቋመ ገና ሰባት ወር ቢሆነውም በምስራቅ ጎጃም ዞን አነደድ ወረዳ ላይ በተረከበው 43 ነጥብ ስድስት ሄክታር መሬት ላይ በሰብል እና በእንስሳት ተፈጥሮ ሀብት የተለያዩ የምርምር ስራዎችን ከመስራት ጎን ለጎን በተወሰኑ ሰብሎች ላይ ደግሞ የመነሻ ዘር ብዜት በማካሄድ ላይ ይገኛል።
ማዕከሉ በምስራቅ ጎጃም ዞን በሚገኙ ስድስት ወረዳዎች በ11 ክላስተር በተደራጁ ሰፋፊ ኩታ ገጠም ማሳዎች ላይ ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅና የማስፋት ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ማዕከሉ ከእህት ማዕከል ያመጣቸውን የዳቦ ስንዴ፤ የብቅል ገብስና የጤፍ ምርጥ ዘሮችን እና በአሲዳማነት በተጠቁ መሬቶች ላይ ኖራ የመጠቀም ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅና የማስፋት ስራ በእነዚህ ወረዳዎች ላይ በሰፊው እየሰራ መሆኑን ይናገራሉ።
አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂውን በፍጥነት ተላምዶ ምርትና ምርታማነቱ እንዲያድግ ማዕከሉ በተግባር ከሰጠው ስልጠናና ክትትል በተጨማሪ፤ በስድስቱ ወረዳዎች በ200 ሄክታር ላይ ለተደራጁ 385 አርሶ አደሮች 253 ኩንታል የዳቦ ስንዴ፣ የብቅል ገብስና የጤፍ ምርጥ ዘሮችን፤ እንዲሁም 807 ኩንታል ኖራ ማሰራጨቱን ተናግረዋል።
እነዚህ 11 ክላስተሮች በከፍተኛ ደረጃ በአሲድ የተጠቁ በመሆናቸው ከአሁን በፊት ገበሬው ለዓመታት የፈለገውን ሰብል ዘርቶ መጠቀም ሳይችል ቢቆይም፤ ማዕከሉ አሲዳማነትን የሚቋቋም ምርጥ ዘር በማቅረብ፤ መሬቱን በኖራ የማከም ቴክኖሎጂን ባለሙያዎች በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ተግኝተው በተግባር የተደገፈ ስልጠናና ምክረ ሀሳብ ለገበሬዎች በመስጠት እና ኖራውን እማሳው ድረስ በማቅረብ ውጤታማ የዳቦ ስንዴ፤ የቢራ ገብስና የጤፍ ሰብሎችን ለማብቀል ተችሏል። ምርቱም ከአርሶ አደሮቹ የምግብ ፍጆታ አልፎ ለውጪ ገበያ የሚቀርብ እንደሚሆን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ በበኩላቸው፤ ምርምሮች በምርምር ማዕከል በሚገኝ በትንንሽ ቦታዎች ላይ ብቻ ይካሄዱ ስለነበር፤ አርሶ አደሩ የምርምሩን ሂደት በተግባር የሚያይበት እድል ስለሌለው የሚገኙ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ተቀብሎ በማሳው ላይ ለመተግበር አሻፈረኝ ይል ነበር። በቴክኖሎጂዎቹ ላይም እምነት አልነበረውም።
አሁን ግን ገበሬዎችን በክላስተር በማደራጀት በቴክኖሎጂ ተደግፈው ማሳቸውን በኩታ ገጠም እንዲዘሩ በማድረግ ውጤታማ ስራ መሰራቱ፤ አርሶ አደሮች በዘርፉ የሚፈልቁ ቴክኖሎጂዎችን እምነት አድሮባቸው እንዲጠቀሙ በር ይከፍታል። ቴክኖሎጂዎችን ከተጠቀሙ ደግሞ ምርትና ምርታማነታቸው በእጥፍ እንደሚያድግ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
አዲሰ ዘመን ጥቅምት 14/2012
ሶሎሞን በየነ