አዲስ አበባ፡- የጀርመን መንግሥት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የለውጥ ሂደት በመደገፍ ለተለያዩ ተግባራት የሚውል የ74 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ ወይም የ2 ነጥብ 4 ቢሊን ብር ድጋፍ ለማድረግ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ተፈራረመ።
የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ አድማሱ ነበበ የፊርማ ስምምነቱን አስመልክተው ሲናገሩ ጀርመን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሁሉን አቀፍ የለውጥ ሂደት ያበረከተችው ድጋፍ ለተለያዩ ተግባራት የሚውል ሲሆን በዋናነትም ከአግሮ ኢንዱስትሪ ጋር በማያያዝ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት፤ በጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም በመካከለኛ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራው ጋር በተያያዘ እና ሌሎች ተያያዥ ዘርፎች ይውላል ተብሏል።
የጀርመን መንግሥት አሁን ከተፈራረመው የድጋፍ ስምምነት በተጨማሪ ቀደም ሲል ለውጡን በመደገፍ ከ100 ሚሊየን ዩሮ በላይ እንደሚሰጥ ቃል መግባቱን አስታውሰው በቅርቡም በዝርዝር ጉዳዩ ላይ ተነጋግረው እንደሚፈራረሙ መግባባት ላይ መደረሱን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እያደረገች ባለችበት በዚህ ወቅት ከጀርመን መንግሥት እንዲህ ዓይነት ድጋፍ ማግኘቷ ራዕይዋን እውን ለማድረግ ትልቅ ትርጉም እንዳለው የገለጹት ምኒስትር ዲኤታው ስለተደረገው ድጋፍ በኢትዮጵያ መንግሥት ስም ምስጋና አቅርበዋል።
በጀርመን በኩል የድጋፍ ስምምነቱን የተፈራረ ሙት በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ብሪታ ዋግነር በበኩላቸው እንደገለጹት የጀርመን መንግሥት ኢትዮጵያ የጀመረችውን የኢኮኖሚ ሪፎርም ለመደገፍ ፅኑ አቋም አላት። የድጋፍ ስምምነትም ይህንኑ ሃሳብ የሚያጠናክር መሆኑን አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2012
ኢያሱ መሰለ