•የኦሮሞን አንድነት ለመበተን ለሚሰሩ ኃይሎች በር መክፈት የለበትም
•መንግስት ሕግን በማስከበር ረገድ ኃላፊነቱን ይወጣል
•ከሌላ ቦታ መጥተው ችግር የፈጠሩ አካላት በቁጥጥር ሥር ውለዋል
አዲስ አበባ፡- የኦሮሞ ህዝብ በተራዘመ ትግልና መስዋዕትነት ያገኘውን ድል ለመቀልበስና ልዕልናውን ለመናድ በተደራጀ መልኩ በተለያየ መንገድ የሚሰሩ ኃይሎች መኖራቸውን ተገንዝቦ መስራትና አንድነቱን መጠበቅ እንደሚገባው የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ አሳሰቡ፡፡ የኦሮሞን ህዝብ ጥቅምና ጥያቄ ለድርድር የሚቀርብ ባለመሆኑም መንግስት ሕግን በማስከበር ረገድ ኃላፊነቱን እንደሚወጣም አረጋግጠዋል፡፡
አቶ ሽመልስ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ የኦሮሞን ህዝብ ልዕልና የማይፈልጉ ኃይሎች ውጥናቸውን ለማሳካት ያላቸው እድል በማደናገር የኦሮሞን አንድነት ማፈራረስ ነው፡፡ በዚህም በህዝቡ መካከል ልዩነትን ከመፍጠር ጀምሮ የኦሮሞ አመራሮችን የማጋጨት፣ የቄሮና ቀሬ ህብረትን መናድ እና መሰል የህብረት ሰንሰለቶችን መበጣጠስ ዓላማ ያደረጉ ናቸው፡፡
እነዚህ ኃይሎች ውጥናቸውን ለማሳካት አቅደውና በጀት መድበው ጭምር እየሰሩ እንደሚገኙ ህዝቡ ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል፤ አቶ ሽመልስ በመግለጫቸው፡፡ ለእቅዳቸው መሳካት ብሔርና ሃይማኖትን ተገን አድርገው ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመው፤ የኦሮሞ ህዝብ ታግሎና መስዋዕትነት ከፍሎ ያመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል የእነዚህን ኃይሎች ሴራ ተገንዝቦ አንድነቱን ማጠናከርና ክፍተት መፍጠር የለበትም ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ሽመልስ ገለጻ፤ ከአክቲቪስት ጀዋር ጋር በተያያዘ ከትናንት በስቲያ በተፈጠረው የተሳሳተ መረጃን ምክንያት በማድረግ በርካታ የኦሮሞ ልጆች በሰላማዊ መንገድ ስሜታቸውን ለመግለጽ የወጡና በሰላምም ሀሳባቸውን ገልፀው የተመለሱ ቢሆንም፤ ይሄን አጋጣሚ ላልተገባ ተግባር የተጠቀሙበት ጥቂት አካላት አሉ፡፡ በዚህም የዝርፊያና ንብረት የማውደም ብሎም የሰው ህይወት እስከማጥፋት የደረሰ ተግባር ተፈጽሟል፡፡ ይህ ደግሞ መሆንያልነበረበት እና ሊደገም የማይገባው ነው፡፡ ከሌላ ቦታ መጥተው ችግር የፈጠሩ አካላት በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ክስተት የኦሮሞን ህዝብ ውድቀት ለሚመኙ ኃይሎች ደስታን የፈጠረ፤ ይልቁንም ችግሩ እንዲባባስ ተግተው እንዲሰሩ ያነሳሳ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሰፊው የኦሮሞ ህዝብ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ቄሮና ቀሬዎች ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር ሆነው ባደረጉት ሰፊ ጥረት ችግሩ ሳይባባስ ከሽፏል፡፡ ይህ ተግባር የሚመሰገንና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው፡፡ በቀጣይም ህዝቡ አንድነቱን ጠብቆ፣ በባህሉ መሰረት ተነጋግሮና ተደጋግፎ በመስዋዕትነት ያገኘውን ለውጥ ለማስቀጠልና ሰላሙን ለማስጠበቅ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
መንግስት ለአክቲቪስት ጀዋርም ሆነ ሌሎች ከውጭ ለገቡ አካላት ተገቢውን ጥበቃ እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሽመልስ፤ ሕዝቡን ያደናገረው ክስተት ለምን እንደተፈጠረ፣ ለጉዳዩም ምሽት ለምን እንደተመረጠና በሂደቱ እነማን እንደተሳተፉ የማጣራት ስራ እንደሚከናወንና ውጤቱም ለህዝቡ ይፋ እንደሚደረግ አቶ ሽመልስ ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በአክቲቪስት ጃዋር መሃመድ ላይ በመንግስትም ሆነ በፖሊስ በኩል ምንም ዓይነት እርምጃ እንዳልተወሰደ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንደሻው ጣሰው ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት አክቲቪስት ጃዋር መሃመድ ለደጋፊዎቻቸውና ለተከታዮቻቸው ‹‹ልታሰር ነው፤ጥቃት ሊደርስብኝ ነው›› በማለት መልዕክት ማስተላለፋቸውን ቢገልፅም በአክቲቪስት ጃዋር መሃመድ ላይ በመንግስትም ሆነ በፖሊስ በኩል እርምጃ አልተወሰደም ብለዋል፡፡
ግለሰቡ እንደተለመደው የየዕለት ተግባራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ ያሉት ኮሚሽነር እንደሻው ፖሊስ ለውጡን ተከትሎ ወደ ሀገር የገቡ አክቲቪስቶች እና ፖለቲከኞች በሚኖሩበት አካባቢ ችግር እንዳያጋጥማቸው የጥበቃ ከለላ ሲያደርግ ቆይቷል ነው ያሉት።
በሀገሪቱ ያለው ሁኔታ እየተረጋጋ እና ሰላም እየተረጋገጠ በመምጣቱ እንደማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል በሰላም መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ከግንዛቤ በማስገባት የግል ጠባቂዎችን ስናነሳ ቆይተናል ነው ያሉት።
ለወደፊትም ባሉት አሰራሮች መሰረት አስፈላጊ በሆነበት ስፍራን በመለየት ይህ ስራ በፖሊስ ውስጥ ሲከናወን የነበረ ተግባር ነው፤ወደ ፊትም ይከናወናል ብለዋል።
በመሆኑም በየትኛውም ፖሊስ ሆነ አካል የተወሰደ እርምጃ እንደሌለ እና ህብረተሰቡም ይህንን በአግባቡ እንዲያውቅ እንፈልጋለን ነው ያሉት ኮሚሽነር እንደሻው።
ወጣቶች፣ ህብረተሰቡ እና የፀጥታ አካላት የተዘጉ መንገዶች እንዲከፈቱ በማድረግ ህብረተሰቡ በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀስ እንዲያደርጉ አሳስበው፤ ህብረተሰቡ በየአካባቢው የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችን በመቆጣጠር የተጀመሩ የልማትና የሰላም ስራዎች እንዲቀጥሉ የየራሳቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር