ምርጫ 2012ን ለማካሄድና ስኬታማነት ወሳኙ ጉዳይ ምንድን ነው? ስትል አዲስ ዘመን ጋዜጣ ትጠይቃለች። ምርጫውን ነፃ፣ ፍትሐዊና በህዝብ ዘንድ ተአማኒ ለማድረግስ መሟላት ወይም መስተካከል የሚገባቸው ወሳኙ ጊዜ ወይስ የፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት?
ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ የህብር ኢትዮጵያ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንደሚያስረዱት ፓርቲያቸው ምርጫ ለማከናወን ጊዜው ይበቃል፤ ችግር የለውም የሚል አቋም አለው። ምርጫው በተያዘለት ጊዜ መካሄዱ ምንም ችግር የለውም። ‹‹ኢህአዴግ ምርጫውን ማከናወን እችላለሁ፤ የመንግሥትነቴን ሚና በአግባቡ እወጣለሁ የሚል ቁርጠኝነት አለው፤›› በማለቱ ፓርቲያቸው ችግር እንደሌለበት አስታውቀዋል።
በዚህም መሰረት የዝግጅትም ሆነ የጊዜ ችግር የለም። ነገር ግን ፓርቲያቸው በፕሮፖዛል ደረጃ ኢትዮጵያ ለምርጫው ምቹ አይደለችምና ምቹ እናድርጋት፤ ይህን ለማሳካት ደግሞ በፓርቲዎች የተነሳ አንዳንድ አካባቢዎች ያለው ከፍተኛ ችግር በፍጥነት ይፈታ ሲሉ ጠይቀዋል።
የምርጫ ቦርድ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስ በበኩሏ ምርጫውን ነፃ ፍትሐዊና በሁሉም ዘንድ ተአማኒ ለማድረግ ጊዜ ለእኛ አንዱ ተግዳሮት ነው ትላለች። የሪፎርሞቹ ብዛትና ያለን ጊዜ በንፅፅር አስቸጋሪ ነው። የጊዜ እጥረትን መቀየር ከአቅም በላይ ቢሆንም ይህን እያጣመሩ መሄድ ደግሞ ግድ ነው።
በእርግጥ ለእነዚህ ተግባራት ከጊዜ ይልቅ ቁርጠኝነቱ በጣም አስገፈላጊ ነው ብላለች። ‹‹ምርጫው እንዲከናወን የጊዜ መለኪያነቱ የፓርቲዎች ዝግጅትን ተመስርቶ መሆን የለበትም፤ ምርጫው በፓርቲዎች መዘጋጀት አለመዘጋጀት ላይ ሳይሆን መመስረት ያለበት በተቋማት ብቃት ሊወሰን ይገባል። ያልተዘጋጀ ፓርቲ ለሚቀጥለው ምርጫ ይዘጋጃል።›› ሲሉ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ሊቀመንበር አቶ የሸዋስ አሰፋ ይናገራሉ።
የመድረክ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በበኩላቸው ‹‹እኛ መጀመሪያውኑ ምርጫው በጊዜ ሰሌዳው መሰረት እንዲፈፀም እንፈልጋለን። አቋምም ይዘን ስንቀሳቀስ ቆይተናል። እሱ ላይ ምንም ብዥታ የለብንም። ነገር ግን የተሳካ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንዲካሄድ የተለያዩ ነገሮች መከናወን አለባቸው›› ሲሉ ያመለክታሉ።
ፕሮፌሰሩ በተቻለ መጠን ከምርጫው በፊት ከጊዜ ይልቅ ቁርጠኝነት በሚጠይቁ ወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረስ ይገባል ይላሉ። በመሆኑም የሀገሪቱን አንድነት በተመለከተ፣ በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ዙሪያ፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን በመገንባት፣ የፖለቲካ ሥርዓቱን በሚመለከት ፍትሐዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ሊፈጠር ይገባል። ኢህአዴግን ጨምሮ ፓርቲዎችን በቁርጠኝነት ልዩነቶቻቸውን ማጥበብ እንደሚገባቸውም ጥሪ ያቀርባሉ።
እንደ አቶ የሸዋስ ገለፃ የዴሞክራሲ ተቋማት በተለይ ደግሞ ነፃና ገለልተኛ ተቋም ከሌለ ከምርጫ በፊትና በኋላ ውዝግብ ቢነሳ ሀገሪቱን ይጎዳታል። ኢትዮጵያ እንደሀገር ምርጫውን ማድረግ አለባት ወይስ የለባትም ነው ንግግሩ፤ ጉዳዩ ፓርቲዎች ይገባሉ አይገቡም የሚለው መሆን የለበትም ሲሉ ይከራከራሉ።
‹‹ቀጣዩ ምርጫ መቼም ይደረግ መቼ እንዳለፉት አምስት ምርጫዎች መሆን የለበትም። ምክንያቱም ከዚህ በፊት የነበሩ ምርጫዎች የኢትዮጵያ ህዝብ በመረጠው እንዲተዳደር ያደረጉ አይደሉም፤ በጡጫ የመጣ አካል ራሱን ያስቀጠለበት ነው። ልክ እንደንጉሡ፣ እንደደርግ ዓይነት ገፅታ ያለው ነበር።›› አቶ የሽዋስ ይናገራሉ።
አሁን በሚዲያዎች መሻሻል እየታየ ያለው በትንሽ የለውጥ ፈላጊዎች መልካም ፈቃድ ብቻ ነው ያሉት አቶ የሺዋስ ስለሆነም ተግባራዊ ለውጥ የሚሽቱ በእርግጥ የፖለቲካ አመራሩን ቁርጠኝነት የሚጠይቁ እንጂ ጊዜ የሚሹ አይደሉም ባይ ናቸው።
እንደ ወይዘሪት ሶሊያና ገለፃ የምርጫ ፍትሐዊነት በምርጫ አስፈፃሚዎች ሚና ብቻ የሚወሰን ሳይሆን የሌሎች ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎና ቁርጠኝነት ይፈልጋል። በምርጫ ቦርድ በኩል የጊዜ ችግር የለም፤ ከዚህ ባለፈ ግን የእነዚህ አካላት ሚና ለብሔራዊ ምርጫው ስኬት እኩል አስፈላጊ ናቸው ብላለች።
ምርጫ ቦርድ እንደ ተቋም ብቻውን የሚያከና ውነው የምርጫ ሥራ የለም። ተአማኒ፣ ፍትሐዊና ነፃ ምርጫ ለማከናወን ምርጫ ቦርድ ብቸኛው ባለድርሻ አካል አይደለም የምትለው ሶሊያና ከምርጫ ቦርድ ውጪ ያሉ ባለድርሻ አካላት አዎንታዊ ሚናሊጫወቱ ይገባል። ፓርቲዎች የምርጫውን ሂደት በሰላማዊ መንገድ መምራት፤ መንግሥትና የመገናኛ ብዙሃን ሰላምና ደህንነትን ማስጠበቅ ቁርጠኛ ሆነው የሚጠበቅባቸውን ሚና እና ሥራ መሥራት ይገባቸዋል።
‹‹ላለፉት 28 ዓመታት ሲያወዛግበን የነበረው ቁርጠኝነት ጠፍቶ ነፃም ገለልተኛም ተቋምና ሰዎችን መፍጠር አለመቻል ነው፤›› ከዚህ በኋላ ኢህአዴግ በቁርጠኝነት ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ሆኖ የተረጋጋና ሰላማዊ ሁኔታ እንዲፈጠር ፓርቲው የገባበትን ገመድ ጉተታ ትቶ በሀገሪቱ ያሉትን የዴሞክራሲ ተቋማት ‹‹ለውጥ›› በሚለው ሂደቱ ታች ድረስ እንዲወርድ መሥራት ይጠበቅበታል። እነዚህ ከተሠሩ ጊዜ ሳይሆን ቁርጠኝነት ብቻ ነው የሚያስፈልገው ሲሉ ፕሮፌሰር መረራ ይገልፃሉ።
ብዙ ጊዜ የማይወስድ ነገር ግን ምርጫው ላይ የራሱ ጫና ሊፈጥር የሚችል ጉዳይ አለ የሚሉት ኢንጂነር ዘለቀ። ‹‹በፓርቲዎች መካከል ባለው ችግር ምርጫውን ስናካሂድ አሁን በሚስተዋለው ተለያይተን ነው? ወይስ ግንባር ተፈጥሮ? ይህ ጉዳይ መመለስ አለበት፤›› ይላሉ።
አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳስቀመጡት የምርጫው መከናወን አለመከናወን ሊወሰን የሚገባው መሠራት ያለባቸው ወሳኝ ተግባራት ሙሉ በሙሉ ሲከናወኑ ነው። ይህ ደግሞ አገሪቱ ካላት በቂ ተሞክሮ ጊዜ የሚጠይቁ ሳይሆኑ ፓርቲዎችንም ሆነ መንግሥትን በተለይ ደግሞ የህዝቡን ቁርጠኝነት የሚጠይቁ ናቸው። ይህ ካልሆነ ግን ዳግም አዙሪት ውስጥ እንዳይገባ ሥጋታቸውን አስቀምጠዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2012
ሀብታሙ ስጦታው