ሐሙስ ጥቅምት 1o ቀን 1959 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ 26ኛ ዓመት ቁጥር 548 ዕትም “ልሰርቅ ሔጄ ጠጅ አስክሮኝ አስያዘኝ” በሚል ርዕስ የአንድ ሌባን ታሪክ እንደሚከተለው አስነብቧል፡፡
ልሰርቅ ሔጄ ጠጅ አስክሮኝ አስያዘኝ
አባዲ ተስፋዬ መስከረም 10 ቀን 1959 ዓ.ም ከሌሊቱ አምስት ሰዓት ላይ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር ሆኖ የአቶ ካህሳይን ቤት ለመስረቅ ሄዶ ፤ ከዚያም ሲደርሱ በሩ ስለተዘጋባቸው በዕድሜና በሰውነት ያነሰው አባዲ በአጥር ተንጠልጥሎ ገባ፡፡ አባዲ የቤቱን በር ከፍቶ እንደገባ እያማረጠ ለመስረቅ ጥሩ ጊዜ ሆነለት ፤ በዚህ ሁኔታው የሰረቀውን ዕቃ በማመላለስ እያጋዘ እውጪ ካስቀመጠ በኋላ ጠጅ ጠጅ ሸተተው፡፡ ወደኋላው መለስ ቢል ጠጅ የሞላ በርሜል አየ፡፡ ጎንበስ ቢል የውሃ መቅጃ ቆርቆሮ አገኘ፡፡ ከዚህ በኋላማ ምን ይጠየቃል ፤ ራሱን በራሱ ጋባዥ ሆነ፡፡ ከዚያ በኋላ ስካር ተጫጭኖት ስለተሸነፈ አባዲ ከወደቀበት ስፍራ ሳይነሳ በዚያው ተኝቶ አደረ፡፡
በማግስቱ ጠዋት ባለቤቶቹ ከእንቅልፋቸው ተነስተው ቤት ሊጠርጉ ሲሉ አባዲ ተጋድሞ አገኙት፡፡ ወዲያው በፖሊስ አስያዙት፡፡ ከዚያም ወደማረፊያ ቤት ተወስዶ በወታደር ደስታ በቃኸኝ አማካይነት ቃሉን ሲሰጥ ፣ ከላይ እንደተገለጠው “ለመስረቅ ሔጄ ጠጅ አስክሮኝ በዚያው ተኛሁ” ሲል አረጋግጧል ብለው ሻለቃ ጌራ ወርቅ ገልጠዋል፡፡
በትግሬ ግዛት የኢትዮጵያ የወሬ ምንጭ
******
ሐሙስ መስከረም 28 ቀን 1963 ዓ.ም የወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ 30ኛ ዓመት ቁጥር 235 ዕትም አጭር ቀሚስ በመልበሳቸው ምክንያት ስለተቀጡ ሴቶች አጭር ዜና አስነብቦ ነበር፡፡
አጭር ቀሚስ የለበሱ ሁለት ሴቶች 30 ብር ተቀጡ
ባህር ዳር (ኢዜአ)፡- ሱፐር ሚኒ ለብሰው በባህር ዳር ከተማ ሲዘዋወሩ የተገኙ ሁለት ሴቶች እያንዳንዳቸው 15 ብር መቀጫ እንዲከፍሉ የባህር ዳር ወረዳ ፍርድ ቤት ከትናንት በስቲያ በዋለው ችሎት ፈረደ፡፡
በማታ ክበብ ባሻሻጭነት የሚሠሩ የ15 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አልማዝ በላይና ሙሉ ካሤ የተባሉት እነዚሁ ወጣቶች በጣም አጭር የሆነ ቀሚስ ለብሰው በምሽት ሰዓት በከተማው ሲዘዋወሩ የተያዙት በፖሊሶች ተከታታይነት ነው፡፡ ተከሳሾቹ በዚሁ አፈጻጸማቸው ተከሰው ባህር ዳር ወረዳ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ፤ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 660ና 799 በሚያዘው መሰረት እያንዳዳቸው 15 ብር እንዲከፍሉ የተበየነባቸው መሆኑን አንድ የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ ገልጧል፡፡
******
ዕሁድ ነሐሴ 5 ቀን 1960 ዓ.ም የወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ 28ኛ ዓመት ቁጥር 83 ዕትም በቬትናም አገር የሆነን አስገራሚ ታሪክ እንደሚከተለው አስነብቦ ነበር፡፡
በንቅሳቱ ሲፎክር ከነቆዳው ተገፈፈ
የደቡብ ቬትናም የጦር ሠራዊት ባልደረባ የሆነው አስር አለቃ ዶን ቫን ኮኑም “ቤትኮንጎዎችን ግደሉ” የሚል ቃል እደረቱ ላይ ተነቅሶ ነበር፡፡ ይህም ንቅሳት ኩራት አሳድሮበት ነበር፡፡ በኋላ ግን ከዕለታት አንድ ቀን በቤተኮንግ ወታደሮች ተማረከ፡፡ እነርሱም የደረቱን ንቅሳት ለማጥፋት ሲሉ ቆዳውን ገፈው ለቀቁት፡፡ ይኸውም ለሌሎች ምሳሌ ይሆናል በማለት ነው፡፡
ነገር ግን አስር አለቃ ኮኑም በደረቱ ጠባሳ ላይ እንደገና “ቤትኮንጎዎችን ግደሉ” የሚል ቃል አስነቅሷል፡፡ ምናልባትም እንደገና ተማርኮ ቤትኮንጎዎች እንደ ገና ንቅሳቱን ከገፈፉት በድጋሚ እነቀሰዋለሁ የሚል እምነት አለው፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2012
የትናየት ፈሩ