የአዕምሮ ህክምና አገልግሎት በቅዱስ አማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለረጅም ጊዜ ሲሰጥ መቆየቱ ይታወቃል፤በአሁኑ ወቅት ደግሞ የሕፃናትና ወጣቶች አዕምሮ ህክምና አገልግሎት ራሱን ችሎ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅና በየካቲት አስራ ሁለት ሆስፒታሎች ውስጥ ህክምናው እየተሰጠ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እየተሰጠ ባለው የሕፃናትና ወጣቶች አዕምሮ ህክምና አገልግሎት ዙሪያ ከሆስፒታሉ የህብረተሰብ አዕምሮ ጤና ሳይንስ ስፔሻሊስትና በህክምና ክፍሉ እየሠሩ ከሚገኙት ዶክተር ትግስት ዘርይሁን ጋር ያደረግነውን አጭር ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
በህክምና ክፍሉ የሚሰጡት የአዕምሮ ህክምና አገልግሎቶች
በሆስፒታሉ የሕፃናትና ወጣቶች አዕምሮ ህክምና አገልግሎት መስጠት የተጀመረው እ.ኤ.አ ከ2008 ወዲህ ነው። በአሁኑ ወቅትም ተመላላሽ የሕፃናትና ወጣቶች የአዕምሮ ህክምና፣ ለአዕምሮ ታማሚ ሕፃናት፣ ወጣቶችና ለወላጆቻቸው የምክር እና የንግግር ህክምና /psychotherapy/ የጨዋታ ህክምና /play therapy/ አገልግሎቶች ይሰጣሉ።
በስፋት ደግሞ የአድገት ውስንነት ላለባቸው ሕፃናትና ወጣቶች ወላጆችና ተንከባካቢዎቻቸው ስልጠና በመስጠት ከስልጠናው በኋላ በራስ አገዝ ህብረት እንዲታቀፉ የማድረግ ሥራዎች ይሠራሉ። የአዕምሮ ህክምና ትምህርት ክፍሉ በበጎ ፍቃደኝነት በትምህርት ቤቶች በአዕምሮ ጤንነት ዙሪያ ለተማሪዎች፣ መምህራንና ወላጆች ስልጠናዎችንና የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን ይሰጣል።
ህክምናውን በብዛት የሚከታተሉት ወጣቶች የሚገኙበት የዕድሜ ክልል
የህክምና ክፍሉ ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር ጀምሮ ላሉ ሕፃናትና ወጣቶች የህክምና አገልግሎቱ ይሰጣል። ታካሚዎቹ ወደ ህክምና ክፍሉ የሚመጡት ከተለያዩ አካባቢዎች ሲሆን፣ ለሕፃናት የአዕምሮ ህክምና ትልቁና ዋነኛው ምንጭ በራሱ በሆስፒታሉ ውስጥ የሚገኘው የሕፃናት ህክምና ክፍል ነው።
ከሌሎች ሆስፒታሎች ተልከው የሚመጡ ሕፃናትም በዚሁ ክፍል ውስጥ ይታከማሉ። በትምህርት ቤቶችና በሕፃናትና ወጣቶች ጤና ላይ የሚሠሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችም የአዕምሮ ህመም ያለባቸውን ሕፃናትና ወጣቶችን ወደ ህክምና ክፍሉ ይልካሉ። ቤተሰብም በተመሳሳይ በራሱ ተነሳሽነት ልጁን ለማሳከም ወደ ህክምና ክፍሉ ይመጣል።
በአማካይም በወር ከ120 አስከ 130 የሚሆኑ ሕፃናትና ወጣቶች በህክምና ክፍሉ የአዕምሮ ህክምና ይደረግላቸዋል። የአዕምሮ ጤና ችግር በሁሉም ዕድሜ ክልል ላይ በሚገኙ ወጣቶች ዘንድ የሚከሰት ከመሆኑ አኳያ ህመሙ በየትኛው የዕድሜ ደረጃ እንደሚበዛ መናገር አይቻልም።
የህክምና አገልግሎቱ ተደራሽነትና ጥራት
በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጣቶች የአዕምሮ ህክምና አገልግሎት የሚሰጠው በአዲስ አበባ በሚገኙ በሁለት ሆስፒታሎች ብቻ ነው። ሁለቱም ሆስፒታሎች በዋናነት የሚሰጡት የህክምና አገልግሎት የተመላላሽ የአዕምሮ ህክምና ነው። የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል አሳሳቢና ድንገተኛ የሆኑ የአዕምሮ ህክምና አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችል የራሱ አልጋና በዘርፉ የሰለጠኑ የህክምና ባለሞያዎች የሉትም። በመሆኑም እየተሰጠ ያለው የህክምና አገልግሎት ሁሉን ያማከለና ተደራሽ ነው ማለት አይቻልም። ለዚህም ሆስፒታሉ የተለያዩ ፕሮግራሞችንና ስልጠናዎችን በማዘጋጀት በተለይ ወላጆችን በማሰልጠን ህመሙን ለይተው ልጆቻቸውን ወደ ህክምና ተቋም ይዘው እንዲመጡ እየረዳ ይገኛል።
በህክምና ክፍሉ የሚያጋጥሙ ችግሮች እና ለመፍታትስ የሚደረጉ ጥረቶች
የሕፃናትና ወጣቶች የአዕምሮ ህክምና አገልግሎትን በበቂ ሁኔታ እንዳይሰጡ ካደረጉ ችግሮች ውስጥ አንዱ የቦታ እጥረት ነው። ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት ሆስፒታሉ ቦታ እያዘጋጀ ይገኛል። በቦታው ላይም ተመላላሽ ህክምናም ሆነ የድንገተኛና አስተኝቶ ህክምና አገልግሎቶች የሚሰጡ ይሆናል።
ሌላው እንደችግር የሚጠቀሰው የመድሃኒት አጥረት ሲሆን መድሃኒቶቹ በዓይነትም ሆነ በመጠን የተስተካከሉ አይደሉም። አንዳንዶቹም ተፈላጊ ቢሆኑም በሀገር ውስጥ እንደልብ አይገኙም። ቢገኙም መድሃኒቶቹ ውድ ከመሆናቸው አኳያ የመግዛት አቅምን ይፋተናሉ። ይህንንም ታሳቢ በማድረግ መድሃኒቶቹ በአግባቡ ለተጠቃሚዎች እንዲደርሱ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ።
ህብረተሰቡ በሕፃናትና ወጣቶች የአዕምሮ ጤና ላይ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ በመሆኑ ዘመናዊ ህክምናን እንደ መጨረሻ አማራጭ የመውሰድ ሁኔታዎች ይታያሉ። በዚሁ የግንዛቤ ማነስ ምክንያትም ሕፃናትና ወጣቶች በጊዜ ወደ ህክምና ተቋማት አይመጡም። ይህም ሕፃናትና ወጣቶቹ ከራሳቸው አልፈው ለወገንና ለሃገራቸው እንዳይተርፉ አድርጓል። ለዚህም ለወላጆች፣ተማሪዎችና መምህራን የግንዛቤ ማስጨበጫዎች እየተሰጡ ነው።
የአዕምሮ ጤና ችግር ያለበት ደረጃ እና የመከላከሉ ሥራ
የአዕምሮ ህክምና ክፍሉ በሆስፒታሉ ውስጥ ከተቋቋመ ወዲህ የተገልጋዮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚከሰቱ የአዕምሮ ህመሞች በሃገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃም እየጨመሩ መጥተዋል። የግንዛቤ ማነስ፣ የወጣቶች አካላዊና አዕምሯዊ ለውጦች፣ እፆችን መጠቀምና ሌሎችም ምክንያቶች ለህመሙ መጨመር የራሳቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
የአዕምሮ ጤና በግለሰብ ፣በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና በሃገር ኢኮኖሚ ላይ ያሚያስከትለው ተፅእኖ የጎላ በመሆኑ መከላከል ትልቁ መፍትሔና ውጤትም የሚያስገኝ ነው። የአዕምሮ ዕድገት የሚጀምረው ገና ከፅንስ በመሆኑ በእነዚህ ጊዜያት ላይ በቅንጅት መሥራት የአዕምሮ ጤና ችግሮች መከሰትን ለመቀነስ ያስችላል። የአዕምሮ ህመምን እንዴት መከላከል፣መለየትና በችግር ውስጥ ያሉ ሕፃናትንና ወጣቶችን እንዴት መርዳት እንደሚቻል የማህበረሰቡን ግንዛቤ መጨመር ያስፈልጋል። ህመሙ አንዴ ከተከሰተ በኋላም ማከምና ማሻሻል ስለሚቻል የህክምና አገልግሎቱን በስፋት ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ ይገባል። የአዕምሮ ጤና ችግር ያለባቸው ሕፃናትና ወጣቶች ተለይተው ከታከሙ በኋላ ወደ ማህበረሱበ ሲቀላቀሉ ነፃ ሆነው የራሳቸውን ህይወት መምራት እንዲችሉ ማገዝ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሞያዊ ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን!!
ዶ/ር ትግስት፡- እኔም አመሰግናለሁ!!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11/2012
አስናቀ ፀጋዬ