በሱዳን ካርቱም የዳቦና የነዳጅ ዋጋ ንረትን መነሻ በማድረግ ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም እየተስፋፋ ነው፡፡ በሱዳን ከአንድ ዓመት ወዲህ የእያንዳንዱ ሸቀጣሸቀጥ ዋጋ በሁለት እጥፍ ጭማሪ አሳይቷል ፤ የዋጋ ግሽበቱም ሰባ በመቶ ያህል ደርሷል፡፡ በዚህም ህዝቡ የኑሮ ውድነቱን መጋፈጥ ባለመቻሉ አሁን ፊቱን ወደ መንግሥት አዙሯል በማለት አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በኑሮ ውድነት ምክንያት ከቀናት በፊት የተቀሰቀሰው ይህ ህዝባዊ አመጽ አሁን ላይ መልኩን ቀይሮ ሌሎች የሀገሪቱን ክልሎችም እያዳረሰ ነው፡፡ አልጀዚራ ሂባ ሞረጋን ከተባለው ጋዜጠኛ አገኘሁት ባለው መረጃው እንዳተተው፤ ህዝባዊ አመጹ አሁን የዳቦ ጥያቄውን ወደጎን ትቶ ለሦስት አስርት ዓመታት በስልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዚዳንት ኦመር ሀሰን አል በሽር ከስልጣናቸው እንዲነሱ ጥያቄ ወደ ማቅረብ ተሸጋግሯል ይላል፡፡
ተቃውሞውም ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተስፋፋ በመሄዱም ከካርቱም በስተ ደቡብ ምዕራብ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኡም ሩዋባ ከተማ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ተቃዋሚዎች አደባባይ ወጥተው ሥርዓቱ ይቀየርልን፤ ለውጥ እንፈልጋለን በማለት መዝሙሮችንና መፈክሮችን ሲያሰሙ ተደምጠዋል፡፡ በስተሰሜን ከካርቱም 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አትባራ ከተማም እንዲሁ ሲቨል ልብስ የለበሱ ደህንነቶችና አድማ በታኝ ፖሊሶች በጋራ ሆነው የተቃውሞ ሰልፈኞቹን በአስለቃሽ ጭስ ለመበተን ሲሞክሩ ታይቷል፡፡ በሌሎች አካባቢዎችም ቢሆን መሰል ክስተቶች እየተከናወኑ ስለመሆኑ አመላካቾች አሉ፡፡
ፖሊሶች አስለቃሽ ጋዝና ቆመጥ በመያዝ የትምህርት ቤቶችንና የዩኒቨርሲቲዎችን ቅጥር ግቢ በአይነ ቁራኛ እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡ እንደውም አንዳንድ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲውን ልቀቁ መባላቸውንም ተናግረዋል፡፡
በካርቱም ከተማ የሚገኙት ዳቦ ቤቶች ሰልፍ የበዛባቸው ሆነዋል፡፡ ዳቦ ሻጮቹም ለአንድ ሰው ከ20 ቁርጥራጭ ዳቦ በላይ እንዳይሸጡ ቁጥጥር እየተደረገባቸው ነው፡፡ ሸማቾች በተቃራኒ እንድንገዛ የተፈቀደልን ዳቦ ከቤተሰቦቻችን ቁጥር አንጻር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም በሚል ቅሬታቸውን እያሰሙ ይገኛሉ፡፡
ሱዳን ኢኮኖሚዋ እየተዳከመ የመጣው እ.አ.አ በ2011 ሦስት አራተኛው የሚገመተውን የነዳጅ ጉድጓድ ለደቡብ ሱዳን ካስተላለፈች በኋላ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሱዳን አሸባሪዎችን ትረዳለች በሚል ተጥሎባት የነበረው ማዕቀብ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ እንዳታገኝ አድርጓታል ፡፡ ሱዳን ለ20 ዓመታት ተጥሎባት የነበረው ማዕቀብ እ.አ.አ ጥቅምት 2017 የተነሳላት ቢሆንም በነዚህ ጥቂት ዓመታት እንኳን ኢኮኖሚዋ መሻሻል አልታየበትም፡፡
ለዳቦ ዋጋ መጨመር እንደምክንያት የሚጠቀሰው መንግሥት ስንዴን ከውጭ በማስገባት ህዝቡን ይደጉም የነበረውን አሠራር አቁሞ ለግል አሰመጪዎች ብቻ በመተዉ ነው፡፡ በዚህም በህዳር ወር ብቻ የዱቄት አቅርቦቱ 40 በመቶ ዝቅ በማለቱ ብዛት ያላቸው ዳቦ ቤቶች ከሥራ ውጭ ሆነዋል፡፡
በሀገሪቱ የተከሰተው የዋጋ ግሽበት 70 በመቶ መድረሱን ተከትሎም ከመስከረም ወር ጀምሮ የሱዳን ፖውንድ ከአሜሪካን ዶላር ጋር ሲነጻጸር የመግዛት አቅሙ 85 በመቶ እንዲወርድ አስገድዶታል፡፡ ሱዳን በጥቅምት ወር 29 ዶላር ይመነዘር የነበረውን የአገሯን ገንዘብ ወደ 40 ነጥብ 5 ዶላር ያሳደገች ሲሆን፤ ይህም በአገሪቱ ለሚታየው የዋጋ መጨመር ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡
የሱዳን ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ (ሱና) ኳታር ሱዳን ከገባችበት ቀውስ እንድትወጣ የገንዘብ እርዳት ለማድረግ መዘጋጀቷን በመዘገብ ህዝባዊ አመጹን ለማርገቢያነት ቢጠቀምበትም ተቃውሞው ግን አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ እንደውም የሀገሪቱ ምሁራንና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃውሞውን እየተቀላቀሉ መጥተዋል፡፡ የሙያ ማህበራት አመራሮች ባስተላለፉት የሥራ ማቆም አድማ የህክምና ባለሙያዎችም ሳይቀሩ አድማውን እንዲቀላቀሉ ጥሪ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡ የአድማው አስተባባሪዎች ሀኪሞች በአድማው መሳተፋቸው መንግሥትን ለማሽመድመድ አጋዥ እንደሆነ በመግለጽ የሥራ ማቆም አድማውን እንዲቀጥሉ ህዝቡም የጎዳና ላይ ተቃውሞውን እንዲያጠናክር እየወተወቱ ነው፡፡
የሱዳን የህክምና ባለሙያዎች ፕሬዚዳንት የሆኑት ሳራ አብደል ጀሊል እንደሚያስረዱት ይህ የአሁኑ ህዝባዊ ተቃውሞ አፋጣኝ ምላሽ ካላገኘና ሱዳን አዲስ የመንግሥት ለውጥ ካላመጣች የከፋ ነገር ሊከሰት እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ፡፡
ዜጎች የተቃውሞ ድምጻቸውን ለማሰማት አደባባይ የወጡት ለዳቦና ለነዳጅ ብለው ነው ብዬ አላምንም፤ እየተቃወሙ ያሉት አጠቃላይ ሥርዓቱን ነው፡፡ በሀገሪቱ የሚገኙት የህክምና ተቋማት እንዳሉ አይቆጠሩም መሰረተ ልማት አልተሟላላቸውም፤ የተሟላ የጤና አገልግሎት ይሰጣሉ ማለት አይቻልም፤ የሚያስከፍሉት ክፍያ ተገቢነት የጎደለው ነው፤ በዚህም ላይ የመድሀኒት እጥረት ያለባቸው ናቸው፡፡ የትምህርት ተቋማትም ሆኑ ሌሎች ዘርፎች እንዲሁ ብዙ ችግሮች ያሉባቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ መንግሥት የተሻለ መምራት ለሚችሉ አካላት ስልጣኑን በመልቀቅ የአገሪቱም ሆነ የህዝቡ ህይወት እንዲለወጥ ማገዝ አለበት በማለት ሳራ አብደል ጀሊል ያስረዳሉ፡፡
በየአካባቢው የሚገኙት ተቃዋሚዎች ቁጥራቸው በመቶና በሺ መካከል ቢሆንም በዚህ አንድ ሳምንት ውስጥ የመንግሥት ወታደሮችን መስደብና የአል በሽርን አስተዳደር መቃወም የቀን ተቀን ተግባራቸው እየሆነ መጥቷል፡፡ የሆስፒታል ሠራተኞችን ጨምሮ የተለያዩ የሙያ ማህበራት ተወካዮች ተቃውሞው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መልዕክት እያስተላለፉ ይገኛሉ፡፡
አንዳንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣ ናትም በሚስጥር ተቃውሞውን እየመራችሁ ነው በሚል እየታሰሩ ይገኛሉ፡፡ በስም ያልተጠቀሱ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትም የተቃውሞው አስተባባሪ ናችሁ በሚል ታስረዋል፡፡ ይህም ሁኔታው እንዲካረር እያደረገና ሱዳንን ወደ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እየከተታት ይገኛል፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆኑት ሳዲቅ የሱፍ እንደሚያስረዱት የፓርቲያቸው ፕሬዚዳንት ፋሩክ አቡ ኢሳን ጨምሮ አሥራ አራት አባላቶች ከስብሰባ ሲወጡ በፖሊስ ተይዘው ወደ እስር ቤት ተወርውረዋል፡፡
የኢኮኖሚ ተንታኙ አቡ አልቃሲም ኢድሪስ ለአልጀዚራ እንዳስረዱት ‹‹በሱዳን የተፈጠረው ተቃውሞና የህዝብ ጥያቄ የኢኮኖሚ መሆኑ ቀርቶ የፖለቲካ እየሆነ መጥቷል ፡፡ይህን ደግሞ መንግሥት ብቻውን ሆኖ የሚፈታው አይደለም፡፡ ስለዚህ ችግሩ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ እየወጣና ሀገሪቱም ወደ ከፋ ቀውስ ውስጥ እየገባች በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገራቸውን ከተጋረጠባት አደጋ ማውጣት እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡
በሱዳን በዋጋ ንረት ምክንያት የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ በመንግሥት ጸጥታ አስከባሪዎችና በተቃዋሚዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ሰዎች መቁሰላቸውንና መሞታቸውን የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ ቢቢሲ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አገኘሁ ባለው መረጃ ግጭቱ በተቀሰቀሰ አምስት ተከታታይ ቀናት ውስጥ ሃያ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን ሲጠቅስ አልጀዚራ ቢያንስ አስር ሰዎች መሞታቸውን ጠቅሷል፡፡ መንግሥት በበኩሉ የሟቾች ቁጥር የተጠቀሰውን ያህል አይደርስም እያለ ነው፡፡
አሁን በሱዳን የተቀሰቀሰው የህዝብ ተቃውሞ አፋጣኝ መፍትሄ ካላገኝ ሀገሪቱ የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት እጣ ፈንታ ሊገጥማት እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞችና የሀገሪቱ ምሁራን ሥጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 18/2011
ኢያሱ መሰለ