ኢትዮጵያ ለዘመናት በውጭ ወራሪዎች ስትፈተን የኖረች ግን አንዴም እጅ ያልሰጠች የአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት የምትባል ታላቅ አገር ናት፡፡ ጠላትን በጋራ የሚመክቱት ዜጎቿ የውጭ ወራሪዎችን በአንድነት ከመለሱ በኋላ ግን በማያባራ የእስር በርስ ግጭት መጠመዳቸው የተለመደ ነበር፡፡ በተለይ ከዘመነ መሳፍንት የጀመረው ይህ ሂደት አገሪቱን አቆርቁዟታል፡፡
በቅርብ ጊዜ ታሪኳ፣ ደርግ የአጼውን ሥርዓት ባስወገደበት ዘመን ቀለም የዘለቃቸው በርካታ ወጣቶች አብዮቱን በመምራት ያደረጉት ተሳትፎ በሃሳብ ልዕልና የበላይነት የሚያገኝ ወገን በምርጫ አሸንፎ ወደ ሥልጣን እንደሚመጣ ተስፋ ቢያጭርም፤ አልተሳካም፡፡ የተፈጠረውን የሥልጣን ክፍተት ተጠቅሞ ወደ ሥልጣን የመጣው ባለጠመንጃው ደርግ አምባገነናዊ ሥርዓት በመዘርጋቱ ሌሎች ሥርዓቱን ለመገርሰስ ጠመንጃ እንዲያነሱ ምክንያት ሆኗል፡፡ በአስተሳሰብ ትግል በማሸነፍ ወደ ሥልጣን የሚመጣበት በር ተዘግቶ የመሳሪያ ትግል የበላይነት በመያዙ የበርካታ ዜጎችን ህይወት ያስገበረው የእርስ በርስ ጦርነት ተከስቷል፡፡
ኢህአዴግ በ1983 ዓ.ም ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ በአገሪቱ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል፡፡ በእዚህም ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገቶች መመዝገባቸው አይካድም፡፡ ይሁንና በፖለቲካው መስክ እመርታዊ ለውጥ ባለመምጣቱና በምርጫ አሸንፎ ሥልጣን የሚያዝበት ምህዳር ባለመስፋቱ በርካታ ያኮረፉ ኃይሎች ተፈጥረዋል፡፡ አንዳንዶቹ ከአገር ወጥተው የቃላት ጦርነት ሲከፍቱ ከፊሎች ደግሞ ነፍጥ አንግበው ሥርዓቱን ለመጣል ሲታገሉ ነበር፡፡ ይህም አገሪቱን የሚመራውን ኢህአዴግ ሲፈታተን የቆየ ሲሆን፤ መሳሪያና ጉልበት እንዲሁም የአስተሳሰብ ልእልና እየተዛነፉ የበላይነት ለመያዝ የሚፎካከሩበት ዘመን እንዲሆን አድርጓል፡፡
በወርሃ መጋቢት 2010 ዓ.ም በኢህአዴግ ውስጥ ተጸንሶ ወደ መንበረ ሥልጣኑ የመጣው በለውጥ መንፈስ የተሟሸው ኢህአዴግ ግን ሁሉም ኃይል በሰላማዊ ትግል በሚያቀርበው የተሻለ አማራጭ ተወዳድሮ አገር እንዲመራ አዲስ ምእራፍ የከፈተ ነው፡፡
‹‹የጠመንጃ ትግል ይብቃ የአስተሳሰብ ትግል ይለምልም›› በሚለው የለውጥ ኃይል በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሾሙትና መደመር በሚለው እሳቤአቸው የሚለዩት ዶክተር አቢይ አህመድም በተያዘው ዘመን የአዲስ ዓመት መልእክታቸው ‹‹አዲሱ ዓመት ለዓመታት ተኳርፈው የዘለቁ ወገኖች እንዲታረቁ፣ የታሠሩ እንዲፈቱ፣ የተለያዩ እንዲገናኙ አስችሏል፡፡ ፍቅርና ይቅርታ፣ መደመርና አንድነት የሚሉ ሐሳቦች በአገራችን ምድርና ሰማይ በጉልህ አስተጋብተው በእውነትም ይህ እርምጃ ከሀገራችን የፖለቲካ አድማስ ላይ ወቅትና ጊዜው ያለፈበትን ጨለማ አስወግዶ በፍቅር ብርሃኑንም፣ አንድአርጋቸውንም፣ ሌንጮንም የሰበሰበ እለት በመሆኑ እጅግ ደስ ይለናል›› ያሉት ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ልዩነት በአስተሳሰብ ትግል እንጂ በጠመንጃ እንደማይፈታ ለማብሰር ነበር።
በእርግጥም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በጀመሩት የመደመር ጉዞ የማይታሰቡ የነበሩ ስኬቶች እውን ሆነዋል፡፡ አንዱና ዋናው በሽብርተኝነት የተፈረጁና በትጥቅ ትግል ጭምር ተሰማርተው የነበሩ ድርጅቶች ወደ ሀገር ቤት መግባታቸው ነው፡፡ በእዚህም ጠመንጃ ጥለው አለን በሚሉት አማራጭ ሀሳብ ተወዳድረው ለማሸነፍ የሰላማዊ ትግል በሩ ወለል ብሎ ተከፍቷል፡፡ ይሁንና አሁንም አለፍ ገደም እያለ ድል በነፍጥ እንጂ በሃሳብ ልእልና አይገኝም የሚል አመለካከት ብልጭ የሚልባቸው ክስተቶች አልጠፉም፡፡
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራል አለማየሁ እጅጉ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፤ በምእራብ ኦሮሚያ ባለፉት አራት ወራት ብቻ በተፈጠሩ ችግሮች 29 ንጹሃን ዜጎች ህይወት መጥፋቱን፣ 12 የፖሊስ አባላት ህይወት ማለፉንም እንዲሁም 77 የፖሊስ አባላት እና 40 ሚሊሻዎች መቁስላቸውን ተናግረዋል፡፡ በመላ አገሪቱ የህገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር በከፍተኛ ሁኔታ እንደደራ በየእለቱ በጸጥታና በደህንነት መዋቅሩ ተይዘው በመገናኛ ብዙኃን ከሚገለጹት መረጃዎች መረዳት ይቻላል፡፡ በአንዳንድ ክልሎች በተለይ በከፍተኛ ሁኔታ የህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሽያጭ እንደሚካሄድም ታውቋል፡፡ ሁኔታው አገሪቱ በሰላማዊ መንገድ በሃሳብ የበላይነት ሥልጣን ከመጨበጥ ይልቅ በነፍጥ ወደ ወንበር ለመውጣት ሩጫ ላይ ያለች ያስመስላታል፡፡
ይህ ትውልድ የመሳሪያ ትግል ያመጣውን ውጤት ከማንም በላይ ያውቀዋል፡፡ የሥልጣኔ ፈር ቀዳጅ የነበረችው አገር ዛሬ ከውራዎቹ ተርታ ተሰልፋ ዜጎቿን እንኳን በአግባቡ ለማኖርና ለመመገብ የምትንገታገተው ለዓመታት በተደረጉት ጦርነቶችና የእርስ በርስ ግጭቶች ነው፡፡ ስለሆነም ነፍጥ አምላኪዎች እባካችሁ ገለል በሉ እያለ ነው፡፡ ከእንግዲህ ሥልጣን የሚያዘው የተሻለ ሃሳብ በማመንጨትና በመተግበር እንጂ በነፍጥ ስላልሆነ ለትውልዱ የማይመጥነው አካሄድ ይቀየር፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 18/2011