ብዙ ጊዜ እየተለመደ የመጣ ጥሩ ያልሆነ አካሄድ አለ። አንድን ሰው ሃሳቡን ስንገመግም ማንነቱ ላይ እናተኩራለን። ሃሳቡን በሃሳባችን ከመተቸት ይልቅ ደካማ ጎኑን በመፈለግ ሃሳቡን ውድቅ ለማድረግ እንጣደፋለን። እንዲሁም መጽሐፍ ስንገመግም ከመጽሐፉ ይልቅ የፀሐፊውን የኋላ ታሪክ እየመዘዝን እናብጠለጥላለን። ደራሲው ወይም ፀሐፊው ከዘረዘራቸው ፍሬ ነገሮች ይልቅ ያልተፃፈውን እያነበብን ባልተባለ ነገር ላይ ፀሐፊውን የማይጠቅምና የማያንፅ፣ ስህተቱን የማያርምና ዕውቀቱን የማይገነባ አላስፈላጊ ሃሳብ እያነሳን ሞራሉን ለማድቀቅ እንጣደፋለን። የሌላውን ስህተት ለማሳየት ሃሳቡን ፈልቅቀን በሃሳብ አሸንፈን ሳናሳይ አልተገናኝቶም በሆነ ጉዳይ አእምሯችንን እንደምጠምደው የመጽሐፍ ሀያሲው እና ዳሰሳ አቅራቢው እሸቱ ብሩ ይትባረክ ይናገራል፡፡
እንደ እሸቱ ገለጻ ከዚህ ቀደም በመልካም ዝና የምናውቀው ፀሐፊ ወይም ደራሲ አዲስ መጽሐፍ ሲያሳትም መጽሐፉን ገና ጨርሰን ሳናነብ ለማድነቅና ምስክርነት ለመስጠት እንሽቀዳደማለን። ከእሱ በላይ ፀሐፊ የለም በማለት እናውጃለን። ለመስቀሉም አውርዶ ለመጣሉም አንደኞች ነን። በሁለቱም ጽንፍ ያለ አስተሳሰብ ልክ አይደለም። ለዚህ ነው ከአተካሮ ፖለቲካ፣ ከጥላቻ ፕሮፓጋንዳ፣ ጥግና ጥግ ሆነን ከመወራወር አዚም ልንወጣ ያልቻልነው፡፡
አብዛኞቻችን አመዛዛኝነት፣ አስተዋይነት፣ መካከለኝነት ይጎድለናል። አንድ ጥግ ላይ እንቸነ ከራለን እንጂ ሌላኛውን ጥግ ለማየትና ለማወቅ ወኔ የለንም። የእኛ ያልሆነ መንገድ ቢሆን እንኳን ሳናውቀው ነው የምንርቀው የሚለው ሀያሲው ብናው ቀው እንረዳዋለን እንጂ አንርቀውም፤ እናከብረዋለን እንጂ አናጥላላውም። እኛ የማንጠቀመው ወይም ምርጫችን ያልሆነ ነገርን ሁሉ የስህተት መንገድ አድርገን እንደመድማለን። አንዱ ይነሳና እንደዚህ የተባለ መጽሐፍ አይጠቅምም አታንቡ ይላል። አንብቦትና ተረድቶት ቢሆን እንኳን ለእኔ የሚጠቅም አንዳች ፍሬ ነገር አላገኘሁበትም ማለት ሲገባው የሌሎችን ሁሉ አስተሳሰብ ወክሎ አታንብቡ የሚል ነጋሪቱን ይጎስማል። ወዳጄ አንተ እና እኔ በብዙ ነገር አንድ አይደለንም። የሕይወት ምርጫችን፣ አስተዳደጋችን፣ አስተሳሰባችን፣ ፀጋችን፣ ወዘተ… ነገራችን አንድ አይደለምና በአንድ መንገድ ልናስብ አንችልም። ግለሰባዊ ልዩነትን መረዳት የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ ነው፡፡
ካረን ቦል (Karen Ball) የተባለ ጸሐፊ ‹‹6 Elements of a Good Book Review›› በተባለ ፅሁፉ አንድን መጽሐፍ ስንገመግም ስድስት ነጥቦችን ማየት አለብን ይለናል። ጥሩ መጽሐፍ ገምጋሚ አመዛዛኝ ነው ፤አዎ መጽሐፉን ቀልባችን ወደደው ጠላው ለውጥ አያመጣም። መጽሐፉ ምርጫችን መሆኑና አለመሆኑ ትርጉም የለውም። ዋናው ጉዳይ የመጽሐፉን ሃሳብ ፍሬ ነገሩን ተረድተን ሚዛናዊ ግምገማ ማስቀመጥ ነው ከጥሩ መጽሐፍ ገምጋሚ የሚጠበቀው። ሃሳብን በታማኝነት ማስቀመጥ ከብልህ አንባቢ የሚጠበቅ ሰናይ ተግባር ነው፡፡
ጥሩ የመጽሐፍ ግምገማ በፀሐፊው ላይ ሳይሆን በመጽሐፉ ላይ የሚደረግ ነው ፤የፀሐፊውን ማንነት፣ የኋላ ያደፈ ታሪክ፣ ደካማ ጎኑ እዚህ ጋር ቦታ የላቸውም። አንዳንዶች እንዴት ትናንት በክፉ መንገድ ከተመላለሰ ሰው መልካም ነገር ይወጣል ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። ትናንት ዛሬ አይደለምና በትናንት ማንነታቸው ዛሬን መበየን ለስህተት ያጋልጣል። ሰው ከትናንት መማር የሚችል አእምሮ አለውና በትናንቱ ማንነታቸው ሰዎችን መመዘን አመክኖያዊ አይደለም፡፡
መጽሐፉን በመልኩ ሳይሆን በፀሐፊው ሃሳቦች መመዘን ከጥሩ ገምጋሚ የሚጠበቅ ተግባር ነው ፤አንዳንዶች መጽሐፉ በተለበጠበት ማሸጊያና የላይኛው ምስል ስለመጽሐፉ ጥሩነትም ሆነ መጥፎነት ለመናገር ሲቸኩሉ ይታያል። የአንድ መጽሐፍ አጠቃላይ መልዕክቱ የሚገኘው ከመጀመሪያው ገፅ እስከመጨረሻው ገፅ ድረስ ነው። የመጽሐፉን የፊት ገፅ ምሰል አይቶና ግማሽ ገፅ አንብቦ ስለመጽሐፉ በሙሉ መተማመን መናገር አይቻልም። በሚታይ ሳይሆን በማንበብና በአእምሮ መረዳት ነው አንድን መጽሐፍ መገንዘብ የሚቻለው፡፡
ጥሩ መጽሐፍ ገምጋሚ አጠቃላይ ስለመጽሐፉ ሃሳብ ደጋግሞ አይነግረንም። ይልቁንስ የእሱ ሃሳብ በመጽሐፉ ሃሳብ ላይ ያለውን አስተሳሰብ ያንፀባርቃል እንጂ ስለመጽሐፉማ ፀሐፊው በመጽሐፉ እየነገረን ነው። የገምጋሚው ሚና መሆን ያለበት የመጽሐፉን ሃሳብ ከራሱ ሃሳብ ጋር እያዋሃደና እያቃረነ፤ የሚስማማበትንና የማይስማማበትን እንዲሁም ገለልተኛ አቋም የሚያንፀባርቅበትን ሃሳብ በተረዳው ልክ ማንፀባረቅ ነው፡፡
ጥሩ ገምጋሚ ምንም እንኳን አስፈላጊ ቢሆንም ሌሎች መጽሐፉን ያነቡት ዘንድ መንገድ ያመቻቻል እንጂ ስለእያንዳንዷ ገፅ ታሪክ፣ ምስጢር፣ መጨረሻ በመንገር አንባቢዎች መጽሐፉን እንዳያነቡት አያደርግም ፤አንባቢ በራሱ አንብቦ ይፈርድ ዘንድ ፍርዱን ለእሱ መተው ይገባል፡፡
ጥሩ መጽሐፍ ግምገማ በጥቅል ድምዳሜ ሳይሆን አንድ በአንድ ሁኔታውን እየመዘዘ መገምገም ነው ፤ አንድን መጽሐፍ የወደድነውም ሆነ የጠላነው ከምን አንፃር እንደሆነ ሁኔታውን እየለየን መዘርዘር ካልቻልን ግምገማችን በችኩል አጠቃሎ ከተቀባይነቱ ፈቀቅ ይላል። ከመጽሐፉ ሃሳቦች ውስጥ የምንጥላቸውንና የምናነሳቸውን ሃሳቦች እንደየሁኔታቸው መዘርዘር ተገቢነት ያለው የመጽሐፍ ግምገማ ነው፡፡
በአጠቃላይ ካረን ቦል ያነሳቸው ስድስት የመጽሐፍ ግምገማ ነጥቦች እነዚህ ናቸው። እነዚህ ለመጽሐፍ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሰዎች ያለንን ግምገማም እንዴት ማድረግ እንዳለብን የሚያሳዩ ነጥቦች ናቸው። አንድን ሰው በአንድ በተናገረው ጉዳይ ብቻ ሁለመናውን መፈረጅ ልክ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው። ሰው በሁሉም ነገር ደግ አያስብም፤ በሁሉም ነገር መጥፎ አያስብም። ደጉንም መጥፎውንም መዝዞ በማውጣት ሃሳቡን በሃሳብ መርታት ከመካከለኛና ከአስተዋይ ሰው የሚጠበቅ አስተሳሰብ ነው፡፡ ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2012
አብርሃም ተወልደ