የዛሬው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በ4 ኪሎ የሳይንስ ፋክልቲ ግቢ ውስጥ ታህሳስ 1 ቀን 1943 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በይፋ ተመርቆ በሰባ ያህል ተማሪዎች ሥራ የጀመረበትን ዓመት እንደ መነሻ ወስደን የዘመናዊ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ጅማሮን ብናሰላ ወደ ሰባ ዓመት ዕድሜ ላይ እንደሚገኝ እንገነዘባለን፡፡ ዩኒቨርሲቲው አሁን የደረሰበት የዕድሜ ጣሪያና በመጀመሪያ የተቀበላቸው ተማሪዎች ቁጥር ተቀራራቢ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ከፍ ያለው ንጉሠ ነገሥቱ ከአባታቸው ከራስ መኮንን በውርስ ያገኙትን የስድስት ኪሎውን ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት በስጦታ ካበረከቱ በኋላ ነበር፡፡ ታሪኩ እንደሚያስረዳን በጄኔራል መንግሥቱ ነዋይና በወንድማቸው የተመራው የ1953 ዓ.ም መፈንቅለ መንግሥት በዚያው በቤተ መንግሥቱ ውስጥ “የትውልዱ ክሬም” ይባሉ የነበሩት የወቅቱ በርካታ ሹማምንት የግፍ ደም ፈሶበት ስለነበር ግቢው በቤተ መንግሥትነት እንዲቀጥል ንጉሡ ባለመፈለጋቸው ምክንያት ለዩኒቨርሲቲነት ተላልፎ እንደተሰጠ ይነገራል፡፡
ንጉሡ ልክ እንደ ዓይናቸው ብሌን ይከታተሉት የነበረው የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ያፈራቸው የነበሩት ተማሪዎች በዕውቀታቸውና በንቃተ ኅሊናቸው ምን ያህል የተመሰገኑና የበቁ እንደነበሩ በሁሉም ዘንድ ይታወቃል፡። እጅግ የሚገርመው ነገር ተማሪዎቹ ራሳቸውን ንጉሡንና አስተዳደራቸውን “ዓናቸውን የመጓጎጥ” ያህል በግራ ዘመም የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸውና በኮሌጅ ቀን ግጥሟቸው ይሸነቁጧቸው የነበረው ፊት ለፊት አስቀምጠዋቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ሹማምንቶቻቸው እንኳን መሰደባቸውንና የአድማቸውን ሴራ እያጋነኑ ሲነግሯቸው “ተዋቸው ልጆች ናቸው፤ ቢያጠፉ ሊታረሙ ይችላሉ” በማለት እንደዘበት ያልፏቸው እንደነበር በሕይወት ከሚገኙ ምስክሮች ማድመጥ ይቻላል፡፡
ተማሪዎቹ “ዓለም አቀፍ ወዛደራዊነትን በሚያቀነቅነው የሶሻሊዝም ፍልስፍና” ናውዘው በመረረ ትግላቸውና ብዙ የሕይወትን የአካል መስዋዕትነት ባስከፈለው የሞት የሽረት ፍልሚያቸው ዘውዳዊው ሥርዓት ከተወገደ በኋላ ሥልጣኑ በአምባገነኑ ደርግ እጅ እንደወደቀ ይታወቃል፡፡ ያኔ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የዘሩት ዘር ጦሱ አለቅ ብሎን ዛሬም ድረስ ተስቦውንና ግርሻውን የሚፈውስ መድኃኒት አግኝተን ልንድን ያለመቻላችን የዕንቆቅልሹን ፍቺ አልባነት ያረጋግጣል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የኮሌጅ ቀን ግጥሞችና ዲስኩሮች ንጉሡን ፊት ለፊት አስቀምጠው የሚጠዘጥዙትና ማርገብገቢያ ይዘው ወላፈኑን ሲያጋግሉ ከነበሩት የያኔዎቹ ተማሪዎች የዛሬዎቹ አዛውንት ፖለቲከኞች እያዳመጥንና እየተመለከትን ያለነው ግርሻው ከሀገራችን ውስጥ ተነቅሎ እንዳልጠፋ ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ “በዳግማዊ ዮሐንስ ዕለት የደነቆረች፤ ዘፈኗ ሁሉ አበባየሆሽ ነው” እንዲሉ መሆኑ ነው።
“ያ ትውልድ” ምንም እንኳ መልህቅ በሌለው የግራ ዘመም ፖለቲካ ጀልባ ላይ ተሳፍሮ በአውሎ ነፋስና በወጀብ ተመትቶ ታሪኩ በብኩንነት ቢጠቃለልም የትምህርት አቀባበሉ፣ የዕውቀት ልህቃቱ፣ የአመለካከት አድማሱ ስፋት በእጅጉ ሰፊና ጥልቅ የሚመሰገንና የሚያኮራ መሆኑን ለመመስከር አፍ አይዝም፤
«መማር ያስከብራል ሀገርን ያኮራል
ጥበብን እውቀትን እንሂድ እንቅሰም እንሻማውም።»
የሚለው መዝሙር በርግጥም በሕይወታቸው ውስጥ ተተግብሮ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ የትውልዱ ዓለም አቀፍ የአመለካከት አድማስ ስፋት እንደተጠበቀ ሆኖ ለአርጀንቲናዊው ቼኩቬራ፣ ለቪዬትናሙ ሆችሚኒ፣ ለቻይናው ማኦ ዜዱንግ፣ ለጀርመኑ ማርክስና ለሶቭዬት ኅብረቶቹ ሌኒንና ስታሊን አይዲዮሎጂዎች ጭልጥ ብለው ተንበርካኪ መሆናቸው ዛሬም ድረስ በታሪካቸው ላይ ደመና ሆኖ አጥልቶባቸዋል፡፡ በትምህርት አቀባበልና አተገባበር ያለመታማታቸው፣ በኢትዮጵዊነት ክብር አለመደራደራቸው፣ በዘረኝነት ምች አለመለከፋቸው፣ የኢምፔሪያሊዝም ወረራ እያሉ ላበሻቀጡት የዘመኑ ጆሊ ጃኪዝም አለመበገራቸውና በንባብ ዕውቀታቸው አለመታማታቸው በምሳሌነት ማስጠቀስ ብቻ ሳይሆን የሚያስመሰግን አቋማቸውና የጎመራው ፍሬያቸው መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
ነጻ ወጥተው ከነበሩት ስምንት የአፍሪካ ሀገራትና የአርነት ንቅናቄዎች መካከል የተመለመሉ 50 ያህል የአህጉሪቱ ልጆች በንጉሠ ነገሥቱ ነጻ የትምህርት ዕድል ተሰጥቷቸው ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ መቀላቀላቸው ይታወሳል። የቅኝ ተገዢ ሰለባ የነበሩት እነዚያ ተማሪዎች ተጽእኗቸው እጅግም ደምቆ ባይነገርም የእኛዎቹ ተማሪዎች ያነሷቸው በነበሩ ሀገረ አቀፍና ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ላይ ትኩሳቱን ለማጋጋል ውስጥ ውስጡን ቤንዚን የማርከፍከፍ ሚና ይጫወቱ እንደነበርም ተመዝግቧል፡፡
የመሬት ላራሹ ትግላቸውና የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክታቸው ከፊሉን ለሞት፣ ከፊሉን ለስደት፣ ከፊሉን ለእስር ቢዳርግም የነቀነቁት የዘውዳዊ አገዛዝ ወድቆ እነርሱም ባክነው፣ አይዲዮሎጂያቸውም ጠንዝቶ የታሪካቸው ምዕራፍ ለወርተረኛው ትውልድ ተላልፏል። የዘመኑን ትውልድ ከሚገልጹት አባባሎች መካከል አንዱ “ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ” የሚለው ይበልጥ ይገልጻቸዋል። የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ካደገበት ጊዜ ጀምሮ በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉት ደጃዝማች ካሣ ወልደ ማርያምና ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ የተመሰገኑና የበቁ መሪዎች መሆናቸውም በራሱ ትርጉሙን ከፍ ያደርገዋል።
በዘመነ ደርግ፤ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተቀላ ቀሉት የሁለተኛው ትውልድ ተማሪዎች ስብጥራቸውም ሆነ አመለካከታቸው የተዥጎረጎረ ነበር። በተለይም የአይዲዮሎጂ ፍልስፍናቸውን በተመለከተ ጥቂት የማይ ባል ቁጥር የነበራቸው ተማሪዎች የቀዳሚው ትውልድ አባላትና የዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ (ከ1967 – 1968 ዓ.ም) ቅሪቶች ሲሆኑ በዕድሜያቸውም ሆነ በትምህርት አቀባበላቸው የበሰሉ ነበሩ፡፡ ዩኒቨርሲቲውን የተቀላቀሉትም ለውጡና ነውጡ አሽቶ ያነጠራቸው ብጤ ስለነበሩ “ከልታይ ልታይ” ይልቅ አንገታቸውን ደፍተው መማርን መርሃቸው ያደረጉና “የፈተና ውጤት ሰቃዮች” የሚባሉ ዓይነት ነበሩ። የያትውልድ ቅሪቶች መሆናቸው ለዚህ ማጠቃለያ ሃሳብ ዋቢ ይቆማል፡፡
በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ ዩኒቨርሲቲዎችን (ጎንደር፣ ዓለማያና አስመራ ዩኒቨርሲቲዎች አይዘነጉም) የተቀላቀሉት አብዛኞቹ ተማሪዎች ደግሞ በቀይና በነጭ ከተሰየሙ ሽብሮች ውስጥ ጠልቀው የዋኙና የደርግን ግፍና እንግልት ዋንጫ በየእስር ቤቱ ተጎንጭተው በተዓምር የተረፉ ናቸው፡፡ እነዚህ ተማሪዎች በየታሰሩባቸው እስር ቤቶች ውስጥ እርስ በርስ በመማማርና ዕውቀታቸውንና አእምሯቸውን አስልተው ብሔራዊ ፈተና ሳይቀር ተፈትነው በከፍተኛ ነጥብ አስመዝግበው ስለነበር ከተፈቱ በኋላ ወደ ዩኒቨርሲቲ የተቀላቀሉት በቂ ዕውቀትና ክህሎት ተጎናጽፈው ነበር፡፡
ሌሎቹና በርካታዎቹ ዩኒቨርሲቲውን የተቀላቀሉት ተማሪዎች ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ለዩኒቨርሲቲ ያበቃቸው “ጮርቃ” ይሏቸው ዓይነት ተማሪዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ምድብተኞች “የክሪስማስ ፈተና ጎርፍ ጠራርጎ እንዳይወስዳቸው” በራሳቸው ትጋትና በቤተሰቦቻቸውና በወላጆቻቸው ፆምና ጸሎት ተደግፈው ይማሩ የነበሩ ናቸው ቢባል ያስማማል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከብሔራዊ ውትድርና ጭምር ታዳጊያቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ያለመታደል ሆኖ በዚህኛው ዘመን ጎልቶ ይደለቅ የነበረው የጦርነት ነጋሪትና የጥይት ጨኸት በአእምሯው ውስጥ ተጠቅጥቆ ስለነበር፤
«አጥንቴም ይከስከስ፤ ደሜም ይፍሰስላት፣
ይህቺ ሀገሬን ጭራሽ፤ አይደፍራትም ጠላት»
በሚሉ ዓይነት ቀረርቶና ፉከራዎች የወጣትነታቸውን ዕድሜ የተቀበሉ ነበሩ፡፡ ከእነርሱ በፊት የነበሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለዓለም አቀፋዊ ወዛደራዊነት እያመረሩ የዘመሩት ከልባቸው ሲሆን እነዚህ ተተኪዎቻቸው ደግሞ “ለሟቾቹ ማርክስና ሌኒን ዕድሜ ይለምኑ የነበረው” በደርግ መንግሥት ላይ ቴአትር እየሠሩና በምጸት እያሽሞነሞኑት ነበር፡፡
በደርግ ሥርዓት ዋዜማ ሳይቀር ርዕሰ ብሔሩ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም ሳይቀሩ ራሳቸው ወታደራዊ ዩኒፎርማቸውን አሳምረው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ዘው ብለው በመግባት “ወይ እንዝመት አለያም እንሰየፍ” በማለት ተማሪዎቹን የዘመቻ ነጋሪት እንዳስጎሰሟቸው አይዘነጋም፡፡
የትውልዱን የሀገር ፍቅር ጉዳይ በተመለከተ ማንም ሕፀፅ ላውጣለት ቢል አጉል ብሽሽቅ አንጂ ፍሬ አይኖረውም፡፡ ያለምንም ጥርጥር ሀገራቸውን ይወዱ ነበር፡፡ ሲመረቁም ሕዝባቸውን ለማገልገል ዝግጁ ብቻ ሳይሆኑ ወደሚመደቡበት ለመሄድ አያቅማሙም ነበር። ከየዩኒቨርሲቲው ይዘው የሚወጡት የትምህርት ማስረጃም በርግጥም በጥረታቸው ያገኙት መረጃቸው እንጂ ተምሯል ለመባል ያቆሙት መታሰቢያ አልነበረም። ተስፋቸው በላባቸው ወዝ የሚያገኙት ወርሃዊ ደመወዛቸው ብቻ እንደሆነ ተረድተዋል፡፡ በሙያቸው “ቢዝነስ ሠርቶ በአቋራጭ ለመክበር” ህልምም ቅዠትም አልነበራቸውም። የሥርዓቱ ጫና ቁልቁል እየተጫነ ቢያጎብጣቸውም መንፈሳቸውና የዜግነት ኩራታቸው ግን የዋዠቀ አልነበረም።
የሦስተኛውን ትውልድ የዘመነ ኢህአዴግን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሥነ ልቦናና አቋም በአጠቃላይ ምልከታ ለመቃኘት እጅግ አስቸጋሪና ፈታኝም ነው። ለከፍተኛ ትምህርት ሕንጻ ግንባታዎችና ለቁጥር ብዛት ካልሆነ በስተቀር ለትምህርት ጥራት እጅግም የሆነው ሥርዓትና የሥርዓቱ አቀንቃኞች ትውልዱ ላይ ብቻ ሳይሆን ትምህርቱንም ጭምር በጫካ ወለድ ፖሊሲ ተኩሰው የገደሉት ገና ከማለዳው ጀምሮ ነበር። በእብሪትና በትዕቢት ታጅሎ ሀገሪቱን የተቆጣጠረው ቡድን መጀመሪያ የወሰደው ርምጃ ቁጥራቸው 42 የሚደርሱ ምርጥና ምስጉን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራንን በወረንጦ እየለቀመ ማባረር ነበር፡፡ በየዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሥርዓቱ ካድሬዎች እንደምን እየሰረጉ እየገቡ የትምህርቱን ብርሃን ለማዳፈን ይሞክሩ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
በረሃ በተቀረፀው የትምህርት ፖሊሲ ፋና እየተመሩም በተማሪው ንጹህ አእምሮ ውስጥ የዘሩት የጎጠኝነትና የዘረኝነትን መርዝ እንዲውጡ የተገደዱት በስመ ዴሞክራሲ ቅባት እያዋዙ ነበር፡፡ መርዙን አንውጥም ብለው ያገረገሩ ተማሪዎችም የምሩቅ ሥራ ፈት እንዲሆኑ ተፈረደባቸው፡፡ የፖለቲካው ምንደኛ ተማሪዎችም በብሔራቸው ፖለቲካ ጥላ ሥር እየተጠለሉ “ነዎሩ” እየተሰኙ ያለውድድር ሰፊ የእንጀራ ገበታ ተዘረጋላቸው። በፖለቲካው ኩሬ ውስጥ እንደልብ እንዲዋኙም “ላይፍ ሴቨር” እየተመደበላቸው ፈላጭ ቆራጭ ለመሆን ቻሉ፡፡
በየዩኒቨርሲቲው ግቢዎች ውስጥ የተቋሰሉትና ደም የተቃቡት ተማሪዎች ጥቁር ገዋን ባጠለቁ ማግስት የትምህርት ማስረጃቸው እንጂ ብቃታቸው ሳይመዘን በሹመትና በሽልማት እሶሶ እየተባሉ እርስ በርስ እንዲጠባበቁ ተፈረደባቸው፡፡ እንደ መጀመሪያው የንጉሡ ሥርዓት ትውልድ ሰፊውን ዓለም ማየት፣ እንደ ዘመነ ደርግ “ለሀገር ሉዓላዊነት ለመሞት እስከ መጨከን” ማሰብ የተረት ያህል እንዲቆጠር የረቀቀ ሥራ ተሰራባቸው። ንፅረተ ዓለማቸው ሁሉ ከጎጥና ከብሔር፣ ከአካባቢ አፍቅሮትና ከማንነታቸው ውጭ የሌላውን ውበት እንዳያዩ ሥርዓቱ ዓይናቸውን ጋረዳቸው፡፡ “ተመርቄ ሀገሬን አገለግላለሁ” ተዘንግቶ “የቢዝነስ ቅዠት” እንደ ወረርሽኝ ትውልዱን እንቅልፍ ነሳው፡፡
የቀዳሚው ሁለት ትውልዶች እርስ በርስ ሲተዋወቁ ዘራቸውና ብሔራቸው ምንም ይሁን ምን እራሳቸውን ይገልጹ የነበረው የአዲስ አበባ ልጅ፣ የአርሲ ልጅ፣ የድሬዳዋ ልጅ፣ የሐረር ልጅ፣ የትግራይ ልጅ፣ የጅማ ልጅ፣ የወለጋ ልጅ፣ የአፋር ልጅ፣ የቢኒሻንጉል ልጅ ወዘተ. እየተባባሉ ነበር፡፡ የእከሌ ብሔር የእዚያኛው ጎሳ፣ የዚያኛው ጎጥ ልጅ እየተባባሉ ራሳቸውን አይሸነሽኑም ነበር፡፡ የዘመነ ኢህአዴጉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ግን ይህንን ፀጋ እንዲገፋና እንዲጥል ተፈረደበት፡፡ እንደተመኙትም ሆኖላቸው እነሆ ዛሬን ወልዶ አስታቀፈን፡፡
እርግጥ ነው ይህ ጥቅል ምልከታና ቀኝት እንጂ ትውልዶቹን በሙሉ ይወክላል ማለት አይደለም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡ ብስልም ጥሬም ፍሬ ተደባልቆ እንደሚገኝ እንኳን ከሰው ፍጡር ቀርቶ ከእህል ዘርም ስለማይጠፋ፡፡ ከብሔራቸው ክልል አሻግረው ለትልቋ ኢትዮጵያ መፍትሔ የሚሆኑ፣ ለሕዝባቸውም መድህን ለመሆኑ የቆረጡ በርካታ ወግ የሚያሳዩን የቁርጥ ቀን ልጆችም እንደነበሩንና ዛሬም እንዳሉን መካድ አግባብ አይሆንም፡፡ ሆ! ተብሎ በሚተረማመስ የጀማ ወጀብ መሃል ጸንተው የቆሙ በርካቶች እንደ ትናንቱ ዛሬም አሉ፤ ወደፊትም መኖራቸው አይካድም፡፡
ከይዋጣልን ፉከራ ይልቅ በመወያየትና በመቀባበል የሚያምኑ በርካታ ልጆች ሀገሬ ዛሬም አላት፡፡ በየዩኒቨርሲቲው የላክናቸው ልጆቻችን ዛሬ እንደ ትናንቱ ከነፈሰው ጋር ለመንፈስ ራሳቸውን እንደማያቀሉ በጽኑ ይታመናል፡፡ “ዘራፍ!” እያሉ የሽብርና የመለያየት ፀብ ለሚዘሩት የትውልዳቸው እንክርዳዶች በሚጠምቁት መርዘኛ ጠበልም ይጠመቃሉ የሚል ግምት ጸሐፊውም ሆነ ሕዝቡ እንደማይኖረው በተለያዩ መንገዶች እየተንጸባረቀ እንዳለ እያስተዋልን ነው፡፡ “ልጆቻችን እንደሚኖሩ ሆነው እንዲማሩና እንዲሰሩ፤ እንደሚሞቱና እንደሚያልፉ ሆነው እንዲኖሩ!” እነሆ ታሪክ እያጣቀስን ቅኝት ማድረግ አስፈላጊ ስለመሰለን ወቅት አዞን ታዘናል። መልካም የትምህርትና የስኬት ዓመት ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቻችን፡፡ ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2012