መንገድ ዳር
በዚህ ቦታ ጢሱ ግራ ይንፈስ ቀኝ ወይንም ወደ ላይ ቦለል ብሎ እንዲወጣ ሊወስን የሚችለው ባለ ሙሉ መብቱ ንፋሱ ብቻ ነው። ወዲህ ንፈስ አይባል ነገር ከቤት ምድጃ ወጥቶ አስፋልት ዳር ያለ እሳት አቅጣጫውም አመሉም አይታወቅም፤ ሁኔታው አይተነበይም። ታዲያ ከመንገድ ዳር ሆኖ በጢስ አቅጣጫ መናጥ ያልሰለቸው ወጣት እንጨቱን እየቆሰቆሰ በእሳቱ ግለትና በጢሱ መሰንፈጥ ሳይታክት የሕይወት መስመሩን ለማቅናት እየተጋ ነው።
ኑሮ ገና በለጋነቱ ጀምራ እንደ ፈለገችው ልትዘውረው ብትዳዳም፤ እርሱም እጅ አልሰጥ እያለ የኑሮን ጫና አሸቀንጠሮ ለመጣል ይታትራል። አንዴ እፎይታ አግኝቶ የስኬት መንገድ ጀመርኩ ሲል በሌላ ጊዜ ደግሞ የተስፋ መቁረጥ ጥግ ላይ ይደርሳል። የሁኔታዎች መለዋወጥ ከታዛዥነት ወደ አዛዥነት፤ ከሰጭነት ወደ ተቀባይነት፣ ከተቀጣሪነት ወደ ቀጣሪነት በሌላ ጊዜ ደግሞ ነገሮች በተገላቢጦሹ እየሆኑ ከኑሮ ጋር ጢባጢቤ እንደሚጫወት ሰው አሽኮለሌ እየተባባሉ ዛሬ ላይ ደርሰዋል።
የጠፋው ልጅ
ሀብታሙ ተሾመ ይባላል። ከሱሉልታ ስምንት ኪሎ ሜትር ገባ ብሎ ካለው ጉለሌ ገብርኤል በሚባል ስፍራ ተወለደ። እስከ ስምንተኛ ክፍል እዚያው ጉለሌ ገብርኤል ተማረ። ከዚህ በኋላ ከቀለም ተቆራረጠ። በ1997 ዓ.ም በ17 ዓመቱ ከተወለደበት ሠፈር ወደ አዲስ አበባ ኮበለለ። ከዚያም ሩፋኤል በሚባል አካባቢ ደረሰ። በወቅቱ ለአዲስ አበባ አዲስ ሰው ነበር። ከኦሮምኛ ውጭ በሌላ ቋንቋ ለመግባባት ይቸገር ነበር። አዲስ አበባ እንደደረሰ በቀለ ከሚባል ሰው ዘንድ ተጠልሎ አደረ። በሂደት አካባቢውን ለመደ። በኮንስትራክሽንና ሌሎች ዘርፎችም ተሰማርቶ ጉሮሮው ለመድፈን ሞክሯል።
ይህ ሥራው ስለከበደው ከአንድ ወር በኋላ መጀመሪያ ያስጠለለው ሰው ዋስ ሆኖት በጥበቃ ሥራ ሲኤምሲ በሚባል ሰፈር አያት መንደር እንዲቀጠር አደረገው። ግን ወጣ ገባ ለማለት ስለከበደው ይህንንም ተወው። ከዚያ ፒያሳ አካባቢ በአንድ ሆቴል በጥበቃ በየወሩ 80 ብር እየተከፈለው ሥራ ጀመረ። አሁንም ከዚህ ለቆ አዲሱ ገበያ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ፊት ለፊት አንድ ሆቴል ውስጥ በጥበቃ ሥራ በ60 ብር ወርሃዊ ደመወዝ ተቀጠረ።
የሆቴሉ ባለቤት አቶ ተክሌ ይባላሉ። በዚህ ቤት ውስጥ ሌላ ሥራ ለመደ። ሰውየው ስለወደዱኝ ሁሉንም ስራ አስለመዱኝ ይላል። አምስት ዓመት ሙሉ በዚሁ ቤት ሠራ። ከጥበቃ ተነስቶ ድራፍት ቀጂ (ባሬስታ) ሆነ። ይሁንና ከዚህም ቤት ወጣ፤ ከዚያን በኋላ ደግሞ ቅደስት ማርያም ግሮሰሪ የሚባል ቤት በባሬስታ ሥራ ተቀጥሮ አራት ዓመት ሰራ። በዚህ አካባቢ ሳለ በሌላ ሆቴል ተቀጥራ ትሠራ ከነበረች እንስት ጋር ፍቅር ጀመሩ። በፍቅር ላይ ሳሉም ለምን የራሳችን ሥራ አንሠራም፤ እስከመቼ ተቀጥረን ስትል ሐሳብ አቀረበችለት። እርሱም ተስማማ። ከዚያም ሰላሌ የሚባል ግሮሰሪ ኩሽናውን በ3000 ብር ተከራይተው ምግብ ይሰሩ ጀመር።
«ኦቦ ቅቅል!»
በዚህ ቤት ሳለ ብዙ ደንበኞችን አፈራ። ከአራቱም አቅጣጫዎች ሰዎች ወደዚህ ቤት እየጎረፉ ይመጡ ጀመር። እርሱም ገበያው ሸጋ ስለሆነለት ሦስት ሰራተኞችን ቀጥሮ ሥራውን ማቀላጠፍ ጀመረ። ምግብ ቤቱ ታዋቂነትን እያተረፈ መጣለት። ‹‹በተለይም‹‹ኦቦ ቅቅል›› የተባለው ምግብ በወረፋ ሰዎች እየተሻሙ ይበሉለት ነበር። የሰፈሩ ሰውም ቀጠሮ ሲኖረው ‹‹ኦቦ ቅቅል›› እንገናኝ እየተባለ ለሰፈሩ መለያ እስከመሆን ደረሰ። ደንበኛው ጎረፈ፤ ዝናንም አተረፈ።
ፑል እና ኪሳራ
ሀብታሙ የምግብ ሥራ እየሠራ ሳለ ከሦስት ዓመት በኋላ ሳይስበው ኪሳራ ደረሰበት። በተለይ ‹‹ካሽ ሪጅስተር›› ማሽን አጠቃቀምን በአግባቡ አለመቻሉ ዋጋ አስከፈለው። ስለዚህ ይህን ቤት ትቶ ወጣ፤ ሠራተኞቹንም በተነ። ደንበኞቹም እጅ የሚያስቆረጥመውን ቅቅል ሲያጡ፤ ልክ ነጥፋ ልጇን ማስታወስ እንደደረሳች ላም በዚያው ጠፉ። እርሱም ለተወሰነ ጊዜ ያለሥራ ለመቀመጥ ተገደደ፤ ስራውንም አቋረጠ።
ችግሩን የተረዳው አንድ በላይ የሚባል ሰው ለምን የእኔን ቤት አልሰጥህም በእኔ ቤት ምግብና መጠጥ ሥራ ሲል መከረው። እርሱም የአንድ ወር ኪራይ ከፍሎ ሥራውን ጀመረ። በመሃል ላይም ቤቱን መርቁልኝ ብሎ ሰዎችን ጠራ። የ80 ሺ ብር ዕቁብም መሰብሰብ ጀመረ። እንዳሰበው አልሆነም።
አሁንም ኪሳራ የሚባለው ነገር አብሮት መጣ። ዓመት ሳይሞላው ነገሮች ሲበታተኑ ተመለከተ። አንድ ነገር ሁሌም መርሳት አይፈልግም። ለመክሰሬ ዋንኛ ተጠያቂ ራሴ ነኝ ይላል። ፑል የመጫወት ሱስ ነበረበት። ሌላው ቀርቶ ሥራ አቋርጦ ወደ ፑል ጨዋታ ይሄድ ነበር። ይህ ሥራውን በአግባቡ እንዳይቆጣጠርና በፈለገው መንገድ ስኬታማ እንዳይሆን ደንቃራ እንደሆነበት ዛሬ ላይ ሆኖ ሁሉን ነገር ያስታውሳል።
ራሴን ላጥፋ?
እንግዲህ ኪሳራ ሲገጥመው እቁቡንም መክፈል ሲያቅተው በ2011 ዓ.ም ቤቱንና ትዳሩን ጥሎ ወደ አዳማ ጠፋ። በዚህ ጊዜ ነገሮች መስመር እየሳቱ መጡ። ግን ደግሞ ጠንካራ ጓደኞች ነበሩት። እየሰራህ ትከፍላለህ ሲሉት አበረታቱት። እርሱም እሺ ብሎ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ። በጓደኞቹ ጉትጎታና እና በራሱ ጥረት ሥራውን ጀመረ። አዳማ እያለ በኩዳዴ ጾም ወቅት አንድ ሰው በራፍ ላይ ዓሳ ሲጠብስ ተመልክቶ ነበር። ታዲያ አዲስ አበባ ስሄድ ለምን ይህን ሥራ አልሰራም ብሎ ወሰነ። ወደ አዲስ አባባ ሲመጣም ሦስት ኪሎ ዓሳ ይዞ መጣና ጠብሶ ገዢ ጠበቀ። ወዲያውኑ እንዳሰበው ተሳካለት። ሰዎችም ያበረታቱት ጀመር። አሁን እዳውንም እየከፈለ ነው። ከ80 ሺ ብር ውስጥ አሁን 42ሺ ብር አካባቢ መክፈል ችሏል። ነገር ግን በአጭር ጊዜ ከፍሎ መጨረስ እንደሚችል በሥራው ተማምኗል።
ሀብታሙ ገንዘብ ባይኖረኝም የሰው ፍቅር አለኝ ባይ ነው። ‹‹ገንዘብ ባጣም ወደ መጥፎ መስመር አልገባም። ነገሮች እንደሚሳኩ አምናለሁ፤ ሥራ ድፍረትም ይልጋል። በወቅቱ ብዙ ነገሮች አሳስበውኝ ነበር። ሌላው ቀርቶ ራሴን ላጥፋ እያልኩ ብዙ ጊዜ እጨናነቅ ነበር›› ይላል። ግን ይርጋለም የሚባለው ጓደኛው መልካም ሃሳብ እና ቅንነት ሞራሉን ጠገነው። መጀመሪያ በዕዳ እያዛለሁ ብሎ ቢጠፋም እኔ አለሁ ብሎ ወደ አዲስ አበባ መለሰው። አይዞህ ሰርተህ ትከፍላለህ እኔ አለሁ ብሎ አበረታታው። ሥራ ለመጀመርም ያስችለው ዘንድ መነሻ ብር ሰጠው።
ለልጄ ዳቦ
በአሁኑ ወቅት ከስምንት እስከ አስር ኪሎ ዓሳ በየቀኑ ይሸጣል። አንድ የተጠበሰ ዓሳ ከ30 ብር እስከ 50 ብር ይሸጣል። ደንበኞች ስላሉት አሳው አያድርም። እርሱም ማትረፍን ዓላማ ያደረገ ሥራ አይሠራም። ዋናው ነገር ትርፍ ብር ሳይሆን ‹‹ለልጄ ዳቦ ከቻለ ይበቃል›› ይላል። ከዚህም በላይ ደግሞ በየወሩ 1ሺ800 ብር የቤት ኪራይ ይጠበቅበታል። ይህን ሁሉ ፈተና እየተጋፈጠ ነገ የተሻለ ነገር እንደሚመጣ ነው ተስፋ የሚያደርገው። ከዓመታት በፊት የሆቴል ሥራ ሲጀምር 2000 ብር ብቻ እንደነበረው ያስታውሳል። አሁንም ቢሆን ብርታትና ጥንካሬ ካለ ሁሉም ነገር ቀላል ነው ብሎ ያምናል። ዛሬም አዲሱ ገበያ አካባቢ አሳዎችን እየጠበሰ ለገበያ ያቀርባል።
ጥበቃ፤ ባሬስታ፤ ባለሆቴል
ሀብታሙ ጥበቃ ሆኖ ሰርቷል። ባሬስታ ሆኖ ድራፍት ቀድቷል ፤ደፋ ቀና ብሎ ደንበኞችን አስተናግዷል። ሥራ ፈጥሮ ሰዎችን ቀጥሮ አሰርቷል። ደግሞ አጥቶ ነጥቶ ድህነት ኪሱን ፈትሾታል። ዳግም አገግሞም ወደ ሥራው ተመልሷል።
በአሁኑ ወቅት ማለዳ ተነስቶ ዓሳዎቹን ለመግዛት ወደ አትክልት ተራ ይሄዳል። ቀን ለተወሰነ ሰዓት ከጓደኞቹ ጋር ይጫወታል። ቀደም ሲል ሦስት ሠራተኞች ነበሩት። አሁን ግን ለራሱም ኑሮ ከብዶታል። ቢሆንም ግን አሁን አዲሱ ገበያ አካባቢ አሳ እየጠበሰ ለደንበኞቹ እያቀረበ ኑሮውን ይደጉማል፤ዕዳውንም ይከፍላል። ዛሬ ለውድቀት ከዳረገው ከፑል ሱስ ነፃ ሰው ነው። የእርሱ ሱስ ሥራውና ልጁን ማሳደግ ብቻ ነው። በሚያለፋ ጊዜ ውስጥ አልፎ እንዲህም ይኖራል ነበር ብሎ መተረክ ይናፍቃል።
ሀብታሙ በሥራው ስኬት እና ለገጠመው ውድቀት እራሱን እንጂ ሌላው ሰው ተጠያቂ አያደርግም። የሆነው ሆኖ ግን በሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ሰዎች ባለውለታዬ ናቸው ሲል ያመሰግናል። ብዙ ሰዎች በአሁኑ ወቅት በዘረኝት ታውረዋል፤ ይህ ምንም አይጠቅምም ሲል ይመክራል። እኔ ኦሮሞ ነኝ፤ ግን ኦሮሞ ይገዛኛል ብዬ ሥራ አልጀመርኩም። ማንኛውም ሰው ገዝቶ የሚጠቀመው ነው። ባለቤቴ ደግሞ ጉራጌ ናት፤ ያስተሳሰረን ፍቅር እንጂ ዘራችን አይደለም። መጀመሪያም ወደ አዲስ አበባ ስመጣ ያስጠለሉኝ ሰው በመሆኔ እንጂ በብሄሬ አይደለም። ስለዚህ አሁን የሚስተዋለው ብሄር ተኮር ጥላቻ አይጠቅምም ሲል ይመክራል። ሰው ሆነን ስንኖር ሰርተን መለወጥ መልካም ዘራችን ተክተንና በጎ ነገር ተግብረን ማለፍ አለብን።
መንግስት ቢያግዘኝ ሃሳብ አለኝ!
ሃብታሙ በእነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ብዙ ነገር ተምሯል። በማጣት ማግስት ማግኘት፤ በማግኘት ማግስት ደግሞ ማጣት እንዳለ ይገነዘባል። አሁንም ቢሆን ፈተናዎችን በድል አልፎ ነገ በሁለት እግሩ የቆመ ኑሮን መምራት ያልማል። ምንም እንኳን ኑሮ ከቤት አሸቀንጥራ ከአስፋልት ዳር አስቀምጣ በጢስ አፍና ዓሳ ጠባሽ ብታደርገውም እሻገረዋለሁ ብሎ ያልማል። እንደእርሱ በኑሮ ትግል የተረቱ ሰዎችን ነገ ከመንገድ ዳር ሰብስቦ ሥራ ሊፈጥርላቸው ያስባል። በዚህም አያበቃም ኑሮን ሊበቀለው የሁሌል ጊዜ ህልሙ ነው። ግን አንድ ነገር አብዝቶ ይመኛል። ለልጁ፣ ለባለቤቱ እና ለራሱ ብሎ በርካታ ውጣ ውረዶችን እያለፈ ቢሆንም አሁንም ኑሮ ከብዶታል፤ ጫንቃውን አጉብጦታል። እናም መንግስት ወጣቶችን እንደሚያደራጅ ሁሉ እኔም እንደ አስፈላጊነቱ ብደራጅ፤ ኑሮዬም ቢደረጅ ሲል ይማፀናል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር