ሐምሌ 21 ቀን 2011 ኢትዮጵያውያን በአንድ ቀን ጀንበር 4 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል ታሪክ የሰሩበት ቀን ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ታሪክ መስራት እናውቃለን። ወራሪን በጋራ ክንድ እንመክታለን፤ ወድቀን ተዋድቀን ሀገርን በነጻነት እናቆያለን፤በዓለም መድረክ ሮጠን ድልን እንጎናጸፋለን፤ የዓለም የኖቤል ሽልማትንም እናሸንፋለን።
ልስራ ካልንና ከቆረጥንም አስደናቂና ዘመን ተሸጋሪ ቅርሶችን ለዓለም እናኖራለን፡፡ የላሊበላ፤ የአክሱም፤ የጎንደር፤ የሀረርና የአባጅፋር ህያው ቅርሶች ለዚህ አባባል ቋሚ ምስክሮች ናቸው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከልብ ከተነሳንና ከቆረጥን ዓመታትን የሚፈጁ ፕሮጀክቶችን በወራት ውስጥ አጠናቀን ዓለምን ጉድ ማስባል እንችልበታለን፡፡ በወራት ውስጥ ቤተ መንግስታችንን አስውበንና የምድር ገነት አስመስለን እንካችሁ ታሪካችንን እወቁ ፤ለዓለምም አንጸባርቁ ማለት እናውቅበታለን፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ያቀተን ታሪክ መስራት ሳይሆን ታሪክን ማቆየትና ማዝለቅ ነው፡፡ በአፍሪካ በቅኝ ያልተገዛን ኩሩ ህዝቦች ሆነን ሳለ ዛሬ ከአፍሪካ መድረክ ወርደን ወደ ቀበሌ አስተሳሰብ ለማሽቆልቆል እየዳዳን ነው፡፡ በዛን ዘመን እንኳን ለመስራት ለማሰብም የሚከብዱ የላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት፤ እንዴት እንደተጓጓዘም ሆነ እንዴት እንደቆመ እስካሁን ለብዙዎች ትንግርት የሆነውን የአክሱም ሀውልትን፤ የነገስታትን ብርታትና የኢትዮጵያን ገናናነት በቁም የሚመሰክሩት የጎንደር አብያተ መንግስታትን የሰራን ህዝቦች ዛሬ ቅርሶቹን መንከባከብ አቅቶን የመፍረስ አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡ ዛሬ እንኳን ቅርሶቹን መስራት መጠገን አቅቶን የውጭ ሀገራትን ደጅ ለመጥናት በቅተናል፡፡
የሃይማኖትን መቻቻልንና አብሮነትን ለቀሪው ዓለም አቀፍ አውጥቶ የሚናገረው የነጃሺ መስጊድን የሰራን ህዝቦች፤ መስጊድና ቤተ ክርስቲያን መቶ ሜትር በማይሞላ እርቀት ውሰት ስንገነባና በጋራ ስናመልክ ቆየን ህዝቦች(መርካቶ የሚገኙትን ራጉኤል ቤተ ክርስቲያንና አንዋር መስጊድን ልብ ማለት ይገባል) ዛሬ በትንሽ በትልቁ ሃይማኖትን ሰበብ አድርገን ስንቆራቆዝ ያየ ያ ሁሉ ጥበብና ማስተዋል የት ገባ ለምንስ ማዝለቅ አቃተን የሚል ቁጭት ያስነሳል፡፡ በቅርብ
ጊዜያት እንኳን የጀመርነውን የህዳሴ ግድብ መጨረስ አቅቶን ስንንገዳገድ ታይተናል፡፡
ከላይ በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት እኛ ኢትዮጵያውያን ታሪክ መስራት ችግር ስለሌለብን በአንድ ቀን ውሎ 4 ቢሊዮን ችግኞችን ተክለን ዓለምን አጃኢብ አሰኝተናል፡፡ የተተከሉት ችግኞች ግን ዛሬ ላይ ምን ላይ እንዳሉ የምናውቅ ስንቶቻችን ነን፡፡ ችግኞቻችንን እንደ ልጆቻችንን ለመንከባከብ ቃል ገብተን የነበርን ሰዎች ቃላችንን አከበርን ወይስ ለቃላችን ታበይን ፤የማዝለቅ ታሪካችን ሰለባ ሆነናል? ወይስ ችግሩን ተሻግረናል ?መልሱ እያንዳንዳችን ጋር ነው፡፡
አንድ ሰው ግን ለገባው ቃል ታማኝ ሆኖ የተከላቸውን ችግኞች ውሃ ሲያጠጣ ተመልክተናል። ያም ለቃሉ የታመነ ሰው የ2012 የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊ የሆኑት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኛ ኢትዮጵያውያን ያለብንን የማዝለቅ ችግር የተረዱ ይመስለኛል፡፡ ሐምሌ 21 ቀን 2011 በአንድ ቀን 4 ቢሊዮን ችግኝ ተክለን ዓለምን ካስደመምን በኋላ የሰራነውን ታሪክ ዘላቂ ለማድረግ ትኩረት የቸርነው አይመስለኝም። የተከልናቸውን ችግኞች መንከባከብና እስኪጠነክሩ ድረስ ውሃ እያጠጣን ከመክሰም መታደግ ካልቻልን የሰራነው ታሪክ ተቀብሮ መቅረቱ አይቀርም፡፡
ሌሊት ማልደን በብዙ ልፋት፤ጭቃን አረንቋ ተቋቁመን የተከልናቸው ችግኞች ለጋ ስለሆኑና ስራቸውን ዘርግተው ምግብ መሻማት ስለማይችሉ ለመድረቅና ለመጠውለግ ቅርብ ናቸው፡፡ ስለዚህም የእኛን ጥበቃና እንክብካቤን ይሻሉ፡፡ በተለይም የክረምቱ ዝናብ እያበቃና የበጋው ሀሩርና ውርጭ እየጨመረ በሚመጣባቸው ከጥቅምት ጀምሮ ባሉት ወራት የተከልናቸውን ችግኞች ውሃ ማጠጣትና መንከባከብ ካልቻልን ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ መሆኑ አይቀርም። ስለዚህም ከጥቅምት ወር ጀምሮ ባሉት የበጋ ወራት ችግኞቻችንን ውሃ ማጠጣትና መንከባከብ ይኖርብናል።በነዚህ ወራት የምንሰራው ስራ ችግኞቹ ስር እንዲሰዱና መሬት ቆንጥጠው እንዲዙ ያደርጋል፤ በሂደትም እድገታቸው ቀጥሎ ለመጪው ክረምት እንዲደርሱና እስከ ወዲያኛው ህያው እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡
ስለዚህም የጠቅላይ ሚኒስትራችንን ፈለግ ተከትለን የተከልናቸውን ችግኞች ውሃ ማጠጣትና መንከባከብ እንጀምር፡፡ የእረፍት ቀናችንን ከቤተሰቦቻችን፤ ከልጆቻችን፤ ከጓደኞቻችን ጋር በመሆን ችግኞቻችንን ብንከባከብ የመንፈስ ደስታ ከመስጠቱ ባሻገር ለሀገራችን ብሎም ለአለማችን የአረንጓዴ ሽፋን መጨመር አስተዋጽኦ እያደረግን መሆኑን መረዳት ይገባናል፡፡
በመንግስትም በኩል ለችግኝ ተከላው የተደረገውን ጥረትንና ብርታትን በሚመጥን መልኩ ችግኞችን ለመንከባከቡና ለማዝለቁ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። እንደ መነሻም ችግኞችን ለመንከባከብና ውሃ ለማጠጣት አንድ ቀን ቢሰየምለት ሁሉም በነቂስ ወጥቶ የተከለውን ችግኝ እንዲንከባከብ መነሳሳትን ይፈጥራል።
በዚሁ ወቅትም ኢትዮጵያውያን በሙሉ ችግኞችን በመንከባከብና ውኃ በማጠጣት ዛፍ እንድናደርጋቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጥሪ ባቀረቡት መሰረትም እኛም ፈለጋቸውን በመከተል የተከልናቸውን ችግኞች ዛፍ ልናደርጋቸው ይገባል፡፡ ጀማሪዎች ብቻ ሳንሆን ዘላቂዎችም ልንሆን ግድ ነውና፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2012
በላቸው ሙላት /ከሸጎሌ