የኢፌዴሪ ሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ‹‹የኢንዱስትሪ ሰላም ለአካታችነትና ለዘላቂ ልማት›› በሚል መሪ መልዕክት ከታህሳስ 17 እስከ 18 ቀን 2011 ዓ.ም የሚዘልቅ ሀገር አቀፍ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ጉባዔ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ትናንት ተጀምሯል፡፡ በጉባዔውም የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉባኤው ሠራተኞችና አሠሪዎች በጋራ ኢንዱስትሪውን ለማዘመን ኃላፊነት ወስደው ለመምከር የታደሙበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ዓለምን የቀየራትና በሥልጣኔም ጉዞ ለመገስገስ ያበቃት ክስተት ሥራና ሥራ ብቻ ነው ያሉት አቶ ደመቀ፤ በቀጣይ ዓመታት የሠው ልጅ ፍላጎቱ ሳይሸራረፍ መልስ የሚያገኝበትና የተመቸ ዓለም መፍጠር የሚቻለውም በሥራ ብቻ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የአሠሪዎችና ሠራተኞች ትሥሥርን በተመለከተ ሲያስረዱ፣ እነዚህ ሁለት አካላት በምንም መልኩ ተለያይተው የሚኖሩ ሳይሆኑ የአንዱ ተጠቃሚነት የሌላውንም ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ሠራተኛው ለአሠሪው አሠሪውም ለሰራተኛው መመቻቸት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ በሀገራችን ያለውን የለውጥ ሂደት ለማገዝና ዘላቂነቱንም ለማረጋገጥ ሁሉም በየዘርፉ ኃላፊነቱን መወጣት ይገባዋል ብለዋል፡፡
የኢፌዴሪ የሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ይህ ሀገር አቀፍ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ጉባኤ የሚመራበት ቃል ‹‹የኢንዱስትሪ ሰላም ለአካታችነትና ለዘላቂ ልማት›› የሚል እንደሆነና ጥልቅና ዘርፈ ብዙ መልዕክትም እንደያዘ ተናግረዋል፡፡ ሀገራችን ካሏት ሀብቶች መካከል የሠው ኃይል ተጠቃሽ ነው ያሉት ሚኒስትሯ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሰው ሀብቷም ወጣትና መሥራት የሚችል በመሆኑ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ለምናደርገው የኢኮኖሚ ሽግግር ትልቅ አቅም ይሆናል ብለዋል፡፡ ያለንን የሰው ኃይል ጥቅም ላይ ለማዋልም የአሠሪና ሠራተኛው ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡
በሀገራችን የሥራ አካባቢዎች ምቹ እንዲሆኑና እንዲሻሻሉ መደረጉ ፣ የአሠሪዎችና የሠራተኞች ሙሉ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥና የኢንዱስትሪው ሰላም የላቀ እንዲሆን ያግዛል ብለዋል፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የአሠሪዎችና የሠራተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱም የኢትዮጵያን መጻኢ እድል መልካም እንደሚሆን ማሳያ ነው፡፡ የሀገር ሰላምና መረጋጋት፤ መንግሥት የሚገነባው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሁም የአሠሪዎችና የሠራተኞች ሙሉ ተጠቃሚነት ሊረጋገጥ የሚችለው ዘላቂ የኢንደስትሪ ሰላም በሰፈነበት ማግስት ስለሆነ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራና በቅንጅት መሥራት ከምን ጊዜውም በላይ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ የአሠሪና ሠራተኛ መልካም ግንኙነት ለኢንቨስትመንት የስበት ኃይል እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
እየተካሄደ ባለው ሀገር አቀፍ የአሠሪና ሠራተኛ ጉባዔ ላይ በነጻነት መደራጀት ለሰላማዊ ኢንዱስትሪዎች እድገት ያለውን ሚና ተግዳሮቶችና የመፍትሄ አቅጣጫ፣ ቅድሚያ የተሠጣቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች ያላቸውን ምቹ የሥራ ሥምሪት ሁኔታ፣ በኢትዮጵያ ወጣቶች ሥራ ስምሪት ያሉ እድሎችና ተግዳሮቶች ውይይት ይደረግባቸዋል ብለዋል፡፡
የኢፌዴሪ ሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተለያዩ የሥራ ሥምሪቶች የተስፋፉባት፣ ምቹ የሥራ ሁኔታ የተረጋገጠባትና ማሕበራዊ ደህንት የሰፈነባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያስችሉት አሠራሮችን በአዲስ መልክ ለመተግበር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ በመድረኩ ተገልጿል፡፡
በአሠሪና ሰራተኛ ግንኙነት ዙሪያ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ላይ በሚያተኩረው ጉባኤ በሀገሪቱ የሚገኙ የአሠሪና ሠራተኛ አደረጃጀቶች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በሥራው ዓለም ላይ የተሠማሩ ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ ከ500 በላይ ሰዎች እንደተሳተፉበት ታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 18/2011
በኢያሱ መሰለ
ፎቶ፡- ሀዱሽ አብርሃ