ይህ አምድ በዋናነት በማይክሮ ደረጃ ያሉ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የሚስተናገዱበት ይሆናል፤ ትልልቅና አነጋጋሪ ሰበር ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች፣ ንግድና አጠቃላይ የቢዝነስ ዘገባዎች ይስተናገዱበታል። ከትንንሽ ስራዎች ተነስተው በትክክለኛው መንገድ ሰርተው ትልቅ ደረጃ የደረሱ ሰዎች ተሞክሯቸውን ያካፍሉበታል። የሳምንቱ ልዩ ልዩ ሸቀጦችና የግንባታ ግብአቶች የገበያ ሁኔታ ይዳሰስበታል።
ወጣት ነው ገና ትዳር ያልመሰረተ እና ከቤተሰቦቹ ጋር የሚኖር። ትልቅ የሥራ ፍላጎት እና ጥረት አለው። በማንኛውም ጊዜ የሚመጡለትን የቴክኒክ ብልሽቶች እና ጥገናዎች አልችልም ብሎ አይመልስም ፤ይልቁንም ከትልቁ የድረገጽ ዓለም ያሻውን ዕውቀት ሸምቶ መፍትሄ ለመስጠት ይነሳል።
በርካቶች ይህንን ጥረቱን አይተው በየቀኑ የተበላሹ ስልኮችን ይዘውለት ሱቁ ድረስ ይመጣሉ። በጎን ደግሞ በተንቀሳቃሽ ስልክ እና በተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች መሸጫ ሱቁ ደግሞ ንግዱን እያቀላጠፈ ይገኛል። የሚያገኛትን ገንዘብ በምንም አይነት ሱስ አያጠፋትም። ይልቁንም ከግል ወጪው የሚተርፈውን ገንዘብ አጠራቅሞ ወዲያውኑ ለሽያጭ የሚሆኑ ተጨማሪ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን ይሸምትበታል።
ወጣት ተመስገን ምትኩ ይባላል፤ የዛሬው እንግዳችን። በአዲስ አበባ ፓስተር አካባቢ ነው ተወልዶ ያደገው። በልጅነቱ ለስፖርት ልዩ ፍቅር እንደነበረው አይረሳውም። በተለይ እግር ኳስ እና አትሌቲክስን ከማዘውተሩ የተነሳ ፈጣን የሰውነት እንቅስቃሴዎችን መከወን ያዘወትራል። በዚህ ላይ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴን እና ቀነኒሳ በቀለን እያየ ማደጉ ሲታከልበት ሲያድግ ሯጭ እንደሚሆን ነበር የልጅነት ህልሙ የሚነግረው። ይሁንና በአትሌቲክሱ ብዙም አልገፋበትም።
አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አዲስ ህይወት እና አዲስ አበባ በተሰኙ ትምህርት ቤቶች ተምሯል። በወቅቱ ደግሞ ወላጆቹ ያዘወትር የነበረውን ሩጫ ብዙም አልወደዱትም እና እነርሱ የሚሰሩትን ቆሎ አሽጎ ለገበያ የማቅረብ ሥራ እንዲላመደው ጥረት ያደርጋሉ። እናቱ ስንዴ ገዝተው ቆሎ ካዘጋጁ በኋላ ቤተሰቡ አሽጎ መርካቶ አካባቢ ያስረክባሉ። የተቀረው ቤተሰብ ደግሞ ገበያው ላይ በስፋት ይሳተፋል።
የቆሎ ንግዱ ለቤተሰቡ ዋነኛው ገቢ እና መተዳደሪያ ነው። እናም አባቱ በዚህ ሥራ እንዲያግዛቸው በርካታ ጊዜ አሻሻጡን አሳይተውታል። ከትምህርት መልስ አሊያም ክረምት ላይ ቆሎ በማሸግ ወደገበያ የማውጣት ሥራውን ቢከውንም መሰላቸቱ ግን አልቀረም። ይህን መሰላቸት የታዘቡት አባቱ ግን የእረፍት ጊዜውን እንጨት ቤት ሙያ እየቀሰመ እንዲያድግ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የእንጨት ውጤቶች ማምረቻ አስገብተውት ነበር።
እንዲህ እንዲህ እያለ በቤተሰብ ቁጥጥር ስር አልፎ አልባሌ ቦታ ሳይውል ከትምህርት እና ጥናት የተረፈውን ጊዜ በሥራ እያሳለፈ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱ ድልበር ትምህርት ቤት ገባ። በወቅቱ ግን ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ በጽኑ ታመመ። በትምህርቱ ጎበዝ የነበረው ወጣት ተመስገንም የ10ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ትምህርት ወስዶ የሚፈልገውን ውጤት ሳያመጣ ቀረ።
ህመሙ ግን እየጠናበት በመምጣቱ አካባቢ እንዲቀይር ምክር ተሰጠው። እናም ከቤተሰቦቹ ፓስተር አካባቢን ለቆ ፒያሳ ወደሚገኙት አክስቱ ዘንድ አመራ። ትንሽ ሻል ሲለውም ትምህርቱን በጀኔራል ዊንጌት በቴክኒክና ሙያ አውቶ መካኒክ ዘርፍ ተቀላቅሎ መማር በመወሰኑ በየቀኑ ከፒያሳ እየተመላለሰ ይማር እንደነበር አይዘነጋውም። በጀኔራል ዊንጌትም ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋም ሶስት የትምህርት ዓመታትን ካሳለፈ በኋላ ተመርቆ ተሰናበተ። ከምረቃው በኋላ ወዲያውኑ ግን በሙያው ሥራ አልጀመረመ። ይልቁንም ፒያሳ አካባቢ የሞባይል ጥገና ሱቅ የነበረው ጓደኛው ዘንድ በረዳትነት ገብቶ ያግዘው ጀመር።
አንድም የሞባይል ጥገና እና ሽያጭ ዕውቀት ያልነበረው ወጣቱ ከጓደኛው ስር ስር እያለ አንድ በአንድ የስልኮችን አይነት እና የብልሽታቸውን ምክንያት ያጠና ገባ። አነስተኛ ጥገናዎችን ወደማከናወን ሲሸጋገር ደግሞ ጓደኛው በማይኖርበት ወቅትም የተበላሹ ስልኮችን በእራሱ ለመጠገን ይሞካክር ጀመር። አንድ ዓመት በፒያሳ እንዲሰራ ደግሞ ጓደኛው አዲስ ሞባይል ቤት ከሚከፍት ሰው ጋር አስተዋወቀው።
ወጣት ተመስገንም ሙያ ያለማመደው ጓደኛውን ተሰነባብቶ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ የሚገኝ የስልክ መሸጫ አዲስ ሱቅ ውስጥ የሞባይል ጠጋኝ ሆኖ ተቀጠረ። በወቅቱ እንደሚያስታውሰው ክፍያው በኮሚሽን መልክ ነበር። እናም አንድ የስልክ ጥገና በ200 ብር ካከናወነ እርሱ ግማሹን ይወስዳል፤ ግማሹን ደግሞ የሱቁ ባለቤት ይወስድና ይለያያሉ። ሥራ ከሌለም ባዶ እጁን ወደቤቱ መመለሱ አይቀሬ ነበር።
ከስድስት ወራት የቦሌ ሚካኤል የሞባይል ጥገና የኮሚሽን ሰራተኝነት ከሰራ በኋላ ግን አንዲት ዘመዱ የእራሷን ሞባይል መሸጫ ሱቅ እንደምትከፍት እና እርሱም አብሯት እንዲሰራ እንደምትፈልግ ታጫውተዋለች። ቤተሰቡም በሥራው ተስማምተዋልና ከዘመዱ ጋር አብሮ ጉርድ ሾላ አካባቢ የተከፈተች አነስተኛ ሱቅ ውስጥ የሞባይል ስልኮችን እየጠገነ ለመስራት ተስማማ። ጉርድ ሾላ አካባቢ የሞባይል መሸጫ ሱቅ ውስጥ ጥገናውን ቀጠለ። እንደወንድም የሚያየው የአጎቱ ልጅ ደግሞ የእርሱ ረዳት ሆኖ የሞባይል ጥገናው ላይ እንዲሳተፍ አደረገ።
ከጊዜያቶች ቆይታ በኋላ ግን የሞባይል ሽያጭ ንግዱ እንዳሰበችው አዋጭ ስላልሆነላት የሱቁን ንብረት ሸጣ ወደሌላ ዘርፍ ለመሰማራት እንደፈለገች አወቀ። በወቅቱ ዘመዱ ቤት እየሰራች ወደማከራየቱ ስትሰማራ እርሱ ደግሞ ከአጎቱ ልጅ ጋር ጥቂትም ቢሆን ደንበኛ እየለመደ የመጣውን ሱቅ ጠቅልለው ለመያዝ ተስማሙ። ከቤተሰብም 20 ሺ ብር በመበደር በወቅቱ የነበሩ ኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን እና ለሽያጭ የቀረቡ ጥቂት ስልኮችን በመግዛት ወደ ሥራ ገባ።
ወጣት ተመስገንም በተባራሪነት የሚመጡ የስልክ ጥገናዎችን እየሰራ ካላገኘም አንድም ስልክ እና የስልክ መሸፈኛ ቢሆን ሸጦ በትዕግስት እየሰራ የቤት ኪራዩን በየወሩ ከፍሎ መስራቱን ቀጠለ። ወጣቱ እንደሚያስታውሰው ሥራውን በእራሱ መምራት ሲጀምር ከሶስት ዓመት በፊት በቀን ቢያንስ 250 ብር የሚያወጡ የጥገና ሥራዎችን ያከናውን ነበር።
ከጊዜ ወደጊዜ አንድ በአንድ የሞባይል ጥገና የሚያስፈልጉ ተጨማሪ መሳሪያዎችን በማሟላት በአካባቢው ጥሩ የሞባይል ጥገና ገበያ ያለው ወጣት ወደመሆን ተሸጋገረ። ከጥገናው በተጨማሪ በጎን ደግሞ <<ጂፓስ>>፣ የሳተላይት መቀበያ ኤሌክትሮኒክስ ወይም<<ሪሲቨር>>፣ የስልክ መለዋወጫዎች፣ እና የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን በማስገባት ሽያጩንም ከአጎቱ ልጅ ጋር ያቀላጥፈው ገባ።
በጥቂት ወራት የቤተሰቡንም ብድር በመመለስ ወደትርፍ በመግባቱ ሥራው ላይ ይበልጥ ትኩረት አድርጓል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከስልክ በተጨማሪ ኮምፒዩተር እና የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ሥራ ሲመጣ ሶፍትዌር በመጫን እና እቃዎችን በመቀየር ሥራውን ለማሳደግ ጥረት ያደርጋል።
አሁን ላይ በሞባይል ጥገናው ብቻ በቀን አንድ ሺ ብር የሚያገኝበት ቀን እንዳለ የሚናገረው ወጣት ተመስገን ከሽያጩ ደግሞ ተጨማሪ ገቢ እንደሚገኝ ይገልጻል። በየዕለቱ የሚያገኘውን ገቢም ወደእቃ በመቀየር ሱቁን እያስፋፋው ነው። የውሃ ማጣሪያ ዕቃዎች፣ ስፒከሮች፣ አዳዲስ የሽያጭ ስልኮችን፣ መፍጫዎች እና ሌሎች ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችንም ከመርካቶ እና ከተለያዩ አስመጪዎች እየተቀበለ ይሸጣል።
በየጊዜው እቃ ሲሸጥ በየጊዜው ተጨማሪ እቃዎችን እያስገባ በትርፍ ላይ ትርፍን እያሳደገ ይነግዳል። በዚህም ምክንያት ሃብቱን በገንዘብ ሳይሆን በንብረት እንዲተምነው የግድ ሆኗል። በተለይ በአማካይ ሶስት ሺ ብር የሚሸጡ ሙዚቃ ማጫወቻ ጂፓስ ኤሌክትሮኒክሶች እና ውሃ ማጣሪያዎች ከፍተኛ ብር ከሚይዙ እቃዎቹ መካከል መሆናቸውን ወጣቱ ይናገራል። በሱቁ በራፍ ላይም በርካታ የሳተላይት ዲሽ መሳቢያ ሳህኖች ተደርድረው ገዥዎችን እየተጠባበቁ ይገኛል። አንዱን ሲሸጥም ባገኘው ትርፍ ሌላ ይገዛበታል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ 20ዎቹ ውስጥ የሚገኘውን አፍላ የወጣትነት ዕድሜው በስራ ያሳልፋል።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ሥራው አልጋ በአልጋ እንዳልነበር የሚያወሳው ወጣቱ በተለይ አምና የ50 ሺ ብር ዓመታዊ ግብር ሲጣልበት ከአቅሜ በላይ ነው በማለት ሥራውን ጭምር ለማቆም የወሰነበት ጊዜ እንደነበር ያስታውሳል። ይሁንና በትዕግስት ነገም ሰርቶ የበለጠ ማደግ እንደሚችል በማመኑ ከቤተሰብም ጭምር ድጋፍ ጠይቆ ግብሩን በመክፈል ሥራው ላይ ትኩረት እንዳደረገ ይናገራል።
በሌላ በኩል ደግሞ የሞባይል ጥገና ሲያከናውን ተጨማሪ ብልሽት ሲያጋጥመው ከደንበኛው ጋር ያለመግባባት ውስጥ የገባባቸው የተወሰኑ ቀናት መኖራቸውን ይናገራል። በተለይ ችግሩን በቶሎ የማይረዱ እና በጉልበት የሚያምኑ ሰዎች በስልካቸው መበላሸት ምክንያት ከእርሱ ጋር የተጣሉበት ጊዜ እንደነበረም አይዘነጋውም። የሚመጡበትን ፀቦች እንዳመጣጣቸው ከመመለስ ባለፈ ግን ስለሥራው በማሰብ ችግሩን በትዕግስት አልፎ ጉዳዩን በሰላም የፈታባቸው በርካታ ጊዜያቶች መኖራቸውን ደግሞ አይዘነጋቸውም።
<<ሥራው ሽያጭ እና ጥገና እንደመሆኑ ከፍተኛ ትዕግስት ይፈልጋል>> የሚለው ወጣት ተመስገን ግልፍተኝነት እና ንዴት ይበልጥ ንግዱን እንደሚጎዱበት ስለሚያውቅ በተቻለ መጠን ጥንቃቄ ያደርጋል። ነገም በተሻለ ደረጃ እንደሚለወጥ ተስፋ ስለሰነቀ ዛሬን ያለድካም አንገቱን ደፍቶ ይሰራል። ነገ ላይ በርካታ እቃዎችን የሚያገበያይ የኤሌክትሮኒክስ ማዕከል ከፍቶ በስልክ ጥገናውን ደግሞ በተሻለ ዕውቀት እና ቴክኖሎጂ ለመስራት ዕቅድ አለው።
የእራሴን ሥራ እየሰራሁ ገቢ በማስገባቴ በእራስ መተማመኑ መጨመሩን የሚናገረው ተመስገን፤ ሥራው በአነስተኛ /በማይክሮ/ ደረጃ ቢሆንም ሥራ አጥ ሆኖ ቤተሰቦቹንና አገሩን ከማስቸገር ተሻግሮ ገቢ እያስገኘለት መሆኑን ይገልጻል። እያንዷንዷም የንግድ ቀን ተጨማሪ ደንበኛ እና ገበያ ይዛ የመምጣት እድሏ ሰፊ ስለሆነ በአግባቡ ጥቅም ላይ ተውላለች።
<<ሥራ አዋጭነቱ ተጠንቶ ከተገባበት በርካታ አትራፊ ዘርፎች አሉ >> የሚለው ወጣት ተመስገን ማንም ወጣት ሥራ መስራት እና ገንዘብ ማግኘት ባይጠላም ያሰቡት ደረጃ ለመድረስ ግን ትልቅ ትዕግስት እንደሚያስፈልግ ይናገራል። በተለይ ተስፋ አስቆራጭ የሥራ አጋጣሚዎችን በጽናት አልፎ ተወዳዳሪ መሆን ካልተቻለ ኪሳራው ከባድ ይሆናል። ንግድ ወጪ እና ገቢን አመዛዝኖ ትርፍ ለማግኘት ጊዜ ይጠይቃል ፤በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ ወጣቶች ታጋሽ መሆን ካልቻሉ አስቸጋሪ ነው። እናም ነገን ብሩህ ለማድረግ ዛሬን በሥራ እና በጥረት እያሳለፉ ለተሻለ ህይወት መትጋት ያስፈልጋል የሚለው ደግሞ ምክሩ ነው።
ፎቶ -በሐዱሽ አብርሃ
ወጣት ተመስገን ምትኩ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2012
ጌትነት ተስፋማርያም