7የተባበሩት መንግስታት ህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) የሕፃናት የአመጋገብ ስርዓት ግምገማ ላይ ተመስርቶ በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት ይፋ ባደረገው ጥናት፤ በዓለም ዙሪያ ካሉ ህፃናት አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ወይም ቁጥራቸው 700 ሚሊዮን የሚጠጉ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ለተመጣጠነ የምግብ እጥረት ወይም ከመጠን በላይ ለሆነ ውፍረት በመጋለጣቸው ምክንያት ለተለያዩ የጤና ችግሮች ተጋላጭ እንደሆኑ ዩኒሴፍ በጥናቱ አስታውቋል፡፡
ጥናቱን አስመልክቶ የዩኒሴፍ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሄንሪታ ፎሬ እንደተናገሩት፤ “ህፃናት በአግባቡ የማይመገቡ ከሆነ የጤና ድሃ ሆነው ይኖራሉ፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ እያለ፤ ግን ጤናማ የአመጋገብ ስርዓት በዓለም ላይ እንዲሰፍን የምናደርገው ትግል መሰረት እያጣ ነው” ሲሉ ችግሩ ስር መስደዱን ይናገራሉ፡፡
የተመጣጠነ የምግብ እጥረትን ለማስወገድ በየዓመቱ ከዓለም ኢኮኖሚ ሶስት ነጥብ አምስት ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት ወጪ እንደሚደረግ ሪፖርቱ ያመላከተ ሲሆን፤ እ.አ.አ ከ1990 እስከ 2015 ባለው ጊዜ በድሃ አገራት ውስጥ ወደ40 በመቶ የሚጠጉ ህፃናት በተመጣጣኝ ምግብ እጦት ምክንያት ለከፋ ችግር ተጋላጭ ሆነዋል። በአሁኑ ወቅትም ከአራት ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው 149 ሚሊዮን ሕፃናት በህይወት የመኖር እድላቸው በጣም አጭር ሲሆን፤ ህፃናቱም ለአዕምሮ እና ለአካል እድገት መቀጨጭ ተጋላጭ እንደሆኑ ጥናቱ አመልክቷል፡፡
ለአብነት ያህል፤ በእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች በምትገኘው የመን እ.አ.አ ከ2013 እስከ 2018 በተሰበሰበ መረጃ መሠረት፤ 46 በመቶ የሚሆኑ እድሜያቸው ከአራት ዓመት በታች የሆኑ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ህፃናት እጅግ ለከፋው የሰብአዊ ቀውስ ተጋላጭ ናቸው። ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ በዚሁ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ሌሎች 50 ሚሊዮን ሕፃናት ለከፋ ድህነት በመጋለጣቸው ለመቀንጭር ተጋላጭ መሆናቸው ተጠቁሟል።
በተመሳሳይ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑት ህፃናት መካከል ግማሽ ያህሉ ጠቃሚ ቫይታሚኖችን እና ማዕድናትን እንዳላገኙ ጥናቱ ያሳወቀ ሲሆን፤ ይሄንን ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ችግር ዩኒሴፍ “የተደበቀ ረሃብ” በማለት ጠርቶታል፡፡
በአንጻሩ፤ ባለፉት ሦስት አስርተ ዓመታት ብቻ በአደጉ አገሮች ውስጥ ጤናማ ያልሆነ እና የህፃናትን ህይወት ለአደጋ የሚያጋልጥ የአመጋገብ ስርዓት በመከሰቱ፤ ህፃናትን ከልክ ላለፈ ውፍረት ተጋላጭ መሆናቸው ተገልጿል።
የዩኒሴፍ የምግብ ፕሮግራም ኃላፊ የሆኑት ቪክቶር አጉአዮ ችግሩን አስመልክቶ ለኤ.ኤፍ.ፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት፤ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት፣ ወሳኝ የሆኑ ንጥረ ነገሮች እጥረት እና ከመጠን በላይ ውፍረት እነዚህ ሶስት ችግሮች በተለያዩ አገራት፣ ሰፈር ብሎም በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ችግሩ እየጨመረ ይገኛል።
በዓለም ላይ በሁሉም የዕድሜ ክልሎች ውስጥ ከ800 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መቋጫ ላጣ ረሀብ ተጋላጭ የሆኑ ሲሆን፤ ሁለት ቢሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በተሳሳተ የአመጋገብ ስርዓት ከመጠን በላይ በመመገብ ከልክ ላለፈ ውፍረት ተጋላጭ በመሆን ለልብ ህመም እና ለስኳር በሽታ ሰለባ እንደሆኑ ኃላፊው ተናገረዋል።
ህፃናት ይችን ዓለም ከተቀላቀሉ ጀምሮ ባሉት የመጀመሪያዎቹ አንድ ሺህ ቀናት ውስጥ ያላቸው የአመጋገብ ስርዓት ለአካላዊ ጤንነት እና ለአእምሮ እድገት መሠረት መሆኑን ድርጅቱ ከአምስት ዓመት በታች በሆኑ ሕፃናት የአመጋገብ ስርዓት ላይ ባጠናው ጥናት ላይ አረጋግጧል። የዓለም አቀፍ የጤና መመሪያዎች እንደሚመከሩት በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወሮች ህፃናት ሙሉ በሙሉ የእናት ጡት ወተት ብቻ ማግኘት ቢኖርባቸውም ቅሉ፤ በዓለም ላይ ከአምስት ህፃናት ውስጥ ሁለቱ ብቻ የእናት ጡት ወተት እንደሚያገኙ ጥናቱ አመልክቷል።
ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው፤ የቫይታሚኖች እና የማዕድኖች እጥረት በሽታ የመከላከል፣ የማየት እና የመስማት አቅምን የሚያዳክም ሲሆን፤ የብረት እጥረት ደግሞ የደም ማነስ እና የማሰብ አቅምን (IQ) እንደሚቀንስ የሪፖርቱ ዋና አዘጋጅ የሆኑት ብሪያን ኬሌይ ለኤ. ኤፍ. ፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
እርሳቸውም፤ በዓለም ላይ የህጻናት ከመጠን በላይ ውፍረት እየጨመረ መምጣቱ በግልጽ የሚታይ ቢሆንም፤ ችግሩ ትኩረት አልተሰጠውም። ምክንያቱም ዓለም አሁንም ችግሩን አልተረዳውም። ችግሩ ከ30 ዓመታት በፊት በድሃ አገራት ውስጥ ያልነበረ ቢሆንም፤ ዛሬ ላይ ግን 10 በመቶ የሚሆኑ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ ከመጠን በላይ ለሆነ ውፍረት ተጋላጭ ሆነዋል።
ስለዚህ፤ “ጊዜው ከማለፉ በፊት ከመጠን በላይ ውፍረት መቀነስ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል። አሁን ላይ ችግሩን ቀድመን የምንከላከልበት መንገድ ላይ ካልተነጋገርን፤ ስር ከሰደደ በኋላ ችግሩን ለመቅረፍ መታገል ‘ከወደቁ በኋላ መንፈራገጥ ትርፉ መላላጥ’ እንዳይሆን እሰጋለሁ” ሲሉ ኬሌይ የችግሩን አሳቢነት ተናግረዋል፡፡
ጥናቱ እንደሚያሳየው በበለጸጉ አገራት ከአምስት እስከ 19 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ ካሉ ልጆች በአሜሪካ 41 ነጥብ 86 በመቶ፣ በጣሊያን 36 ነጥብ 87 በመቶ እና በፈረንሣይ ደግሞ 30 ነጥብ 09 በመቶ ከመጠን በላይ ለሆነ ውፍረት ተጋላጭ በመሆን ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ሲይዙ፤ በአንጻሩ ጃፓን 14 ነጥብ 42 በመቶ የሚሆኑ ህፃናት ብቻ በችግሩ ተጠቂ በመሆናቸው ከአደጉ አገራት መካከል ዝቅተኛውን ደረጃ መያዟ ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል፤ የተመጣጠነ የምግብ እጥረትን ለመቅረፍ የሚደረገው እርብርብ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሊገታ እንደሚችል ጥናቱ ያስጠነቀ ሲሆን፤ ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ጀምሮ አንድ ዲግሪ ሴልሺየስ የሙቀት መጠን በመጨመሩ በግብርናው ዘርፍ ከ80 በመቶ በላይ ለተከሰቱ ጉዳቶች እና ኪሳራዎች ምክንያት በመሆን አያሌ ሰዎችንና አካባቢዎችን ለረሀብና ለድርቅ ተጋላጭ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም፤ እ.አ.አ በ2100 የምድር አማካይ የሙቀት መጠን ሌላ ሁለት ወይም ሶስት ዲግሪ ሴልሺየስ የሙቀት መጠን እንደሚጨምር ጥናቱ ያመላከተ ሲሆን፤ የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ሊቃውንት ባጠኑት ጥናት ደግሞ፤ የካርቦን ልቀት መጨመር በሰብሎች ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ ማለትም ዚንክ፣ ብረት እና ቫይታሚን ቢን የመሳሰሉ ለሰውነት ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮች እና ቫይታሚኖች እየቀነሰ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
በአጠቃላይ፤ ጥናቱ እንደሚጠቁመው ጤናማ የልጆች የአመጋገብ ስርዓት ማረጋገጥ የነገ አገር ተረካቢ ትውልድን በህይወት የመኖርና ህልውና ማረጋገጥ በመሆኑ፤ በተለይ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦትን ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጠው የፖለቲካ ውሳኔ ሊሆን እንደሚገባ አሳስቧል።
ምንጭ: አልጄዚራ
እና ኤኤፍፒ የዜና ወኪል
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2012
ሶሎሞን በየነ