አምባሳደር ፍራንሲስኮ ማዴራ በሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ልዩ መልእክተኛና የአፍሪካ ሕብረት ተልእኮ በሶማሊያ (አሚሶም) ዋና ኃላፊ ናቸው። በአሁኑ ወቅት በሶማሊያ ሀገራዊና ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለምን ተስፋ እንዳሳደሩ እንዲሁም በ2021 (እኤአ) የሶማሊያ ጸጥታ ኃይሎች ሙሉ በሙሉ ኃላፊነቱን ወስደው ከአሚሶም እንደሚረከቡ ለኒው አፍሪካን መፅሔት አስተያየታቸውን ገልጸዋል። ተስፋቸው ምን ላይ የተመሰረተ ይሆን?
በሚያዘያ 30 2018 (እኤአ) የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ጸጥታ ምክርቤት በሰፊው ከመከረበት በኋላ የሶማሊያን የሽግግር ግዜ እቅድ አጽድቋል። ከዚያን ግዜ ጀምሮ የአፍሪካ ሕብረት ተልእኮ በሶማሊያ (አሚሶም) የተሰጠውን ግዳጅ ተቀብሎ የቀጠለ ሲሆን በሽግግሩ ግዜ በተቀመጠለት የግዜ ሰሌዳ በመመራት የተሰጠውን ኃላፊነት በመጠቀም ለውጦችን ማስመዝገቡን ቀጥሎአል ብለዋል የአሚሶሙ ቁንጮ ፍራንሲስኮ ማዴራ።
የሶማሊያ የሽግግር ግዜ እቅድ በሶማሊያ ፌደራል መንግስትና በአጋሮቹ የተዘጋጀ ሲሆን አሚሶም በ2021 (እኤአ) ለቆ ከመውጣቱ በፊት የጸጥታና ደህንነት ኃላፊነቱን ሙሉ በሙሉ ለሶማሊያ ብሔራዊ የደህንነት ኃይሎች ለማስረከብም ያለመ ይመስላል። ምን ያህል የተሳካ ይሆናል የሚለው ጊዜ የሚመልሰው ነው።
በሶማሊያ የደህንነት ቀጠና ውስጥ ዋነኛ የሆነው አሚሶም በ2018 (እኤአ) የመጀመሪያዎቹን የሽግግር ፕሮግራሞች ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚናዎችን ተጫውቷል። ማዱሮ ከሶማሊያ የመውጪያ ስትራቴጂ ብለን ያስቀመጥናቸውን አሳክተናል ይላሉ። ‹‹ከአምስት በላይ የዘመቻ ማዘዣ ቦታዎችን (ኮማንድ ፖስት) ለሶማሊያ ብሔራዊ የደህንነት ኃይል ያስረከብን ሲሆን የሰማሊያን ብሔራዊ የጸጥታ ኃይል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ስልጠናዎችን እየሰጠን እንገኛለን›› ብለዋል ማዱሮ። ይሄ ሁሉ ስራ የተሰራው የሶማሊያ ባለስልጣናት ስትራቴጂካዊ ትብብርና ተሳታፊነት በመኖሩ ነው።
ባለፈው አመት በጸጥታው ግንባር እድገቶች ተመዝግበዋል። የሶማሊያ የጸጥታ ኃይሎች ግዳጃቸውን በብቃት የመወጣት አቅማቸው ጨምሯል። የሶማሊያ ብሔራዊ ሠራዊት ራሱን ችሎ ማጥቃት ሰንዝሮ ሲያሸንፍና ቦታዎችን ሲቆጣጠር አይተናል። ይህ ለአሸባሪዎች የአሸባሪነት ቀናቸው እየተቆጠረና እያለቀ መሆኑን የሚያሣይ ጠንካራ መልእክት ነው ብለዋል ኃላፊው ።
በሙያ ብቃት በሚገባ የሠለጠነውና የታጠቀው የሶማሊያ ብሔራዊ ሠራዊት አገሪቱ ውስጥ ከአሸባሪዎች ጋር የሚደረገውን የውጊያ ጨዋታ በተግባር የሚለውጥ ነው። በታችኛው ሸበሌ አካባቢ የሶማሊያ ሠራዊትና አሚሶም ባካሄዱት የጣምራ ወታደራዊ ዘመቻ አካባቢውን ተቆጣጥረው የነበሩ አሸባሪዎችን እንዲያፈገፍጉ አድርገዋል።
በቅርቡ ሳቢድና ባሪሬ በተባለው ቦታ ከአሸባሪዎች ጋር በተደረገው ውጊያ ከፍተኛ ድል ተመዝግቦአል። ለሰባት አመታት ሳቢድ የተባለው ቦታ የአሸባሪዎች ፈንጂ መገጣጠሚያ ነበር። አሁን ግን ነጻ ወጥቶአል። ይህ የሚያረጋግጠው የሶማሊያ ብሔራዊ ሠራዊት የተሳካ ጸረ አሸባሪ ዘመቻዎችን ራሱን ችሎ መምራት እንዲሁም የሀገሩን የደህንነትና ጸጥታ ኃላፊነት ተረክቦ መስራት የሚያስችል አቅምና ችሎታ ያለው መሆኑን ነው።
ይህ ከሌሎች ሁኔታዎች ጋር ተዳምሮ ተፈላጊውን የሠራዊት ቁጥር በምልመላ ማዘጋጀት፤ተገቢ ስልጠና መስጠት፤ አስፈላጊ ትጥቆችን ማሟላትና ለሠራዊቱ የሚደረገውን የደመወዝ ክፍያ በአግባቡ መፈጸምን ያካትታል። በዚህ አጋጣሚ አለም አቀፍ አጋሮች የሶማሊያን የፌደራል የጸጥታ ኃይልና የፌዴራሉን አባል መንግስታት ፖሊስና መከላከያ አቅም ለመገንባት በምልመላና ስልጠና ድጋፋቸውን በመቀጠላቸው የአውሮፓ ሕብረትን፤ አሜሪካን፤ እንግሊዝን ‹‹እናመሰግናለን›› ብለዋል ፍራንሲስኮ።
በአለም አቀፍ አጋሮች ድጋፍ የሶማሊያ የጸጥታ ኃይሎች በቅርቡ ነጻ በወጡት አካባቢዎች የሕዝቡን ሰላም እያስከበሩ፤ ቅኝት እያደረጉ፤ መሰረተ ልማቶችን መንገድ ሆስፒታሎችንና ትምህርት ቤቶችን እየጠበቁ እንዲሁም መረጋጋቱን እየደገፉና በመልሶ ግንባታ እንቅስቃሴዎችም እየተሳተፉ ይገኛሉ።
‹‹በሶማሊያ የምናደርገው ዘመቻ የሚመራው በአፍሪካ ሕብረት ሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት፤ እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ነው። ከታህሳስ 2017 (እኤአ) ጀምሮ አሚሶም የተባበሩት መንግስታትን ውሳኔ በመከተል በሶማሊያ የሚገኘውን የሠራዊቱን ቁጥር ቀንሶአል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በታህሳስ 2021 (እኤአ) አሚሶም ሙሉ በሙሉ ከሶማሊያ የሚወጣ መሆኑን ወስኖ ማስታወቁን ፍራንሲስኮ ያስታውሳሉ።
በዚህ አመት የካቲት አሚሶም ሌላ 1000 ሠራዊቱን ከሶማሊያ ይቀንሳል። በአሚሶም የሠራዊት ቁጥር ቅነሳ ማለት ማዘዣ ጣቢያዎችንና ሌሎችንም ተቋሞች ለሶማሊያ ብሔራዊ ሠራዊት ያስረክባል ማለት ነው። በአለፈው አመት የአሚሶም ኃይሎች የመቋዲሾ ዩኒቨርሲቲን፤ የመቋዲሾ ብሔራዊ ስታዲዮምን እንዲሁም የጃሌ ሲያድ ወታደራዊ አካዳሚን ጥበቃ የጸጥታና የደህንነት ኃላፊነት ለሚመለከታቸው የሶማሊያ ተቋማት ማስረከባቸውን ኃላፊው ገልጸዋል።
አሚሶም የሶማሊያን የሽግግር ግዜ እቅድና የአወጣጥ ስትራቴጂን ለማሳካት አዲስ የዘመቻ ፕላን በማውጣት አስተዋውቋል። የራሱን የወታደር፤ፖሊስና ሲቪል ኃይሎች አደረጃጀት ለውጧል። የአሚሶምና የሶማሊያ ወታደራዊ አዛዦች ከወታደራዊ ጎኑ አኳያ እቅዱን በጋራ መክረው አዳብረዋል። በዚህም መሰረት አሚሶም አንዳንድ ክፍሎችን ያከስማል ወይንም ለሶማሊያ የጸጥታ ኃይሎች ያስረክባል። በጁባላንድ ግዛት ቪያ አፍማዶው የተባለውን ወታደራዊ ጦር ሰፈር ለጁባላንድ የጸጥታ ኃይሎች ማስረከቡን ማዱሮ ተናግረዋል።
ጀግኖቹ የአሚሶም ወንዶችና ሴት ፖሊሶች ለፌደራሉና የፌደራሉ አባል ለሆኑ መንግስታት የዘመቻ ድጋፍና ስልጠና መስጠታቸውን ቀጥለዋል። ሁለት አሚሶም የመሰረታቸው የፖሊስ ክፍሎችና 67 የፖሊስ መኮንኖች ስልጠና ለመስጠት ለመቆጣጠርና መጪውን ብሔራዊ ምርጫ ለመደገፍ ይሰማራሉ። የአሚሶም ሲቪል ሠራተኞች ድጋፍ ለማድረግ የፌደራሉ አባል መንግስታት በሆኑት ጁባላንድ፤ ደቡብ ምእራብ እና ሂርሸበሌ ተሰማርተዋል። በዚህም አሚሶም በሶማሊያ በመጀመሪያ ከተሰማራበት ከ12 አመታት በላይ የሰራቸውን ስራዎችና ያስገኛቸውን ውጤቶች ያስጠብቃል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2012
ወንድወሰን መኮንን