በኢንዱስትሪው እና በትምህርት፣ ስልጠናና ምርምር ተቋማት መካከል ሊኖር የሚገባው ትብብር አንዱ ለአንዱ አጋዥና የውጤታማነት አጋር በመሆን ከራሳቸው አልፎ ለአገር ሁለንተናዊ የእድገት ጉዞ ውስጥ ድርሻው ተኪ የሌለው ስለመሆኑ ይነገራል። ይሁን እንጂ በሁለቱ በኩል ያለው ተናብቦና ተቀናጅቶ የመስራት ሂደት በሚፈለገው ልክ ያልተጓዘ፤ ይልቁንም በምክንያት ታጥሮ የቆየ መሆኑ ይገለጻል። ይሄን ችግር ለማቃለልም የሁለቱን ጥምረት የሚከታተልና አቅጣጫ የሚያሰጥ ብሔራዊ ካውንስል ተቋቁሞ ወደስራ የገባ ሲሆን፤ ይህ ካውንስል ሰሞኑን ሁለተኛ ስብሰባውን በማድረግ በ2011 ዓ.ም የነበረውን አፈጻጸም በመገምገም የ2012 ዓ.ም እቅዱ ላይ ተወያይቷል።
እኛም በዛሬው እትማችን በመድረኩ ላይ የነበሩ ሀሳብና አስተያየቶችን መነሻ በማድረግ፤ ዘርፉን በዋናነት እንዲያስተባብር ኃላፊነት ከተሰጠው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እያከናወነ ያለውን ስራ በተመለከተ ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያምን ያነጋገርን ሲሆን፤ በተለይም በዘርፉ የተስተዋሉ ችግሮች፣ የተወሰዱ እርምጃዎች እና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት በማድረግ በሚከተለው መልኩ ይዘን ቀርበናል።
እንደ ፕሮፌሰር ሂሩት ገለጻ፤ የትምህርት ስልጠና ምርምር ተቋማት እና ኢንዱስትሪው ተሳስሮና ተቀናጅቶ እንዲሰሩ የሚፈለገው የምርምር ውጤትን ኢንዱስትሪው ተግባራዊ አድርጎ፤ ኢንዱስትሪው ውስጥ ያለው ባለሙያም በትምህርት ተቋማት መጥቶ ተግባራዊ ልምምዱን እንዲያስተምር ለማድረግ ነው። ተማሪውም በኢንዱስትሪው ሄዶ ተግባራዊ ልምምዱን እንዲያደርግ እና ልምምድ እንዲያገኝ፤ የምክር አገልግሎትና የጋራ ምርምር፣ ችግር ፈቺና የኢንዱስትሪውን ምርታማነት የሚያሳድግ ብሎም ተወዳዳሪ የሚያደርግ ስራንም ታሳቢ ያደረገም ነው።
ይሄ መሆኑ ደግሞ ትልቅ አገራዊ ፋይዳ ይኖረዋል። ምክንያቱም የኢንዱስትሪው ምርታማነትና ውጤታማነት ሲጨምር የቴክኖሎጂ አጠቃቀምም ሆነ የኢኮኖሚ እድገቱ ይጨምራል። የስራ እድል ፈጠራውም ይሰፋል። ትምህርቱም ምርምሩም ተግባራዊ በሆነ ጉዳይ ላይ ትኩረት እያደረገ ይሄዳል። በመሆኑም ትስስሩ ለሁለቱም አካላት፤ ለአገርም ጥቅም ያለው ነው።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ የሳይንስ፣ ቴክሎኖጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ የትኩረት አቅጣጫ ተብለው ከወጡት ውስጥ አንዱ ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ምርምር ትስስር ነው። ይህ ካውንስልም ያንን ነው የሚመራው። ይህ ደግሞ አሁን በአዲሱ መዋቅር ወደ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተካትቷል። ይሄን መነሻ በማድረግም ሚኒስቴሩ ጥናት ያስጠና ሲሆን፤ የነበሩ መልካም ተሞክሮዎች ታይተዋል፤ ተግዳሮቶቹም ተለይተዋል።
በዚህም ትስስሩ በታሰበው ደረጃ ለምንድን ነው ያልተሰራው፤ ሂደቱስ ለምን በደንብ ተሳልጦ አልሄደም፤ ጉድለቱስ ምንድን ነው፤ ምንስ ቢደረግ ይሻላል፤ የሚል አጠቃላይ ዳሰሳ የተደረገ ሲሆን፤ ለዚህ በርካታ ምክንያቶች መኖራቸው የታየበት እና ችግሮቹም ሁለቱም ላይ (የምርምር ተቋማቱም ላይ ኢንዱስትሪውም ላይ) ያሉ መሆናቸው ተለይቷል።
በዚህም የትምህርት ስልጠናና የምርምር ተቋማቱ የራሳቸው የሆነ ትኩረት ሰጥተው ያለመስራት፤ በማስተማሩ ላይ ብቻ ትኩረት የማድረግ፤ የሚሰራው ምርምርም ቢሆን ለፕሮሞሽን ፍጆታ እንጂ ችግር ፈቺና ውጤቱ ወደ ኢንዱስትሪ የሚገባ ከፍ ያለ ጠቀሜታ ያለው አድርጎ ትኩረት ሰጥቶ አለመስራት ይታያል። በተመሳሳይ በዚህ ዙሪያ በሁለቱም አካላት ተቀራርቦ ያለመስራት ትልቅ ክፍተት መኖሩ ታይቷል።
በተለይ ተቀራርቦ ከመስራት አኳያ ኢንዱስትሪው ወደትምህርት ተቋማት ሄዶ እዚህ ላይ ምርምር ብታደርጉልኝና ይሄን ችግር በምርምር ብትፈቱልኝ፤ እዚህ ላይ የአቅም ግንባታ ስራ ብትሰሩልኝ ወይም ብታሰለጥኑልኝ፤ እያለ አይደለም፤ እኛም ስንሄድ በሩ ክፍት አይደለም፤ የሚል ሀሳብ ከትምህርት ተቋማቱ ይነሳል። በተመሳሳይ በኢንዱስትሪው በኩል፣ ከፍ ያለ ችግር የሚፈታልን አይነት ምርምር እየመጣልን አይደለም የሚል ምክንያት ይቀርባል። እናም እነዚህ ሀሳቦች ቀረብ ብሎ በደንብ ማየት፣ መፈተሽና ማጥራትን የሚፈልጉ ናቸው።
ምክንያቱም ስራው ትልቅ አገራዊ ፋይዳ ያለው ነው። ሁለቱ አካላት አንድ ላይ ተደምረውና በጋራ ተቀናጅተው ከሰሩ፤ ከካሪኩለሙ ጀምሮ የትምህርት ፕሮግራም ሲቀረጽ የኢንዱስትሪውን ችግር የሚፈታ መሆን ይጠበቅበታል። ኢንዱስትሪ ሲባል ደግሞ የአምራች ዘርፉን ብቻ ሳይሆን፤ አገልግሎቱንም የሚመለከት ነው። በመሆኑም በሁሉም ዘርፍ የሚከናወን ስራ በምርምርና እውቀት የታገዘ፤ ቴክኖሎጂን የሚጠቀምና የሚያላምድ፤ አዳዲስ አሰራርና ፈጠራዎችን ይዞ በመሔድ ተወዳዳሪና ውጤታማ እንዲሆን ያስፈልጋል።
ሚኒስትሯ እንደሚሉት፤ እነዚህ ሁለት አካላት ተባብረው መስራት ቢችሉ እንደ አገር ትልቅ ሀብት አለ። አርባ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ አራት የግል ዩኒቨርሲቲዎች፣ 200 የግል ኮሌጆች እና ከ1500 በላይ የቴክኒክና ሙያ ክህሎት ማሰልጠኛ ተቋማት እንዲሁም ራሳቸውን ችለው የቆሙ በርካታ የምርምር ተቋማት መኖራቸው በራሱ ትልቅ እድል ነው። ምክንያቱም እነዚህ ተቋማት በተለያዩ ሙያዎች የሰለጠኑ ባለሙያዎችን የሚያወጡ፤ ምርምርም እያከናወኑ ያሉ ናቸው።
እነዚህን አካላት ተቀናጅተው እንዲሰሩ የሚያግዘው ብሔራዊ ካውንስሉ ደግሞ የሁለቱ አካላት ጥምር ሲሆን፤ 27 አካላትን አካትቶ የያዘም ነው። ሆኖም ሁለቱ አካላት የተቀናጀ ስራ እንዲያከናውኑና የሚጠበቀው ውጤት እንዲገኝ በጋራ እያቀዱ መጓዝ ይገባል። በጋራ ችግሩን ለይቶና ለችግሩ መቃለልም ሁሉም እኩል ኃላፊነትና የየራሱን የቤት ስራ ወስዶ በአንድ ላይ ስራውን ከአንድ ገጽ መጀመር ይኖርበታል። በዚህ ላይ ደግሞ በችግሮቹም ሆነ በጥቅሞቹ ዙሪያ የጋራ አረዳድ ይዞ ለመጓዝ እንዲቻል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአዋጅ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት ዘርፉን የሚከታተል አንድ ዳይሬክቶሬት በማደራጀት በዳይሬክተር ጄኔራል ደረጃ እየሰራ ነው።
ለዚህ ስራ ስኬታማነትም ያሉ የሕግ ማዕቀፎችን እየፈተሸና እያስተካከለ ይገኛል። ለምሳሌ፣ የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ የተከለሰ ሲሆን፤ አዋጁ ሲከለስም የከፍተኛ ትምህርትና ኢንዱስትሪው በጋራ የሚያስተምሩበትን እድል የሚሰጥ ይዘት እንዲካተትበት ሆኗል። በዚህም ኢንዱስትሪው በዩኒቨርሲቲው ዩኒቨርሲቲውም በኢንዱስትሪው ተሳትፎ ኖሯቸው ሰልጣኞች ንድፈ ሀሳብን ከተግባር አጣምረው የእውቀትና ክህሎት ባለቤት ሆነው የሚወጡበት፤ በገበያውም ተወዳዳሪና ተፈላጊ የሚሆኑበትን እድል የሚፈጥር ነው። በአፈጻጸሙ ላይ ያለውን ሂደት ደግሞ ካውንስሉ የሚከታተልና የሚቆጣጠር ሲሆን፤ ያሉ ችግሮችን እየለየና በጋራ እየመከረ አቅጣጫም የሚሰጥ ይሆናል።
በተመሳሳይ የከፍተኛ ትምህርት ኢንተርፕራይዞች ማቋቋሚያ በሚኒስትሮች ካቢኔ ቀርቦ ጸድቋል። ይህም እያንዳንዱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም (ዩኒቨርሲቲ) የምርምር ውጤቶቹን ወደ ውጤት፣ አገልግሎትና ኢንዱስትሪው የሚሄዱበትን እድል የሚፈጥር ወይም ለማበልጸግ እድል የሚሰጥ ነው። ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ውጤቶቻቸውን ወደሌላ ኢንዱስትሪ ከመውሰድ ባለፈ በራሳቸው ኢንተርፕራይዞች አማካኝነት አበልጽገው ወደገበያ የሚያወጡበትና ወደ ስራ የሚያስገቡበት ነው። ካውንስሉ የሚመራበት መመሪያም መነጠኛ የቴክኒክ ማሻሻያ ተደርጎበታል። በመሆኑም እነዚህና መሰል ለስራው አስፈላጊ የሆኑ የሕግ ማዕቀፎችን የማደራጀትና ለስራ ዝግጁ የማድረግ ተግባራት ተከናውነዋል።
የሕግ ማዕቀፎችን ከማዘጋጀትና ማደራጀት በተጓዳኝ የጋራ ግንዛቤና ተግባቦት እንዲኖር የማስቻል የውይይት መድረኮች እየተካሄዱ ሲሆን፤ እስካሁንም ስድስት ያክል አውደ ጥናቶች ተካሂደዋል። በዚህም ችግሩን በአግባቡ ለይቶ ለችግሩ የሚሆን መፍትሄ በጋራ የማምጣትና የመደገፍ እድልን ይፈጥራል። በመሆኑም ይህ ዓላማ እውን እንዲሆን ድጋፍ እየተደረገ ነው።
በምክክር መድረኩ ከተሳታፊዎች በተነሱ ሀሳቦች እንደተገለጸው ደግሞ፤ በዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ሂደት ውስጥ የተቋማት ድርሻ ማደግ አለበት፤ ከተቋማት ባለፈ የሰዎች የግለሰቦች ሚና ጉልህ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። የኢንዱስትሪዎች፣ ዩኒቨርሲቲዎች/ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና መንግስት የየድርሻቸውን መወጣት አለባቸው። የክትትልና ቁጥጥር ስርዓቱ መላላት ችግር በመኖሩ ይሄም ሊታረም ይገባል። የኢንተርፕሩነር ሺፕ ፕሮግራሙም መታየት ይኖርበታል። በየውይይት መድረኮችና ወርክሾፖች የሚነሱ ሀሳቦችና የሚቀመጡ ጭብጦች ከመድረክ ፍጆታ ባለፈ ሊሰራባቸው ያስፈልጋል፤ ተሳታፊዎችም ከተሳትፎ በዘለለ ስለጉዳዩ ግንዛቤ ይዘውና ለስራ ራሳቸውን አዘጋጅተው መውጣት ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 3/2012
ዘላለም ግዛው