የዓለምን ህዝብ ቁጥርን በተመለከተ ማንም ሰው ቢጠየቅ ቀንሷል ወይም እየቀነሰ ነው የሚል መልስ እንደማይሰጥ ምንም ጥርጥር የለውም። ለማሾፍ ካልሆነ በስተቀር፤ ይህንን ምላሽ የሚሰጠው ደግሞ ዓለምን በመፈተሽ ወይም ጥናቶችን በማገላበጥ አይደለም። ይህን መልስ የሚሰጠው ከሰፈሩ፣ ከአካባቢው፣ ከራሱና ከቤቱ ተነስቶ እንጂ፤ ብዙዎቻችንም እንዲሁ ነን። በምን ያህል ይጨምራል፣ ምንስ ዕድል/ተግዳሮቶች አሉት? የሚሉት ግን ጥልቅ ጥናትንና ሙያዊ ትንተና የሚሹ ናቸው።
ይህ ከላይ የሰነዘርነው አስተያየት የማንም ሰው አስተያየት ነው። ከዚህ ከማንም ሰው አስተያየት ወጣ ብለን አንዳንድ መረጃዎችን መለዋወጥ ተገቢና እጅግ ወቅታዊ ነውና አለፍ አለፍ እያልን እንመለከታቸዋለን።
የህዝብ ቁጥር ነገር ሲነሳ መስማት አዲስ ነገር አይደለም። ከመገናኛ ብዙሃን ጀምሮ እስከ አገራት መሪዎች፤ ከግለሰብ አንስቶ እስከ ትላልቅ ጉባኤዎች ድረስ ስለጉዳዩ ሲነሳና ሲጣል ነው ውሎና አዳሩ፤ ይሁን እንጅ፤ ስለጉዳዩ ውስብስብነት፣ የወደፊት ተግዳሮት፣ በዓለማችን፤ በተለይም በራሱ በሰው ልጅ ላይ ሊያስከትል ስለሚችለው ዘርፈ ብዙ ችግር አብዝተው የሚጨነቁ፣ ተግተው የሚሠሩና ሳይታክቱ የሚጮሁ የዘርፉ ምሁራንና ተቋማት ከላይ የጠቀስናቸውን አካላት «ከወሬ ያለፈ ምንም የማይሠሩ» በማለት ሲወርፏቸው መስማት አዲስ አይደለም። የወቅቱን፣ የመጪውን ሁኔታና የዓለም ህዝብ ቁጥር እያሻቀበ መሄዱን በተመለከተ አባባላቸውንም ሆነ ነቀፋቸውን «ትክክል» ብሎ ከማድነቅ አይመለስም። ጉዳዩ እንዲህ ነው።
በቅርቡ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ የዓለም የምግብ ፕሮግራም፤ የዓለም ባንክ፤ ዓለም አቀፍ የገንዝብ ድርጅት፤ የምግብና ግብርና ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ እንዲሁም ከታወቁ ከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ተቋማት በተከታታይ የሚወጡ መረጃዎች የጉዳዩን አሳሳቢነት አብዝተው የሚያትቱ፤ መፍትሔ ያሉትን ሃሳብ የሚሰነዝሩ፤ አፋጣኝ ዕርምጃ እንዲወሰድ የሚሰብኩ ሆነው ነው የተገኙት፤ እ.ኤ.አ በ1800 አንድ ቢሊዮን የነበረው የዓለም ህዝብ ቁጥር አሁን ወዳለበት ደረጃ የደረሰበትን ፍጥነት በማስላት፣ በመተንተን ትኩረታቸውን 2050 ላይ ያሳረፉትና በብዛት እየጎረፉ ያሉት ሰነዶች እንደሚያመለክቱት፤ በአሁኑ ሰዓት የዓለም ህዝብ ቁጥር በየዓመቱ በ1.1 በመቶ (83 ሚሊዮን) እየጨመረ ነው። በ2017 ከነበረበት 7,486,520.598 በ1.21 በመቶ (90,430,787) በመጨመር፤ በ2018 7, 576,951,385 ይደርሳል ተብሎ የተተነበየው የህዝብ ቁጥር፤ ከወዲሁ መስከረም 2018 በ92,157,695 ጨምሮ ተገኝቷል። በዚሁ ዓመት መጨረሻም 7,669,109.08 ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም ባለፈው ዓመት ተተንብዮ ከነበረው መብለጡን ያሳያል።
እዚህ ላይ የህዝብ ቁጥር ማሻቀብ ፋይዳው ምንድን ነው? ተብለው ሲጠየቁ «ከጦርነት፣ እርስ በእርስ ግጭት፣ የኑሮ ውድነት፣ ዓለም አቀፍ ወንጀል፣ በሽታ . . . በስተቀር የሰው ልጅ ያተረፈው አንዳች ነገር የለም» የሚሉ እየተበራከቱ መምጣታቸውን ሳይጠቅሱ ማለፍ አይቻልምና ይህም እንደ አንድ የጥናት ርእሰ -ጉዳይ ሊወሰድ የሚችል ነው።
እዚህ ጋ ለዚህ የህዝብ ቁጥር እያሻቀበ መሄድ ምክንያቱ ምንድን ነው? ብሎ መጠየቅ አግባብ ነው። ምክንያቱ ምንድን ነው?
ከፈተሽናቸው ጥናቶች መረዳት እንደተቻለው፤ በዓለማችን በየቀኑ 414,085 (በሰዓት 17,253.54) ሕፃናት ይወለዳሉ። ይህም የዓለም ህዝብ ቁጥር በየቀኑ (ይህ በ2018 ነው) በ252,487 ሰዎች ይጨምራል። በረሀብ ምክንያት የሟቾች ቁጥር በአማካይ 162,545 (በሰዓት 6, 772.72) መሆኑና ከወሊድ ምጣኔው ማነሱም ለቁጥሩ መጨመር የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል። (የወሊድ ምጣኔው ከሞት ምጣኔው ጋር ሲነፃፀር በ91,812,002 መብለጡን መረጃዎች ያመለክታሉ።)
ቁጥሩን ጨምቀን ስናስቀምጠው እ.ኤ.አ በ2000 ስድስት ቢሊዮን የነበረው በ2018 7.616 ቢሊዮን መድረሱን፤ በ2030 8.6፣ በ2050 9.8 ቢሊዮን፣ እንዲሁም በ2100 11.2 ቢሊዮን እንደሚደርስ ያሳያል። ይህ ደግሞ መሬት፣ በውሃ የተሸፈነውን ጨምሮ፣ ባላት 136,120,354 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ስፋት ልትመግበው ከምትችለው 10 ቢሊዮን ህዝብ ይበልጣል። በመሆኑም ይላሉ ተመራማሪዎች የሚመለከታቸው ሁሉ ከወዲሁ ሊያስቡበት ይገባል። በተለይ ትምህርትን ከማስፋፋት፣ ግንዛቤን ከማዳበር . . . አኳያ ብዙ ሥራ መሠራት አለበት።
እዚህ ላይ ከህዝብ ቁጥር ጋር በተያያዘ በተለይ ችግሩ ጎልቶ የሚታየው በአፍሪካ፣ በተለይም ከሰሃራ በታች ባሉት አገራት መሆኑን ሁሉም ይስማሙበታል። በአካባቢው የህዝብ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ፣ የምርት መጠን በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መሆኑንም ሁሉም በሚባል ደረጃ እኩል ያሰምሩበታል። ይህም 40 በመቶ የሚሆነውን የአካባቢውን ህዝብ ለረሀብ ዳርጎታል። እንደተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ ሌሎች ጥናቶች ግኝት አንድ አስደማሚ ጉዳይ ቢኖር፣ አካባቢው ለሌሎች ሊተርፍ የሚችል የተፈጥሮ ሀብት ያለው መሆኑ ነው። በአፍሪካ ይህ የተፈጥሮ ሀብት ባለበት የገጠር አካባቢ ከሚኖረው ህዝብ 90 በመቶው በድህነት ውስጥ መኖሩንም ይጠቅሳሉ። እዚህ ላይ የ1977 በሀገራችን የተከሰተውን አስከፊ ድርቅ ቢቢሲ «አረንጓዴው ረሀብ» ሲል ዶክመንታሪ መሥራቱ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚታወስ ነው።
ከላይ የተመለከቱትን አሃዞች መደርደሩ ለምን አስፈለገ? የሚል ጥያቄ/ግርምት ሊመጣ ይችላል። ያለምክንያት አይደለም፤ ይልቁንም ዓለማችን እነዚህን እዚህ የተደረደሩትን «ቁጥሮች» ለማስተናገድ፤ በተለይም ከሁሉም በላይ የሆነውን «ቀለብ መስፈር» ትችላለች ወይ? ነው ጉዳዩ አሁን ያለንበት ሁኔታ ይህን ዓይነት ስለመሆኑ አመላካች ነውን? መልሱ፤ ከላይ እንዳየነውም ሆነ ከታች እንደምንመለከተው አይደለም።
የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንጻር ዓለማችን ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ
በአሁኑ ሰዓት፤ ቀደም ሲል የጠቀስነው 815 ሚሊዮን ህዝብ በምግብ እጥረት ይሰቃያል፤ ሦስት ቢሊዮን በቀን ከ1.25 እስከ 2.50 ዶላር እና በታች የሚያገኝ በመሆኑ የዕለት ጉርሱን መሸመት አይችልም። 22ሺህ ሕፃናት በምግብ እጥረት በየቀኑ ይሞታሉ፤ ከዘጠኝ ሰዎች አንዱ (795 ሚሊዮን ህዝብ) በቂ ምግብ አያገኝም፤ ከእነዚህ መካከል የሚበልጠው፣ 12.9 በመቶ (11 ሚሊዮን) በማደግ ላይ ባሉ 19 የአፍሪካ አገራት የሚኖሩ ናቸው። በየዓመቱ 9.1 ሚሊዮን ህዝብ ከረሀብ ጋር በተያያዝ ህይወቱ ያልፋል። ሌሎች ምግብ ባስቸኳይ ሊደረስላቸው የሚገባ 20 ሚሊዮን ወገኖች ለረሀብ ተጋልጠው ይገኛሉ። የዓለማችን አብዛኛው ሰው በቀን ማግኘት የሚገባውን 2,100 ካሎሪ የምግብ ንጥረ ነገር አያገኝም።
በአፍሪካስ?
እንደ ዓለም ባንክ (2016) ሪፖርት በአፍሪካ ድህነት ይቀንስ እንጅ በኢ-ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ በኋላቀር አሠራር፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመኖር፣ የተሻሻለ እህል ዘር አለማግኘት . . . (ዝርዝሩ ብዙ ነው)፤ በተለይም የህዝብ ቁጥር እያሻቀበ መሄድ ምክንያት በ1990 ከነበረው ሁኔታ የተሻለ ነገር እየታየ አይደለም። በ1990 280 ሚሊዮን የነበረው ለረሀብ የተጋለጠው ህዝብ ብዛት፤ በ2012 330 ሚሊዮን ሆኗል። በአፍሪካ ምንም እንኳን የመሻሻል፤ ሀብት የመፍጠር . . . ነገር ይኑር እንጂ በነገሠው ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግር ግለሰብ ሚሊየነሮችንና ቢሊየነሮችን ከመፍጠር ባለፈ ለአህጉሪቱ ሕዝብ የፈየደው ነገር የለም።
አፍሪካን በተመለከተ፤ አፍሪካ ህብረትን ጨምሮ፣ ሁሉም የሚስማሙበት መሰረታዊ ጉዳይ ቢኖር ምድሪቱ በተፈጥሮ ሀብትና በአስተማማኝ (ወጣት) የሰው ኃይል የታደለች ሆና ሳለ፤ ሕዝቡ ለረሃብና ቸነፈር የተጋለጠ መሆኑ ነው። የቅኝ ገዢ ሀገራት ለነሱ ያደላ የውሃ አጠቃቀም ህግም ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ምርት መቀነስና መራብ ሚናው ከፍተኛ መሆኑ ብዙዎች የሚስማሙበት ነው። እራሳቸው ጭምር፣
ሌላኛውና አሳዛኙ የረሀብ ምክንያትና ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ በአፍሪካ በሄክታር (ከ300 – 500 ኪሎ ግራም) የሚሰበሰበው ምርት አሜሪካን ከመሳሰሉ ያደጉ አገራት ምርት (በሄክታር 2.2 ቶን)ጋር ሲነጻጸር ልዩነቱ አስደንጋጭ የመሆኑ ነገር ነው። በአፍሪካ ውስጥ ከመሰብሰብ በፊት ከ15 – 25 በመቶ፤ በመሰብሰብና በማስገባት ወቅት ከ15 – 20 በመቶ ምርት እንደሚባክን ስንገነዘብ ምን ሊሰማን እንደሚችል ለማንም ግልጽ ነው። እውነታው ይህ ከሆነ እንዴት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ይቻላል? የሚለው ቢያሳስብ ምን ይገርማል?
የመፍትሔ ሃሳብ
ከላይ በጥቅሉ እንዳመለከትነው፤ የዓለም የሕዝብ ቁጥር፣ በተለይም የአፍሪካ፤ በተለይ በተለይ ከሰሀራ በታች በሚገኙ አገራት ባልተጠበቀ ፍጥነት እየጨመረ ይገኛል። ይህም ከፍተኛ ትኩረት ስቦ በቅርቡ የተካሄደውን የG20ን ስብሰባ ጨምሮ በተለያዩ መድረኮች አነጋጋሪ ሆኗል። ይሁን እንጂ፣ እስከአሁን እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች እንኳንስ ለወደፊቱ (ለመጪው ትውልድ) የሚሆን ቀለብ ከወዲሁ ለማሟላት ቀርቶ፣ አሁን ያለውን መመገብ እየተቻለ አይደለም። የሥራ ዕድል መፍጠር፣ ስደትን ማስቀረት፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ . . . ቀርቶ ግብርናው ገና ከበሬ፣ ማረሻና ሞፈር አልተላቀቀም። መንግሥታት ፖሊሲዎቻቸውን መከለስ፣ ከራሳቸው ልዩ ሁኔታ ጋር በተገናዘበ በፈጠራ ማስደገፍ፣ ወቅቱን በተለይም የወቅቱን የህዝብ ቁጥር ባገናዘበ መልኩ ሲያስተካክሉ አይታዩም። ጉዳዩን ከእኛው ጋር ለማስተሳሰር ያህል የሚከተለውን እንጥቀስ።
በቅርቡ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቃለ-ምልልስ ያደረጉት የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ አቶ ሳኒ ረዲ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 70 ሚሊዮን በነበረበት ወቅት የተቀረፀው የአገሪቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ችግሮችን ሊቀርፍ፣ የግብርናውን ዘርፍ የታሰበውን ያህል ሊያዘምን ያልቻለ . . .(ብዙ ብዙ ችግሮችን ዘርዝረዋል)፤ ብቻ ሳይሆን ከላይ ስንዝሯቸው የነበሩትና ሌሎች በርካታ ችግሮች ያሉበት ነው።
በአጠቃላይ፤ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን በቂ ምርት ለማግኘት፣ በዘርፉ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ አሁን ያለውን ምግብ ፈላጊ የሕብረተሰብ ክፍል ለማርካት፣ ለመጪው ትውልድ የሚሆን ጥሪት ለማኖር፤ አገራት የህዝብን ቁጥር መጨመር መቆጣጠር፣ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም፣ የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን ሥራ ላይ ማዋል፣ ኅብረተሰቡን የዘመናዊ ቴክኖሎጂና የመረጃ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ፣ ምንጭን በማፈላለግ ዘርፉን ማጠናከር እንደሚገባቸው የመሳሰሉት በቀዳሚ መፍትሔነት የተቀመጡ ናቸው። በተለይ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የዓለም ህዝብ ቁጥር በ2050 9.8 ቢሊዮን፣ በ2100 ደግሞ 11, 185, 333, 718 እንደሚደርስ ለቀረበው ትንበያ ትኩረት መስጠት፣ ምክንያቱም የ2100ዱ ምድር ልትመግበው ከምትችለው 10 ቢሊዮን በላይ ነውና፤ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት «ችግሩን ከመሰረቱ ለማስወገድ በየአመቱ $30 ቢሊዮን ያስፈልጋል» የተባለውን ለማሳካት መረባረብ፣
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2011
ግርማ መንግስቱ