እ.አ.አ መስከረም 23 ቀን 2019 የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ንግግር ባደረጉበት ወቅት በሩዋንዳ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የሆነው ስይሊዲኦ ዱስአቡሙሬምይ በሚሰራበት ቦታ ላይ ባልታወቀ ሰው ተገደለ። ይህ ሰው የዴሞክራሲ ዩኒፍሪ ወይም ፌዱ ሊንኬጅ ፓርቲ አስተባባሪም እንደነበረ የአልጀዚራ ዘገባ ያሳያል።
እ.አ.አ 2019 ሐምሌ ወር ሌላው የዴሞክራሲ ዩኒፍሪ ወይም ፌዱ ሊንኬጅ ፓርቲ በምሥራቅ ሩዋንዳ የሚገኝ ክንፍ መሪ የሆነው ኡጌኔ ንዴሬይማና የተሰወረ ሲሆን እስካሁን የት እንዳለ የሚታወቅ ነገር የለም። በተመሳሳይ እ.አ.አ 2019 መጋቢት ወር ውስጥ የፓርቲው ቃል አቀባይ አንስሌሜ ጫካ ውስጥ ሞቶ መገኘቱን ዘገባው ያሳያል።
ከዱስአቡሙሬምይ ግድያ በኋላ የአገሪቱን የደህንነት ጠባቂዎች ተሳድብሀል በሚል ለስምንት ዓመታት ታስሮ የነበረውና በቅርቡ የተለቀቀው የዴሞክራሲ ዩኒፍሪ ወይም ፌዱ ሊንኬጅ ፓርቲ ሊቀመንበር ቪክቶሬ ኢንጋቢሬ ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገረው፤ እሱ የሚመራው ፓርቲ አባላት ግድያ እስካሁን ተጣርቶ እልባት አለማግኘቱን በመጥቀስ፤ የዱስአቡሙሬምይ ግድያም ተጣርቶ መፍትሄ አያገኝም ሲል ፅፏል።
ይህ ሁኔታ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ላይ የሰላ ትችት የሚሰነዝሩ ሰዎች ላይ የሚፈፀመው ግድያና የማይታወቅ ቦታ መሰወር አንዱ አካል ነው። ነገር ግን ግድያውና ወዳልታወቀ ቦታ መሰወሩ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት ይኑረው አይኑረው የሚታወቅ ነገር የለም። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ እየደረሰ ያለው በደል እንዲቆም በተደጋጋሚ ለፖል ካጋሜ መንግሥት ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
ነገር ግን ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ባላቸው የሕዝብ ተቀባይነት ደስተኛ ሆነው እየመሩ ይገኛሉ። አብዛኛው የሩዋንዳ ሕዝብ ፕሬዚዳንቱን ባለራዕይ፣ ለአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ያመጡ እንዲሁም አገሪቱን ከርስበርስ ግጭት ያወጡ ሰው አድርገው ይቆጥሯቸዋል። በእርግጥ እሳቸው የሚመሩት አማጺ ቡድን እ.አ.አ 1994 ሚያዝያ 7 ቀን የተጀመረው የ 100 ቀን የዘር ማጥፋት ዘመቻን በማስቆም የሀገሪቷ መሪ እንደመሆኑ መጠን ሥልጣኑን ከተረከቡ በኋላ ሩዋንዳን ለመለወጥ ብዙ ነገር አድርገዋል።
ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ በማምጣቱ እና ሙስናን በመዋጋቱ ክብር ይገባቸዋል የሚሉት በርካታ ናቸው። አገሪቱን ለንግድ እንቅስቃሴ በመክፈት አዳዲስ ኢኮኖሚያዊ ዘርፎችን እድገት በማበረታታት እና ቢሮክራሲውን በማሻሻል በዓለም አቀፍ የድርጅት የንግድ ሥራ አገሪቱ 29 ኛ ደረጃ አገሪቱ እንድትይዝ አድርገዋል ሲሉ ድጋፋቸውን የሚሰጡት በርካታ ናቸው።
ፕሬዚዳንት ካጋሜ የውጭ እርዳታን በዘዴ የተጠቀሙ ሲሆን የሩዋንዳ የተፈጥሮ ሀብቶችን በጥበብ ጥቅም ላይ አውለዋል። በወረቀት ላይ ብቻ እድገትን ከሚያሳዩት ብልሹ የአፍሪካ መንግሥታት በተቃራኒ ሩዋንዳ የተራውን ሕዝብ ሕይወት በከፍተኛ ደረጃ ያሻሻሉ የኢኮኖሚ ልማት፣ የትምህርት፣ የሕክምና፣ ወዘተ ስኬት አስመዝግበዋል። በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ብዙ ሴቶች እንዲገቡ ግፊት አድርገዋል::
በዚህም በሩዋንዳ ፓርላማ ውስጥ ካሉት የሕግ አውጭ አካላት ውስጥ 64 ከመቶ የሚሆኑት በዓለም ላይ ከማንኛውም ሀገር በተለየ ሴቶች እንዲሆኑ ተደርጓል። በተጨማሪም በአብዛኛዎቹ አህጉራት ላይ ጉዳት የሚያመጣውን የጎሳ ግጭት በማስቆም አገሩን አንድ አድርገዋል። ላለፉት ጥቂት ዓመታት ሩዋንዳ «የአፍሪካ የስኬት ታሪክ» ተደርጋ እንድትቆጠር አስችለዋታል።
እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ሩዋንዳውያን ፕሬዚዳንቱን ይደግፋሉ። ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ አገሪቱን እየመራ የሚገኘው ፖል ካጋሜ በሚያስገርም ውጤት ሦስት ምርጫዎችን በተከታታይ ማሸነፍ ችለዋል። እ.አ.አ. በ2015 ሩዋንዳውያን ፕሬዚዳንቱ እስከ 2034 ድረስ በሥልጣን ላይ መቆየት እንዲችሉ በሕገ መንግሥቱ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ከፍተኛ ድምጽ መስጠታቸው ይታወሳል።
ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎች በቡሩንዲ እና በዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባሉ አገራት መካከል ብጥብጥና አለመረጋጋት እንዲፈጠር ምክንያት ቢሆኑም በሩዋንዳ ውስጥ ግን ሰላም እንዲመጣ አድርገዋል። ሆኖም ዛሬ ካጋሜ የታወቀውን የቅኝ ዘመምነት መንገድ በመከተል ይህንን ሁሉ አደጋ ላይ የጣለው ይመስላል። ተቃዋሚዎችን በማደናቀፍ፣ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ግድያ መፍትሄ እንዲያገኝ በማድረጉ ምክንያት አገሪቱ ወደ ብጥብጥ እና ጭቆና ዳግመኛ እንዳታመራ እየተፈራ ይገኛል።
ምናልባትም በካጋሜ እይታ 800 ሺ ሰዎችን ለሞት ካበቃው የዘር ማጥፋት ዘመቻ በኋላ በጥቂት አሥርተ ዓመታት ውስጥ የመጣው ዴሞክራሲ ለአገሪቱ ፀጥታ እና መረጋጋት ትልቅ አደጋ ሊያመጣ ይችላል ብለው ያምናሉ። አምባገነን መሪ መሆን ግን የካጋሜ ብቸኛው አማራጭ አይደለም። አምባገነንነትን መምረጥ በጣም አደገኛው ሊሆን ይችላል። የፖለቲካ ጭቆና የመረጋጋት ዋስትና ሊሆን አይችልም።
እ.አ.አ ከ2011 ጀምሮ በሰሜን አፍሪካ የተፈጠረው ሁከት ለዚህ ጉዳይ በማስረጃነት ይቀርባል። በሀገሪቱ ውስጥ ያለው የካጋሜ አገዛዝ እና ፖሊሲዎች እሱን የሚቃወሙ ፖለቲከኞች ሩዋንዳ ገሃነም እንድትሆንባቸው አድርጓል። የእነሱ ጭቆና በእሱ ሥልጣን ላይ ማንኛውንም ሊፈታተን የሚችል ሁኔታ ሊያስወግድ ቢችልም በረጅም ጊዜ ውስጥ ግን ካጋሜን የሚከተሉ ሰዎች ቁጥር እንዲቀንስ በማድረግ የሰራቸውን በጎ ተግባራት ሊያጠፋበት ይችላሉ። ዘገባው የአልጀዚራ ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 3/2012
መርድ ክፍሉ