ትልቅ ትንሹን አክባሪ፣ ሩህሩህ፣ ለተቸገረ ደራሽ ፣ደግሞ ሰርቶ ሮጦ የማይጠግብ፣ እንጀራ አጉራሽ ስራን ሁሉ የሚያከበር ሰው ነው፡፡ያለውን ማካፈሉ ደስታን ብቻ ሳይሆን ሀብትንም እንደሚጨምርለት ያምናል፡፡ስለዚህም ሁልጊዜ እጁ ለተቸገሩ የተዘረጋ እንደሆነም ብዙዎች ምስክርነታቸውን ይሰጡለታል፡፡ከሊስትሮነት ጀምሮ ሌሎች 39 አይነት ስራዎችን ሲሰራ ለእኔ ሁሉም ድንቅ ሥራና ከፍ ዝቅ የማላደርጋቸው ናቸው ይላል፡፡በልፋትና ትጋቱ ለብዙዎች አርኣያ ሆኖ ሰርተው እንዲለወጡ መንገድ አሳይቷቸዋል፡፡
እቁብ እየሰበሰበ ብዙዎች ከነበራቸው ችግር እንዲላቀቁም እያደረገና በሁለት ትምህርት ቤቶች ችግረኛ ተማሪዎች በቋሚነት የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ጡረታ የወጡ የልጅነት መምህራኑ በእርሱ ልብ ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸውና ሱፍ አልብሶ፣ ገንዘብና መፅሐፍ በመስጠት አመስግኗቸዋል። የዛሬው ” የህይወት እንዲህ ናት” አምድ እንግዳችን አቶ ተስፋዬ መኮንን፡፡ትንሽ ከህይወት ተሞክሮው በአርአያነቱ ልናነሳው ወደናል።
ልምጩ በአካባቢው ማህበረሰብ በእጅጉ ቦታ የሚሰጠውና ትንሽ ሆኖ እንደትልቅ የሚከበር ልጅ ነው፡፡በዚህም ማንም አዞት እንቢ አይልም፤ በፍጥነት የታዘዘውን ይፈጽማል፡፡ከከበደውም መፍትሄ ያፈላልጋል፡፡ከዚህ ጋር ተያይዞም የአካባቢው ሰዎች ‹‹ልምጩ›› ሲሉ ይጠሩታል፡፡ምክንያቱም ልምጭ እንደፈለጉት የሚታዘዝ እርጥብና ቀጭን ነው፡፡ተስፋዬም የልብ አድራሽ በመሆኑና በፍጥነቱ እንዲሁም ቀጫጫ በመሆኑ ይህንን ስም እንደሰጡት ይናገራል፡፡
ተስፋዬ ጭምትና ሥራ ወዳድ ልጅም ነው፡፡ብዙ መናገር አያስደስተውም፤ እንደ አዲስ አበባ ልጅነቱም በእነርሱ አባባል ‹‹ዘመነኛ›› ያደርጋል የሚሉትን አይቀበለውም፤ አያደርገውም፡፡እናም ከዚህ ጋር ተያይዞም የሰፈር ጓደኞቹ ቅጽል ስም አውጥተውለታል፡፡‹‹ተስፋዬ ሞኙ›› የሚል፡፡እርሱ ግን በዚህ አይከፋም፡፡ምክንያቱም የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን ያውቃል፡፡”አራድነት” ከሚባለው የሱሰኝነት፣ቀማኛነት… ጎራ አምልጧል። ከመጥፎ ነገር እንዲቆጠብ አድርጎታል፡፡
ተስፋዬ በ1968 ዓ.ም በቀን 21 ተወልዶ ያደገው በመሃል ከተማ በቦሌ ሚካኤል አካባቢ ሲሆን፤ እናቱም ሆኑ አባቱ የእስልምና እምነት ተከታዮች ናቸው፡፡ግን እርሱ፣ እህቱና አንዱ ወንድሙ የቤተሰቡን እምነት አልተከተሉም፡፡ይህ የሆነው ደግሞ በእርሱ ብቻ ሳይሆን በእናቱም ፈቃድ እንደነበር ያስታውሳል፡፡‹‹ መቼም ቢሆን በልጅነቴ እናቴን ማሳዘን አልፈልግም፤ እርሷ ያለችኝን ብቻ ነው የማደርገው፡፡ስለዚህም ወደ ክርስትና እምነት ለመቀየር ሳስብ መጀመሪያ ፈቃዷን ጠይቄ ነው›› ይላል፡፡
ተስፋዬ በልጅነቱ ብዙ ችግሮችን አሳልፏል፡፡ እርሱ እንዳለው፤ ጫማ ሲሰፋ ወስፌው የወጋውና በብዙ ጥረት የዳነው በገብርኤል ቀን ነው፡፡የቀን ሥራ ሲሰራ ከሁለተኛ ፎቅ ወድቆ የተሰባበረው በገብርኤል ቀን ነው፡፡እናቱ እንደነገሩት ደግሞ ምጥ የጀመራቸው በዚሁ በቀን 19 ነው፡፡ሞቷል ተብሎ ተጥሎ የተነሳውም በዚሁ ቀን መሆኑን ይናገራል፡፡ወደ ክርስትና እምነት ልቀይር ሲልም ፈቃድ የተቸረው በዚህ ምክንያት እንደሆነ ያስረዳል፡፡
ተስፋዬ በልጅነቱ ሳይቀር እንደ ሽማግሌ ሰዎችን የሚያስታርቅ፣ የሚያስተባብርና መልካም ነገሮች እንዲደረጉ የሚታትር ነው፡፡የሰፍር ልጆች ከእርሱ ሃሳብ ፈቀቅ አይሉም፡፡ተስፋዬ ተብሎ የተጠራበትም ምክንያት እንዳለው ይናገራል፡፡የመጀመሪያው በገብርኤል እለት ሞተ ተብሎ ከተጣለበት በመነሳቱ እናቱ የእምነቱ ተከታይ ባይሆኑም ከእንደገና ድኖ በማየታቸው አምላክ ተስፋ ሰጠኝ ሲሉ እንዳወጡለት ያስታውሳል፡፡ሁለተኛው ደግሞ ከአባቱ ሞት በኋላ ተስፋና መሸሸጊያ የሆናቸው እርሱ ስለሆነ ያወጡለት መሆኑን አጫውቶናል፡፡
ተስፋዬ ለቤተሰቡ የበኩር ልጅ ነው፡፡የበኩር ልጅነቱን በሚገባ የተወጣና ልጅ ሆኖ እንደትልቅ ሰው ቤተሰቡን ያስተዳድር እንደነበርም ይናገራል፡፡ተስፋዬ በልጅነቱ ጥሩ የእግር ኳስ ተጫዋች ሲሆን፤ የተከላካይ ቦታን በመሸፈን ሰፈሩን የሚወክል ነበር፡፡በዚህም ከእርሱ ውጪ ያንን ቦታ እንዲይዝ ብዙዎቹ ጓደኞቹ አይፈቅዱም፡፡ተስፋዬ ግን ብዙ ጊዜ ስለሌለውና ቤተሰቡን በገንዘብ ለመደገፍ የተለያዩ ሥራዎችን ስለሚሰራ ይህንን አያደርግም፡፡እንዳውም ዛሬ ላይ ሆኖ ሲያስበው በዚህ ብቃቱ ጥሩ የእግር ኳስ ተጫዋች ይሆን እንደነበር ያነሳል፡፡ሆኖም አምላክ ያለው እንጂ እኛ ባሰብነው አንጓዝምና አልተሳካም ይላል፡፡
ተስፋዬ ከልጆች ሁሉ ለየት የሚያደርገው ነግዶም ሆነ ጫማ አሳምሮ(ጠርጎ) አለያም ተሸክሞ የሚያገኘውን ገንዘብ ምንም ሳያጠፋና ሳያባክን በቀጥታ የሚሰጠው ለእናቱ ነው።ኮንስትራክሽን ላይ በቀን ሥራ ተቀጥሮ እየሰራ እንኳን ምግብ ለመብላት እናቱን ያስፈቅዳል፡፡የደመወዝ ቀን ሲደርስ ደግሞ ‹‹እናቴን ጥሩና ስጧት›› ይል እንደነበር አይረሳውም፡፡በዚህ ድርጊቱ ደግሞ ብዙዎች ያሰሩታል፤ ለልጆቻችንም አርአያ ነህ ይሉት እንደነበርም ያነሳል፡፡
የ12ኛ ክፍል ውጤት
ተስፋዬ በትምህርቱ በጣም ጎበዝ ከሚባሉት ተርታ የሚመደብ ነው፡፡የማንበቢያ ጊዜ ባይኖረውም ከትምህርት ቤት ስለማይቀር በተማረው ብቻ ውጤታማ ይሆናል፡፡አልፎ አልፎ ደግሞ ቤት ከገባ በኋላም ያነባል፡፡ያው ተወልዶ ያደገው በቦሌ ሚካኤል አካባቢ ስለነበር ቄስ ትምህርትም ቆጥሯል፡፡እንደውም ‹‹ፊደል አስቆጣሪዬ ቄስ ትምህርት ቤት ነው›› ይላል፡፡ከዚያ ዘመናዊ ትምህርቱን በአየር አምባ ትምህርት ቤት እስከ ስምንተኛ ክፍል በጥሩ ውጤት ተከታትሏል፤ ከዘጠኝ በኋላ ያለውን ደግሞ በቦሌ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል፡፡
12ኛ ክፍል ሲደርስ ተስፋ አስቆራጭ ነገር እንደገጠመው የሚያነሳው ተስፋዬ፤ ውጤት መበላሸቱን ያወቀው ገና ፈተና ሲጠናቀቅ እንደነበረና ወዲያው ጊዜ ሳይፈጅ በቀጥታ ወደ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ በመሄድ የሥራ አጥ መታወቂያ እንዳወጣ ይናገራል፡፡‹‹ለሥራ ክፍት መሆን ካልቻልኩ ወይም በውጤቴ ረክቼ ቀጣዩን ጉዞዬን ካላስተካከልኩ ቤተሰቤንም ሆነ ራሴን መለወጥ አልችልም፡፡ስለዚህም ትምህርቱን አቁሜ ወደ ሥራ የተሰማራሁት ለዚህ ነው፡፡እስካሁንም ሳልማር የቆየሁት መማር ጠልቼ ሳይሆን ማን ያቆመኛል በሚል ነው፡፡እናም ዛሬ ከዲፕሎማ ተነስቼ ዶክትሬት እስክደርስ እማራለሁ በሚል ዲፕሎማን አንድ ብዬ ወደ ትምህርት አለም ተመልሻለሁ›› ይላል፡፡
ይህ የውጤት መበላሸት በልጅነት ጊዜው ይመኘው የነበረውን ጋዜጠኝነት እንዳሳጣው የሚናገረው ባለታሪኩ፤ በትምህርት ተስፋ መቁረጥን እንደማይፈልግ ይናገራል፡፡መማር ሙሉ ሰው ያደርጋል ብሎ ስለሚያስብም በተከታታይ ጊዜ አጫጭር የኮምፒውተር ስልጠናዎችን ወስዷል፡፡በ2020 ዓ.ም ዶክትሬቱን የመያዝ ግብ አስቀምጧል፡፡ስለዚህ የ12ኛ ክፍል ውጤት ተስፋ ቢያስቆርጠውና ለጊዜው መማርን ቢገታም ‹‹መማር ማቆም አለማደግ፣ አለመኖር ነውና ያ ሁኔታ በአዲስ ተስፋ መተካት አለበት›› ይላል፡፡
የልጅነት ጫንቃ
የተስፋዬ የልጅነት ጉዞ ሲታሰብ የሥራ ህይወቱን ሳያነሱ ማለፍ አይቻልም፡፡እናም አባቱ ልክ እንደእርሱ ደግና ለሰው አዛኝ በመሆናቸው ያላቸውን ሁሉ ሊያጡ ችለዋል፡፡ይህ ደግሞ ቤተሰቡን ሳይቀር የሚያስተዳድሩበት ገንዘብ እንዳይኖራቸውና በጥበቃነት ተቀጥረው እንዲሰሩ አድርጓቸዋል፡፡ከዚያም አልፎ ህይወታቸው በብስጭት እንዲጠናቀቅም ምክንያት ሆኗል፡፡የበለጠ የሚከፋው ደግሞ ከእርሳቸው የህይወት ህልፈት በኋላም ለትንሹ ልጃቸው ይህንኑ የቤተሰብ አስተዳዳሪነት ጫና አስተላልፈው ማለፋቸው ነበር፡፡ስለዚህ ተስፋዬ ገና የልጅነት እድሜ ላይ እንዳለ ቤተሰብ አስተዳዳሪ እንዲሆን ተፈረደበት፡፡
በእርግጥ የሥራ ጅማሮው ‹‹ሀ›› የተባለው አባቱ ብቻ እንዳይለፉ በማለትና እርሱም የበኩሌን ላድርግ ብሎ በመነሳቱ ነው፡፡ገና ትምህርት ቤት ሲገባ ጀምሮ ነበር አብሮ ሥራንም መለማመድ የጀመረው፡፡እናም አባቱን ጠይቆ ለሊስትሮ ሥራ የሚያስፈልገው ግብዓት እንዲሟላለት አደረገ፡፡ይህንን ጥያቄ ሲያቀርብ በወቅቱ አባቱ ፊት ላይ ያነበበውን ስሜት መቼም አይረሳውም። ይህንን ሥራ ልስራ ማለቱ አስከፍቷቸዋል፡፡ግን ምርጫ እንደሌላቸው ያውቃሉ፡፡በመሆኑም ቢያሳዝናቸውም ያለውን አደረጉለት፡፡እርሱም አቅሙን አሟጦ የስራ ጥማቱን ለማርካትና ቤተሰቡን ለመደገፍ የጫማ ማሳመር ስራውን ተያያዘው፡፡
ተስፋዬ ቤተሰቡንም ሆነ ራሱን ከችግር ለማላቀቅ አማራጩ ይህ እንደሆነ አምኖም ብዙ ደንበኞችን በፍቅር መሳቡን ቀጠለ፡፡ልጅና አዋቂ ሁሉ የሚወደው ስለነበረ ደግሞ ብዙም አልተቸገረም፡፡ብዙ ደንበኞች ሊያፈራ ችሏል፡፡በቋሚነት እስከ 80 የሚደርሱ ትልልቅ አባወራዎችም አይዞህ እያሉ በደንበኝነታቸው ያበረቱት እንደነበረም ያነሳል፡፡እንደውም ጫማ ለማስጠረግ እርሱ ጋር ሰልፍ እንደነበርም አይረሳውም፡፡
ተስፋዬ በጫማ ማሳመር ብቻ አልነበረም የሰራው፡፡ጫማ ይሰፋም ነበር፡፡ከዚያ ደግሞ ከጫማው ሳይወጣ ማደስ ጀመረ፡፡በዚህ ሁሉ ስራው ደግሞ የአካባቢው መለያ እስኪሆን ድረስ ደርሷል፡፡ዛሬም ለአካባቢው ምልክት ተስፋዬ ጫማ ቤት ነው የሚባለው፡፡ከዚህ ያለፈ ሥራም ይሰራ ነበር፡፡ሌዘር ጃኬትና ቦርሳም ያድሳል፡፡ከዚያ ሲያልፍ ደግሞ ይሸከማልም፡፡እናም ተስፋዬ ብዙ ሥራዎች ላይ ተሳትፏል፡፡አጠቃላይ 39 የሚደርሱ ስራዎችን እንደሰራም አጫውቶናል፡፡
በሊስትሮ ሥራ ገቢ የተጀመረው የአስር ብር እቁብ ለዛሬው ህይወቱ ትልቅ አሻራ ያላት ናት፡፡ይሄ እቁብ መሰረቱን ሳይለቅ በታማኝነት፣ እንደ ስራ በጥንካሬ ይዞት እስካሁን ዘልቋል። ዛሬ አንድ ዕጣ አንድ ሚሊዮን ስምንት መቶ ሺ ብር ደርሷል። እናም ከእርሱ ጋር የሰሩ ሁሉ የቤትና የመኪና ባለቤት መሆን የቻሉት በዚህ በእቁብ እንደሆነ ይናገራል፡፡እርሱም ቢሆን ከነበረበት ደረጃ ከፍ እያለ የመጣው በዚህ በእቁብ ሰብሳቢነቱ እንደሆነ ያነሳል፡፡
ተስፋዬ ዛሬ መኪኖችን እየገዛና እያስመጣም ይሸጣል፡፡ቤቶችና ሌሎች ኢኮኖሚውን ከፍ የሚያደርጉ ነገሮች ካገኘም ገዝቶ ለማትረፍ ይሰራል፡፡ከዚያ በተጨማሪ በቋሚነት ‹‹ተስፋዬ ለሁሉ ቢዝነስ ሴንተር›› የሚል ከፍቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ይህንን ሁሉ ተግባር ለመፈጸም የቻለው ደግሞ አምስት ሰዓት ብቻ ተኝቶ ሌላውን ጊዜውን ሥራ ላይ በማዋሉ እንደሆነ አጫውቶናል፡፡
ባለውለታ
በልጅነቱ ከአባቱ የተረከባት ያችን የእንጨት ሥሪት የሊስትሮ እቃ ‹‹ውበቴና ጸጋዬ ናት›› ይላታል፡፡‹‹ለዛሬ እዚህ መድረሴ የእርሷ መኖር ያመጣው ነው፡፡እናም ከሚስቴ ጋር ቆይተን ልጅ ከወለድን በኋላ ነበር የጋብቻ ሥርዓታችንን ከልጃችን ልደት ጋር ያደረግነው፡፡እናም የዛን ቀን አምስት ድንኳን ህዝብ ተጋብዟል።ሶስት ድንኳን ክርስቲያን ሁለት ድንኳን የእስልምና እምነት ተከታዮች እናም ሁሉም ሰው በሚተላለፉበት ቦታ ላይ ያቺ ባለውለተኛ ሊስትሮዬ ከፍ ብላ እንድትታይ አደባባይ አውጥቻታለሁ።
እርሷ ያስገኘችውን ውጤት መሆኑን ለማስረዳት ነው። ዛሬ የደረስኩበትን ቦታ ሳስብ ሁልጊዜ መነሻዬን እንዳስታውስ ታደርገኛለችና በሄድኩበትና በማዘጋጀው ፕሮግራም ሁሉ ከፍ አድርጌ አነሳታለሁ።በመኖሪያ ቤቴ ውስጥም ትልቅ ቦታ ሰጥቻት የራሷ የሆነ መቀመጫ ተሰርቶላት ንጉስ ናትና በሳሎን ውስጥ ተቀምጣለች›› ይላል፡፡
‹‹መነሻውን የማያውቅ መድረሻውን ይለያል ብዬ አላምንም›› የሚለው ባለታሪኩ፤ በሊስትሮ ስራ እህቶቹን አስተምሮ ለቁምነገር አብቅቷል፡፡እርሱ ዝቅ ብሎ ሌሎችን ከፍ አድርጓል።ቤተሰቦቹን ደግፏል። ያለው ሰጪ በመሆኑም እጁን ከዘረጋባቸው ቦታዎች ሁሉ ምርቃቱን አፍሷል።
የማህበረሰብ አገልጋይ
‹‹ እኔን ያሳደገኝ የአካባቢዬ ሰው ነው፡፡ስለዚህ እኔም ለእነርሱ መኖር አለብኝ፤ ለችግሩም ልደርስለት ይገባል፡፡›› የሚለው እንግዳችን፤መጀመሪያ ሊስትሮ እየሰራ ሳለ ነበር አስር ሆነው እቁብ መጣል የጀመሩት፡፡ከዚያች ላይም ከእቁብ ሽያጭ የተሰበሰበውን ገንዘብ ከእነርሱ የደከሙትን ያግዝበት ነበር፡፡
እቁቡ እየበረታና እርሱም ከሊስትሮ ሥራ ወጥቶ ጫማ ማደስና ከመርካቶ እያመጣ ጫማ መነገድ ሲጀምር እቁብ የሚጣለውም ገንዘብ እና የሚሰበሰበው የሽያጭ ገንዘብ እያደገ በመሄዱ ከእዛ ላይ እንደነመቆዶኒያ፣ሙዳይ እና ሌሎች ችግረኞችን ማገዝ ተጀመረ፡፡የእቁብ ጣዮቹ አቅም ከፍ በማለቱ ድጋፉ ወደ አካባቢ ተመለሰ፡፡በረሀብ ምክንያት መማር ያቃታቸው አንዳንዴም በትምህርት ቤት ውስጥ የሚወድቁ ህፃናት አሉ የሚለውን ከየትምህርት ቤቶቹ በመስማቱም ያንን የእቁብ ሽያጭ ገንዘብ እቁብተኞቹን በማሳመንና በማስተባበር የነገ ተስፋ የሆኑ ህጻናትን በሁለት ትምህርት ቤቶች መመገብ ጀመሩ።
ተስፋዬ ከሌሎች ሰዎች ለየት የሚያደርገው ሌላው ጉዳይ ደግሞ መምህራንን የማስታወስ ሥራ መስራቱ ነው፡፡በመጀመሪያ ሁለት ጡረተኛ የነበሩ መምህሮቹን ካሉበት አፈላልጎ የእናንተ ውለታ ላቅ ያለነው ሲል ሱፍ አለበሳቸው፡፡ቀጥሎ ደግሞ ለአስር የቀድሞ መምህሮቹ እናንተ የአለም ብርሃን ናችሁ ሲል መጽሐፍ ለቤታችሁ ትንሽ ይደጉማል ሲል ደግሞ ለእያንዳንዱ ሁለት ሺ ብር ሰጥቷቸዋል፡፡አሁንም ይህ ድጋፉ ለእራሱ መምህራን ብቻ ሳይሆን በአገር ደረጃ አንቱታን ያተረፉ ግን አስተዋሽ የሌላቸውን ማገዝ ላይ እንደሚያተኩር አጫውቶኛል፡፡
ተስፋዬ ግብር በመክፈል፣ የሥራ ፈቃድ በማሳደስ ከአካባቢው ሰዎች ቀዳሚና አርአያ የሆነ ሰው ነው፡፡በዚህም ገቢዎች ሳይቀር ብዙ ጊዜ ሽልማት አበርክቶለታል፡፡በሚያደርጋቸው ልዩ ልዩ እገዛዎችም ከሰላሳ የማያንሱ ዋንጫዎች በቤቱና በሥራ ቦታው ተደርድረው ይታያሉ፡፡እናም ይህ ሽልማቱ ሁልጊዜ ብርታት እንደሚሆነውና ለእርሱ የሆነውን ሁሉ ለሌላም እንዲሆን እንደሚሰራም ይናገራል፡፡
እምነት ያልከፈለው ቤተሰብ
በእነ ተስፋዬ ቤት የእምነት ልዩነት ይኑር እንጂ የቤተሰብ ጥምረቱ ፣ ማህበራዊ ህይወቱና መቻቻሉ አንድም ቀን ክርክርም ሆነ ጸብ ፈጥሮ አያውቅም፡፡እንዳውም የአረፋ እለት የአረፋ ድግስ፣ የፋሲካ እለት የፋሲካ ድግስ እየተደረገ በጋራ መመገብና መወያየቱ ይሰፋል፡፡መተሳሰቡና መረዳዳቱ ይበረታል።እንደ ሀገርም ይሄ ቤተሰብ ትልቅ አርአያነት ያለው ነው።ሁሉ ነገር ማህበራዊ ህይወትን በሚያጠናክር መልኩ ብቻ ነው የሚከናወነው፡፡
አባቱ በህይወት ባይኖሩም የቤተሰቡ ማህበራዊ ህይወት ባለበት ነበር የቀጠለው፡፡በቤተሰብ ውስጥ ስግደት እንኳን ሳይቀር ቦታ ይሰጠዋል፡፡ለልጅ ልጅ ይህንን የመረዳዳት ባህል እንዴት ማስተላለፍ እንደሚገባም ምክክር ይደረጋል፡፡ይህ ደግሞ እናት ሳይቀሩ የእምነቱ ተከታይ ባይሆኑም ቤተክርስቲያን እንዲሄዱ አድርጓቸዋል፡፡
ምስክርነት
” ውርስ አላገኘም፤ሎተሪ አልወጣለትም፤ ከትንሽ ተነስቶ ግን ትልቅ ቦታ አግኝተነዋል። በዕድሜ ታናሻችን ሆኖ በስራና በአስተሳሰብ ከታላላቆቹ ልቆ ተገኝቷል። ትልልቁን የማይረሳ ወጣቱን የማይረሳ ሰው ነው። ሀገራችን ዛሬ የምትፈልገው ሰርቶ የሚያሰራ፣ አርቆ የሚያስብ፣ የተቸገረን የሚረዳ ጠንካራ ራዕይ ሰንቆ የሚራመድ ሰው ነው።ተስፋዬ ይሄንን ያሳየ ለብዙዎቻችንን አርአያ የሆነ ሰው ነው። ” ሲሉ ጓደኞቹ አወድሰውታል።
ውሃ አጣጭ
የሁለት ልጆቹን እናት ያገኛት ጫማ ሲሰፋና ቦርሳ ሲያድስ ነው፡፡እርሷ ቦርሳዋን ለማሳደስ በመጣች ልቧም በዚያው ቀረ፡፡ምክንያቱም ተስፋዬ በወቅቱ አንድን ልጅ አጠገቡ አስቀምጦ እየመከረውና ከእርሱ እንዲማር እየረዳው ነበር፡፡እርሷም ቦርሳዋን ሰርቶ ቢሰጣትም ምክሩ በጣም ስቧታልና ቶሎ ልትወጣ አልፈቀደችም፡፡አመስግናው ከወጣች በኋላም ቢሆን እርሱን አለማስታወስ አልቻለችም፡፡እናም እግሯ ሁልጊዜ ወደዚያ ቦታ መመላለስ አበዛ፡፡እርሱ ባይኖር እንኳ በዚያች ተስፋዬ ጫማ ቤት ቀርታ አታውቅም፡፡
መመላለሷ ደግሞ በጣም አቀራርቧቸው ኖሮ እርሱ ከልቡ አስገባት፡፡ፍቅረኛው እንድትሆንም ጠየቃት፡፡የሁለቱም ልብ የሚነግራቸው ስለነበረ ትዳር ተመሰረተ፡፡ልጅ ከተወለደ በኋላም ለክርስትናው ድል ባለ ድግስ ይበልጥ ቤቱን አሞቁት፡፡ዛሬ ሁሉም የተመኘውን አግኝቶ በደስታ መኖር ተጀምሯል፡፡
ቀጣይ እቅድ
ተስፋዬ በየጊዜው ውሎውን በዲያሪ የሚያሰፍር ሲሆን፤ የየቀን ተግባራቱን በእቅድ የሚያሰፍርና የሚተገብር ነው፡፡የማይሰራውንም በምንም ተአምር በእቅዱ ውስጥ አያስገባም፡፡እናም ሁልጊዜ ለአምስት ሰዓት ብቻ እየተኛ ሌላው ጊዜውን በስራ ስለሚያሳልፍ በየቀኑ ሰፊ የቀጣይ እቅዶች አሉት፡፡ለአብነትም እርሱም ሆነ ሰራተኞቹ ባላቸው የትምህርት ደረጃ ላይ ከፍ እንዲሉ ማድረግ፣ ሰራተኞችን እርስ በእርስ በማወዳደር ማበረታቻ መስጠት፣ የበጎ ሥራዎችን ማጠናከር፣ አገርን መጎብኘት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ እንዳይባል እንጂ ተስፋዬ ልጆቼ ሥራ ወዳድ እንዲሆኑ በሚል መኪናውን ያሳጥባቸዋል። ጫማውንም ከእነርሱ ውጪ ማንም እንዲጠርግ አይፈልግም፡፡ምክንያቱም አንድ ቀን እኔ ባልኖር ሰርተው ራሳቸውን ማስተዳደር አለባቸው ስለሚል በቤት ውስጥ በአቅማቸው የማይሰሩት ሥራ አይኖርም፡፡
መልዕክተ ተስፋዬ
ጭለማ እንዳለ ሁሉ ብርሃን እንደሚመጣ ማሰብ ትልቅ ደረጃ እንደሚያደርስ ሰዎች ከኔ ቢማሩ ደስ ይለኛል ይላል። ወቅታዊ ነገሮችን ከራስ ጋር በማዛመድ ህይወትን ማስቀጠል ይገባል፡፡የሚሰራው ስራ በምድርም በሰማይም የማያስጠይቅ ማድረግ፤ ሰው እንዲመርቀን እንጂ ሰው እንዲረግመን አለመፍቀድ በጣም ከፍ ያደርገናል ብሎ ያምናል፡፡
‹‹ በእኔ ምልከታ የተናቀ ሥራ የለም፡፡ምክንያቱም አውሮፕላን አብራሪ ሽክ ብሎ ወደሥራው መግባት የሚችለው ሊስትሮው ባሳመረለት ጫማ ነው፡፡እናም አስተሳሰብ ነው ትልቅም ትንሽም የሚያደርገውና አስተሳሰብን መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ውጪ አምላኪነትንም መግታት ይገባል›› ይላል፡፡
ተስፋዬ የራሱን ስም መሰረት አድርጎ እየተነተነም ምክርን ይለግሳል፡፡‹‹ተ ማለት ተፍጨርጭሮ ለቁም ነገር የበቃ፤ ስ ስሙ ለዋስትና የሚበቃ፤ ፋ ፋዬር ኤጁ ወይም የጉልምስና ጊዜው በችግር ያበቃ፤ ዬ የእኔ የሚለው ሀብቱ የሰው ልጅ ነው ›› በማለት ተንትኖ ሰዎችም እነዚህን መሰረታዊ ነገሮች ከያዙ ለስኬት የማይበቁበት ሁኔታ የለም ይላል፡፡እናም የጉልምስና ጊዜን ብቻ ትታችሁ ሌላውን ለማድረግ ጥረት አድርጉ ሲል ይመክራል፡፡ተስፋዬን በዚህች ገጽ ብቻ መናገር ከባድ ቢሆንም አባይን በጭልፋ ከሆነው ታሪኩ ጨለፍ ባደረግነው እንደተማራችሁበት በማሰብ ለዛሬ በዚህ ቋጨን፡፡ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው