መንግሥት በለውጡ ሂደት ማዕከል ካደረገባቸው ጉዳዮች የሕግ የበላይነትን ማስከበር ዋነኛው ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሀገርን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ከሚደረገው እንቅስቃሴ ባልተናነሰ መልኩ በሌብነት የሕዝብን ገንዘብ የመዘበሩ አካላትን ወደ ሕግ የማቅረቡ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡
መንግሥት የሰጣቸውን ኃላፊነትና አደራ ወደ ጎን ትተው የራሳቸውን ጥቅም ለማካበት በማለም የመንግሥትን ካዝና ያራቆቱ፤ በድጎማና በድካም የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ የመዘበሩ ቀበኞች በሕግ ጥላ ሥር ውለው እንዲጠየቁ የማድረግ ሂደቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በፌዴራል መንግሥት ደረጃ በሜቴክ ውስጥ ይሠሩ የነበሩ ተጠርጣሪ የሥራ ኃላፊዎች ከፍተኛ መጣራትና ክትትል ተደርጎባቸው በሕግ ፊት መቅረባቸው አንዱ እርምጃ ነው፡፡
የመንግሥትንና የሕዝብን ሀብት የመዘበሩትን በአደባባይ ሌቦች ብሎ በመጥራት ሌብነታቸውን በማውገዝ በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ ሕዝብ የሚፈልገው መንግሥትም እንደ መንግሥት መውሰድ የሚገባው እርምጃ ነው፡፡ በዚህ በኩል የተጀመሩ ሥራዎች የፌዴራል መንግሥት ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ ሀገርና ሕዝብን እንዲያገለግሉበት የተሰጣቸውን ሥልጣንና ኃላፊነት ወደ ጎን ትተው የግል ጥቅማቸውን ሲያሳድዱ የነበሩ ቡድኖችንና አካላት በየሥፍራው በየደረጃው ሊጠየቁ ይገባል፡፡
በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም የተወሰደው እርምጃ የዚሁ የሕግ የበላይነትን የማስከበር አንዱ አካል ነው፡፡ በተለያዩ የሥልጣን እርከኖች ላይ ሲሠሩ የነበሩና ከመሬት፣ ከገንዘብና ከሌሎች ተዛማጅ የመንግሥትና የሕዝብ ንብረቶች ምዝበራ ጋር በተያያዘ ሰባ አምስት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ በሕግ ፊት ማቅረቡን የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) የገጠር የፖለቲካ አደረጃጀት ኃላፊ ከትናንት በስቲያ አስታውቀዋል፡፡ ይህ በክልሉ የተጀመረው መዝባሪዎችን ተከታትሎ ወደ ሕግ የማቅረብ ሂደት በሌብነት የተሰማራ ማንኛውም አካል ሆነ ግለሰብ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር እንደሚደረስበትና ተጠያቂ እንደሚሆን አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በመግለጫ የግል ምቾታቸውን ሲያስከብሩ የነበሩ ሙሰኞችን ወደ ሕግ የማቅረቡ ጉዳይ እንደሚቀጥልም ተጠቅሷል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የተወሰደው አይነት እርምጃ በዚያ ብቻ ተወስኖ መቅረት የለበትም፡፡ እነዚህ የመንግሥትንና የሀገርን ንብረት የዘረፉ፤ ፍትህ አጓድለው ሕዝብን ያስለቀሱ፤ ሕዝብን በሕዝብ ጎሳን በጎሳ ላይ እንዲነሳሳ የሀሰትና የፈጠራ ወሬ ሲነዙ የነበሩ አካላት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ አሁንም የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ሁሉም አጥፊዎችን ወደ ሕግ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ለጥፋታቸው የሚመጥን ቅጣት ማግኘታቸው አይቀርም፤ የግድም ነው፡፡
በመሆኑም ከፌዴራል መንግሥቱ ቀጥሎ እርምጃ በመውሰድ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የጀመረውን በሌብነትና በምዝበራ የተጠረጠሩ ሰዎችን ወደ ሕግ የማቅረቡ ሂደት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ሌሎቹም ክልሎች ይህን በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የተጀመረውን ሥራ በአርአያት በመውሰድ የራሳቸውን እርምጃ መውሰድ ይገባቸዋል፡፡ በየአካባቢውና በየደረጃው የሚገኙ መዝባሪዎችን ተከታትሎና ወደ ሕግ አቅርቦ የሕዝብን እንባ ማበስ የግድ ይላቸዋል፡፡
የፌዴልል መንግሥትም ሆነ ክልሎች የሕግ የበላይነትን በማስከበር ጥረታቻው ውስጥ ሌላ ትኩረት የሚሻ ጉዳይም አለ፡፡ ሀሰተኛ የገንዘብ ሥርጭትና የሀገርም ይሁን የውጭ አገር ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመከላከል ረገድ በሁሉም ደረጃ እስካሁን እየተደረገ ያለው ክትትልና የሚወሰደው ርምጃ ተገቢ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ገንዘብ አዘዋዋሪዎቹ ከሚጠቀሟቸው ዘዴዎችና ከሚቀያይሯቸው ስልቶች አንፃር ወደፊት መንግሥት ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠብቀው የሚያመላክት ነው፡፡
ሕገ ወጥ ገንዘብ አዘዋዋሪዎች በየብስ የሚጠቀሙባቸውን መውጫ ቀዳዳዎች ለመድፈን ሁሉም የፀጥታና የደህንነት ኃይሎች እስከጠረፍ የሚደርስ ክትትልና ቁጥጥር የማድረጉን ሥራ አጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡ ምግባር የጎደላቸውን የበረራ ተረኞችና የአየር መንገድ ሠራተኞች በመጠቀም የሚደረገውን ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር የመያዝ ሥራ በፊት ከነበረው በስልትም፣ በይዘትም፣ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
መዝባሪዎች በሕገ ወጥ መንገድ ያከማቹትን ሀብት ለመጠቀም የሀገሪቱን ሠላምና የሕዝቧን ደህንነት ለማወክ በተጠና መልኩ ከሚንቀሳቀሱ ሥርዓት አልበኞች ጋር ማበራቸው አይቀርምና ህብረተሰቡ ሁለቱንም ተመጋጋቢ አካላት የማይታገስ መንግሥት ይሻል፡፡ በቅርቡ በምዕራብ ወለጋ ዞን አካባቢ የተፈፀመው የወንጀል ተግባር እንደ ሀገር አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡ መንግሥትም በትዕግሥት ሰበብ ሕዝብ ይህን ያህል ሲበደል መመልከት የለበትም፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖረው አንድ መንግሥት ነው፡፡ የተደራጀ ኃይል ሊኖረው የሚገባም ይኸው አካል ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ያሉት አካላት በምንም መልኩ ሕገ-ወጥ ናቸውና ሃይ ሊባሉ ይገባል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የተጀመረው ለውጥ መቀጠል ካለበት ሕዝቡም በተጀመረው ለውጥ እዚህም እዚያም ያያቸውን ጅምር ፍሬዎች የበለጠ መጎምራትና ለውጤት መብቃት ካለባቸው በፌዴራል መንግሥትም ይሁን በክልል ደረጃ የተጀመሩት ወንጀል ፈፃሚዎችን እያደኑ ወደ ሕግ የማቅረብ ጉዳይ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ የፌዴራል መንግሥትም ይሁን የክልል መንግሥታት አርቆ ከማሰብና ሆደ ሰፊ ሆኖ ነገሮችን በሠላማዊ መንገድ ከመፍታት ባለፈ የትኛውንም ችግር አግባብ ያለው እርምጃ ወስዶ ወንጀለኞችን ማስቆም እንደሚችሉ ሊያሳዩ ይገባል፡፡
በመንግሥት ታጋሽነት ሰበብ በሕዝብ ላይ የሚደርሰው ግፍና ሰቆቃ መቆም አለበት፡፡ በአንድ በኩል ሙሰኞችንና ሌቦችን እየመነጠረ በማውጣት ወደ ሕግ ፊት በማረቅብ በሌላ በኩል በግልም ይሁን በቡድን መሣሪያ ታጥቆ የሕዝብን ሠላምና ፀጥታ በሚያውኩ ሥርዓት አልበኞች ላይ አግባብነት ያለው እርምጃ በመውሰድ የሕግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነቱን ዛሬም መወጣት ይገባዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2011