ዕድሜው ገና በሰላሳዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው የሚገኘው። በጠይም ፊቱ ላይ ጥቅጥቅ ያለው ሪዙ ልዩ መለያው ነው። ስራ ወዳድ እና ትሁት የንግድ ሰው መሆኑ ደግሞ ከአርሶ አደሩም ከባለሀብቱም ጋር በተሻለ ሁኔታ ተግባብቶ ስራውን እንዲከውን እንዳደረገው የሚያውቁት ይመሰክራሉ። ልቡ ከወደኪነጥበቡ ቢሆንም አምርቶ መነገዱንም ግን እንደሚችልበት ሰርቶ አሳይቷል። ከጣሊያኖች በተማረው የቺዝ ምርት አዘገጃጀት ሙያ በመላ ኢትዮጵያ የሚዳረሱ የወተት ተዋጽኦዎችን እያመረተ ይገኛል።
ከአዲስ አበባ ደብረብርሃን በህዝብ ትራንስፖርት እየተጓጓዘ የጀመረው ስራ ፈጠራ አሁን ላይ አድጎ በሚሊዮኖች ብር የሚንቀሳቀስበት የስራ መስክ ሆኗል። በመላ አገሪቷ በሚገኙ አቅጣጫዎች ቺዝ፣ አይብ፣ ቅቤ እና ሌሎች የወተት ተዋጽኦዎችን አምርቶ ያቀርባል። በዚህም ምክንያት በየቤታቸው እና በበርካታ ሆቴሎች እንዲሁም በየሬስቶራንቶቹ ውስጥ የተስተናገዱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወጣቱ ያመረታቸውን የወተት ተዋጽኦዎች ተመግበዋል ፡፡
ከሁሉም በላይ ግን የቺዝ ምርቶቹ በደንበኞቹ ዘንድ በጥራታቸው ተወዳጅ በመሆናቸው ለመንገዱ መሰረት ጥለዋል። የማወራችሁ በቢሾፍቱ ተወልዶ አዲስ አበባ ኖሮ ደብረብርሃን ላይ ፋብሪካ ስለከፈተው ወጣት ኤፍሬም ስዩም ነው። ኤፍሬም በሰባቱ ሐይቆች ለምለሚቷ ከተማ እየተባለች በምትሞካሸው ቢሾፍቱ ነው ውልደቱ። አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በቢሾፍቱ ንጋት ጎህ እና ሞዴል የተሰኙ ትምህርት ቤቶች ተካትቷል።
ከአባቱ ጋር ቢሾፍቱ ያደገው ወጣቱ በልጅነቱ ብዙውን ጊዜ ወደትምህርቱ ቢያደላም ለኪነጥበቡ ከፍተኛ ፍቅር እንደነበረው ያስታውሳል። በተለይ የድራማ፣ ፊልም ፣ ስነጽሁፍ እና ዳንስ ስራዎች ላይ ትኩረቱ ከፍተኛ ነበር። 12ኛ ክፍልን እንዳጠናቀቀ ደግሞ የኮምፒውተር ትምህርት በመውሰድ ለስድስት ወራት የካሜራ ቀረጻ እና ኤዲቲንግ ስራዎች ላይ መሳተፍ ጀመረ። ይሁንና ስራውን ሳይገፋበት አዲስ አበባ ወደሚገኙት እናቱ ዘንድ ለመኖር ወደመዲናዋ መጣ። ገርጂ አካባቢ መቀመጫውን ያደረገው ኤፍሬም አሁንም የልጅነት ፍላጎቱ አልለቀቀውምና ወደዳንስ ሙያ፣ ድራማ እና ጭውውቶችን ወደ ማዘጋጀቱ ነው ያደላው።
የፊልም ኤዲቲንግ ስልጠና ወስዶም የተለያዩ የሙዚቃ ምስሎችን እና ፊልሞች ላይ በዳይሬክተርነት እና ኤዲተርነት ስራዎች ላይ ተሳትፏል። በተለይ የሳልሳ ዳንስን ተምሮ ጁቬንቱስ ክለብ የተሰኘው ተቋም የውጭ ዜጎችን በማሰልጠን የሰራበት ጊዜ አይረሳውም። ለአራት አመታት በሙያው እንደሰራ ግን ስለሚሰራው ስራ እና ስለሚያገኘው ገቢ ሲያስብ ገቢው ከእጅ ወደአፍ መሆኑ አልዋጥልህ ይለዋል። ለሙያው ፍቅር ስላለው ብቻ ቢሰራውም ለቀጣይ ዘመኑ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት ግን ሙያውን ቢቀይር የተሻለ እንደሚሆን ማሰላሰል ጀምሯል።
አንድ ቀን አብረውት የአርት ስራ ከሚያከናውኑ ወጣቶች ጋር ሲነጋገሩ ሁሉም ለተጨማሪ ስራ የሚሆን ዕቅድ ይዘው እንዲመጡ እና አዋጭ የሆነው ተመርጦ እንዲሰራበት የሚል ሃሳብ ይነሳል። ኤፍሬምም የወተት ተዋጽኦዎችን አምርቶ ለገበያ ስለማቅረብ የሚያትት ዝርዝር እቅድ ይዞ አቀረበ። በወቅቱ ግን ወጣቶቹ በእርሱ ሃሳብ ሳይስማሙ የተለያዩ የመድረክ ዝግጅቶችን በየከተሞቹ እየተዘዋወሩ ማዘጋጀት ላይ የሚያተኩረውን እቅድ መርጠው አብረው ለመስራት ተስማሙ።
ኤፍሬምም እቅዱን ቤቱ አስቀምጦ የመድረክ ዝግጅቶች ላይ በተለያዩ ከተሞች ከጓደኞቹ ጋር ከሰራ በኋላ የእራሱን የንግድ እቅድ ለመተግበር ምንም እንደማይከለክለው አዕምሮውን አሳመነ። እናም ዕቅዱ ከተጻፈ ከስድስት ወራት በኋላ ቤቱ ተቀምጦ ዳግም የጻፈውን ንድፍ እያገላበጠ በማንበብ ስለሙያው የሚረዱ ጽሁፎችን ወደመሰብሰብ እና ሙያተኞችን ወደማማከሩ ገባ። ሳልሳ ዳንስ ከሚያሰለጥናቸው ሰዎች መካከል ደግሞ አንድ ጀርመናዊት ነበረችና ሃሳቡን በመደገፍ ወደጣሊያን ቢሄድ የተሻለ እውቀት እንደሚያገኝ ነገረችው።
ጀርመናዊቷም የኤፍሬምን ፍላጎት በመረዳቷ ለአንድ ወር የሚቆይ የጣሊያን አገር የቺዝ አሰራር ስልጠና እድል አመቻቸችለት። ይህ ጊዜ ለኤፍሬም ትልቅ የህይወት አጋጣሚ ነበር። ወደጣሊያንም በመሄድ ስለተለያዩ የወተት ተዋጽኦዎች በተለይም ስለቺዝ አሰራር እና አጠቃላይ ስለወተት ጥራት ትምህርቱን ቀስሞ ተመለሰ። ሲመለስ ደግሞ በቀጥታ ወደስራ ከመሰማራቱ በፊት አዲስ አበባ እና በዙሪያዋ የሚገኙ ስድስት ከተሞች ላይ በመዘዋወር ለቺዝ ምርት የሚሆን ወተት የሚገኝባቸው ቦታዎችን ማጥናት ቀጠለ።
በመጨረሻ ደብረብርሃን ለስራው ምቹ እንደሆነች ኤፍሬም አምኗል። እናም 10 ሺ ብር መነሻ በመያዝ ከስምንት ዓመታት በፊት በደብረብርሃን አንድ ግቢ በ1 ሺ 500 ብር ተከራየ። በደብረብርሃን ዙሪያ ገጠራማ አካባቢዎች ምን ሊሰራ እንዳቀደ እና ሰዎች በምላሹ ምን እንደሚፈልጉ ለወተት አምራች ገበሬዎች በማወያየት ነበር የተጠመደው። የተለያዩ ውይይቶችን በማዘጋጀት አብሮ ከነዋሪው ጋር የተላመደው ወጣት ከሶስት ወራት ቆይታ በኋላ አነስተኛ የወተት መያዣ ፕላስቲኮችን በእጅ የሚሰሩ የቺዝ ማዘጋጃዎችን እና የወተት ማፍያ ድስቶችን በመያዝ “ሀ” ብሎ ስራውን ጀመረ።
በወቅቱ ወተት ከአርሶ አደሮች ላይ ሲሰበስብ ከሚፈልገው መጠን በታች በየቀኑ 20 ሊትር ነበር የሚያገኘው። ቺዝ ለመስራት 100 ሊትር ወተት ቢያንስ ማግኘት እንዳለበት የሚያውቀው ወጣት ወተቱን መልሱ ብሎ አቅራቢዎችን አላስከፋም። የወደፊቱን በማሰብ ይቀበላቸው እና ግማሹን እየሸጠ የተወሰነውን እየጠጣ የተቀረውን ሲበላሽ እያስወገደ መቀበሉን ቀጥሏል።
በርካታ ወተት ተረካቢ ፋብሪካዎች ባሉባት ደብረብርሃን ከተማ አምራቾችን መሳብ እንዳለበት የተገነዘበው ኤፍሬም፤ የአርሶአደሮችን ፍላጎት በመረዳት በአቅራቢ ያቸው የእንስሳት መኖ የሚያገኙበትን አማራጭ አቀረበ። ቡራዩ ከተማ ከሚገኝ የዱቄት ፋብሪካ ጋር በመነጋገር ፉርሽካ በዱቤ የሚያገኝበትን መንገድ አመቻችቶ ለአርሶአደሮቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ሲያቀርብ በምላሹ ደግሞ ተጨማሪ ወተት አርሶአደሮቹ ይዘው መምጣት ጀመሩ።
በእርግጥ በላክቶሜትር እና አልኮል ዘዴዎች ለክቶ ጥራቱን አረጋግጦ የተቀበላቸው ወተቶች በውስጣቸው ተጨማሪ ችግር ሲኖርበት ከሌሎች ሰዎች ገዝቶ ያስቀመጣቸውንም ወተቶች ያበላሹበት ወቅቶች በርካታ ናቸው። በተለይ አንድ የታመመች ላም መርፌ ከተወጋች በኋላ ወተቱን አልበው አስረክበውታል። እርሱም በመሳሪያው የውሃ መጠኑን እና ጥራቱን አረጋግጦ ካሳለፈ በኋላ ወተቱ ከሌሎች ወተቶች ጋር ተደባልቆ ሲፈላ ብጥስጥሱ የወጣበት ጊዜ ኪሳራው በእርሱ ነበር የሆነው። ይህን ሁሉ ፈተና ተቋቁሞ ለማለፍ ግን ጥንካሬው የነበረው ወጣት ተስፋ ሳይቆርጥ መስራቱን ቀጠለ።
ስራ በጀመረ ዓመት ሲመላው ደግሞ ለቺዝ መስሪያ የሚሆነውን 100 ሊትር ወተት ማግኘት የጀመረው ወጣቱ 10 ኪሎ ቺዝ ማምረት ቻለ። እንዲህ እንዲህ እያለ ስራውን እያሳደገ በቀን 11 እና 20 ኪሎ ቺዞችን መደማምረቱ ተሸጋገረ። ምርቱንም አዲስ አበባ ለሚገኙ ሆቴሎች በማሳየት ተቀባይነት በማግኘቱ እየተመላለሰ አንዱን ኪሎ በ90 ብር መሸጡን ተያያዘው። በወቅቱ ግን ከአዲስ አበባ ደብረብርሃን ድረስ በህዝብ የትራንስፖርት አማራጮች እየተመላለሰ መነገዱ አድካሚም አሰልቺም ሆኖበት እንደነበር ያስታውሳል።
ድካሙን ተቋቁሞ የሰራው ኤፍሬም ከሁለት አመታት በኋላ ስራው በማደጉ ዘመናዊ የቺዝ መስሪያ ማሽኝ ገዛ። ማሽኑን ሲገዛ ደግሞ የወተት ቅበላው እና ምርቱን በመሻሻሉ አምስት ሰራተኞችን ቀጥሮ ነበር። ሞዛሬላ፣ ፕሮቫሊን፣ የቺዝ አይነቶችን እና ክሬም ከወተት በማዘጋጀት የሚነግደው ወጣቱ በአዲስ አበባ በሚገኙ በርካታ ሆቴሎች እና ሬስቶራንቶች ምርቶቹ ተቀባይነታቸው ጨምሯል።
በትርፍ ላይ ትርፍ በመጨመር በደብረ ብርሃን የሚገኘውን ማምረቻ በማዘመን እየሰራ አንድ ተሽከርካሪም ገዛ። እያለ እያለ በአዲስ አበባ ገርጂ አካባቢ የምርት ማከማቻ በመከራየት በቀን ከመቶ ኪሎ በላይ ቺዝ እና የተለያዩ የወተት ውጤቶችን ማምረቱን ቀጥሏል። በተለያዩ ሱፐር ማርጀኬቶች እና ግለሰቦች ተፈላጊ የሆኑ ምርቶቹን ለማከፋፈል አዲስ አበባ ላይ ሱቆችን መክፈት እንዳለበትም አምኗል። እናም በገርጂ መብራት ሃይል፣ ቺቺንያ እና መገናኛ 24 የተባሉ አካባቢዎች ላይ ሶስት የምርት መሸጫ ሱቆችን በመክፈት ተጨማሪ ደንበኞችን እየሳበ ይገኛል።
በ20 ሊትር ወተት የተጀመረው የኤፍሬም ስራ አሁን ላይ በቀን 3ሺ 200 ሊትር ወተት በቀን የሚቀበል ትልቅ ድርጅት እስከመሆን ደርሷል። በደብረብርሃን ያለው የወተት ተዋጽኦዎች ማምረቻ እና በአዲስ አበባ በአጠቃላይ 52 ሰራተኞችን ቀጥሮ እያሰራ ይገኛል። እርጎ፣ የምግብ ቅቤ፣ ቺዝ እና የተለያዩ በጥራታቸው ተፈላጊ የሆኑ ምርቶቹም ኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴልን ጨምሮ በትላልቅ ሆቴሎች የምግብ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል። እስከ መቀሌ እና ሐረር የሚላኩት ጣፋጭ ቺዞች አዲስ ወተት የተሰኘውን የድርጅቱን ስም ይዘው በአራቱም አቅጣጫ እየተሸጡ ይገኛል።
ኤፍሬም አሁን በ10ሺ ብር መነሻ የጀመረው ስራ በሚሊዮኖች ገንዘብ እያንቀሳቀሰለት ነው። ሁለት ፒክአፕ ተሽከርካሪዎች እና አንድ ‘‘ዲ4ዲ’’ የተሰኘ ተሽከርካሪም ባለቤት ሆኗል። ስራውን ማስፋፋት በመፈለጉም ደብረብርሃን ላይ ሆቴል ለመሆን የሚችል ባለሶስት ወለል ህንጻ ግንባታ ጀምሯል። የእራሱን ምርቶች በእራሱ ሆቴል እያበሰለ ንግዱን ለማሳደግ ከማሰቡ በተጨማሪ ደግሞ በቀጣይ የወተት ማቀነባበሪያ እና ማሸጊያ ፋብሪካ የመገንባት እቅድ አለው።
አሁንም የአርት ፍቅሩ ከውስጡ ያልወ ጣው ወጣት በቢሮው አካባቢ ፒያኖ እና የተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎች ይታያሉ። ይሁንና ለኪነጥበቡ የሚሆን ብዙ ጊዜ የለውም። የወተት ተዋጽኦ ምርቶችን በጥራት ለማምረት አሁንም ሙያውን ለማሻሻል ሁልጊዜም በተለያዩ አማራጮች የሚገኝ ዕውቀትን በመቀበል ዝግጁ መሆኑን ይናገራል።
ኤፍሬም እድሜው ገና 32 ነው። በዚህ የወጣትነት ጊዜው ሰርቶ መለወጥን እና ለሌሎች ስራ መፍጠርንም በተግባር አሳይቷል። ስራ ወዳድነት ብቻ ሳይሆን ከሰዎች ጋር ተግባብቶ የመስራት ችሮታንም በማዳበሩ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ ለመድረስ እንዳገዘው አይደብቅም። በተለይ ጥራት ያለው ወተት ከአርሶ አደሮች ለማግኘው አስቸጋሪ በሆነበት ዘመን ትዕግስት እና በግልጽ ተወያይቶ መስራት አስፈላጊ መሆናቸውን ይናገራል። ማንኛውም ሰው ለመስራት ካሰበ ተስፋ መቁረጥን አስወግዶ እስከመጨረሻው ለመታገል አምኖ መነሳት አለበት። ይህ ከሆነ ስራው ትርፋማ የማይሆንበት ምክንያት የለም የሚለው ደግሞ ምክሩ ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2012
ጌትነት ተስፋማርያም