
ሻዕቢያ ጋር ያልተቀደሰ ጋብቻ የፈጸመው የሕወሃት አንጃ ለጦርነት ሽር ጉድ እያለ ነው። ቆሜለታለሁ የሚለውን ሕዝብ ደጋግሞ ለመከራ መዳረግ ልማዱ የሆነው ስብስብ፣ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም በእብሪት ተወጥሮ ከመታው አለት ጋር ደግሞ ለመላተም “ምቹ ጊዜ” ያለውን ክረምት እየናፈቀ ይገኛል።
በአንጻሩ ከጦርነት የሚገኝ አንዳች ፍሬ እንደሌለ የተረዱት የቀድሞ የሕወሃት አመራሮች የጦርነት ናፋቂዎቹን እንስቃሴ አጥብቀው እየተቹ ይገኛሉ። “ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና ልማት በትግራይ እድሎች እና ፈተናዎች” በሚል መሪ ሃሳብ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ሴንተር ፎር ሪስፖንሲብል ኤንድ ፒስፉል ፖለቲክስ በትብብር ባዘጋጁት የውይይት መድረክ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ጥቂት ፖለቲከኞች ሙሉ ሕዝቡን በተደጋጋሚ ለጦርነት የሚዳርጉበት ሁኔታ ሊያከትም እንደሚገባ ገልጸዋል።
በዚሁ መድረክ የታደሙ የውይይቱ ተሳታፊዎች በትግራይ ክልል ዳግሞ ጦርነት ይቀሰቀሳል ከሚል ስጋት ያለፈ ተጨባጭ መረጃ እንዳላቸው ከሰነዘሯቸው ሃሳቦች መረዳት ይቻላል። መሬት ላይ እየተደገሠ ያለውን እንደሚያውቅ እማኝ የቀድሞ የሕወሃት አባላት እያስተጋቡ ያሉት የጦርነት ይብቃ ውትወታ ሰሚ ቢያገኝ ምንኛ በታደልን። ዳሩ ነገሩ ያደቆነ ሠይጣን… አይነት ነውና ምቹ ጊዜ እየጠበቀ ያለው በደም የሚነግድ ቡድን ያሰበውን ካልፈጸመ አያርፍም።
ዛሬ ጥቂት እየተባሉ የሚገለጹት የሕወሃት ጦር ሰባቂ አንጃ አባላት እንደ ትናንቱ በቁጥር ያልበረከቱት በጦርነት የተከፈለውን የደም ዋጋ በቅጡ የሚገነዘቡ በርካቶች በመሆናቸው ነው። ይህን ሚዛን መጫወቻ ካርድ ማድረግ ይገባል። ደም የጠማው አንጃ ትናንት በክልሉ ሕዝብ ላይ ዘግናኝ የጦር ወንጀሎችን ከፈጸመው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ጋር የፈጸመው ስትራቴጂካዊ ያልሆነ ታክቲካል ጥምረት ቆሜለታለሁ ከሚለው ሕዝብ የሚለየው መርህ አልባ ጋብቻ መሆኑን በማስገንዘብ ስብስቡን የማጋለጥ ሥራ መሥራት አለበት።
ከሪፍረንደም ቢሆን የሰላምን ዋጋ ተገንዝበው “ጦርነት ይብቃ” እያሉ የሚገኙትን የቀድሞ የሕወሃት አባላት፣ የክልሉ ምሁራን፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ድምጽ በሜንስትሪሚንግ ሚዲያው ደጋግሞ ማስተጋባት ያስፈልጋል። የሃሳብ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ከመፍታት ውጭ ያለ አማራጭ ሁሉ አጥፊ መሆኑ በአጽንኦት ሊነገር ይገባል።
በተለይም ኢትዮጵያ ተዳክማለች ብሎ ባሰበ ቁጥር በውስጥ ጉዳይዋ ገብቶ የሚፈተፍተውን የሻቢያ መንግሥት እኩይ ዓላማ በመደግፍ በራስ ወገን እና ሕዝብ ላይ ጦር አዝማች በመሆን የእናት ጡት የሚነክሱ ባንዳዎች ይቅር የማይባል ተግባር የሚሰጠው ምላሽ ምህረት የለሽና የከፋ እንደሚሆን ለያደቆነው ሰይጣን ስብስብ በማያሻማ መንገድ መንገር ይኖርበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን የፓርላማ ንግግራቸው፤ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ ወደ ጦርነት እንዳይገባ አሁኑኑ የሰላም ሚናችሁን ተወጡ። መንግሥት አንድም ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የለውም። መልማት ነው ፍላጎታችን። ሁሉም ሕዝብ ማወቅ ያለበት ጦርነት አያስፈልግም ማለታቸው ቡድኑ የደረሰበትን ጫፍ ከማሳየት በላይ ብዙ አንድም ታዎች ያሉት ነው።
የትግራይ ሕዝብ ጦርነት ፈጽሞ እንደማይፈልግ ገልጸው፣ የዓለምን ሁኔታና የዘመኑን ውጊያ ባለመገንዘብ፣ መንግሥት በተለያዩ ችግሮች ተወጥሯል፤ የሚያግዙን ሀገራት አሉ በሚል የተሳሳተ ስሌት ጊዜው አሁን ነው በሚል ውጊያ ለመክፈት የሚፈልጉ አሉ። ይህ የተሳሳተ አካሄድ ነው ትግራይ የሚያስፈልገው ሰላም፣ ችግሮችን በውይይት በንግግር መፍታት ነው ሲሉ የመንግሥታቸውን መሻት አሳውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሃይማኖት አባቶች ያስተላለፉት ጥሪ “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” አይነት አካሄድ ይበቃል የሚል መልዕክት ያዘለ ነው። ትክክል ናቸው። የሃይማኖት አባቶች የአቋም መግለጫ ከማውጣት ያለፈ ሚና ሊኖራቸው ይገባል። ጦርነት ከመፈጠሩ በፊት መጓዝ ያለባቸውን ርቀት ተጉዘው ሰላምን መስበክ ይጠበቅባቸዋል። ከዚያ በመለስ የሚከታተል የመግለጫ ጋጋታ ተቋማቱ በሕይወት መኖራቸውን ከመግለጽ ባለፈ አንዳች ፋይዳ አይኖረውም።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በቅርቡ ባካሄደው ሶስተኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ ላይ የተሳተፉት የበላይ ጠባቂ አባቶች፣ ተወካዮች እና የቦርድ አባላት ጉባዔያቸውን ያጠቃለሉት በተለመደው መንገድ ነው። “በተለያዩ አካባቢዎች ያጋጠሙንን አለመግባባቶች እና ግጭቶች በንግግር በመፍታት በሰላም እና በፍቅር በአንድነት ልንኖር ይገባል” የሚል የሰላም ጥሪ አቅርበዋል። የሚነድ እሳትን ከብቦ በመወያየት ማጥፋት አይቻልም።
ሕወሃት መራሹ የቀድሞ መንግሥት ከተሳኩለት ሴራዎች አንዱ የኢትዮጵያዊ ማህበራዊ እሴቶቻችንን ጉልበት ቄጤማ ማድረግ ነው። የሃይማኖት አባቶችም ሆኑ የሀገር ሽማግሌዎች ዛሬም ድረስ ሰላምን በማስፈን ረገድ የሚጫወቱትን ቁልፍ ሚና እንዳይጫወቱ የሆኑት ሆነኝ ተብሎ በተቀናጀ መንገድ የተቋማቱን ማህበራዊ መሠረት ለመናድ ለዓመታት በተሠራ ሥራ ነው። ይህ መቀልበስ አለበት።
ሰላም ሚኒስቴር “ማህበራዊ ሀብቶቻችን ለህብረ ብሄራዊ አንድነታችን” በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ የሀገር ሽማግሌዎች እና የማህበራዊ የሰላም ተቋማት አመራሮች የምክክር መድረክ በቅርቡ ማካሄዱ ይታወሳል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ሰላምን ለማፅናት እና ብሔራዊ መግባባትን ለማጎልበት የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ሚናን አስመልክቶ ውይይት አድርገዋል
በውይይታቸው የሀገር ሽማግሌዎች ሕዝብና መንግሥትን የሚያስታርቁ ገለልተኛ ሆነው ለዕውነት መቆም ይገባቸዋል የሚል ሃሳብ ተነስቷል። በመድረኩ የተገኙት የሰላም ሚኒስትሩ መሐመድ እድሪስም፤ ሽምግልና ከሁሉም ነፃ የሆነ ተቋም ሊሆን ይገባል። የሀገር ሽማግሌዎች ከእኔነት ትርክት ይልቅ አሰባሳቢ ትርክት ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
የዛሬዋ ኢትዮጵያ የምትሻው እንዲህ ያሉ የሃይማኖት አባቶችን እና የሀገር ሽማግሌዎችን ነው። ኢትዮጵያዊ ማህበራዊ እሴቶቻችን ችግር ከመፈጠሩ በፊት የምንድንባቸው መፍትሄዎቻችን መሆን መቻል አለባቸው። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የመንግሥትን ጥሪ ሳይጠብቁ ለሕዝባቸው ግድ እንደሚላቸው በተግባር ማሳየት መቻል አለባቸው። የሃይማኖት አባቶቻችን በዚህ መንገድ ከዘለቁ … ያደቆነው ሰይጣን ወደ ቀልቡ ሊመለስ ይችላል፤ ማን ያውቃል ?
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
መግነጢስ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም