
ሻሎም ወዳጆች እንዴት ከረማችሁ ! በዛሬው መጣጥፌ አንድ ጉዳይ ላካፍላችሁ ወደድኩ። በሰው ልጆች ታሪክ በዓለም ላይ ለማየት የሚሰቀጥጡ እና ለመስማት የሚዘገንኑ ብዙ ግፎችና ጭቆናዎች ተስተውለዋል። አውሮፓውያን አፍሪካን በቅኝ ግዛት ለመቀራመት በነበራቸው ስግብግብ ፍላጐት የተነሳ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ያለምንም ጥፋቱ ያሳረፉበት የግፍ ጡጫ በታሪክ መዝገብ በጥቁር ብዕር ታትሞ ዘመናትን ተሻግሯል።
ከዚህ ሌላም ዜጐች በአምባገነን መሪዎቻቸው እነዚህኑ ተላላኪ አድርገው በሾሙ ምዕራባውያን አለቆች እየተሞገሱ እና እየተበረታቱ የሰው ልጅ ሊሸከመው የማይችል ጭቆናና ግፍን አድርሰውባቸው ሰምተናል በሚዲያም ተከታትለናል።
ጥቁር ናችሁ በሚል የዘረኝነት መነጽር እና የተንሸዋረረ ዕይታ የደቡብ አፍሪካ ዜጎች በገዛ ሀገራቸው ነጮች በገቡበት ሆቴል እንዳይገቡ ሲባሉ፣ ነጮች የሚማሩባቸው ት/ቤቶች እንዳይማሩና እነርሱ በሚያመልኩባቸው ቤተ እምነቶች ፈጣሪያቸውን እንዳይማጸኑ የተደረገበት የአፓርታይድ የዘር መድልዎም በሰው ልጆች ታሪክ መከሰት ባልተገባቸው ከሚባሉ እኩይ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
ግፍ እና ጭቆናው ምንም እንኳን ዜጐችን ያልተገባ ዋጋ ቢያስከፍልም እምቢ ለጭቆና፤ እምቢ ለግፍ ያሉና ለዚሁ ቅዱስ ዓላማ ግንባራቸውን ለአረር አሳልፈው የሰጡ እልፍ የነፃነት ታጋዮች እንዲወለዱም በር ከፍቷል።
የወጣትነት ዕድሜውን ጭምር ለነፃነት እና ለሕዝቦች እኩልነት ሲል መስዋዕት ያደረገውን የደቡብ አፍሪካ የነፃነት ቀንዲል ኔልሰን ማንዴላን በዚሁ አጋጣሚ መጥቀስ ሊዘለል የማይገባው ጉዳይ ይመስለኛል። ኔልሰን ማንዴላ በወገኖቹ ላይ የደረሰውን የአፓርታይድ ዘረኛ አገዛዝ ለመታገል ቤተሰብ፣ ትዳሬ እና ሕይወቴ ሳይል በሮቢን ደሴት ለ27 ዓመታት በወህኒ ተቀምጦ መራር ሕይወትን ገፍቷል።
የእንግሊዞችን ኢፍትሃዊነት እና ቅኝ አገዛዝን በመቃወምም ማሕተመ ጋንዲ በሰላማዊ ትግል ራሱን ለከፍተኛ ጉስቁልና ዳርጎ አብነታዊ የነፃነት ታጋይ ለመባል በቅቷል። በለጋ ዕድሜው በምዕራባውያን ሴራ በወንድሞቹ እጅ ውድ ሕይወቱን ያጣው የአፍሪካና የቡርኪናፋሶው እንቁ ቶማስ ሳንካራንም ሳላነሳ ማለፍ ትዝብት ላይ የሚጥለኝ ይመስለኛል። እነዚህን ጉዳዮች ለሀሳቤ መንደርደሪያነት ከተጠቀምኩ ዘንዳ ዛሬ ላወጋችሁ ስለፈለግሁት ስለእኛዎቹ ስመ ነፃ አውጪዎች የተወሰነ ነገር ልበል።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ “በሕዝብ ተጨቆነ ስም” ድርጅት ያቋቋሙ እና ነፍጥ አንግበው የተታኮሱ ድርጅቶች ቁጥራቸው የትየለሌ ነው። የፖለቲካ ድርጅቶች በተመሠረቱም ቁጥር ነጻነት፤ ነፃ አውጪ እና ዴሞክራሲ የሚሉ ቃላት የስያሜያቸው ማዕከል ቢደረጉም የብዙዎቹ ምግባር ግን ከዚሁ ተቃራኒ ሆኖ ታዝበናል።
የፖለቲካ ልዩነት ትናንት የነበረ፤ ዛሬም ያለ፤ ነገም የሚኖር ነው። በልዩነቶች ውስጥ የሃሳብ ልዕልናን ተጎናጽፎ ማሸነፍ እና ሀገርን መምራት ይበል የሚያሰኝ ነው። ከዚህ ውጭ ለርካሽ የፖለቲካ ፍላጎት ሲባል በሀገር ጥቅም መቆመር እና ሕዝብን መጠቀሚያ ማድረግ በሰማይም ሆነ በምድር ውድ ዋጋ የሚያስከፍል እኩይ ተግባር መሆኑ ለማንም የተገለጠ ነው።
”ፍየል ቦሌ ቅዝምዝም ጉለሌ ” እንደሚለው ብሂል በነፃ አውጪነት እና የዴሞክራሲ ጠበቃነት ስም የተደራጁ የስም ነፃ አውጪዎች ቆመንለታል ባሉት ሕዝብ አናት ላይ ቆመው ደም እንባ ሲያስለቅሱትም በተደጋጋሚ ተስተውሏል። ነፃ አውጪነት መሠረታዊ ትርጉሙ የራስን ጥቅም እና ተድላ ለሕዝብ እና የሕዝብ ጥቅም ሲባል በመተው ለተገፉ እና ለተጨቆኑ ዜጐች መታገል ቢሆንም የዚህ ተቃራኒ ሆነው አሁንም ድረስ የሕዝብ ምሬት ምንጭ የሆኑ የስም ነፃ አውጪዎች የተግባር የሕዝብ ጸሮች አሁንም ድረስ አልታጡም።
ይኼንን ጉዳይ ወደ መሬት አውርዶ ለመመልከት በሀገራችን ኢትዮጵያ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የድንቁርና ጌቶችን በማሳያነት መውሰድ ይቻላል። ነጻ አውጪነት በራሱ ክቡር እና የሞራል ልዕልናን የተጎናጸፈ ጉዳይ ቢሆንም ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ዓላማውን በጠመዘዙ ግለሰቦች እና የፖለቲካ ቆማሪዎች እጅ ሲገባ ግን ክብሩን ያጣል።
ለሕዝብ መቆም የሚለው ቅዱስ ዓላማው ተዘንግቶም ሕዝብ ላይ መቆም፤ ሕዝብን መዝረፍ፣ ሰላሙን መንሳትና ዘላቂ ጥቅሞቹን ማሳጣት ይሆናል። ከዚህም አልፎ ሕዝብ እየከሳ እና እየመነመነ የስም ነጻ አውጪዎች ቦርጭ እየሰፋ እና እየገዘፈ ይሄዳል። በስመ ነጻ አውጪዎቹ ፋኖ እና ሸኔ በኩል እየታየ ያለው እውነታም ይኼንኑ የሚያረጋግጥ ነው።
እነዚህን ኃይሎች ማንን ከማን እና ከምን ነጻ እንደሚያወጡ በአግባቡ ተረድተው ማስረዳት የማይችሉ፤ እራሳቸው ከተያዙበት ጽንፈኛ እና የከሰረ የፖለቲካ አስተሳሰብ ነጻ የሚያወጣቸው፤ ብረት አንግቦ ከመፎከር በስተጀርባ ካለው የረከሰ የትውልዶችን ተስፋ የመናጠቅ የተልዕኮ እርግማን የሚታደጋቸው የሚፈልጉ ናቸው።
እነዚህ ኃይሎች እራሳቸውን ነጻ አውጪ አድርገው የመታየታቸው እውነታ” ጅብ በማያውቁት ሀገር ቁርበት አንጥፉልኝ ”አለ እንደሚባለው፤ ድንገትም አሁን ባለው ትውልድ የአስተሳሰብ ልዕልና ከዚያም በላይ ማለት የሚችል አባባል የሚፈልግ ነው።
በርግጥ ጅብ እንግድነት ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ ማለቱ ከጅብነት ፍጥረታዊ ማንነቱ አኳያ ብዙ ላያስብል ይችላል። ከመሸ የእንደምን አመሻችሁ ሰላምታ ይዞ እንግድነት መምጣቱም እንዲሁ። ግን ጅብ ጅብ ነው፤ ከዚያ የተለየ መሻት ሊኖረው አይችልም፤ ይኖረዋል ብሎ ማሰብም በየዋህነት ያልተገባ ዋጋ ከማስከፈል ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም።
በእኛ ሀገር ያለውን የነጻ አውጪነት እንቅስቃሴ የትናንትም ሆነ የዛሬ ትርክት ስናጤን በመሰረታዊነት የምናነሳቸው ጥያቁዎች ብዙ ናቸው። ከእነዚህ ወስጥ በዋናነት፤ በሕዝብ ነጻ ፍላጎት ላይ በተቃርኖ መቆም፤ በሕዝብ ስም እየማሉ እና እየተገዘቱ፤ በሕዝብ መሰረታዊ ፍላጎቶች ላይ በጠላትነት መሰለፍ፤ ከነጻ አውጪነት ጋር ያላቸው ዝምድና የስሌት መነሻው ምን ይሆን! የአስተሳሰብ መሠረቱስ?
እወክለዋለሁ የሚሉትን ሕዝብ ገድሎ በመፎከር፤ ንጹሃንን አግቶ ገንዘብ በመጠየቅ የሚሰላ ነጻ አውጪነት ትርጓሜው ምንድነው፤ የሕዝብ መገልገያ መሰረተ ልማቶች በማውደም፤ ትምህርት ቤቶችን አዘግቶ በትውልድ የመማር መብት በማላገጥ፤ የሕዝቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ በመረበሽ የጣር ሕይወት እንዲኖር በማድረግ ላይ የቆመ ነጻ አውጪነት ትርጓሜው ምን ሊሆን ይችላል ?
በሕዝብ ሞት እና ስደት ላይ፤ መከራ እና ጭንቀት ላይ የሚመሰረት፤ ይህንንም የስኬት የፖለቲካ ስትራቴጂ አድርጎ ከሚመለከት ክፉ አእምሮ እና በክፉ አእምሮ ከደነደነ ልብ በሚመነጭ የክፋት /የአመጽ አስተሳሰብ የሚነዳ ”ነጻ አውጪነት” ለሕዝብ ፍላጎት እና ልዕልና ከሚቆም ነጻ አውጪነት ያለው አንድነት በምን ይተረካል?
ሁለንተናቸው አራት ኪሎ ከመግባት እና ትናንቶችን ከማስቀጠል ያልዘለለ፤ ዘመኑን አውቆ ለመዋጀት የሚያስችል የዛሬ የእውነት ጠብታ የሌለበት፤ ነገን በዛሬ የጥላቻ እና የጽንፍ ፖለቲካ ቁማር የእኔ አደርጋለሁ ብሎ የሚያስብ እና ለዚህም የትኛውንም መከራ እና ስቃይ በሕዝብ ላይ ለመጫን ሁለቴ ለማሰብ ያልተፈጠረ ኃይል፤ የነጻ አውጪነት ስሪት መሰረቱ ምን ሊሆን ይችላል ?
በ24 ሰዓት 4 ኪሎን እቆጣጠራለሁ ከሚል የበዛ ፉከራ እና ቀረርቶ ባለፈ በሁለት ዓመት አራት ኪሎ ሜትር መራመድ የተሳናቸው፤ በቆመ ቀር አስተሳሰባቸው፤ የቆሙበትን መሬት አኬልዳማ ያደረጉ፤ ይህንንም እንደ ድል ከፍ ባለ ድምጽ ጮክ ብሎ ለመናገር የማያፍሩ፤ ልበ ደንዳኖች የነጻ አውጪነት ጉዞ ፍጻሜው ምን ሊሆን ይችላል ?
እነዚህ የዘመኑን ነጻ አውጪዎች /በነፃነት ስም የሚቆምሩ ቆማሪዎችን ስመለከት ወደ አዕምሮዬ የሚመጣው የስያሜ እና የባህሪ ተቃርኖዎች ብቻ ሳይሆን፤ለአዕምሮ የሚከብድ የልብ ድንዳኔ እና ከዚህ የሚመነጭ የሕዝብ ንቀት ነው። በሕዝብ ነገዎች ላይ የማመንዘር እና የመሸቀጥ ድፍረት ነው ።
ይኼንን የተመለከተ አንድ ወዳጄ ንግድ እና ቢዝነስ አላዋጣ ሲል እና በሃሣብ ሳይሆን በጥላቻ የሚመሩ የፖለቲካ ነጋዴዎች ሲበዙ ነፃ አውጪዎች ጠብድለው ሕዝብ ደግሞ ይከሣል ብሎኝ ነበር። የዚህ ጓደኛዬ አባባል እውነት መሆኑንም የእኛዎቹን ነፃ አውጪዎች የትናንት እና አሁናዊ እውነታዎች ተመልክቼ አረጋግጫለሁ።
የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታ የሆኑት የሸኔ እና የጽንፈኛው ፋኖ መሪ ነን ባዮች የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ የተገነዘቡ አይደሉም። የሀገር ዘላቂ ጥቅምና የሕዝቦች ወዳጅነት በእነዚህ ግለሰቦች ዘንድ ቦታ የለውም። ለእነርሱ ይሳካላቸው እንጂ የሚፈፅሙት ተግባር ሕዝብ እና ሀገር ላይ ስለሚደርሰው ጉዳት ማሰብ ፈጽሞ አይፈልጉም። ዓላማቸው በታወረ እና በማይሳካ ራዕይ በመመራት ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨት፣ንጹሃንን መጨፍጨፍ፣የልማት ተግባሩን ማደናቀፍ እና የማይጠረቃ ሆዳቸውን በዘረፋ መሙላት ነው።
ኢትዮጵያዊ እሴቶች በእነዚህ ግፈኞች በኩል ቦታ ስሌላቸው የሃይማኖት አባቶች እና ትልልቅ የሀገር ሽማግሌዎችን በእንብርክክ ያስኬዳሉ ይገድላሉም። አርሶአደሩ እንዳያርስ ማዳበሪያ እየዘረፉ፣ ትውልድ እንዳይማር መምህራንን እየገደሉና ት/ቤት እና ጤና ጣቢያን እያዘጉ ለሕዝብ ቆመናል ሲሉ ትንሽ እንኳን አያፍሩም።
ሆዳቸው አይጉደል እንጂ አርሶ አደር አረሰ አላረሰ፤ አረንጓዴ ዐሻራ ተሳካ አልተሳካ፤ ተማሪ ተማረ አልተማረ፤ ሕሙማን ታከሙ አልታከሙ ደንታ አይሰጣቸውም። ሀገር ከፈረሰች በቀላሉ ትጠገን ይመስል ሀገር በሚያፈርስ ተግባር ላይ ተሰማርተውና ከባዕዳን ጋር አብረው ዓላማችን መንግሥትን ማፍረስ ነው ከዚያ ሀገር አንገነባለን ይሉናል።
የእነዚህ ሆዳም ነጻ አውጪ ነን ባይ አመራሮች የሁልጊዜም ሃሳብ ርካሽ ግለሰባዊ ፍላጎታቸውን በስግብግብነት ማሟላት ነው። ጋንዲ፤ማንዴላንና ቶማስ ሳንካራን ስናውቃቸው በረሃብ ተጎሳቁለው እና ጢማቸውን እንኳ የሚላጩበት ጊዜ አጥተው በተንጨባረረ መልክ ነው። እናስ የሸኔ እና የፋኖ መሪ ነን ባዮች በቅቤ የተወለወለ የሚመስል መልክና ሹሩባ እንዲሁም ቦርጭ ከየት የመጣ ይሆን? ይሄን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቆም ብሎ ሊያስብበት እና ማንታቸውን ሊረዳበት የሚችል ጥያቄ ይመስለኛል!
ሰናይ ዘመን
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
በፍቃዱ ከተማ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም