ወራት የየራሳቸው ባህሪ አላቸው። እንዲያውም አንድ ባህረሀሳብ (ካላንደር) ላይ ያየሁትን ልንገራችሁ። በየጠረጴዛችን ላይ ያሉት የቀን መቁጠሪያዎች በተለያዩ ተቋማት የሚዘጋጁ ናቸው። ታዲያ እነዚህ ተቋማት በቀን መቁጠሪያዎቹ ጀርባ ላይ የሚያደርጉት ፎቶ የተቋሙን የገጽታ ግንባታ የሚያሳይ ነው (ማስታወቂያ መሆኑ ነው)።
ባለፈው ዓመት በሀገራችን ከሚገኙት ባንኮች አንዱ ያዘጋጀው የቀን መቁጠሪያ ነበር ጠረጴዛዬ ላይ የከረመው። እናም አጠገቤ የመጡ ሁሉ እያነሱ ያዩት ነበር። የጀርባው ፎቶዎች ለአገራቸው ውለታ የዋሉ ታዋቂ ሰዎች፣ አርበኞች እና የተፈጥሮ ቦታዎች ነበሩ። የተጠቀሱትም፤ ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ፣ እቴጌ ምንትዋብ፣ ፊት አውራሪ አመዴ ለማ፣ ንጉሥ ተክለሃይማኖት፣ ራስ ደስታ ዳምጠው፣ የዝቋላ (ቢሾፍቱ) አካባቢ ተፈጥሮ፣ አጼ ሰርፀ ድንግል፣ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ፣ እቴጌ ጣይቱ፣ ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ፣ ደጃዝማች ዑመር ሰመተር እና ይድነቃቸው ተሰማ ነበሩ።
ይሄ ቀላል ማስታወቂያ አይደለም። አንድን ተቋም ወይም ግለሰብ ማስተዋወቅ ሳይሆን አገርን ማስተዋወቅ ማለት ነው። ውብ የተፈጥሮ አካባቢዎችን ማስተዋወቅ ነው።
በዚህ ዓመት ደግሞ አንድ ጠረጴዛ ላይ አንድ የቀን መቁጠሪያ አየሁ። እያንዳንዱ ወራት ላይ የተቀመጠው ፎቶ የወራቱን ባህሪ የሚገልጽ ነው። በዚያ ወር ያሉ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ነገሮችን ያሳያል። ለምሳሌ የመስከረም ወር ገጹ ላይ የመስቀል በዓል እና የኢሬቻ በዓልን የሚያሳዩ ፎቶዎች አሉ። ጥቅምት አበባና ለምለም ሳር፣ ህዳር የታላቁ ሩጫ ፎቶዎች፣ ታህሳስ የገና ጨዋታ፣ ጥር የጥምቀት በዓል፣ የካቲት የዓድዋ አርበኞች… እያለ የየወራቱን መለያ አስቀምጧል። የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን ባህሎችና ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት ያሳያል።
እስኪ እኛ ደግሞ ስለጥቅምት ወር ጥቂት እንበል።
የጥቅምት ወር የአበባ ወር ነው። በእርግጥ የአበባ ማበቢያ ሁሉ መስከረም ተደርጎ ነው የሚታየው፤ ግን ጥቅምት ይበልጣል፤ መስከረም ላይ የአደይ አበባ ነው፤ ጥቅምት ላይ ግን የሰብል እና የሌሎች ተክሎች አበቦች ናቸው የሚበዙት። መስከረም ላይ የነበረው ዝናብ ሙሉ በሙሉ የሚቆምበትና መሬቱ ደረቅ የሚሆንበት ነው። ጥቅምት ጭቃም አቧራም የሌለው በለምለም ሳር እና በአበባ የተሸፈነ ምድር ነው የሚታየው። ያው እንግዲህ የጥቅምት ብርድ እንደተጠበቀ ሆኖ ነው። በነገራችን ላይ ጥቅምት ብርዱ ብቻ ሳይሆን ፀሐዩም ሃይለኛ ነው።
ጥቅምት በአርሶ አደሩ ዘንድ የማር እና የእሸት ወቅት ነው። የማር ወቅት የሆነው ያው የአበባ ወቅት በመሆኑ ነው። ከመስከረም ጀምሮ የሚያብበው አበባ በጥቅምት ሙሉ ይሆናል። በዚህ ወር ውስጥ በየውሃ ዳር የሚታየው ንብ ነው። አርሶ አደሮች በዚህ ወር በንብ ክትትል ሥራ ላይ ይጠመዳሉ። በተለይም በባህላዊ ቀፎ የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች በዚህ ወር አዲስ ንብ ሊያገኙ ይችላሉ። ንቡ በመንጋ ሲሄድ ድንገት የሆነ ዛፍ ወይም ትልቅ ድንጋይ ላይ ይሰፍራል፤ ያኔ ይዘው ወደራሳቸው ቀፎ ይወስዱታል፤ የማን ንብ እንደሆነም ስለማይታወቅ።
አበባው አበበ ንቡም ገባልሽ
እንግዲህ የአገር ልጅ ማር ትበያለሽ
የሚለው የልጅ አገረዶች ዘፈንም የዚህ ማሳያ ነው። ጥቅምትና አበባን በተመለከተ ብዙ የተባሉ ነገሮች አሉ። በብዛት የሚታወቀው አባባል ‹‹በጥቅምት አንድ አጥንት›› የሚለው ነው። በጥቅምት አንድ አጥንት የተባለበት ምክንያት የወሩ ብርዳማነት ነው። ብርድን ደግሞ መከላከል የሚቻለው በልብስ መደራረብ ሳይሆን በሰውነት መደራረብ ነው። ሰውነት ለመደራረብ ደግሞ የሥጋ ምግቦች መመገብ አለብን ለማለት ነው።
በነገራችን ላይ «ሥጋ ለጥጋብ አጥንት ለትካዜ» የሚለውን የአማርኛ ምሳሌያዊ አነጋገር ታውቁታላችሁ? ብዙ መመገብም ችግር አለው ለማለት ነው። ‹‹በጥቅምት አንድ አጥንት›› ይባል እንጂ ለምግብነት የሚውለው ግን ሥጋ ሥጋው ነው። የአማርኛ ፈሊጣዊ ንግግር ውስጠ ውይራነት ስለሚበዛበት አንዳንዴ ደርበው የሚናገሩት መልዕክትም ይኖር ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ግን ብዙ መብላትም ችግር እንዳለው ይናገራሉ።
‹‹ከራበው ለጠገበ አዝናለሁ›› የሚባለው አባባል ትልቅ መልዕክት የያዘ ነው። ይሄንኑ አባባል የሚያጠናክር ‹‹ካልጠገቡ አይዘሉ፤ ካልዘለሉ አይሰበሩ›› የሚባል አባባልም አለ። የሁለቱም መልዕክት ጥጋብ ለጉዳት እንደሚዳርግ ነው። በተለይ ‹‹ከራበው ለጠገበ አዝናለሁ›› የሚለው ከተራበ ሰው በላይ ጥጋበኛ ጉዳት እንደሚደርስበት ለመግለጽ ነው። ‹‹ጎመን በጤና›› እንደማለት ነው።
የጥቅምት ነገር ነው ይህን ሁሉ ያስወራን። ‹‹የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል›› ነውና የጥቅምት አጥንት ስለምግብ አስወራን። አባባሎችንም አበዛን። መስከረም እና ጥቅምት አባባል ይበዛባቸዋል። በኪነ ጥበብ ዘርፍም እንደዚያው! የሦስተኛ ክፍል የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መጽሐፍ ላይ ‹‹ትምህርት በልጅነት አበባ በጥቅምት›› የሚል ረዘም ያለ ግጥም አስታውሳለሁ (አሁን ይኑር አይኑር አላውቅም)። ትምህርት በልጅነት ሲሆን በንጹህ ሰሌዳ ላይ እንደመጻፍ ነው የሚል መልዕክት አለው።
አበባም የሚያምርበት በጥቅምት ነው። ከዚሁ ከልጅ እና ከጥቅምት ጉዳይ ሳንወጣ፤ ‹‹ልጅን በጡት እህልን በጥቅምት›› የሚባል አባባልም አለ። ሁሉም በወቅቱ ነው መሆን ያለበት ለማለት ነው። ልጅ በስነ ማግባር የታነጸ ይሆን ዘንድ ገና ጡት በመጥባት ላይ ሳለ ነው መቀረጽ ያለበት። እህልም እንደዚያው፤ ደርቆ ከመበታተኑና ከመርገፉ በፊት ነው በለጋነቱ ነው መሰብሰብ ያለበት እንደማለት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ እህል በእሸትነቱ የሚተናኮለው ስለሚበዛ ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግለታል። ይሄም የሚሆነው በጥቅምት ነው።
የኢትዮጵያ ወራት ባህሪያት ከግብርና ጋር የተያያዘ ነው። ለዚህም ነው አባባሎች እና ስነ ቃሎች ግብርና ነክ የሆኑት። 12ቱ ወራት በአራት ወቅቶች ይከፋፈላሉ። አራቱም ወቅቶች ግብርናን መሰረት አድርገው የተሰየሙ ናቸው።
መስከረም፣ ጥቅምት እና ህዳርን የያዘው ወቅት የመኸር (ጸደይ) ወቅት ይባላል። የመኸር ወቅት የተባለው የግብርና ምርቶች የሚሰበሰቡበት ስለሆነ ነው። የግብርና ሚኒስቴርም በእነዚህ ወራት በምድብ በምድባቸው ነው የሥራ ዕቅድ የሚያወጣው። እነዚህ ሦስቱ ወራት ከባህሪያቸው አንጻር ደግሞ ጸደይ ተብለውም ይጠራሉ። የጸዳ፣ የፈካ ወቅት እንደማለት ነው።
ታስሳስ፣ ጥር እና የካቲትን የያዘው ወር ደግሞ የበጋ ወቅት ይባላል። ይህ ወቅት በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል አርሶ አደሩ አንፃራዊ እረፍት የሚያገኝበት ነው። አሁን አሁን ግን የመስኖ ሥራ እና የሌሎችም የእርከን ሥራዎች ስለተለመደ ሥራ የሚፈታበት አይደለም፤ ሆኖም ግን እንደሌሎች ወራት አይሆንም። የበልግ እና የክርምት ወራትን የያዙት ሁለቱ ወቅቱችም እንደዚሁ ከግብርና ጋር የተያያዙ ናቸው።
በነገራችን ላይ ከአምስት ዓመት በፊት በ2007 ዓ.ም ጀምሮ ‹‹በጥቅምት አንድ አጥንት›› በሚል የሥጋ ፌስቲቫል በኢትዮጵያ መካሄድ ጀምሯል። በዝግጅቱም ከውጭ አገራት የመጡ ዜጎች ሁሉ ይሳተፉበታል። በእንዲህ አይነት አጋጣሚም ብዙ ሥጋ ይሸጣል። እንዲህ አይነት ፌስቲቫሎች በውጭ አገራት በስፋት የተለመዱ ናቸው። ታዲያ ይሄ የእኛ የአበባ ወቅት ፌስቲቫል ቢኖረው ምን ያንስበታል?
የጥቅምት አበባ በሚለው የንዋይ ደበበ ዘፈን እንሰናበታለን።
የጥቅምት አበባ
የጥቅምት አበባ
የጥቅምት አበባ ነሽ አሉ
አወድሽው አካሌን በሙሉ
የጥቅምት አበባ
የጥቅምት አበባ ለሽታ
ለኔ ግን ጣልሽብኝ ትዝታ…
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2012
ዋለልኝ አየለ