ታሪክን ከተረክ ነጥሎ የሚያቀርብ፤ ኢትዮጵያን በአንድ ማዕከል የሚያስመለክት፤ ስለቀጣዩ ትውልድ ብልጽግና የተሻለ አቅጣጫና መሠረት የሚያስቀምጥ፤ በጥቅሉ የኢትዮጵያውያንን የዘመናት አሻራ ከነገው ተስፋ ጋር አስተሳስሮ በአንድ ማዕከል ይዞ ብቅ ያለው የአንድነት ፓርክ፤ ለወራት በጉጉት ሲጠበቅ ቆይቶ ትናንት በይፋ ተመርቆ ተከፍቷል፡፡
ፓርኩ የጥቁር አንበሳ ፓርክ፣ የአገር በቀል እጽዋት ቦታ፣ አሁን ያሉ የኢትዮጵያ ክልሎች የሚገለጹበት መንደር፣ አረንጓዴ ስፍራ፣ ታሪካዊ ሕንፃዎችና እልፍኞች፤ እንዲሁም የእንስሳት መመልከቻ ፓርክ ያካተተ፤ የኢትዮጵያን የዘመናት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁነቶች ያቀፈ ሲሆን፤ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ አገራት ተጋባዥ እንግዶች፤ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ሚኒስትሮች፣ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆነ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎች ተገኝተው ጎብኝተውታል፡፡
የፓርኩ አስጎብኚዎችም በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛ፤ በፈረንሳይኛ እና በሌሎች የተለያዩ ቋንቋዎች እንግዶቹን ማስጎብኘታቸውን ቀጥለዋል፡፡እንግዶቹም በአንክሮ ያዳምጣሉ፤ በዓይናቸው ግራ ቀኝ ያማትራሉ፤ የታሪክ፣ የባህል፣ የእምነት የፖለቲካ፣ ወዘተ. ጉዳዮች በአንድ ተሰድረው ማየታቸው አስደምሟቸዋል፡፡ከዳግማዊ ምኒልክ እስከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ድረስ የነበሩ መሪዎች ፎቶ እስከምግባራቸው በወጉ ተሰናስሎ ቀርቧል፡፡የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ከየት ወደየትነትም ተቀምረው ተገልጸዋል፡፡
አሁን ያሉት የኢትዮጵያ ክልሎች የተወከሉበት ስፍራም አበይት የክልሎቹ መገለጫ በሚባሉ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ እሴቶች እየተወከሉ፤ ስለ ክልሎቹ አጠቃላይ ገጽታ ያለአስጎብኚ መገንዘብ በሚያስችል መልኩ በጽሑፍ፣ በድምጽና በተንቀሳቃሽ ምስል የታገዘ ገለጻ እንዲገኝባቸው ተደርገው ሁሉም በየፈርጃቸው ቀርበዋል፡፡እነአክሱም፣ ላሊበላና ኤርታሌን የመሳሰሉ የየክልሉ የቱሪዝም ሀብቶችም በአካል ያገኟቸው እስኪመስል ድረስ በሚያስደምም ጥበብ በየክልሎቹ ስፍራ ተገልጸዋል፡፡
ከአንድ ሰዓት ለላቀ ጊዜ በእነዚህና ሌሎች በርካታ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን መገለጫዎችን የጎበኙት አምባሳደሮች፣ በጉብኝታቸው ማገባደጃ ላይ «ለሀገሬ ሕልሜ…» የሚል ጽሑፍ ያለበት ስፍራ የተቀመጡ የምኞት ማስፈሪያ ሰነዶች ላይ ሃሳባቸውን ማኖር ነበረባቸው፡፡እናም አደረጉት። ሁሉም ግን ምኞታቸውን ከማስፈራቸው በፊት ስላዩት ነገር መደመማቸውን፤ ኢትዮጵያ የድንቅ ታሪክና ሥልጣኔ ባለቤት ስለመሆኗ፤ አሁን ባለው አመራር በተጀመረው መልኩ መጓዝ ከቻለችም ነገ ታላቅ መሆኗ እውን ስለመሆኑ የምስክርነት ቃላቸውን አኖሩ፡፡ለአገራቸው ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም የሚመኙት ሰላም፣ፍቅር፣ ብልጽጋናና አንድነት መሆኑንም አሰፈሩ፡፡
አምባሳደር ፒተር ዶሊ፣ በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ አምባሳደር ሲሆኑ፤ ከጽሑፍ ባሻገር ሃሳባቸውን በቃል እንዲያጋሩን ከጠየቅናቸው መካከል አንዱ ናቸው፡፡እርሳቸው እንደሚሉት፤ ከሁለት ወራት በፊት ስፍራውን የጎበኙ ቢሆንም በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በዚህ መልኩ ይጠናቀቃል የሚል ሃሳብ አልነበራቸውም፡፡በዕለቱ ባዩት ነገርም እጅጉን የተደሰቱ ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያን በታሪክ እንደሚባለው ብቻ ሳይሆን አሁንም ማድረግ የሚፈልጉትን ማድረግ የሚችሉ መሆኑን ተገንዝበዋል፡ ፡ፓርኩም የኢትዮጵያን ያልተቆራረጠ የታሪክ ፍሰት፣ የሥልጣኔ ባለቤትነትና እምቅ የቱሪዝም ሀብት ባለቤትነት ያረጋገጠ ነው፡፡ተግባሩም የኢትዮጵያን ገጽታ ለዓለም ከማሳየትና የቱሪዝም ፍሰቱን ከማሳደግ ባለፈ፤ ለሌሎች አገራትም ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡
በዚህ መልኩ የፓርኩን ገጽታ ከጎበኙትና ከገለጹት ባለፈ፤ የዕለቱ ታላቅ እንግዶች የነበሩት የምሥራቅ አፍሪካ አገራት መሪዎች በሥነሥርዓቱ ላይ የተገኙ ሲሆን፤ መሪዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ገለጻ እየተደረገላቸው ፓርኩን ጎብኝተዋል፡፡ መሪዎቹ ሁሉንም በአንክሮ ተመልክተው፤ ባዩትም ተደምመው፤ ኢትዮጵያን በአንድ ማዕከል ያገኟት ያክል ዙሪያ ገባውን ተዟዙረው ተመለከቱ፡፡ያዩት እውነታ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ ጋር ተዳምሮ ጉብኝታቸውን አስደሳች ማድረጉን ከሁኔታቸው መረዳት ይቻላል፡፡የዚህ ምስክሩ ደግሞ የጉብኝታቸውን ማጠቃለያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሰሩት ሥራ ከቃል በላይ በአንድ ላይ በሆነ ጭብጨባ ስሜታቸውን ገለጹላቸው፡፡
በዚህ መልኩ የቀጠለው የፓርኩ ጉብኝትም፣ በምኒልክ የግብር አዳራሽ በራት ግብዣ የቀጠለ ሲሆን፤ መርሃ ግብሩም ኢትዮጵያ የብዝሃነት ነገር ግን የአንድነት አገር መሆኗ የተገለጸበት፤ የብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ ሙዚቃዎችና ጭፈራዎች ታጅቦ፤ የፓርኩ እዚህ መድረስ አስተዋጽዖ ላደረጉ አካላት ምስጋናና እውቅና የቀረበበት ነበር፡፡
ይህን ፓርክ በመስራት የኢትዮጵያን የዘመናት ታሪክ በዚህ መልኩ ማቅረብ በመቻላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የኢትዮጵያን መንግሥት እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፤ ተግባሩ ቀደም ሲል በተበጣጠሰና በተበታተነ መልኩ ይገለጽ የነበረውን የኢትዮጵያን የዘመናት አሻራ በአንድ ላይ ማግኘት እንዲቻል ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ርምጃውንም የኢትዮጵያን ታሪክ በአንድ ቦታ አቅርቦ የመግለጽ ራሱን የቻለ ታሪክ የተሰራበት ሌላ ታሪክ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በተመሳሳይ ይሄን ፓርክ እውን ማድረግ በመቻላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን «እንኳን ደስ አለዎ!» በማለት መልዕክት ያስተላለፉት የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በበኩላቸው፤ የአንድነት ፓርክ በዚህ መልኩ መገንባቱ ኢትዮጵያ ያላትን የታሪክና የባህል እሴት በአንድ የሚያሰባስብና አዲስ አበባም የዚህ ድምር የታሪክ ማዕከል እንድትሆን የሚያደርጋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ህብረት እዚህ መድረስ የማይተካ ሚና የተጫወቱ መሪዎች ባለቤት እንደመሆኗ ታሪካቸው በዚህ መልኩ መሰደሩ የሚበረታታ እንደሆነ በመግለጽም፤ አፍሪካውያን ያላቸውን እምቅ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እምቅ ሀብት እንዲህ አቀናጅተው እንዲያለሙ፣ እንዲያስተዋውቁና እንዲጠቀሙ የሚያስችላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባደረጉት ንግግር፤ ይህ ግቢ ብዙ ይናገራል፤ የሚያኮራ ታሪክ እንዳለን በደንብ ያሳያል፤ የሚያሳፍር ታሪክ እንዳለንም እንዲሁ ያሳያል፤ የተሟላም ያልተሟላም እንዳለን ያሳያል፡፡ ትውልድ ከድል ብቻ ሳይሆን ከውድቀትም መማርን፤ እያፈረሱ ሳይሆን ባለው ላይ እየደመሩ መስራት እንደሚገባ፤ ከቆረጡ ሁሉንም ማድረግ እንደሚቻል፤ ኢትዮጵያም ይሄን ለማድረግ ቆራጥ ልጆች እንዳሏት ያሳየም ነው፡፡
አገር ወረትም ውዝፍ እዳም አላት፤ ይህን እንደሚዛኑ መጠቀም ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያን ታሪክ አላቸው፤ ነገር ግን በታሪክ የሚኖሩ ሳይሆን ታሪክ በውስጣቸው የሚኖር ናቸው፡፡ ሥልጣኔም የተከማቸ ጥበብ እንደመሆኑ ከትናንት ወደዛሬ፣ ከዛሬም ወደነገ ይፈስሳል፡፡ እናም በአባቶች ጀግንነት እንደምንኮራው ሁሉ በጥፋቶቻቸውም ሳናፍር የእነርሱን ጥፋት ላለመድገም መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
አያይዘውም፤ ፓርኩም ታሪክን አንድ አድርጎ ማቆየትና ለትውልድ ማሸጋገርን የሚያስተምር፤ የቆሸሸና ማገልገል የማይችል የሚመስል ጥቅም እንደሚሰጥ የሚያሳይ፤ ቤተ መንግሥትም ተጋድለው የሚገቡበት ሳይሆን እንደማንኛውም አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም መሆኑን ማሳያ ነው፡፡
በመሆኑም ለተተኪ ትውልድ የሚተርፈውን ነገር አሸንፎ የተሻለ ሥራ ማሸጋገር፤ የኢትዮጵያ ብልጽግና የሚጀምረው ዛሬ መሆኑን አምኖ መስራት ይገባል፡፡ ነገር ግን የተሰፋ የሚተረተርበት አጋጣሚ የበዛ፣ ፈተናውም የከበደ ቢሆንም፤ የተጀመረ ተጨርሶ ሪቫን ይቆረጣል እንጂ ተስፋ የሚቆረጥ አይሆንም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 30/2012
ወንድወሰን ሽመልስ