ከመቶ ዓመት በፊት፤ እንዲያውም ብዙ ሳንርቅ ከሃያ ዓመታት በፊት ያለ መሬትና አርሶ አደሮች ግብርናን ማካሄድ ይቻላል ብሎ ማሰብ ህልም ነበር። በጃፓን ግን ይህ እውን ሆኗል። ጃፓናዊው ተመራማሪ ዩቺ ሞሪ ፍራፍሬዎችንና አትክልት ሲያበቅል መሬትም ሆነ አፈር ለሱ አስፈላጊ አልሆኑም።
በአማራጩ የጃፓን ሳይንቲስቶች የሰውን ልጅ ኩላሊት ለማከም የተሰራውን በግልፅ የሚያሳይና ፈሳሽም ሆነ አየር ማሳለፍ የሚችል “ፖሊመር ፊልም” የተባለውን ፕላስቲክ መሳይ ቁስ ለግብርና ሥራ መጠቀም ከጀማመሩ ሰነባብተዋል።
ዘሩ በ“ፖሊመር ፊልሙ” ላይ የሚበቅል ሲሆን፤ ፈሳሽም ሆነ ንጥረ ነገሮችን ለማጠራቀም ይረዳል። ‘ፖሊመር ፊልሙም’ ዕፅዋቱን የትኛውም አካባቢ እንዲበቅሉ ከማስቻሉ በተጨማሪ ከባህላዊው ግብርና 90 በመቶ ያነሰ ውሃ በመጠቀምና ምንም አይነት ፀረ ተባይ መድሃኒቶች ሳያስፈልጉ ምርታማ የሚያደርግ ነው። ምክንያቱም ፖሊመሩ ቫይረስንም ሆነ ባክቴሪያን ማገድ ስለሚያስችል ነው።
ይህ ዘዴ ጃፓን በጥቂት የሰው ኃይልና ያለምንም መሬት የግብርና አብዮት የፈጠረችበት አንዱ መንገድ ሲሆን፤ በኩላሊት እጥበት (ዲያሊሲስ) ወቅት ደም ለማጣራት የሚጠቅመውን “ፖሊመር ፊልሙ” የተባለውን ፕላስቲክ በመጠቀም አትክልትና ፍራፍሬ ማምረት መቻሉን ጃፓናዊው ሳይንቲትስ ዩይቺ ሞሪ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ሜቢኦል የተባለው የጃፓኑ ኩባንያ ይሄንን የፈጠራ ሥራ በ120 አገራት በፈጠራ ሥራ ባለቤትነት መብት ማስመዝገብ የቻለ መሆኑን ቢቢሲ በድረገፁ ያስነበበ ሲሆን፤ በጃፓን እየተካሄደ ባለው የግብርና አብዮት የእርሻ መሬቶች ወደ ቴክኖሎጂ ማዕከላት እየተቀየሩ ነው። ለዚህም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስና የመጠቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተግባራዊ በመሆን ላይ ናቸው ተብሏል።
በዚህ ዓመት የተባበሩት መንግሥታት የውሃ ሀብትንና ልማትን በተመለከተ ባወጣው ሪፖርቱ፤ የአፈር መሸርሸርና የውሃ ሀብት መመናመን በዚህ ከቀጠለ እ.ኤ.አ በ2050 40 በመቶ የሚሆነው የአዝርዕት ምርቶችና 45 በመቶ የሚሆነው የዓለም ምርት ቀውስ ውስጥ እንደሚወድቅ ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ ይህ የአበቃቀል ዘዴ ነገ ላይ ዓለም ለሚገጥመው የምርት እጥረት አንድ መፍትሄ ይሆናል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።
በተለይም ይህ ዘዴ በጎርጎሮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2011 በጃፓን የተፈጠረውን የኒውክለር ቀውስ ተከትሎ ጨረር የእርሻ ማሰዎች ላይ ያስከተለውን ብክለት ለማስተካከልም ይረዳል ተብሎ የታመነበት ሲሆን፤ ዘዴውም በጃፓን ከ150 በላይ ማሳዎች ላይ ተግባራዊ ከመደረጉ ባሻገር የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ አገራትም የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ሆነዋል።
እ.ኤ.አ በ2050 የዓለም ህዝብ ቁጥር ከ7.7 ቢሊዮን ወደ 9.8 ቢሊዮን ያድጋል ተብሎ እየተገመተ ባለበት ወቅት፤ የተለያዩ ኩባንያዎች ሊመጣ የሚችለውን የምግብ ፍላጎት ለሟሟላት የተለያዩ የቢዝነስ አማራጮችን በመፈተሽ ላይ ናቸው። በመሆኑም፤ የጃፓን መንግሥት በአሁኑ ሰዓት በግብርና ሥራዎች ከመዝራት እስከ ማረም ባለው ሂደት ላይ ሊያግዙ የሚችሉ 20 አይነት ሮቦቶች እንዲመረቱ ከፍተኛ እርዳታ እያደረገ ይገኛል።
በዚህም ከሆካይዶ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመጣመር ያንመር የተባለው የሮቦት አምራች ድርጅት አንድ ሮቦት አምርቶ በእርሻ ማሳ ላይ እየተሞከረ ሲሆን፤ “ዳክየ” (ደክ) የሚል ስያሜ የተሰጠውና ሳጥን የሚመስለው ይህ ሮቦት በሩዝ እርሻዎች ውስጥ በመመላለስ በውሃው ውስጥ ያለውን የኦክስጅን መጠን በመጨመር፤ የፀረ ተባይ መድሃኒቶችን መጠን መቀነስ አስችሏል ተብሏል።
በመሆኑም በጃፓን አርሶ አደሮች ለእርሻ ሥራ ፊታቸውን ወደተለያዩ ማሽኖችና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ያዞሩ ሲሆን፤ ሰው አልባ አውሮፕላኖችም (ድሮኖች) በከፍተኛ ሁኔታም ጥቅም ላይ እየዋሉ ናቸው። ሰው አልባ አውሮፕላኖቹም አንድ ሰው ሙሉ ቀን የሚፈጅበትን ሥራ በግማሽ ሰዓት ውስጥ ማጠናቀቅ መቻላቸው ተነግሯል።
ሌላኛው የጃፓንን የግብርና ሥራ የሚገድበው የአገሪቷ መልክዓ ምድር አቀማመጥ ሲሆን፤ በዚህ ምክንያት ምርት ማምረት የሚቻለው 40 በመቶ በሚሆነው የአገሪቷ የእርሻ ቦታ ላይ ብቻ ነው። ምክንያቱም 85 በመቶ የሚሆነው የአገሪቷ የእርሻ ቦታ ተራራማ ሲሆን፤ ቀሪው ደግሞ የሚያበቅለው ሩዝ ብቻ ነው።
ስለዚህ፤ ምንም እንኳን ሩዝ ለዘመናት የጃፓናውያን ተወዳጅ ምግብ ሆኖ ቢቆይም፤ በአገሪቱ የአበላል ባህል በመቀየሩ እንደጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር በ1962 በአማካኝ በዓመት አንድ ሰው በጃፓን 118 ኪሎ ግራም ሩዝ ይመገብ የነበረ ሲሆን እ.ኤ.አ በ2006 ወደ 60 ኪሎ ግራም ቀንሷል። በዚህም ሩዝን አዘውትሮ መጠቀም በአገሪቱ እየቀነሰ በመምጣቱ የጃፓን መንግሥት የተለያዩ አዝርዕትን የሚያመርቱ አርሶ አደሮች እያበረታታ ይገኛል።
በዚህም ጃፓናውያን የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን በመጠቀም ከመሬት ይልቅ ውሃ ውስጥ የሚያድጉ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን ለማምረት የቻሉ ሲሆን፤ ይህ በውሃ ላይ የማምረት ቴክኖሎጂም የአርቲፊሻል ብርሃን፣ የእርጥበት መጠን፣ ካርቦንዳይኦክሳድና የሙቀት መጠንን ይቆጣጠራል።
አርቲፊሻል ብርሃን ዕጽዋት በከፍተኛ ፍጥነት እንዲያድጉ የሚረዳ ሲሆን፤ በበሽታ የመጠቃት ችግራቸውንም ሙሉ በሙሉ ያጠፋዋል። ይህ ዘዴም ምርታማነትን በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረ ሲሆን፤ በትይዩ በጃፓን አትክልት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ቁጥርም በሦስት እጥፍ አድጓል። በውሃ ውስጥ የሚመረተው (ሃይድሮኒክስ) ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ቢዝነስ የያዘ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ በ2023፤ ስድስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ይደርሳልም ተብሏል።
በአጠቃላይ፤ ጃፓን ከራሷ አልፋ የአፍሪካ አገራት የሩዝ ምርታቸውን በማሳደግ እ.ኤ.አ በ2030 50 ሚሊዮን ቶን እንዲያመርቱ ለማስቻል ፕሮጀክቶችን ቀርፃ እየሠራች ትገኛለች። በአንዳንድ ቦታዎችም፤ ለአብነት በሴኔጋል በግብርና ላይ ለተሰማሩ ሰዎች ስልጠና ከመስጠት በተጨማሪ በመስኖ ሥራ ላይም የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ድጋፍ እያደረገች ነው። ይህንንም ተከትሎ በሴኔጋል በሄክታር አራት ቶን ይመረት የነበረውን የሩዝ ምርት ወደ ሰባት ቶን በማሳደግ የአምራቾቹም ገቢ በ20 በመቶ እንዲጨምር ሆኗል ተብሏል።
በተጨማሪም፤ ጃፓን በቪየትናም፤ በማይናማር፤ እንዲሁም በብራዚል ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን ቀርፃ እየሠራች ሲሆን፤ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የጃፓን አላማ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የህዝቧን የምግብ ፍጆታ ከማረጋገጥ ባሻገር ነገ በዓለም ላይ ሊከሰት ለሚችል የምግብ እጥረት ከወዲሁ መላውን እንካችሁ እያለች ትገኛለች።
አዲስ ዘመን መስከረም 30/2012
ሶሎሞን በየነ