አዲስ አበባ፡- በዓለማችን በአዕምሮ ጤና መጓደል ምክንያት በየዓመቱ 8 መቶ ሺ የሚጠጉ ሰዎች ራሳቸውን እንደሚያጠፉ ተገለፀ።
የቅዱስ አማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤዳኦ ፈጆ ዓለም አቀፍ የአዕምሮ ጤና ቀን ትናንት በተከበረበት ወቅት ዓለም አቀፍ ጥናቶችን ጠቅሰው ባስተላለፉት መልዕክት በየዓመቱ በአዕምሮ ጤና መታወክ ምክንያት ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ስምንት መቶ ሺ ይደርሳሉ።
በዚህም ዓለም ለአዕምሮ ህመምተኞች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ዕለቱን ያከብራል ብለዋል።
በየዓመቱ ጥቅምት አስር ቀን የአዕምሮ ጤና ቀን እንደሚከበር የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ በዘንድሮው ዓመትም ‹‹ትኩረት ራስን በራስ ማጥፋትን ለመከላከል›› በሚል መልዕክት እየተከበረ እንዳለ ገልፀዋል። በዓለማችን ከ15 እስከ 29 ዓመት ዕድሜ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ህይወታቸውን የሚያጡት በአዕምሮ ጤና ጉድለት ምክንያት እንደሆነ ጥናቱን መሰረት አድርገው ተናግረዋል።
በአዕምሮ ጤንነት መጓደል ምክንያት በዓለም ላይ እራሳቸውን የማጥፋት ክዋኔ የሚያደርጉት 8 መቶ ሺህ ሰዎች ውስጥ 78 በመቶ የሚሆኑት በመካከለኛና በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ በሚገኙ አገራት የሚኖሩ ሰዎች እንደሆኑ ጥናቶቹን ጠቅሰው ገልፀዋል።
የአዕምሮ ችግር ተጠቂ የሆነውን ወጣት በመጉዳት በሀገር ልማት እና ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ጫና የሚያሳርፍ መሆኑም ተጠቅሷል። በአሁኑ ወቅት መነሻቸው ብዙ የሆኑ የአዕምሮ ህመሞች ሰዎችን ከመጉዳት ባለፈ ችግሩን የበለጠ እንዳወሳሰበው ተናግረዋል። በመሆኑም ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና የማህበረሰባችንን የአዕምሮ ጤንነት መጠበቅና መንከባከብ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 29/2012
ኢያሱ መሰለ