ራስ ተፈሪ መኮንን በንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ እጅ ዘውድ ጭነው ንጉስ ተፈሪ የተባሉት ከ91 ዓመት በፊት በዚህ ሳምንት መስከረም 27 ቀን 1921 ዓ.ም ነበር።
በ1909 ዓ.ም የልጅ ኢያሱን ከሥልጣን መውረድ ተከትሎ ዘውዲቱ ንግስተ ነገስት፣ ተፈሪ አልጋ ወራሽ እንዲሆኑ እንግዳ ውሳኔ ተወሰነ። ከዚያ በፊት በነበረው ልማድ ንጉስ አልያም ንግስት ዘውድ ሲጭኑ አልጋወራሽ ይሰየም የነበረው ዕድሜያቸው ለጋ ሲሆን ነው። በዘውዲቱና በተፈሪ መካከል የሆነው ግን የተገላቢጦሽ ነበር። ለተፈሪ እናት ሊሆኑ የሚችሉት ዘውዲቱ ለስሙ ንግስተ ነገስት ተብለው ልጃቸው ሊሆኑ የሚችሉት ተፈሪ በአልጋ ወራሽነት ሙሉ ሥልጣኑን ጠቀለሉ። ቀስ በቀስም ተፈሪ አልጋወራሽ ብቻ መሆናቸው ቀርቶ እንደ ሙሉ ባለሥልጣን መታየት ጀመሩ።
ይህ ሁኔታም አመጾችን አስነሳ። ከተነሱት አመጾች መካከል ተፈሪ አልጋ ወራሽ እንጂ እንደራሴ ስላልተባሉ ንግስተ ነገስት ዘውዲቱ በሕይወት እስካሉ የፖለቲካ ሥልጣን ለመጠቅለል ከመሞከር መታቀብ አለባቸው በሚል ሊጋባ በየነ የመሩት አመጽ ይጠቀሳል። ይህም አመጽ ተፈሪ ላይ እንደተነሱት ቀደምት አመጾች ከሽፎ ሊጋባ በየነ በአደባባይ ተገርፈው ወደ ሐረር በግዞት እንዲላኩ ተደርጎ ተቋጨ። ተፈሪም ሁነኛ ሰዎችን በዙሪያቸው አሰባስበው ለንግሥና የሚያደርጉትን የተጠና ግስጋሴ አጠናክረው ቀጠሉ።
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከተወለዱበት ጊዜ አንስቶ ምን ዓይነት ሁኔታ እንደነበረ፣ የልጅ ኢያሱን ጉዳይ፣ የንግሥት ዘውዲቱን መምጣትና ራስ ተፈሪ አልጋ ወራሽ የሆኑበትን መንገድ እንዲሁም በዘመኑ የነበረውን የአስተዳደር ሁኔታ የሚያስረዳውን «ተፈሪ መኮንን ረጅሙ የሥልጣን ጉዞ» የተሰኘ መጽሐፍ የጻፉት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጋዜጠኛና ዲፕሎማት የነበሩት አምባሳደር ዘውዴ ረታ፣ ራስ ተፈሪ የምኒልክ ሥልጣን በቀጥታ ወደ ልጅ ኢያሱ እንዳይተላለፍ ለማድረግና ተቀናቃኞቻቸውን ለመገዳደር ጸሐፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስንና አቶ መኮንን ሀብተ ወልድን አስጠግተው እንደሰሩና እነዚህ ሁለት ሰዎች ራስ ተፈሪን እጃቸውን ይዘው እንደመሯቸው ይገልጻሉ።
ተፈሪ ራሳቸው ካደረጉት ስልታዊ አካሄድ በተጨማሪ ጉዟቸውን አልጋ በአልጋ ያደረጉ ወሳኝ ታሪካዊ ክስተቶች ነበሩ። በ1910 ከጦር ሚኒስትሩ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ በስተቀር የሚኒስ ትሮቹ በጅምላ ከሥልጣን መውረድ አገሪቱን በፈለገው አዲስ ጎዳና ለመምራት አመቺ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። በኋላም በ1916 ዓ.ም ኢትዮጵያ የዓለም መንግሥታት ማህበር አባል ሆና ወደ አውሮፓ ጉዞ አድርገው ዓለምአቀፋዊ ዝናን አግኝተው የአውሮፓን ሥልጣኔ በኢትዮጵያ ለመትከል በነበራቸው መሻት ጸንተው እንዲመለሱ አድርጓል። ይሁን እንጂ የንግስቲቱና የአጼ ምኒልክ ታማኞች ይቃወሟቸው ስለነበር የኢትዮጵያ ንጉስ ለመሆን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጨርሶ ከእንቅፋት የጸዳ አልነበረም።
ዕውቁ የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እንደጻፉት፣ ተፈሪ የመጀ መሪያው ግልጽ ተቃውሞ የገጠማቸው በወቅቱ የሲዳሞ ገዥ ከነበሩት ደጃች ባልቻ ሳፎ ነበር። ተፈሪ ቀስ በቀስ የንግስት ዘውዲቱን ሥልጣን በመገዝገዛቸው ባልቻ ተቆጥተው ነበር። በ1920 ዓ.ም ተፈሪ ታማኝነታቸውን ለመፈተን ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ጥሪ ቢያደርጉላቸውም በሰበብ አስባብ ሳይመጡ ቀርተው ንግስት ዘውዲቱ በላከችላቸው የማግባቢያ ቃል ጦራቸውን እየመሩ ወደ አዲስ አበባ መጡ። ጦራቸውን ከአዲስ አበባ በስተደቡብ በሚገኘው ፉሪ አስፍረው እርሳቸው ጥቂት ጭፍሮችን አስከትለው ወደ ቤተ መንግሥት አመሩ።
ባልቻ በተፈሪ ላይ ያላቸውን ቅራኔና ጥላቻ በግልጽ ሲያሳዩ፤ ተፈሪ ግን ጮማውን ጠጁን እያቀረቡ እኚህን የጥንት ጦረኛ የሚያርዱበትን ቢለዋ ይስሉ ነበር። ባልቻ ከታማኝ ጭፍሮቻቸው ጋር በቤተ መንግሥቱ በነበሩበት ጊዜ ተፈሪ ደጃች ብሩ ወልደ ገብርኤልን የሲዳሞ ገዥ አድርገው ሾመው ፉሪ አካባቢ ለሰፈረው የባልቻ ጦር እንዲለፈፍ አደረጉ። ይህን ሲሰማ የባልቻ ጦር አዲሱን ገዢ ተከትሎ ተጓዘ። ወዲያውም ባልቻ ያለሠራዊት ስለቀሩ እጅ ከመስጠት ውጪ ምርጫ አጡ።
ቀጥሎ የተፈሪን ሥልጣን ይፈታተኑ የነበሩት የቤተመንግሥቱ ዘበኞች አለቃ አባ ውቃው ብሩ ነበሩ። በምኒልክ ቤተ መንግሥት ያደጉት አባ ውቃው ዋና መጠሪያ የሆነውን ይህን አስፈሪ ስም ያገኙት ከልጅነታቸው አንስቶ በዕድሜ የሚበልጧቸውን በትግል እየወቁ በንጉሡ ዘንድ ታዋቂነትን ስላገኙ ነው ይባላል። ለምኒልክ ያላቸው ፍቅርና አክብሮት ከንጉሠ ነገስቱ ሞት በኋላም ቀጥሏል።
በተፈሪ ላይ የተነሱት ንግስት ዘውዲቱን ደግፈው ብቻ ሳይሆን ለምኒልክ አጽምና መንፈስ ያላቸው አክብሮትም ጭምር ገፋፍቷቸው ነው። አባ ውቃው የምኒልክ አጽም ካረፈበት የምኒልክ መታሰቢያ ቤት ከሚባለው ስፍራ ከተከታዮቻቸው ጋር መሽገው አንድም ሰው አላስጠጋ አሉ። በዚህ ጊዜ ተፈሪ ለመተኮስ ሳይሆን ለማስፈራራት በሚል በአገሪቱ ታሪከ የመጀመሪያ የሆነውን ታንክ የምኒልክ መታሰቢያ ቤት ፊት ለፊት ጠመዱ። አባ ውቃው ለግልግል የተላኩ ሽማግሌዎችን በሙሉ እየሰደቡና እያሳፈሩ መለሱ። በኋላ ነገሩ የተፈታው ተፈሪ ዘውዲቱ ዘንድ ሄደው አንቺን ስለሚሰማሽ ታማኝ አሽከርሽ ላይ መልዕክተኛ ላኪበት ካሉ በኋላ ነበር።
አባ ውቃው በእርግጥም መልዕክተኛውን የላኩባቸው ንግስቲቱ መሆናቸውን ስለተጠራጠሩ ለዚሁ ሲባል ወደ መታሰቢያው ቤት የስልክ መስመር ተዘርግቶ ንግስቲቱ ምንም ስጋት የለብህምና እጅህን ስጥ ስላሏቸው ወትሮም ለእርስዎ ብዬ ነው ብለው እጃቸውን ሰጡ። ተፈሪም ወዲያው ለፍርድ አቅርበዋቸው የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ወደ ዕድሜ ልክ እስራት ተቀየረላቸው።
በአባ ውቃው መያዝ የተደፋፈሩት የተፈሪ ደጋፊዎች የከተማው ከንቲባና የተፈሪ ቡድን አቀነባባሪ በነበሩት ነሲቡ ዛማኑኤል እየተመሩ ተፈሪ ንጉስ እንዲባሉ በይፋ ጥያቄ አቀረቡ። የተዋከቡት ንግስት ዘውዲቱም ለተፈሪ የንጉስነት ማዕረግ ሰጥተዋቸው መስከረም 27 ቀን 1921 ዓ.ም የውጭ አገራት ልዑካን በተገኙበት ንጉስ ተባሉ። ተፈሪ ንጉስ የተባሉት እንደልማዱ በአንድ ክፍለ አገር ላይ ሳይሆን በደፈናው በመሆኑ የአገሪቱ ዋና ባለሥልጣን ለመሆናቸው ማረጋገጫ ሆነ።
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2012
የትናት ፈሩ