ጸሐፌ ታሪክ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ እንደ ጻፉትና በደጀን ተወላጆች በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው በአሁኑ የአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ውስጥ የሚገኘው የደጀን ሕዝብ የጥንት እናቱ ዮጊት የተባለች ሴት ወይዘሮ ናት፡፡ በአንዳንዶች አባባል አመጣጧ ከሰሜን ሸዋ መንዝ ከተባለው ሀገር ነው ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ከሰላሌ ኵዩ ውጫሌ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ ቃላዊ አተራረክ ሁሉም ከራሱ ግንዛቤ በመነሣት ጨምሮም፤ ቀንሶም ስለሚያወራ ስምምነት የለም፡፡ ቢሆንም የሥነ ቃሉ ታካዊ ፋይዳ በአጥኚዎች የበለጠ መመርምር ያለበት ሆኖ በሥነ ቃሉ የሚነገሩ ጭብጦች ግን ለሀገራችን ሕዝብ መዋሐድና የእርስ በርስ መስተጋብር ማሳያ ሊሆን ስለሚችል እንደሚከተለው ተተርኳል፡፡
በጥንት ዘመን ከጎሐ ጽዮን እስከ ደጌን (የጥንት አጠራሩ ነው፤ ጌ ወደ ጀ ሳትለወጥ) ድረስ ባለው ሀገር የዓባይ ሸለቆና ወንዝም፤ ቆላም፤ ደጋም አልነበረም፡፡ ይልቁንም የዛሬው ሸለቆ ለጥ ያለ ሜዳና የሰው ቁጥሩም አነስተኛ ነበር ይባላል፡፡
የደጀን የሀገር ሽማግሌዎች እንደሚያወሱት ዮጊት አስቀድማ ትኖርበት በነበረው መንዝ ውስጥ ትንቢት ተነግሯታል፡፡ ትንቢቱም ዐውራ እየነዳሽ (እያስነዳሽ) ወደ ሰሜን ሒጂ፤ ዐውራሽ ወይም ወይፈንሽ ከደረሰበት ቦታ ላይ በቀንዱ የመሬት ዐፈር ሲዝቅ (ሲወጋ) ምንጭ ይፈነዳል፡፡ ውሃ ከፈለቀበት ቦታ ላይ ደግሞ የዶግ እንጨት (የራምኖን ማገዶ )አንድደሽ ፍሙ ከአደረ የመኖሪያ ሰፈርሽን እዚያው መስርቺ፤ ባልም በዚው ቦታ ታገቢያለሽ፤ ርስት ትካፈያለሽ ተብላለች፡፡
ዮጊት እንደተነገረችው መንዝ ውስጥ የወለደቻቸውን ዐራቱን ወንዶች ልጆች ማለት ዥሬን፣ ገልገሌን፣ ይብዛን እና ዝብጋሻን አስከትላ፤ በብዙ ሠራዊት ታጅባ (አንድ ሺህ ) ከብት እያስነዳች ስትሔድ ውላ ሲመሽ ውጫሌ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ታድራለች፡፡ ከውጫሌ በጧት ተነስታም ግንደ በረት በአንዳንዶች አባባል ዋሻ ሚካኤል ትደርሳለች፡፡ ዋሻ ሚካኤል ከጎሐ ጽዮን ከተማ ጥቂት ወረድ ብሎ ወይም ከፍልቅልቅ የገጠር ከተማ ከፍ ብሎ ጣሊያን ከሠራው ድልድይ አካባቢ የሚገኝና በ400 ዓመተ ምሕረት በእነአብርሐና አጽብሓ ነገሥት የተመሠረተ ታሪካዊ ገዳም ነው፡፡
እንደተባለውም ዐውራዋ መሬቱን በቀንዱ ቢወጋው ትንሽ ውሃ ፍልቅ ብሎ ይቀራል፡፡ ያም የዋሻ ሚካኤል ጸበል ያለበት ቦታ ነው፡፡ ወዲያው ንግርቱ ይኸ አይደለም፤ ውሃውም አነሰ ብላ ምንጩ ስላልበረታ አውራዋንና ሌላውን የከብት መንጋዋን እያስነዳች ወደፊት ስትጓዝ በፊት እነጥር ወይም እንደጂር፤ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ኩራር ወይም እሞግ ተብሎ ከሚጠራው ውሃ ገብ ቦታ ላይ ትደርሳለች፡፡ እዚያም ዐውራዋ በቀንዱ መሬቱን ቢወጋው የበረታ ውሃ ፈለቀ፡፡ ከደስታ ብዛት የተነሣም የዶግ እሳት አንድዳ፤ በሠራዊቷ ታጅባና ድንኳኗን አስጥላ እነጥር ከተባለው ቦታ ታድራለች፡፡ ከአዳሯ ቀን ቀጥሎ የዮጊት ታሪክ የሚያያዘው በአንዳንዶች አባባል ድራርድ ከተባለ የአካባቢው ባላባት ጋር በሌሎች አገላለጽ ደግሞ ድራር ከተባለው ከትግሬ መነኩሴ ጋር ነው፡፡
ድራር በትግርኛ ራት ማለት ሲሆን ይህ መነኩሴ (ድራር)መንኖ ጫካ ውስጥ ሲኖር በአካባቢው አዲስ ነገር መከሰቱን ሰምቶ በማብሰልሰል ላይ እንዳለ በድንገት የዮጊትን የቤት አሽከር ያገኛትና ‹‹አንቺየ እሞግ ላይ ድንኳን የተከለው ማን ነው?›› ይላታል፡፡ እርሷም ‹‹ሴት ናት›› ትለዋለች፡፡ ‹‹እንዴት ሴት ትሆናለች? ብዙ ሠራዊት መጣኮነው የሚባለው›› ይላታል፡፡ ‹‹አዎ ሠራዊቱን እየመራች ከሸዋ በኩል የመጣቺው ሴት ናት›› ትለዋለች። ‹‹ይህ በምን ይታወቃል?›› ይላታል፡፡
‹‹እግሯን ስትታጠብ መጀመሪያ የግራ እግሯን ስለምታጥበው በዚህ ትታወቃለች፤ ለማረጋገጥ ከፈለጉ አብረን ሄደን ለማየት ይችላሉ›› ብላ መነኩሴውን ድራርን ይዛ ወደ ድንኳኑ ታስገባዋለች፡፡ ዮጊትም እግሯን ስትታጠብ በግራ እግሯ ስለጀመረች በዚህ የዚያ ሁሉ ሠራዊት አዛዥ ሴት መሆኗን ድራር አወቀ፡ ፡ እዚያም ቆቡን ደፍቶ፤ መቋሚያውን ተደግፎና በቀይ ጉንጩ ላይ የተንዠረገገ ጢሙን እያሻሸ ቆሞ ሁኔታዋን ሲመለከት ዮጊት የደም ግባቱን አይታ ስለወደደችው አብሯት እንዲያድር ታደርጋለች፡፡ በዚህ ግንኙነት ኩራር ይፀነሣል፡፡
በተለየው ትርክት መሠረት ደግሞ የአካባቢው ኗሪ የነበረውና ድራርድ ተብሎ የሚጠራው ሰው ዮጊትንና ሠራዊቷን ፈርቶ ከትልቅ ገደል ሥር ከሚገኘው የዐርባዕቱ እንስሳ ቤተ ክርስቲያን በላይ ከሚገኝ ዋሻ ውስጥ ገብቶ ይደበቃል፡፡ እዚያም ሆኖ ሁኔታውን ሲከታተል ስለ ራበውና ስለጠማው እሳት ለኩሶ ምግቡን በዋሻ ውስጥ ሲያበስል ጭሱ ትን ብሎ ሲጨስ ይታያል። በወቅቱ ልክ እንደ ንግሥት ትታይ የነበረችው ዮጊት እሞግ ከተባለና ለጥምቀት በዓል ድንኳን ከሚተከልበት ቦታ ላይ ማለት ዐውራዋ በቀንዱ መሬት ወግቶ ከአፈለቀው ውሃ ዳር ሆና ድራርድ የሚያጨሰውን ጭስ በንጋት ጮራ ተመልክታ ምንድን ነው? በማለት ስትጠይቅ የአካባቢው ባላባት ድራርድ መሆኑን ትረዳለች፡፡
ወዲያው ዮጊት ወደ ሰዎቿ አስተዋለችና “ሒዱና ድራርድን ማርካችሁ አምጡልኝ፤ ያገኛችሁትንም ወንድም ሆነ ሴት ይዛችሁ ኑ፤ “ ብላ ታዝዛቸዋለች፡፡ ሰዎቿ ወደ ዋሻው ሲሔዱ መውጫ መሰላል ያጣሉ። ዘዴውም ይጠፋባቸዋል፡፡ እንጨት ቆርጠው፤ መሰላል ሠርተው ወደ ዋሻው ሲገቡ ድራርድን ያገኙታል፡፡ በአገኙት ጊዜ ልብሱ ያደፈ፤ ሰውነቱ የቆሸሸና ማንነቱ የማይታወቅ ሰው መሆኑን ይረዳሉ፡፡ እንደ ወርቅ ወደምታበራው ወደ ዮጊት ሲወስዱት በክብር ተቀብላ እርሷ ከአለችበት ድንኳን ውስጥ ታስገባዋለች፡፡ ሰውነቱንም በእንዶድና በዋሽት ቅጠል እምቡራቡጭ (ልዝብ ጠጠር፤ ደንጋይ) እስኪመስል ድረስ ታሳጥበዋለች። ከዚያም “ድራርድ ሆይ! ዛሬ የእኔ እንግዳና ባልም ነህ ስትለው እንደመደንገጥም፤ እንደመደሰትም፤ እያለ “እሽ ምን ችግር አለ” ይላታል፡፡ አብረውም ያድራሉ፡፡ በዚህም ግንኙነት ፀንሣ ኖሮ ኩራር የተባለው ልጇን ወልዳለች፡፡
ስለዚህ ትግሬው ድራር (ድ) የኩራር አባት ነው ማለት ነው፡፡ ዮጊት ጎጃም ደርሳ ከወለደችው ከኩራር በስተቀር ሌሎች ማለት ዥሬ፤ ገልገሌ፤ ይብዛ፤ ዝብጋሻ ገቦዎች ናቸው ይባላል፡፡ ገቦ ዋና መሠረት ያልሆነ ቅጥያ ማለት ነው፡፡ ዥሬ፤ ገልገሌ፤ ይብዛ፤ ዝብጋሻ የሚለው የስም አጠራር በተለይ ከኦሮምኛ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ለምሳሌ ጅሬ “ጂራ” አለን ከሚለው፤ “ገልገሌ” ገልገለ ማታ ከሚለው፤ የወጣ ነው፡፡ ገልገሌ በኦሮምኛ የሴት ስምም ነው፡፡ ትርጉሙ የማታነሽ እንደ ማለት ነው፡፡ ወይም ‹‹መሸብን እንደር›› ማለት ይሆናል፡፡
ይብዛ የሚለውም ምናልባት ኢብሳ (ኤባ) ከሚለው ቃል የወጣ ሊሆን ይችላል” በማለት አንዳንድ ሰዎች ግምታቸውን ይሰነዝራሉ፡፡ ዮጊት ከድራርድ ኩራርን ከወለደች በኋላ የዘንዶ ግልገል ትወልዳለች፡፡ ላም እሳት ወልዳ እንዳትልሰው ፈጃት፤ እንዳትተወው ቆጫት እንደሚባለው ዘንዶውን ግልገል እንዳትገድለው ልጇ ሆነባት፤ በሰው ፊት እንዳታሳድገው ይሉኝታ ያዛትና በአገልግል ውስጥ አስቀምጣ የተወቀጠ ኑግ፤ ተልባና ማር እየመገበች ታሳድገው ጀመር፡፡
ኩራር በዚያው አካባቢ ስለተወለደ ብዙ መሬት ሲበዛበት ከሸዋ የመጡት ወንድሞቹ ግን ገቦዎች ስለሆኑና ከዘር የሚወረስ ብዙ ርስት ጉልት ስላላገኙ መሬት “አካፍለን፤ አለበለዚያ እንገድልሃለን “ ይሉታል፡፡ ኩራርም አይሆንም ለእኔና ለልጅ ልጆቼ ያንሰናል ብሎ ይከለክላቸዋል፡፡ ወንድሞቹም ዝም ብለው ከቆዩ በኋላ ከእለታት በአንዱ “ ኩራር ወንድማችን ና! ወደ መንገድ እንሂድ” ይሉታል፡፡
እርሱም “እሺ ወንድሞቼ ?”ብሎ ተከትሏቸው ሲጓዝ ሊገድሉት እንደተማከሩበት ተጠራጠረና ሻፎ ዋርካ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ሲደርስ ‹‹ከዚህ በኋላ አልሄድም፤ ከፈለጋችሁ እዚሁ ከቆምኩበት ቦታ ላይ በካራ ሼፍ አርጉና ግደሉኝ›› ይላቸዋል፡፡ በአካባቢው አነጋገር ‹‹ሼፍ አርጉኝ›› ማለት በካራ እረዱኝ እንደ ማለት ነው፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሼፍ የሚለው ቃል ወደ ሻፎ ተለውጦ ሻፎ ዋርካ ተብሎ ይጠራል፡፡ ሕዝብ የሚሰባሰብበት የሻፎ ዋርካ እንደ ሰው ልጅ ዘር እየተካ እስከ ዛሬ ድረስ ፈጠገቱ ( ምልክቱ) ይገኛል፡፡ በዚህ ዓይነት ኩራር ‹‹ሼፍ አርጋችሁ ግደሉኝ›› ብሎ ከቆመበት ከሻፎ ዋርካ በላይ ርስት ጉልት ሳይኖረው ቀርቷል። እስከ ዛሬ ድረስ የኩራር መሬት ምልክት ተደርጎ የሚታየው የሻፎ ዋርካ ነው፡፡
ወንድሞቹ ግን (ከሸዋ የመጡት ዥሬ፤ገልገሌ፤ ይብዛ፤ዝብጋሻ) ከሻፎ ዋርካ አልፈው በቀኝም በግራም በአለው አገር ላይ ርስት ጉልት አድርገው ሰፈሩና አካባቢውን አቀኑት፡፡ በዚህ ዓይነት ታላቁ የዮጊት ልጅ ዥሬ ከሻፎ ዋርካ በስተግራና በስተምዕራብ በኩል ቄጠማን ከተባለው ቀበሌ አልፎ በደጀን ደቡባዊ ምዕራብ ሄዶ ተቀመጠ። የተከለው ታቦትም ዥሬ ሚካኤል ይባላል፡፡ ቦታው ቆላ ነው፡፡ ገልገሌ የተባለው ልጅ በደጀን አካባቢ በኋላ ላይ በወለደው ልጁ በሚጠራው በተክለየሱስ አገር ሰፍሮና ከደጀን አልፎ እስከ ጢቅ ድረስ የሚዘልቀውንና ወይ እናት ተብሎ የሚታወቀውን ሰፊ ሜዳ ይዞ ርስት ተክሏል። ገልገሌ በፊት የሰው ስም፤ ዛሬ ደግሞ የቦታ መጠሪያ ሆኗል፡፡ ይብዛም እንዲሁ ወንድሙ ዥሬ ከሰፈረበት አልፎ በመስፈር ይብዛ ሚካኤልን ተክሏል፡፡ እናም በፊት የሰው ስም የነበረው ይብዛ ዛሬ የቦታ መጠሪያ ስም ሆኗል፡፡
ዐራተኛው የዮጊት ልጅ ዝብ ጋሻ እንዲሁ ከደጀን (ውሻ ጥርስ) ምሥራቃዊውን ቆላማ ክፍል ይዞ እስከ ደጋማው አካባቢ ሰንጠይት አቦ፤ ቦረቦር ሥላሴና ጢቅ ጊዮርጊስ ድረስ ያለውን ስፍራ ያካልላል፡፡ ዝብጋሻ ዘርአ ጽዮንና ዐርብጋት የተባሉ ሁለት ወንድ ልጆችን ይወልዳል፡፡ የዝብጋሻ ልጆች ዘርአ ጽዮንና ዐርብጋት ተራብተውና እንደ ርስት ጉልት አርገው ከ800 ዓመት በላይ የሆነውን አራውጭኝ ጊዮርጊስን፤ ሰንጠይት አቦን፤ እናምቡር ሚካኤልን፣ ሸንቻ ማርያምን፤ ቦረቦር ሥላሴን ተክለው ይኖራሉ፡፡
በመሆኑም ከዘንዶው ግልገል በስተቀር አምስቱ የደጀን አባቶች የሚባሉት የዮጊት ልጆችዥሬ፤ገልገሌ፤ይብዛ፤ዝብጋሻ፤ ኩራር ሲሆኑ አምስቱ የደጀን አባቶች (ልጆች) በመከራም ሆነ በደስታ ጊዜ ሲገናኙ በመጨረሻ ላይ የሚመርቀውና የሚያሳርገው የመጀመሪያው የዮጊት ልጅ ዥሬ ነው ፡፡ ዥሬም ምርቃቱን የሚጀምረው ‹‹ገልገሌ ተባረክ›› ብሎ ነው፡፡ ከአምስቱ የደጀን ባላባቶች ሌላ የገልገሌ ልጆች ከሆኑት ከተክለ ኢየሱስ (መርሕ ኢየሱስ)እና ከዮሐንስ ርስትና ጉልት የሚካፈለው ባያንም ትልቁ የደጀን አባት ተብሎ ይጠራል፡፡ ዥሬ ተሟጋች፤ ተከራካሪና የመከረው ምክርም የማይፈታ፤ ነገረኛ በመሆኑ፤ ይብዛም ኮኛ ( በተፈጥሮ የደንጋይ ንብርብር የበዛበት ቦታ) ስለሆነ “ከዥሬ መንጎኛ፤ ከይብዛ ኮኛ ይሰውረን›› ይባላል፡፡
እነዚህ አምስቱ የዮጊት ልጆችና የደጀን ሕዝብ አባቶች በያሉበት ትዳር መሥርተውና ሀብት አፍርተው በመኖር ላይ እያሉ ከጢቅ ጊዮርጊስ በላይ በአለው አገር ቁይንና ቢቸናን ያስተዳድር የነበረና ውድሚት እየተባለ የሚጠራ ኃይለኛ ሰው በጊዜው በደጀን ዙሪያ ታዋቂና ኃይለኛ ለነበረችው ለዮጊት መልእክት ይልክባታል፡፡ መልእክቱም “ ዮጊት ሆይ! የግዛት መሬት እንካፈል፤ አንቺም በፈረስ፤ እኔም በፈረስ ጋልበን የተገናኘንበትና የደረስንበት ቦታ ድንበራችን ይሆናል “ የሚል ነው፡፡ ዮጊትም ትስማማለች፡፡ ከውድሚት ጋር የያዘችው ቀነ ቀጠሮ እንደደረሰም ልጆቿን ሰብስባ “ አደራችሁን ልጆቼ ይህ የዘንዶ ግልገል ወንድማችሁ ነው፡፡ ከመንገድ እስክመለስ ድረስ እንዳይርበውና እንዳይጠማው ተንከባከቡት» ትላቸዋለች፡፡ ይህንን ለልጆቿ ተናግራ ስትኳኳል፤ ስታጌጥ ይረፍድባታል፡፡
ሰዎቿን ይዛና ከኩራር ተነሥታ ወደ ሰሜን 7 ኪሎ ሜትር ያህል ሳትራመድ ወይናት ሜዳ ጎንጂ ከተባለችው ትንሽየ ጉብታ ላይ ውድሚት ቆሞ ሲጠብቃት አስተዋለች፡፡
ውድሚት ከቁይ በላይ ከአለው ሀገር ከአጋምና ሌሊት ተነሥቶና ገስግሶ በፈረስ በመጋለብ 50 ኪሎ ሜትር ያህል ተጉዞ ደርሷል፡፡ ዮጊት በበቅሎ ላይ ሆና፣ አሽከሮቿን አስከትላ በወይናት ሜዳ ስትመጣ ውድሚት ያያታል፡፡ በመዘግየቷ ምክንያትም ተናድዶ ስለነበር አጠገቡ ስትደርስ ምራቁን ጢቅ ይልባታል፡፡
ያም አካባቢ ከዚያች ዕለት ጀምሮ «ጢቅ » ተብሎ ተጠራ፡፡ ዛሬ ጢቅ ጊዮርጊስ ታቦቱ ከመንዝ መጥቶ በታላቅ ደብርነቱ የሚጠራና የሚታወቅ ሀገር ሆኗል፡፡ «ወይናት» የተባለው ሜዳም ጥቅጥቅ ያለ የደራና የጎድር ሣር የበዛበት ለጥና ጭር ያለ ቦታ ነበር፡፡ አንድ መንገደኛ በጓዝ ሣሩ እየዋጠውና እግሩንም እየተበተበው ፤ አቅጣጫ እየጠፋው ተቸግሮ ፤ ተርቦ፤ ተጠምቶና «ወይ እናቴ» ብሎ ሞተ ይባላል፡፡ ወይ እናቴ ዛሬ እንዲህ ስቸገር፤ ስንገላታ ሲርበኝና ፤ሲጠማኝ በተገኘሽልኝ ማለቱ ነው፡፡ ከዚያ መንገደኛ ሞት በኋላ ያ ቦታ ሣሩ፤ ሰንበሌጡና ደራው ጠፍቶ፤ በውስጡ የነበረው የሚዳቋና የቡሆር መንጋ ተሰድዶ የእርሻ ቦታ ሆኗል፡፡
ውድሚትና ዮጊት በተገናኙበት ቦታ ላይ ቆመው ሲደራደሩም እግሬ የረገጠው፤ እጄ የጨበጠው ወሰን ድንበራችን ነው ብሎ የእርሱ ፈረሶች ተለቅቀው ሣር ሲግጡ እስከነበረበት ቦታ ድረስ ያለውን እንደ ድንበራቸው አድርገውና መሬት ተካፍለው ተለያዩ፡፡ ከዚያም ዮጊት ብዙ መሬት ባለማግኘቷ እያዘነችና ጡቷ እየፈሰሰ ወደ ቤቷ ስትመለስ በመንገድ ላይ ልቧ መሸበር ይጀምራል፡፡ ወደ አሽከሮቿ እየተመለከተች ‹‹እናንተየ ሆዴን ባር ባር አለው፤ ተጨነቅሁ፤ ጡቴም እየፈሰሰ ነው›› ትላቸዋለች፡፡ እነርሱም ‹‹አይዞሽ እናታችን ደክሞሽ ነው፤ በርቺ እያሉና በበቅሎ ላይ ሆና እየደጋገፉ ከመኖሪያ ቤቷ መር ኢየሱስ ያደርሷታል፡፡ ከበቅሎዋ ወርዳ ወደ ቤት ስትገባ በአገልግል ውስጥ ያስቀመጠችውን ልጇን (የዘንዶውን ግልገል) ብታይ ታጣዋለች፡፡ ‹‹እሪ›› ብላ ስትጮህ ተገድሎና በአጥር ላይ ተዘርግቶ እንደሚገኝ ይነገራታል፡፡
ይህንንም አይታ ትጮህና ‹‹ማን ነው ልጄን የገደለው?›› ትላለች፡፡ ይብዛ አስቀድሞ እንደፈለቀው፤ እንዳነቆረውና እንደመታው፤ ዝብጋሻም ወንድሙን ይብዛን አይቶና ራስ ራሱን ብሎ እንደጨረሰው ትረዳለች፡፡ በግድያው ላይ ትንሹ ልጅ ኩራር፤ ታላቁ ልጅ ዥሬና ገልገሌ አልነበሩበትም፡፡ ዮጊትም በከፍተኛ የኀዘን ስሜት ተውጣ ከመካከላችሁ ‹‹ተው የሚልና የሚገላግል አልነበረም?›› ብላ ትጠይቃለች፡፡ ገልገሌ መልስ ሲሰጣትም ‹‹እናታችን እስክትመለስ ድረስ አደራ ያለችንን ነገር አክብረን መቆየት ሲገባን ያደረጋችሁት ነገር አግባብ አይደለም ብየ ለመገላገል ብሞክርም ሳልችል ቀረሁ፡፡ ኋላ ትጸጸታላችሁ ብየ ለምኛቸው ነበር፡፡ ኩራርም አገልግሉን እንዳትነኩት ብሏቸው ነበር፡፡ ግን ሁለቱ ጀማሪና ጨራሽ ሆነው በጭካኔ ገደሉት›› ይላታል፡፡ ኩራርም አለመቻሉን ያስረዳታል፡፡ ታላቁ ልጅ ዥሬ ግን ዘንዶው ሲገደል እንዳልነበረና፤ በምክሩም እንደሌለበት ተገነዘበች፡፡
በሁለቱ ልጆቿ በይብዛና በዝብጋሻ ድርጊት የተበሳጨችው ዮጊት እንደሚከተለው በልጆቿ ላይ እርግማኑንና ምርቃቱን አወረደችባቸው። ዥሬ ነገሬን ሁሉ ትቀበላለህና ከጎበዝ በላይ ያውልህ፤ ገልገሌ ገላግሌና ለእናትህ አዛኝ ስለሆንክ ግዛ እንጂ አትገዛ፤ በነፋሻውና በለምለሙ ቦታ ሁሉ ያኑርህ፤ የዘራኸው፣ የገዛኸው፣ የወለድኸው ሁሉ የተባረከ ይሁን፡፡ ኩራር ነገርህ ሁሉ ማር ነውና ርስትህ ቦታህ ይስፋ፤ ዘርህ ይባረክ፤ በልምላሜና ፍራፍሬ ይባርክህ፤ እደግ፤ ተመንደግ፡፡ ይብዛ አትነስ አትብዛ ከፍም ዝቅም አትበል፤ እንዲያው በድርበቡ ያኑርህ ልጄን ትገድለው አንተ፡፡ ዝብ ጋሻ ዠግናና ተፈሪም ብትሆንም ደስ አይበልህ፤ ሁል ጊዜ እንዳዘንክ ኑር፤ ፈተና ይብዛብህ፤ እግርህ በእባብ ይነከስ ፤ ቂመኛ— ክፉ፤ ልጄን ትገድለው አንተ…?›› በማለት ስሜቷን ትገልጻለች፡፡
ከዚህ ጽሑፍ የምንረዳው ትልቁ ቁም ነገርም የኢትዮጵያ ሕዝብ ማለት ትግሬው፤ ኤርትሬው፤ ኩናማው፤ ኦሮሞው፤ አማራው ፤ሶማሌው፤ ጉራጌው፤ ወላይታው፤ ከፋው፤ ሲዳማው፤ አፋሩ፤ ጋምቤላው —በታሪክ፤ በደም፤ በሥጋ፤ በጋብቻ፤ በእምነት፤ በድንበር፤ በመከራና በደስታ፤ በፖለቲካ፤ በኢኮኖሚ፤ በማኅበራዊ ኑሮ በባህል- — እርስ በርሱ የተሣሠረና የተዋሐደ፤ በዘመን አመጣሽ የብሔርና የዘር ፖለቲካ ተለያይቶ የማይለያይ መሆኑን ነው፡፡ ክፉ ስንሠራ ሰውም፤ እግዜሩም እንዳይረግመን፤ እንዳይፈርድብን፤ እያስተዋልን መራመድ እንዳለብን የዮጊት ታሪክ ያመለክተናል፡፡
ዘመን መፅሔት መስከረም 2012
ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)