ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በ2007 ዓ.ም የግብር ገቢ ከአጠቃላይ አገራዊ ዓመታዊ ምርት 13 ነጥብ 4 በመቶ ነበር። በ2012 ደግሞ ወደ 17 ነጥብ 2 በመቶ ለማሳደግ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው። ነገር ግን የግብር ገቢ እያሽቆለቆለ በመምጣቱ በ2010 በጀት ዓመት ማጠናቀቂያ ላይ 10 ነጥብ 7 በመቶ ነው የሆነው፣ይህም ከሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (2007) መነሻ በ3 በመቶ በዕቅዱ ማጠቃለያ(2012) ሊደረስበት ከታሰበው ደግሞ በ6ነጥብ5 በመቶ ያነሰ ነው፡፡
በአገራችን የሚሰበሰበው የግብር መጠን ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት አማካይ ከሆነው 16 በመቶም ያነሰ ነው፡፡ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ያንሳል፡፡ ሞዛምቢክ 20 በመቶ፣ደቡብ አፍሪካ 27 በመቶ፣ኬንያ 16 በመቶ ከአጠቃላይ ዓመታዊ ሃገራዊ ምርታቸው ግብር ይሰበስባሉ፡፡ ስለዚህ የአገራችን የግብር ገቢ ማነስ አሳሳቢ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ይህንን ችግር መፍታት የሚያስችሉ ሥራዎችም መከናወን አለባቸው፡፡
የአገራችን ኢኮኖሚ በተከታታይ በፍጥነት እያደገ ነው፡፡ ኢኮኖሚው ከፍተኛ እየሆነ ባለበት ወቅት የግብር ገቢው መቀነሱ አነጋጋሪ ነው፡፡ ክስተቱ በእርግጥም ከነባራዊው ሁኔታ ጋር የሚቃረን ነው፡፡ ስለሆነም ከዕድገቱ በተመጣጣኝ የግብር ገቢውም አብሮ ማደግ አለበት፡፡
አገሪቱ የግብር ገቢ ለመሰብሰብ የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዳላት ግንዛቤ ተይዞ ባለፉት ዓመታት በግብር አስፈላጊነት ላይ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስ በስፋት መሰብሰብ ውስጥ ተገብቷል፤ለግብር አሰባሰቡ ይረዳሉ የተባሉ እንደ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ያሉ መሳሪያዎች ተግባራዊ ተደርገዋል፤በርካታ ነጋዴዎች ወደ ግብር መረብ ውስጥ እንዲገቡ እየተደረጉ ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ በሆነበት ሁኔታ የሚሰበሰበው ግብር ከሚጠበቀው በታች እየሆነ ከመጣ ህብረተሰቡ ግብር መክፈል ላይ ያለው ግንዛቤ እና የግብር አሰባሰቡ ሂደት ችግር አለበት ማለት ነው፡፡
ለግብር አሰባሰቡ አነስተኛ መሆን ከሚጠቀሱት ምክንያት መካከል የግብር ከፋዩ ግንዛቤ ማነስ፣ የሚተመነው ግብር ከፍተኛ መሆን፣ የግብር መሰረቱ አለመስፋት፣ የተደራጀ ሌብነትና ኮንትሮባንድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ስለሆነም እነዚህን ችግሮች መፍታት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል፡፡
የኮንትሮባንድ ንግድ ህጋዊ ነጋዴዎችን ከሥራ እያስወጣ፣ በኮንትሮባንድ ንግድ ሳቢያ ጎዳናዎች ሁሉ ሸቀጥ በሸቀጥ እየሆኑ ባለበት ሁኔታ ፣ግብር መሸሸግ ነውር መሆኑ ቀርቶ እንደ ብልጠት እየተቆጠረና ገቢ አሳውቆ ግብር በመክፈል በኩል ድብብቆሽ ጨዋታ እየተካሄደ ባለበት ሁኔታ ተገቢው ግብር ይሰበሰባል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ ስለሆነም የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ፣የአሰራር ስርዓትን በማዘመን፣ ህገ ወጥነትንና የተደራጀ ሌብነትን መከላከል የሚያስችሉ ስራዎች መስራት ያስፈልጋል፡፡የተጀመረው የግብር ንቅናቄ ዘመቻም ወቅታዊና ተገቢ ነው፡፡ ግብር መንግሥት ለሚያከናውናቸው ተግባራትና ለአገር ህልውና እስትንፋስ ነውና፡፡
ግብር በወቅቱ እንዲሰበሰብ ቅድሚያ ግንዛቤ መፍጠር ላይ በትኩረት መሰራት ይኖርበታል፡፡ይህም ሥራ ዘላቂ እንጂ ወቅታዊ ሊሆንም አይገባም፡፡ህጻናትን ከትምህርት ቤት ጀምሮ ከመቅረጽ አንስቶ ግብር ከፋዩ የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱ እንዲከፍል እስከ ማድረግ የሚደርስ ሊሆን ይገባል፡፡
ግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤትም ሠራተኞቹን በስነ ምግባር ማነጽ ይኖርበታል፡፡ከግብር ከፋዩ ጋር እየተመሳጠሩ የሀገር ገቢ እየተቀራመቱ የሚያስቀሩ ከሆነ ሀገር በእጅጉ ትጎዳለች፡፡ችግሩን ቢያውቁትም ግንዛቤ ላይ መስራቱ የሚያመጣው ጉዳት የለም፤ በኋላ ሊወሰድ ለሚችለው እርምጃም ይጠቅማል፡፡
የንግዱ ማህበረሰብ ለዚያውም ስለግብር በሚገባ እንደሚያውቅ የሚጠበቀው የህብረተሰብ ክፍል ግንዛቤ አያስፈልገውም፤ ‹‹አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማም›› ብሎ መተውም አይገባም፡፡ በዚህም በዚያም ብሎ እየተመሳጠረ የሚያስቀረው ገንዘብ ሀገርንም ህዝብንም እንደሚጎዳ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ የንቅናቄ መድረኩ አንዱ ዓላማም ይሄው ነው፡፡ የትምህርት፣የጤና፣የመንገድ፣የንጹህ መጠጥ ውሃ፣የግብርና ፣የሠላምና የደህንነት፣ ወዘተ ሥራዎች ያለ ግብር አይከወኑም፡፡ ስለዚህ ግብር መክፈል ግዴታም ውዴታም መሆኑ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡
ሰው ሠርቶ እስከ ኖረ ድረስ የሚጠበቅበትን ግብር መክፈል አለበት፡፡ ይህን ሁሉ በሚገባ የሚያውቁ እንዳሉ ሁሉ የማያውቁም፣አውቀው የማያውቁም በርካታ ናቸው፡፡እናም እነዚህ ወገኖች ስለ ግብር ፋይዳ እንዲያስቡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡አውቀው ግብርን ለመሰወር በሚንቀሳቀሱት ላይ ደግሞ ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡ ግብር በአግባቡ በመክፈል የጋራ ጎጇችን የሆነችውን አገራችንን ብልጽግና እናረጋግጥ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2011