በጎ አስተሳሰብ ያለው፣ በመልካም ስነምግባር የታነጸ እና በእውቀት ብሎም በክህሎት የዳበረ ማህበረሰብን የመፍጠር ስራው አንድ ብሎ የሚጀመረው በታችኛው እርከን ላይ ባሉ ትምህርት ቤቶች እና በታችኛው እድሜ ላይ ባሉ ልጆች ላይ መሆኑ እውን ነው። ወቅቱ መስከረም እንደመሆኑም ተማሪዎች በአዲስ አስተሳሰብና መንፈስ ለአዲስ ክፍል ራሳቸውን አዘጋጅተው አዳዲስ እውቀቶችን ለመቅሰም ወደየትምህርት ቤቶቻቸው የሚያቀኑበት ነው።
አዲስ ዓመትና አዲስ የትምህርት ዘመን ተደምረው በሚቀርቡበት በዚህ ወቅት ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ወጣቶች ከሚፈትኗቸው በርካታ ጉዳዮች መካከል ደግሞ አንድም የትምህርት ቤት ቁሳቁስ ሲሆን፤ ሁለተኛም በትምህርት ቤቶች ቅጥር የሚስተዋል ከንጽህና ጀምሮ ያለ የትምህርት አዋኪ ጉዳይ ነው። በዚህ መልኩ በኢኮኖሚም ሆነ በአካባቢዊ ጉዳዮች ተጽዕኖ ውስጥ ሆነው ትምህርት እንዲከታተሉ የሚገደዱ ታዳጊዎች ደግሞ የሚደርስባቸው የአዕምሮ፣ የስነልቡናም ሆነ የአካል ተጽዕኖ ቀላል ካለመሆኑም በላይ፤ ተማሪዎቹ እንዲያስመዘግቡ በሚጠበቀው ውጤት ላይ አሉታዊ ጫናው ጉልህ ነው።
ይሄን የተገነዘበው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ችግሩን ለማቃለል በማሰብ ክረምቱን በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱ ይታወሳል። ታዲያ በዚህ ረገድ ከተማ አስተዳደሩ በክረምቱ አቅዶ ሊያከናውናቸው ያሰባቸው ተግባራት ምን ነበሩ፤ ምን ያህሉንስ አሳካ፤ ለትምህርት ዘመኑ ያለው ዝግጅትስ ምን ይመስላል፤ በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አበበ ቸርነት ያደረሱንን መረጃ በሚከተለው መልኩ ይዘን ቀርበናል።
የክረምቱ ቅድመ ዝግጅት ዕቅድና ተግባራት
የ2012 የትምህርት ዘመን ውጤታማ የትምህርት ዘመን እንዲሆን ለማስቻል የከተማ አስተዳደሩ የዝግጅት ምዕራፍ ወቅት ላይ በርካታ ተግባራት እንዲከናወኑ በገባው ቃል መሰረት መሬት ላይ ወርደው እንዲፈጸሙ ተደርጓል። ከእነዚህ መካከል አንዱ 488 የሚጠጉ የመንግስት የትምህርት ተቋማት እድሳት ነው። በተመሳሳይ እስከ 600 ሺ ለሚደርሱ ተማሪዎች የሚሆኑ የመማሪያ ቁሳቁሶችን (ከደብተርና የደንብ ልብስ ዩኒፎርም ጀምሮ) ዝግጁ ማድረግ፤ እንዲሁም እስከ 300ሺ ለሚሆኑ እስከ ስምንተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ትምህርት ሲጀመር ማስጀመር የሚሉትም በክረምቱ እንዲፈጸሙ የተቀመጡ የስራ አቅጣጫዎች ናቸው።
በዚህ መሰረት የከተማ አስተዳደሩ በርካታ ተግባራትን ያከናወነ ሲሆን፤ የትምህርት ቤት እድሳቶቹ፣ የተማሪዎች የትምህርት ግብዓትን የማሰባሰብና ሁለት የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ስራው ዝግጁ ማድረግ ተችሏል። በተቀመጠው አቅጣጫም መሰረት ስራዎቹ በመጠናቀቃቸው እና ስራዎችም ውጤታማ ሆነው በመከናወናቸው በከተማ አስተዳደሩ ስር በሚገኙ ሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ዛሬ ትምህርት ይጀምራል። ሁለቱ የአዳሪ ትምህርት ቤቶችም በተመሳሳይ በዛሬው ዕለት ስራ የሚጀምሩ ሲሆን፤ ተማሪዎች በፈተና ተለይተዋል፤ የመምህራን ቅጥርም ተከናውኗል።
ቁሳቁሶችን ተደራሽ የማድረግ ስራዎች
ለመማር ማስተማሩ ሂደት የሚሆኑና ለተማሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ አስፈላጊ ቁሳቁሶች ተሰብስበው እንዲቀመጡ አልተደረገም፤ የመሰብሰባቸው ዓላማ ለተማሪው እንዲደርሱ ስለሆነም የማሰራጨት ስራ ተከናውኗል። በአግባቡ እንዲሰራጭ ሆኖም በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት ውስጥ ላሉ ተማሪዎች እንዲደርስ ተደርጓል። ከዚህ በተጓዳኝ በግል ትምህርት ቤቶች ያለን የመጽሐፍት ክፍተት ለመሙላት የሚያስችሉ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን፤ በዚህም ትምህርት ቤቶቹ ቀደም ብለው ፍላጎታቸውን እንዲያስገቡ በመደረጉ በጠየቁት መሰረት የሕትመት ስራ ተከናውኖ፤ ስርጭትም ተካሂዷል። በጠየቁት አግባብም እንዲደርሳቸው ተደርጓል። ተጨማሪ ፍላጎት ላስገቡትም ቢሆን ባቀረቡት መሰረት አሁንም ድረስ እየተስተናገዱ ናቸው።
አዋኪ ጉዳዮች ላይ ከመስራት አኳያ
ምንም እንኳን ጉልህ ሚና ቢኖራቸውም ትምህርት ቤቶች መታደሳቸውና ተማሪዎችም የትምህርት ቁሳቁስ ማግኘታቸው ብቻ የመማር ማስተማሩን ለውጤት ሊያበቁት አይችሉም። ይህ ተግባር በትምህርት ቤቶች ውስጥና ዙሪያ ያሉ የትምህርት አዋኪ ጉዳዮችን መቅረፍን ይጠይቃል። አዋኪ ጉዳዮችን በተመለከተም የትኞቹ ትምህርት ቤቶች ላይ ነው አዋኪ ጉዳዮች ያሉት በሚል ተለይተዋል። በዚህም የትኞቹ ትምህርት ቤቶች ላይ ውስጣዊ አዋኪ ጉዳዮች አሉ፤ የትኞቹ ትምህርት ቤቶች ላይ ውጫዊ አዋኪ ነገሮች አሉ የሚለው ተለይቶ ከሚመለከታቸው ጋር እየተሰራ ነው፤ የሚሰራም ይሆናል።
ለምሳሌ፣ ውስጣዊ አዋኪ ጉዳዮች የሚባሉት በትምህርት ቤቱ አመራሮች ሊወገዱ የሚችሉ ሲሆኑ፤ በዚህ ላይ ባለፈው ዓመትም በርካታ ተግባራት በመከናወናቸው ብዙ ችግሮችን ማቃለል ተችሏል። ውጫዊ የትምህርት ቤት አዋኪ የሚባሉትንም ከትምህርት ቤት ማህበረሰብና አስተዳደሮችም ሆነ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን በጋራ የሚሰራባቸው ናቸው። በውጫዊ አዋኪ ጉዳዮች ላይ ባለፈው ዓመትም ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በመሆን ሰፊ ስራዎች የተሰሩና ችግሮችን መፍታት የተጀመረ ቢሆንም፤ ችግሩ በአንድ ጊዜ የሚቀረፍ ባለመሆኑና የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ ተከታታይ ስራን ስለሚጠይቅ በዛው አግባብ እየተሰራ ነው።
ምክንያቱም ትምህርት ቤቶችን ተገን አድርገው የሚከፈቱ በርካታ ቤቶች አሉ። ይህ ደግሞ ለትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራው ችግር ስለሚፈጠርና ለተማሪዎችም እንቅስቃሴ አዋኪ ስለሚሆን፤ እነዚህን ቤቶች ከከፈቱ ሰዎች፣ ከንግድ ቢሮና መሰል ተቋማት ጋር በችግሩ ዙሪያ መስራትና ችግሩን መቅረፍ ያስፈልጋል። በ2012 የትምህርት ዘመንም እንደ 2011 ሁሉ በዚሁ ላይ በትኩረት በቂ ስራ የሚሰራ ሲሆን፤ የእርምጃው መጠናከርም ውጤታማ የመማር ማስተማር ዘመን እንዲሆን ያስችላል የሚል እምነት አለ።
መምህራንን የማብቃት ስራ
የመምህራንን ብቃት ከማሳደግ አኳያ ተከታታይ ስራ እየተከናወነ ይገኛል። በዚህም ክረምቱን ጨምሮ በተከታታይ የትምህርት መርሃ ግብር አቅማቸውን እንዲያሳድጉ እየተደረገ ነው። በተመሳሳይ በቅዳሜና እሁድ መርሃ ግብርም መምህራን የትምህርት ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ እየተደረገ ሲሆን፤ በክረምቱም ሆነ በቅዳሜና እሁድ መርሃ ግብሩ በርካታ መምህራን የትምህርት ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ የማድረግ ስራ ተከናውኗል። ይህ ስራ የአንድ ወቅት ስራ ስላይደለም ተጠናክሮ የሚቀጥል፤ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብርም የሚሰራበት ይሆናል።
ለትምህርት ዓመቱ በስኬት መጠናቀቅ
የትምህርት ዓመቱ በውጤትና በስኬት እንዲጠናቀቅ ስራው ለአንድና ሁለት ተቋም ተሰጥቶ የሚተው ሳይሆን የሁሉንም ባለድርሻ ጥረት የሚጠይቅ ነው። ምክንያቱም የትምህርት ዘመኑ የትምህርት ውጤታማነት የሚወሰነው ከተማሪዎች እስከ ወላጆች፣ ከትምህርት ቤቶች እስከ ሌሎች ባለድርሻዎች ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነትን ወስዶ በሚሰራው ልክ ነው። በመሆኑም አንደኛ፣ ተማሪዎች መንግስት በተቻለው አቅም ድጋፍ ሲያደርግ የተሻለ ትውልድን ለመፍጠር ያለውን ጥረት ከግምት በማስገባት፤ የወላጆቻቸውንም ህልምና ምኞት ለማሳካት የሚያስችላቸውን የስነልቡና ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል። በትምህርት ቤት ቆይታቸውም በመልካም ስነምግባር ታግዘው አስፈላጊውን እውቀት መገብየትን ዓላማ አድርገው መማርና ውጤታማ ሆኖ ለማጠናቀቅ መትጋት ይጠበቅባቸዋል።
ትምህርት ቤቶችም ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ ለተማሪዎች ስነምግባር መጠበቅ ትኩረት ሰጥተው መስራት ይኖርባቸዋል። በዚህም ለተማሪዎች ስነምግባር ለትምህርት ቤቶች የወረደን የስነምግባር መመሪያ በውጤታማነት ማስተግበር ይጠበቅባቸዋል። ይህ መመሪያም ውጤታማ ሆኖ ከተተገበረ የሚነሱ የባህሪ ችግሮች የመከሰት እድላቸው የመነመነ ይሆናል፤ እንዳይከሰቱ ስለሚያደርግም መመሪያው ተግባራዊ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይገባል።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ለትምህርት ዘመኑ ውጤታማነት ተኪ የሌለው ተግባር የወላጆች እንደመሆኑ፤ ወላጆች ይሄን ሚናቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም ሁሉም ስራ ከትምህርት ቤት በፊት ወላጆች ላይ የሚያርፍ እንደመሆኑ የተማሪዎችን ባህሪ ከማረቅና ከማስተካከል፤ በትምህርታቸው በመደገፍና በማበረታታት በየቀኑ ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ ረገድ የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ ነው።
በመሆኑም ወላጆች ልጆቻቸውን በተለያዩ ማህበራዊ እሴቶችና ስርዓት ከማሳደግ እና ወደ ትምህርት ቤት ከመላክ ጀምሮ፤ ልጆቻቸው ትምህርት ቤት ገብተው እስኪመለሱ ድረስ በየጊዜው ራሳቸውን እንዲጠብቁ ማገዝ ይጠበቅባቸዋል። ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ሲገቡም የመማር ማስተማር ውሏቸውን በተመለከተ እገዛ በማድረግ ረገድ ያላቸውን ትልቅ ኃላፊነት ሊወጡ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2012
ወንድወሰን ሽመልስ