ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ እየተባለ ለሚጠራው ቱሪዝም ተቀዳሚ መዳረሻዎች የአገር ውስጥ መስህቦች ናቸው። የአክሱም ሃውልቶች፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የጀጎል ግንብ፣ የኮንሶ ባህላዊ እርከን ስራ፣ የገዳ ስርዓት፣ የመስቀል በዓል፤ የሰሜን ተራሮች ፓርክና ሌሎችም በተባበሩት መንግስታት የባህል፤ የትምህርትና የሳይንስ ማዕከል በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡት፤ እነዚህ ቅርሶች ለኢትዮጵያ የገቢ ምንጭ በመሆንና የስራ ዕድል በመፍጠር የራሳቸው ድርሻ ቢኖራቸውም የሚፈለገውን ያህል ግን ገቢ እያስገኙ አይደሉም።
ኢትዮጵያ ካላት የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችና ባህሎች አኳያ የሚፈለገውን ያህል ከዘርፉ ተጠቃሚ አይደለችም የሚለውን ሀሳብ የሚጋሩት የኢትዮጵያ የሆቴል ባለሙያዎች ማህበር የቦርድ ፀሐፊ አቶ ክፍሉ ገብረጊዮርጊስ፤ በተለይ በኢትዮጵያ በሆቴሎች ለቱሪስቶች የሚሰጠው የአገልግሎት የጥራት ችግር አንዱ መሆኑን ያነሳሉ። ኬንያና ታንዛንያ በሆቴልና በአስጎብኚ ድርጅቶች የተሻለ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች በማፍራት ለቱሪስቶች የተሻለ አገልግሎት ይሰጣሉ። በዚህም ከዘርፉ የሚያገኙት ገቢ ከፍተኛ ብቻ ሳይሆን ከዓመት ዓመት እየጨመረ የሚሄድ ነው ይላሉ።
በአንጻሩ፤ በኢትዮጵያ ብዛት ያላቸው የተፈጥሮ፤ ታሪካዊና ባህላዊ የቱሪስት መስህቦች ቢኖሩም በሆቴልና በአስጎብኚ ድርጅቶች አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት መጓደል ችግር ይስተዋላል። በዚህ ምክንያትም ኢትዮጵያ የሚፈለገውን ያህል ተጠቃሚ እየሆነች አይደለችም የሚል ቁጭት አላቸው።
ለአብነትም፤ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶች የእንግሊዘኛ፤ የፈንሳይኛ፤ የጀርመንኛና ሌሎች ቋንቋዎች ተናጋሪዎች ናቸው። የሆቴልና የአስጎብኚ ባለሙያዎቹ እነዚህን ቋንቋዎች ጠንቅቀው አውቀው ቱሪስቶች ስለኢትዮጵያ የቱሪስት መስህቦችና ስለ ድርጅታቸው አገልግሎቶች ማስረዳትና ማስተዋወቅ ቀርቶ ባለሙያዎቹ ትዕዛዝ ተቀብሎ ለማስተናገድ የሚቸገሩ ናቸው ይላሉ። ይህም ለቱሪዝም ዕድገት ዋናው ተግዳሮት ነው ባይ ናቸው።
በተለይ የሆቴል ሙያ ተግባር ተኮር ትምህርት የሚፈልግ ቢሆንም፤ በአገሪቱ የሚሰጡ ትምህርቶች በንድፈ ሀሳብ ላይ ብቻ ያተኮሩ ናቸው። ባለሙያዎቹ ከኮሌጆች ወይም ከዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው ወደ ሙያው ሲቀላቀሉ እንደገና ስልጠና የሚሹ መሆኑን በተደረገ ጥናት መረጋገጡን ነግረውናል። ይህ በትምህርት ተቋማት በኩል ሙያዊ እውቀት በማስጨበጥ ረገድ ሰፊ ክፍተት መኖሩን ያሳያል ነው ያሉት።
ስለዚህ አሉ፤ ክፍሉ ስርዓተ ትምህርቱ ዘመኑ የደረሰበትን ነባራዊ ሁኔታ የቃኘና ተግባር ተኮር እውቀት በማስጨበጥ ላይ ያነጣጠረ መሆን አለበት። ተማሪዎች በስራ ላይ ውጤታማ የሚሆኑበትን እውቀት ለማስጨበጥ ደግሞ የሆቴል ባለንብረቶች፤ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና የሙያ ማህበራት በጋራ መስራት እንደሚኖርባቸው ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል። አቶ ክፍሉ፤
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ዘርፍ አማካሪ አቶ መኮንን ገብረእግዚብሔር፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.አ.አ በ2018 የቱሪዝም መስህቦችን የሚጐበኙ ሰዎች ቁጥር ስድስት በመቶ ጨምሯል። በዚሁ ዓመትም አንድ ቢሊዮን 403 ሚሊዮን ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን እንደጎበኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ጠቅሰዋል። በዚሁ ዓመት ከፍተኛውን የጎብኚዎች የዕድገት ምጣኔ ያስመዘገቡት አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ መሆናቸውን በአብነት አውስተዋል። ሆኖም፤ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ሰፊ የቱሪዝም ሀብት ቢኖራቸውም የስራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ትልቅ ችግር አለባቸው። የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን አለማልማት፤ የእውቀትና ክህሎት ውስንነት፤ ዘላቂ ራዕይ አለመሰነቅና ሌሎች ችግሮች ተደማምረው በቂ የስራ ዕድል እንዳይፈጥሩ መሰናክል ሆነዋል የሚል ሀሳብ አላቸው።
እንደ ዓለም አቀፍ የጉዞና የቱሪዝም ካውንስል (WTTC) ጥናት መሰረት፤ እኤእ በ2017 ቱሪዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ 10 ነጥብ አራት በመቶ አጠቃላይ አገራዊ ምርት (ጂድፒ) ድርሻ ሲኖረው፤ ለ313 ሚሊዮን ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ይህም ከአምስት ዓመት በፊት ከነበሩት 10 ተከታታይ ዓመታት የስራና አጠቃላይ አገራዊ ምርት ድርሻ በእጥፍ የሚበልጥ መሆኑን እንደሚያመላክት በጥናታዊ ጹሁፋቸው አቅርበዋል።
ለምሳሌም፤ ከአምስት ዓመት በፊት ቱሪዝም ከ10 የስራ ዕድሎች ውስጥ አንድ የስራ ዕድል ይፈጥር ነበር። ባለፉት አምስት ዓመታት ግን በዓለም ላይ ካሉ አምስት የስራ ዕድሎች አንድ የፈጠረ ሲሆን፤ በዚህም መስኩ የስራ ፈጠራ ሞተር መሆኑን አሳይቷል ባይ ናቸው። መንግስታት ለቱሪዝም ተስማሚ ህግጋት ካወጡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ቱሪዝም 100 ሚሊዮን አዳዲስ የስራ ዕድሎች ሊፈጥር እንደሚችል መተንበዩን አመላክተዋል።
በኢትዮጵያም እ.አ.አ በ2017 የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች የጎበኙ የዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ብዛት 933 ሺህ ሲሆን፤ ከቀደመው ዓመታት በሰባት ነጥብ ሶስት ብልጫ አለው። እንደ ዓለም አቀፍ የጉዞና የቱሪዝም ካውንስል ሪፖርት እንደሚያሳየው ቱሪዝም ለአጠቃላይ አገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ዕድገት በቀጥታ ያበረከተው 49 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ነው። በቱሪዝም በዚሁ ወቅት የነበረው ቀጥታ የስራ ዕድል 604 ሺህ መሆኑን ኢንዱስትሪው ለስራ ዕድል ፈጠራ ያለውን ድርሻ በማጣቀሻነት አቶ መኮንን አቅርበዋል።
ቱሪዝም በትራንስፖርት፤ በሆቴሎች፤ በእንግዳ ማረፊያዎች፤ በካፌዎች፣ በሬስቶራንቶች፤ በታሪካዊ፤ በባህላዊ፤ በተፈጥሯዊ፤ በዕደ ጥበብ ምርትና በመዝናኛዎች ስራዎችን እንደሚፈጥር ጠቅሰዋል። “በዓለም ላይም ሆነ በሀገራችን ውስጥ የጎብኚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው” የሚሉት አቶ መኮንን የጎብኚዎች ቁጥር መጨመር ደግሞ የአገልግሎት ሰጪውን ቁጥር እንዲጨምር ያደርጋል። የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቁጥር ብቻ ሳይሆን የአገልግሎት ዓይነቱንም እንዲጨምሩ ያደርጋል። ይህም ለስራ ፈጣሪዎችም ሆነ ለስራ ፈላጊዎችም ብዙ ዕድሎችን ይፈጥራል ብለዋል።
ሆኖም፤ እነዚህን መልካም እድሎች በአግባቡ ለመጠቀም የማህበረሰብ አባላት በስራ ውጤታማ እንዲሆኑ ቀለል ያሉ ክህሎቶችን ማስጨበጥ ያስፈልጋል። ለምሳሌ፤ መሪነትን፣ ተግባቦትና ሰዓት አጠቃቀምን እንዲገነዘቡ ማድረግ ይገባል። ሌላው በቱሪዝም ስራ ፈጠራ ወቅት የተፈጥሮ፤ አካባቢና ባህላዊ እሴቶቻችን ጉዳት እንዳይደርስባቸው እንዲከላከሉ ግንዛቤ መፍጠር ይጠበቃል። ለዚህ ደግሞ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል። የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማልማት፣ የሆቴሎችን አገልግሎቶችን ጥራት ማሻሻልና የቱሪዝም ንግድ ስራ ለመጀመር ለሚፈልጉ ዜጎች አመቺ ሁኔታ መፍጠር የቀጣይ ትኩረት አጀንዳዎች መሆናቸውን ይገልጻሉ።
በሆቴልና ቱሪዝም ኢንስቲትዩት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት አቶ ማዘንጊያ ሽመልስ፤ የቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት አለበት ይላሉ። ለአብነትም፤ በአገር አቀፍ ደረጃ በኦሮሚያ፤ በአማራ፤ በደቡብ፤ በትግራይ፤ በሀረሪ ክልሎች በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞችና በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ሆቴሎችና በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ያሉትን ባለሙያዎች የትምህርት ደረጃ ለማወቅ በተካሄደ ጥናት ዲግሪና ከዚያ በላይ ያላቸው 11 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ብቻ ናቸው።
በቴክኒክና ሙያ ተቋማት በተለያዩ የሌብል ደረጃዎችና በዲፕሎማ የተማሩ ባለሙያዎች ደግሞ 37 ነጥብ ሶስት በመቶ ሲሆኑ፤ ቀሪው 49 በመቶ በሰርተፍኬትና ከ12ኛ ክፍል በታች የክፍል ደረጃ ያላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህም ኢንዱስትሪዎቹ የሚፈልጉትን የሰለጠነ የሰው ኃይል በቁጥር ብቻ ለማሟላት ብዙ ስራ የሚጠይቅ መሆኑን ያሳያል ብለዋል። በመስተግዶ፤በምግብ ዝግጅትና የአስጎብኚ ድርጅቶች ተቆጣጣሪ የስራ መስኮች የተማረ የሰው ኃይል እጥረት የሚታይባቸው መካከል እንደሚገኙበት በጥናቱ ተመልክቷል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም ዩኒቨርሲቲዎች፤ ኮሌጆችና ሆቴሎችና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በጋር መስራት ይጠበቅባቸዋል። በተለይ፤ በሆቴልና በቱሪዝም ሙያ የተሻለ ክህሎትና እውቀት ያላቸውን ባለሙያዎች በብዛትና በጥራት በማፍራት ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በእጅጉ ማሳደግ የሚገባ መሆኑን ገልጸዋል።
“ዛሬ ዓለም ፊቱን ወደ ጭስ አልባው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እያዞረ ነው፤” የሚሉት አቶ ማዘንጊያ ኢትዮጵያም ቱሪስቶች የሚፈልጉትን አገልግሎት በጥራት በመስጠት የሚፈለገውን ገቢ ለማግኘት ርብርብ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ሙያዊ ስነ ምግባርና ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ማፍራት ቀዳሚው ስራ ነው። ይህን ለማሳካት ዩኒቨርሲቲዎች፤ ኮሌጆች በቱሪዝምና በሆቴል የትምህርት መስኮች ተግባር ተኮር ትምህርት መስጠት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
በቱሪዝም ዘርፍ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በመፍታት ለዜጎች በርካታ የስራ ዕድል ለመፍጠርና ገቢውን ለማሳደግ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ከውይይት ባለፈ የተግባር ስራ ይጠበቅባቸዋል። መንግስት የቱሪስቱን ፍሰት ለመጨመር ታላቁን ቤተ መንግስት የማደስ ስራ እየሰራ ሲሆን፤ የአዲስ አበባ የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክትና የብሄራዊ ቤተ መንግስት ለመስህብነት ለማዋል አቅዶ በመንቀሳቀሱ ለቱሪዝም ትኩረት የሰጠ ነው። ይሁን እንጂ፤ አሁንም ታሪካዊ ቅርሶችን በመጠገንና የቱሪስት መዳረሻ ስፋራዎችን በማልማት ረገድ ብዙ ስራ ይጠብቀዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 23/2012
ጌትነት ምህረቴ