አለማችን ባለፉት አስርት ዓመታት በታሪኳ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ እጅግ በሀብት ከብራለች። የተስፈነጠረው የሀብት ክምችትና እድገት በሕብረተሰቡ ውስጥ ባለውና በሌለው መካከል ያለውን ልዩነት መገመት በማይቻል መልኩ አስፍቶታል። በአፍሪካና በቀሪው አለምም። በሕብረተሰቡ ውስጥ ያለው የሀብት እኩልነት አለመመጣጠንና ልዩነት መገመት በማይቻልበት መልኩ ገዝፎአል። ጥቂቶች በሀብት ክብረትና ባለቤትነት ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል ተለይተው በጣም ርቀው ተወንጭፈዋል። አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል በከፋና አሰቃቂ ድህነት ውስጥ ይኖራል። አስፈሪውም ነገር ይኸው ነው።
ታላላቅ አመጾች፤ የሕብረተሰብ አለመረጋጋት፤ በኃይል የታጀቡ ነውጦች፤ ረብሻዎች እንዲያም ሲል አብዮቶች በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች በእርግጠኝነት የሚከሰቱት በሀብት እኩልነት አለመኖር ነው። የሀብት ክፍፍል እኩል አለመሆን፤ ጥቂቶች በገነት ኑሮ አብዛኛው ሕዝብ ደግሞ የሲኦልና የገሀነም ኑሮ በሚኖርበት ሁኔታ ውስጥ አመጾች መቀስቀሳቸው እንግዳ ነገር አይደለም። የእኩልነት አለመኖር፤ ኢ-ፍትሀዊነት መስፈን፤ የአብዛኛው የአለማችን ሕዝብ በድህነት ውስጥ መገኘቱ፤ የቀጣዩን ዘመን ሰላም የአለምን ፖለቲካና ኢኮኖሚ እንደሚያናጋው የተገኘውም የኢኮኖሚ እድገት ዳግም ሊቀለበስ እንደሚችል ኢኮኖሚስቶች ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
የቀደሙት ዘመናት የአለማችን አብዮቶች መነሻ መሰረታዊ ምክንያቱ ይኸው ነው። የእኩልነት አለመኖር፤ የፍትህ እጦት፤ ኢ-ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል፤ የሰራተኛ ጉልበት ብዝበዛና ባርነት፤ የገዘፈ የስራ አጥ ቁጥር፤ የጥቂቶች መክበር፤ የብዙሀኑ ሕዝብ በአሰቃቂ ድህነት ውስጥ መዘፈቁ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ወዘተ የአብዮቶች መነሻዎች መሆናቸውን ታሪክ ያስረዳል። ዛሬም አለም ከቀደሙት ዘመናት በላቀ ሁኔታ በሀብት ብትከብርም የቀደሙት ችግሮች አልተፈቱም። በተመሳሳዩ መንገድ እየተራመደች ነው። የገዘፉ ያልተፈቱ ማህበራዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የእኩልነት አለመኖር ያልተፈቱ ውስብስብ ችግሮች ሆነው ቀጥለዋል።
ግጭቶች ሁሉ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች አላቸው፡፡ በተለይም በሕብረተሰቡ ውስጥ የእኩልነት አለመኖር። በአለማችን የታየው የሀብት እድገት አፍሪካን ጨምሮ በባሕሩ ላይ ያሉትን ሁሉንም ጀልባዎች ወደ ከፍታ ማውጣቱ እውነት ነው። አፍሪካ ከ2017 (እኤአ) የ4.4 በመቶ የሀብት እድገት ጭማሪ በማሳየት ወደ 108 ቢሊዮን ዶላር መድረሷን አንቨር ቨርሲ የእኩልነት አለመኖር በአፍሪካ በሚለው ጽሑፉ አስፍሮታል።
አለም ባልተጠበቀና ባልተገመተ የሀብት እድገት እየፈነጠዘች ባለችበት በዚህ ወቅት ሞልቶ ከተትረፈረፈው ሀብት ወደ አፍሪካ የሚሄደው ትንሽ ነው። በአለም አቀፍ ደረጃ ካለው የእኩልነት አለመኖር በተጨማሪ በአፍሪካም የሀብትና የገቢ ክፍፍል እኩልነት የለም። አብዛኛው ሕዝብ በከፋ የድህነት ችግር ውስጥ ይገኛል።ይህ ሁኔታ የሰውን ልጅ ተፈጥሮአዊ ክብር ይገፋል።ታሪክ እንደሚያሳየን የድህነቱ ስር መስደድና የእኩልነት አለመኖር ተዳምረው በአጠቃላይ በሕዝቡ ውስጥ የታመቀው ሁኔታ ለመፈንዳት የተቃረበ መሆኑን ያሳያሉ። አለማችን እንዳለፉት አስርት ዓመታት እንዲህ በሀብት እጅግ የከበረችበት ጊዜ የለም። የዛኑም ያህል የገቢ አለመመጣጠን እንደአሁኑ ወቅት የገዘፈበት ጊዜም የለም።
ክሬዲት ሲዩሴስ ግሎባል ዌልዝ ሪፖርት እንደገለጸው ሚሊኒየሙ ከተጀመረ በኋላ የአለም ሀብት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮአል። ከቀደመው 117 ትሪሊየን ዶላር በአሁኑ ሰዓት 317 ትሪሊዮን ዶላር ደርሶአል። በ2008 (እኤአ) ከደረሰው እጅግ የገዘፈ አለም አቀፍ ከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ ተነስቶ ማለት ነው።
የሀብት ማዕበሉ ሁሉንም ከፍ አድርጓል። አፍሪካንም ጨምሮ። አፍሪካ በ2017 (እኤአ) 4.4 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 108 ቢሊዮን ዶላር ደርሳለች። ከሰሜን አሜሪካ ጋር ሲነጻጸር በ2018 (እኤአ) የአፍሪካ አጠቃላይ ሀብት 2.553 ቢሊዮን ነበር። ሰሜን አሜሪካ በ2018 (እኤአ) በአጠቃላይ ያስመዘገበው አጠቃላይ ሀብት 106. 513 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን ከ2017 (እኤአ) በላይ የ4.6 በመቶ ( 6.486 ቢሊዮን) ጭማሪ አሳይቶአል።
በ2018 (እኤአ) በአፍሪካ የአንድ ሰው መካከለኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ ሀብት 4.138 ዶላር ሲሆን በሰሜን አሜሪካ ደግሞ 391.690 ዶላር ነው። በእርግጥም የነፍስ ወከፍ ሀብት አማካይ በስታስቲክስ ከሚገለጸው ትንሽ ከፍ ያለ ስለሆነ ፈጣን ማመሳከሪያ ለመስጠት ያስቸግራል። እውነቱ ግን ሁሉም አፍሪካዊ 4000 ዶላር ወይንም ሁሉም ሰሜን አሜሪካዊ 300.000 ዶላር አያገኝም። ቢሆንም ነጥቡ ተገልጾአል።
ምን ያህል ግለሰቦች ሀብት አላቸው ወይንም ገቢ ያገኛሉ፤ ወይንም ሊያገኙ ይችላሉ የሚለው ነጥብ የሚወሰነው በአህጉራዊው የኢኮኖሚ አቅም መጠን ነው። የተገኘው የሀብት እድገት ከፍተኛ በሆነ ቁጥር ቢያንስ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ እያንዳንዱ ግለሰብ የሚያገኘው ሽርፍራፊም ትልቅ ይሆናል። በተግባርም እያንዳንዱ የሚያገኘው ከፍተኛ እንዲሁም ዝቅተኛ የገቢ መጠን በሀገሮች ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ይለያያል።
ይህ የገቢ አለመመጣጠንና የእኩልነት አለመኖር መሰረታዊ ችግር ሁለቱም በከፍተኛ ደረጃ ስሜትን የሚፈታተኑና የሚያንሩ ናቸው። ብዙዎች የፖለቲካ ሳይንቲስቶች አለም አቀፍ ታሪክን በመጥቀስ በመደቦች መካከል የገቢ መመጣጠንን ለመፍጠር የሚካሄዱ ማብቂያ የሌላቸው ትግሎች መኖራቸውን ይገልጻሉ። ታላላቅ የኢኮኖሚ ስርአቶች ኮሚኒዝምና ካፒታሊዝም የተመሰረቱት ኢኮኖሚው እንዴት እንደሚሰራና እንደሚከፋፈል በሚገልጽ መሰረት ላይ ነው። አብዮቶች፤ ጦርነቶች፤ የቅኝ ግዛት ጀብዶች፤ በትክክልም ሁሉም በሕዝብ ቡድኖች መካከል የሚካሄዱ ግጭቶች መነሻቸው የኢኮኖሚ ባለቤትነት የጋራ ክፍፍል ጥያቄ ጉዳዮች ናቸው።
የሕብረተሰብ የጥንት ሕመሞች ተብለው የሚጠቀሱ አሉ። ዘመናትን አልፈው የተሻገሩ ዛሬም በሰው ልጅና በሕብረተሰብ ሕይወት ውስጥ የሚገለጹ። ግሪካዊው ፈላስፋ ፕሌቶ ጥልቅ ድሕነትና የተትረፈረፈ ሀብት የታላቅ ሰይጣናዊ ሕብረተሰብ ውጤቶች ናቸው ሲል ጽፎአል። ፕሉታርክ በበኩሉ በሀብታምና በድሀ መካከል ያለው አለመመጣጠን በጣም ጥንታዊና የሁሉም ሪፐብሊኮች በሽታ ነው ሲል አስጠንቅቋል።
ዛሬም ቢሆን እጅግ የገዘፈ የቴክኖሎጂ እመርታ ውጤቶችና ግሎባላይዜሽን ባለበት ዘመን ከቀድሞው ጊዜ በላቀ ሁኔታ አለም በጣም ሀብታም ሆናለች። በሕብረተሰቡ ውስጥ የእኩልነት አለመኖርም የዛኑ ያህል ገዝፏል።
የገቢ አለመመጣጠንና እኩል ያለመሆን ጥያቄ የፖለቲካው ነጸብራቅ ነው። በጣም ሀብታም በሆነውና በሌላው መካከል ያለው የእድገት ልዩነት ፖለቲካውን በማጋጋም ብሬክሲትና ጽንፈኛ ቀኝ አክራሪዎች በከፊል አውሮፓ በአሜሪካ እንዲነሱ ምክንያት ሆኖአል።
የእኩልነት አለመመጣጠን ሀብታም በሆኑት ሀገራትና ታዳጊ በሆኑት አፍሪካን በመሳሰሉት አካባቢዎች በአይነቱ፤ በይዘቱ፤ በሚያስከትለውም ውጤት አንድ አይነት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። የእኩልነት አለመኖር ወይንም እኩል ያለመሆን ግንዛቤ በህብረተሰቡ ውስጥ መፈጠር የፖለቲካው መገለጫ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይል ነው። በየቦታው በመደጋገም እንደምናየው ይህ ሁኔታ እየተብላላና እየፈላ ሲመጣ ከፍተኛ አመጽ ወይንም አብዮት ሆኖ ፈንድቶ ይወጣል። ይቀጣጠላል። ይጋጋማል።
አንዳንድ ኢኮኖሚስቶች ይህንን ክስተት የትም መላወስ በማያስችል የትራፊክ መጨናነቅ ሲመስሉት ሌሎች ደግሞ ነጻ በሆነ መንገድ ላይ እንዳሻቸው በፈለጉት ፍጥነት ከሚጋልቡበት ሁኔታ ጋር ያገናኙታል። ሁኔታው የፍትህ አለመኖርን ስሜት በሰው ሕሊና ውስጥ ያስቀምጣል። ተፈጥሮአዊ ነው። ጥቂቶች ከሌሎች በጣም በበለጠ እኩል ናቸው የሚለውን ይገልጻል። ይህ እጅግ ኃይለኛ ስሜትን በሰው ውስጥ ስለሚፈጥር በተለመደ መልኩ ወንጀሉን ከዋናው ቦታ ውጭ በሌሎች ላይ ያሳርፋል።
በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ እንዳየነው የውጭ ዜጎች፤ ስደተኞች፤ የተለዩ ዘሮች ወይንም የሀይማኖት ቡድኖች ሰለባ ሆነዋል። ይህ ሁኔታ ወደተቃውሞ ሰልፍ፤ ጥላቻ፤ ያልተጠበቁ ጥቃቶችን ወደመሰንዘር ከማምራት አልፎ በከፋ ሁኔታ ወደ ሙሉ የሲቪል ጦርነት ሊሻገርም ይችላል። ከዋነኞቹ ሀብታሞች ለሕዝቡ ድህነትና እኩልነት አለመኖር ተጠያቂ ከሚሆኑት ውጭ የሕዝቡ ቁጣና እርምጃ ለድህነታችን ምክንያት ናቸው በሚል በሌሎች ላይ ያርፋል ማለት ነው። .
በ2017 (እኤአ) የአለም ኢኮኖሚ ፎረም ባደረገው ስብሰባ እያደገ የመጣው የእኩልነት አለመኖርና የሕብረተሰብ ሁለት ጎራና ጽንፍ ለይቶ መቆም እነዚህ ሁለቱ ለግሎባል ኢኮኖሚው ታላቅ አደጋ መሆናቸውን፤ ውጤቱም ግሎባላይዜሽንን ወደኋላ ሊመልሰው እንደሚችል በመግለጽ አስጠንቅቆአል። ለዚህ ነው የእኩልነት አለመኖር በአለም ደረጃ ዋነኛው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሕበረሰቦች ጭንቀትና አሳሳቢ ችግር እየሆነ የመጣው።
አዲስ ዘመን መስከረም 22/2012
ወንድወሰን መኮንን