መንግስት ከማህበራዊ መሠረቶቹ መካከል አንዱ የሆነውን ሕዝብ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብሎም ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በማስመዝገብ ከድህነት አዘቅት ውስጥ ለመውጣት በነደፈው የኢኮኖሚ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ጥቃቅንና አነስተኛ ቁልፍ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም በርካቶች ተደራጅተው የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት ከመለወጥ አልፈው በአገሪቱ ገቢና ወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ሲያበረክቱ፤ አንዳንዶች ደግሞ ካሰቡት ሳይደርሱ በማህበር አባላት የውስጥ ግንኙነት መሻከር ተሰናክለው ሲወድቁ ይስተዋላል:: እኛም ለዛሬ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ወደ ተቋማችን የመጣ ቅሬታን ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡
ከጅማሮው
በ2002 ዓ.ም ጌሴም ኮንስትራክሽን ግንባታና ግብዓቶች ምርት ኃላፊነቱ የተወሰነ ህብረት ሥራ ማህበር በሚል መጠሪያ እንደተደራጁ አቶ በለጠ ሙላት ያስታውሳሉ፡፡ ባለቤታቸው ወይዘሮ አሰፋሽ ፍቃዱም በማህበሩ ውስጥ እንደተደራጁና አባላቱም ይህንን አምነውበት ወይዘሮ አሰፋሽን በሥራ አስኪያጅነት እርሳቸውንም በገንዘብ ያዥነት እንደመረጧቸው ይናገራሉ፡፡ በሥራቸው ወጪን በመቀነስ ትርፋቸውን ለመጨመር በነበራቸው ፍላጎት የሠው ኃይል ቀጥሮ ከማሠራት ይልቅ በደንብ እስኪቋቋሙና ማህበራቸውም በሁለት እግሩ እስኪቆም በራሳቸው ጉልበት ይሠሩ እንደነበር የሚናገሩት አቶ በለጠ፤ ሥራውን ሲጀምሩ ከነበሩት 10 አባላት መካከል አንዱ የጉልበት ሥራ መሥራት እንደማይችል በማሳወቅ እንደወጣ ይገልፃሉ፡፡
ሥራቸውን ሲያከናውኑ ከዕለት ወደ ዕለት ከዓመት ዓመትም ሥራቸው ፍሬ ሲያፈራና እነርሱም ይህንኑ የልፋታቸው ውጤት የሆነውን ትርፍ ሲከፋፈሉ ይቆያሉ፡፡ ከቀሪ ዘጠኙ ውስጥ አንድ ዓመት በሥራ ላይ እያሉ 155 ሺህ ብር ትርፍ ማግኘት በመቻላቸውም ሥራቸውን ሲጀምሩ ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ለሥራ መጀመሪያ የወሰዱትን 800 ሺህ ብር በተወሰነ መልኩ ለማቃለል ያግዛቸዋል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያሉ የወሰዱትን ብድር መልሰው ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ የተወሰኑ የማህበሩ አባላት ብሩን ተከፋፍለው የመሄድ ፍላጎት እንዳደረባቸው ገንዘብ ያዡ ይናገራሉ፡፡
ጉልበታቸውን አሟጥጠው ሕይወታቸውን ለመለወጥ ያደርጉት በነበረው ጥረት ሁሉም አባላት በሚፈለገው መልኩ ተባባሪና በሥራው ላይ ተሣታፊ ሳይሆንም ይቀራል፡፡ እንደ አቶ በለጠ ገለፃ፤ የሚያፈነግጡት የማህበሩ አባላት ከማህበሩ ውጪ ሌላ ሥራ መሥራት መጀመራቸው በአንድ በኩል የማህበሩን ሥራ አፈፃፀም ዝቅ ማድረጉ ሳያንስ ግለሰቦቹ ወሩን ሙሉ በሥራ ላይ ሳይገኙ ያልሰሩበትን ለመካፈል በትርፍ ክፍፍል ወቅት የማህበሩን ደጅ መርገጣቸው ቅራኔን ይፈጥራል፡፡
በማህበሩ ውስጥ የታቀፉ ሌሎች አባላት በሥራ ላይ እንዳልተገኙና ሌላው ደክሞ ጥሮና ግሮ ያስገኘውን ያልሠሩበትን ገቢ ለመከፋፈል ወር ሲገባ መገኘታቸው ተገቢነት የጎደለው ተግባር እንደሆነ ሲነግራቸውም ድብድብ በመግጠም ማህበሩን ይበጠብጡ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ይህም ጉዳይ እስከ ፖሊስ ጣቢያ ደርሶ እንደነበርና ሠዎች ይማራሉ በሚል ራሳቸው ዋስ ሆነው እንዳስወጧቸውም ነው የሚያስታውሱት፡፡
ችግሩ እንዳሰቡት ሊስተካከል ባለመቻሉ ጉዳዩን ወደአደራጃቸው የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የወረዳ አራት አስተዳደር የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽሕፈት ቤት ይወስዱታል፡፡ በወቅቱም ወረዳው ሥራ እንደሚሻላቸው እንዳማከራቸውና አባላቱም እንዳነጋገሯቸው ይገልፃሉ፡፡ ሆኖም ግን መሻሻል ሊመጣና ማህበሩን ከመነሻቸው በታሰበው ደረጃ ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት የሁሉም ርብርብ ሳይታከልበት ይቀራል:: ይልቁንም ማህበሩ ከሥራ ይልቅ የብጥብጥና ሁከት ቀጣና ይሆናል፡፡
ማህበሩ ያለመግባባት ችግሮች እንደሚቀረፉና ሁሉም የማህበሩ አባል ሠርቶ የመለወጥ ተስፋ እንዳለው በማመን የኮንስትራክሽን ሥራ የሚሠራ በመሆኑ ለሥራው ቅልጥፍና የሚረዳውን ተሽከርካሪ ለመግዛት ያቅዳል:: ለዚህም ያግዛቸው ዘንድ በድጋሚ ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም 200 ሺህ ብር ይበደራሉ፡፡ ብድር ወስደው ተሽከርካሪውን ለመግዛትና ሕልማቸውን ዕውን ለማድረግ ደፋ ቀና በሚሉበት ብድር በወሰዱበት በሁለተኛው ቀን ግን የድርጅቱ የ140 ሺህ ብር ኮምፓክተር፣ ሚክሰርና መበየጃ ማሽን ንብረት የመዘረፍ ዱብ ዕዳ ያጋጥማቸዋል፡፡
ዝርፊያው እንደታወቀ የፀጥታ አካላት በቦታው ተገኝተው ቤቱ እንደተፈተሸ የሚገልጹት አቶ በለጠ፤ አሻራ ሲነሳ የድርጅቱ ጥበቃዎችም ተሳታፊ እንደሆኑ እንደተደረሰበት ይናገራሉ፡፡ ፖሊስ አሻራ ሲያነሳ የወታደር ጫማ በጠረጴዛው ላይ እንደተገኘና ንብረቱ በተሽከርካሪ ተጭኖ እንደተወሰደ ይደረስበታል፡፡ በወቅቱ ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት በማህበሩ በጥበቃ ሥራ ላይ ይሠራ የነበረው ግለሰብ አካባቢ ይታወቅ ስለነበር ወደ ጎጃም በማቅናት አራት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደቻሉ ያብራራሉ፡፡ ሆኖም ግን ባልታወቀ ሁኔታ በዋስ ወጡ በሚል ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንደተመለሱ ይሰማሉ፡፡
በሥራቸው ላይ ያጋጠማቸው ችግር ወደ ኋላ ሳይጎትታቸው ለተሽከርካሪ ብለው የወሰዱትን ብድር የተዘረፉትን ዕቃዎች ለማሟላት ይጠቀሙበታል፡፡ ነገር ግን ከማህበሩ አባላት መካከል አቶ ፍቃዱ ገብረሚካኤልና አቶ ሺበሺ ተሾመ የተባሉት ግለሰቦች መበጥበጣቸውን ሊያቆሙ አልቻሉም፡፡ ሁለቱ የማህበሩ አባላት ለሥራው እንቅፋት ሲሆኑ ቆይተው መጨረሻ ላይ ሊወጡ አካባቢ አቶ ፍቃዱ በ2007 ዓ.ም ለአንድ ወር ያክል ቀርተው እንደመጡ ይገልፃሉ፡፡ ሁኔታው ግርታን የፈጠረባቸው የማህበሩ አባላትም በምን ምክንያት እንደቀሩ ጥያቄን ያቀርብላቸዋል:: በሕመም ምክንያት ከሆነም በሕገደንባቸው መሠረት የሐኪም ማስረጃ እንዲያመጡ ይጠየቃሉ፡፡ አቶ ፍቃዱም ለቀረበላቸው ጥያቄ መሥራት እንደማይፈልጉ ያሳውቃሉ፡፡
በሕመም ምክንያት መሥራት እንደማይችሉ የገለፁት የማህበሩ አባልም ለዚህ ማረጋገጫ የሚሆን የሕክምና ወረቀት እንዲያመጡ ይጠይቃቸዋል፡፡ አቶ በለጠ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውሱ፤ ድርጅቱ እስከ አምስት ሺህ ብር የሚደርስ ወጪን እንደሚያሳክም ተቀምጧልና በሕመም ከሆነ በማህበሩ የመታከም ዕድሉን እንዲያገኙ ቢጠየቁም አቶ ፍቃዱ ግን ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ በዚህ መልኩ በሥራው ላይ እኚህ አባል ወጣ ገባ ማለታቸው የረበሻቸው የማሕበሩ አባላት የወረዳ አስተዳደሩን መፍትሔ ይጠይቃሉ፡፡
ለወረዳው የገጠማቸውን ችግር ገልፀው በጠየቁት መሠረት ወረዳውም ጠርቶ ያናግራቸዋል:: ወረዳው የሚጠበቅበትን አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው የሚናገሩት አቶ በለጠ፤ እንቅስቃሴያቸው ጥሩ ሥለነበር ድጋፍ ለማድረግ ቀና ትብብር እንደነበረው ያስረዳሉ፡፡ ችግሩንም ከሥር ከመሠረቱ ስለሚያውቀው ጠርቶ ሲያነጋግራቸው ሥራ እንደሚበዛባቸውና ጫና ስላለባቸው መሥራት እንደማይችሉ ለአስተዳደሩ ያሳውቃሉ፡፡ ይህን ምላሽ በመቀበል መሥራት የማይችሉ ከሆነ በማህበሩ ሕገደንብ ላይ በሰፈረው መሠረት ሰው ከሠራ ብቻ ነው እንዲያገኝ የሚፈቅደው በመሆኑም የማይሠሩ ከሆነ ማሕበሩን ለቅቀው ሊወጡ እንደሚገባ ካልሆነ ደግሞ ከአባላቱ ጋር ተስማምተው ሊሰሩ ይገባል በማለት ምርጫ ያስቀምጥላቸዋል፡፡
ወረዳው ቃለ ጉባዔ ይዞ በየጊዜው ያወያየ ሲሆን፤ ችግሩ ግን ሊቃለል አልቻለም የሚሉት አቶ ሙላት፤ በዚህም ምክንያት የአባላቱ ቁጥር እየተመናመነ እንዲሄድ እንዳደረገውም ያስታውሳሉ፡፡ በዚህም ሰባት ሠዎች ይቀራሉ፡፡ በሁለቱ ግለሰቦች ማስፈራሪያ ቀድሞ ከማህበሩ ለቅቀው ወጥተው የነበሩ አባላት ወረዳው እንዲጠሩ በማዘዙ የትራንስፖርት ወጪያቸው ተሸፍኖ ከክፍለ ሀገር ማህበሩ ወዳለበት አዲስ አበባ እንዲመጡ ማድረጋቸውንም ይገልፃሉ፡፡
ገንዘብ ያዡ፤ ግለሰቦቹም በአቶ ፍቃዱና አቶ ሺበሺ ማስፈራሪያ ይደርስባቸው ስለነበር እንጂ ከሌላው የማህበሩ አባላት ጋር ተስማምቶ የመሥራት ችግር ስላሌለባቸው መመለስ እንደሚፈልጉ በማሳወቃቸው ሁለቱ ግለሰቦች በሕገደንቡ መሠረት ሲሰናበቱ እነርሱ ደግሞ እንዲመለሱ ተደርገዋል ይላሉ፡፡ በወቅቱ በማህበሩ ማቋቋሚያ ሕገደንብ መሠረት እንዲሰናበቱ ሲደረጉ እንዲወጡ ታስቦ ሳይሆን ምናልባትም ይቅርታ ጠይቀው ይመጣሉ ከሚል ተስፋ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በዚህም የማሕበሩ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የነበሩትን አቶ ፍቃዱ ገብረሚኪኤል በ7/1/2007 ዓ.ም ይሰናበታሉ፡፡
አቶ ሺበሺ ተሾመ ብቻቸውን በድርጅቱ ውስጥ ማመጽ እንደጀመሩ ያስታውሳሉ፡፡ በወቅቱ በጋራ መሥራቱ እንደሚሻል ቢነገራቸው ቢለመኑም በጄ አለማለታቸውን ነው የሚያስታውሱት፡፡ ማሕበሩን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረትም ፈቃደኛ ባለመሆን እንቅፋት ሲሆኑ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡ በድጋሜም ወረዳውን ምን ማድረግ ይሻላል? በሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ በግድ ሥሩ ማለት እንደማይቻልና ማሰናበት እንደሚችሉ እንዳሳወቃቸው ይገልፃሉ፡፡እያንዳንዱን እንቅስቃሴያቸውን ለወረዳ እያሳወቁ እንደሚሠሩ የሚናገሩት አቶ በለጠ፤ አቶ ሺበሺ ለሦስት ወራት ቆይተው ወደ ሥራ ሲመለሱ ወረዳው ሲያነጋግራቸው መሥራት እንደማይፈልጉ ያሳውቃሉ፡፡
ወረዳውም እንዲያሰናብቱ ይነግሯቸውና መልቀቂያ ለአቶ ሺበሺ ሲሰጡ ወደ ክፍለ ከተማ እንዳመሩ ይናገራሉ:: አቶ ሺበሺ በተሰናበቱበት በ9/4/2007 ዕለት ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱበት አካውንታቸው መዘጋቱን ይናገራሉ፡፡ግብር ለመክፈል ሲያመሩ ማወቃቸውን የሚናገሩት አቶ በለጠ፤ ማሕበራት ማደራጃ እንዳዘጋው እንደተገለፀላቸው ያስታውሳሉ፡፡
ማሕበራት ማደራጃ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳይኖር እንዴት መዝጋት ይችላል? ማህበሩን የሚቆጣጠረው ገቢዎች ሆኖ ግብር ከፋይ የሆነን ማህበር እንዴት ሊዘጋው ቻለ? የሚል ጥያቄ አንስተው በደብዳቤ ቢጠይቁም ሊከፈት እንደማይችል ምላሽ እንደተሰጣቸው ይናራሉ፡፡ በቅድሚያ ግለሰቦቹ የወጡበትን ምክንያት መፈተሽ ይገባል በሚል አስተያየት ቢሰጡም የሚመለከታቸው አካላት ግን ጉዳዩን በሚገባ ሳይመረምሩ ውሳኔውን ያሳርፋሉ፡፡
ጉዳዩ በሽምግልና መታየት ሲጀመር ደግሞ የእነርሱ ሽማግሌዎች ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ብዙ ጊዜ ተቀያይረዋል፡፡ በስተመጨረሻም ለወራት ቆይቶ ወደ ማህበሩ የመጣ ግለሰብ በራሱ ጊዜ የለቀቀ ሠው ጉዳይ ማየት ተገቢ ባይሆንም በማህበሩ ያለውን ድርሻ እንዲወስድ ማድረግ ነው የሚሻው የሚል ሐሳብ ይነሳል፡፡ በዚህም ማህበሩ ኦዲት ይደረግ በሚል ወደ ማህበራት ማደራጃ ኦዲተር ይላካል፡፡ ሥራ አስኪያጇም ጉዳዩን ይዛ ስትሄድ ማህበሩን ኦዲት የሚያደርገው ገቢዎች እንጂ ማሕበራት ማደራጃ እንዳልሆነ ይገለጽላቸዋል፡፡
ማህበራት ማደራጃ ከግብር ነፃ የሆኑ ኦዲት የማድረግ ሥልጣን እንዳሌላቸው ይነገራቸዋል፡፡ ይህንን ምላሽ በመያዝ ገቢዎች ጽህፈት ቤት በማቅናት ጉዳዩን ሲያሳውቁም ማህደራቸው ያለው በጽሕፈት ቤቱ በመሆኑ ማህበራት ማደራጃ እንደማይመለከተው ይነገራቸዋል፡፡ ግብር ካልከፈሉ ንግድ ፈቃድ እንደማይታደስላቸው፤ ይህ ካልሆነም ቤተሰባቸው እንደሚራብ ገልፀው ይጠይቃሉ፡፡ ይህንን የገቢዎች ጽሕፈት ቤት ምላሽ በመያዝ ወደ ማህበራት ማደራጃ ለሽምግልና ዳኞች ሲያሳውቁ ከድርጅቱ አምስት ሺህ ብር ወጪ ተደርጎ ኦዲት ተደርጎ እንዲቀርብ ያዝዛሉ፡፡
ከብዙ ምልልስ በኋላ ገንዘብ ወጪ አስደርጎ ኦዲት ለማስደረግ በመቸገራቸው ለወረዳው ጭምር ጥያቄ ማቅረባቸውን አቶ በለጠ ይናገራሉ፡፡ ሁለቱ ግለሰቦች ያለአግባብ ከወጡ ወደ ማህበሩ ይመለሱ፡፡ በአግባቡ ከሆነም የሚገባቸው ድርሻ ወስደው ይውጡ በሚል እንዲወሰን ይጠይቃሉ፡፡ በዚህ መሐል በሽምግልና ዳኛ ሲታይ የቆየው ጉዳይ 2009 ዓ.ም በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ ችሎት አፈፃፀም መላኩን ይናገራሉ፡፡
ፍርድ ቤት ሳይመረምረው እንዴት ሊያየው ይችላል? በሚል የሕግ ባለሞያ ቀጥረው ጉዳዩን ሲከታተሉ ይቆያሉ፡፡ ማህበሩ ኦዲት ሳይደረግ የተሠራው ብር ሰፍሮ አንድ ሚሊየን ብር ለሁለቱ ግለሰቦች እንዲሰጥ ተወስኗል፡፡ ይህም ግብር ሳይገበር የወሰዱት ብር ተቀናሽ ሳይደረግ ከማህደራቸው ሳይታይ ይህን መሰል ውሳኔ ማረፉ ትክክል እንዳልሆነም ገንዘብ ያዡ ይናገራሉ፡፡
በወጣው አፈፃፀም መንግስት በዕጣ የሰጣቸው የጋራ መኖሪያ ቤት ተሸጦ እንዲከፈል ይወስናል፡፡ በዚህም የቀን ጨለማ ሆኖባቸው ቤተሰባቸው ሁሉ መረበሻውን ይገልፃሉ:: ውሳኔው አለአግባብ በመሆኑ ይግባኝ በማለት ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረባቸውን ይናገራሉ፡፡ ፍርድ ቤቱም ይግባኝ አያስቀርብም በሚል ይወስናል፡፡ ጠበቃቸውም ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጊዜውን በማሳለፉ በአፈፃፀም ላይ ይግባኝ ይጠይቃሉ፡፡
ቤታቸውን ለማትረፍ ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያቀርባሉ፡፡ በዚህም የማህበሩ ንብረት ከሌለ ቤታቸው ተሸጦ እንዲከፈል በማለት ተወስኖባቸዋል፡፡ የተወሰነው ውሳኔም ግርታን የሚፈጥር እንደሆነ ያነሳሉ:: ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም የመጀመሪያው ውሳኔ ትክክለኛ እንደሆነ ወስኗል፡፡ ውሳኔው ያረፈው በማህበሩ ላይ ቢሆንም በግል ያፈሩት ንብረት ላይ ወደ ግለሰብ ዞሮ ቤት ተሸጦ እንዲከፈል መወሰኑ ግን ቤተሰባቸውን እንዳሳዘነ ይናገራሉ፡፡
በሌላ በኩል ሥራ ካቆሙ ቆየት ያሉ ቢሆንም የማህበሩ አካውንት የተዘጋው በ2007 ዓ.ም ቢሆንም የግብር ዕዳው ግን ተወዝፎ 680 ሺህ ብር ዕዳ እንዳለ ገቢዎች አሳውቋል:: አካውንቱ ሲዘጋ ማህበሩ ካለው ብር ላይ የመንግስት ዕዳ ለመክፈል ቢጠይቁም ሰሚ ማጣታቸውን ይናገራሉ፡፡ ከሳሾች ያልሰሩት ቤት ተሸጦ እንዲከፈላቸው መፈለጋቸው በእጅጉ አሳዛኝ ነው ይላሉ፡፡
ሰነዶች
ጌሴም ኮንስትራክሽን ግንባታና ግብዓቶች ምርት ኃላፊነቱ የተወሰነ ሕብረት ሥራ ማህበር በሚል የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ በኅብረት ሥራ ማህበር ለሚደራጁ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሞዴል መተዳደሪያ ደንብ ከሰነዶች መካከል ለመመልከት ችለናል፡፡ በእነዚህ ሰነዶች የአባላቱ መብትና ግዴታን ጨምሮ የተለያዩ አስፈላጊ ማስረጃዎች ተካትተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተደራጅተው ወደ ሥራ ሲገቡ 10 የማህበሩ አባላት ወይዘሮ አሰፋሽን በሥራ አስኪያጅነት አቶ በለጠን ደግሞ ገንዘብ ያዥ አድርገው የመረጡበት ቃለጉባዔ ይገኛል፡፡ በቃለጉባዔው ላይ በማህበሩ አመራሮች በኩል ዝምድና ወይንም ትዳር መኖሩን አውቀው እንደተስማሙ በፊርማቸው ማረጋገጣቸውንም ይነበባል፡፡
በቀን 28/02/2005 ዓ.ም ማህበሩ ተሰብስቦ የያዘውን ቃለጉባዔ ተመልክተናል፡፡ በዚህም አቶ አስፋው ሽፈራውና አቶ ሺበሺ ተሾመ ተጣልተው እንደነበር በመጥቀስ፤ አቶ ሺበሺ ባደረጉት የመግደል ሙከራ ማህበሩ ግራ ቀኙን አይቶ በአጥፊው ላይ ውሳኔ መስጠቱን ያሳያል፡፡ በውሳኔውም ለማህበሩ አንድ ሺህ ብር እንዲሁም ለተጎጂው አቶ አስፋው አንድ ሺህ ብር ካሳ እንዲከፈል በመወሰን ተስማምተው እንዲታረቁ መደረጉን አስቀምጧል፡፡ በዛው ዕለት በድጋሚ የወጣው ደብዳቤ እንደሚያሳየው ደግሞ አቶ ሺበሺ በማህበሩ አባል አቶ አስፋው ላይ ባደረሱት ድብደባና በፊርማ ማጭበርበር የአባላቱ ጠቅላላ ጉባዔ ተስማምቶ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንዲሰጣቸው መወሰኑን ያሳያል፡፡
በቀን 17/03/2005 ዓ.ም አቶ ሺበሺ ለማህበሩ ይቅርታ የጠየቁበት ደብዳቤ ይገኛል፡፡ በደብዳቤያቸው በቀን 28/02/2005 ዓ.ም የማህበሩ አባል የሆኑትን አቶ አስፋው ሽፈራው ላይ ባደረጉት ድብደባ በሕግ ቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር ገልፀዋል፡፡ በወቅቱም የማህበሩ ገንዘብ ያዥ አቶ በለጠ ዋስ ሆነዋቸው ከደንበል ፖሊስ ጣቢያ መለቀቃቸውን በጽሑፋቸው አብራርተዋል፡፡ ማህበሩም በጠቅላላ ጉባዔ ጥፋተኛ እንደሆኑ በመወሰን ይቅርታ ጠይቀው እንዲታረቁ ቢያደርጓቸውም በእርቅና ቅጣት ደብዳቤው ላይ ግን በስህተት ከፊርማቸው ጎን ጥያቄ ምልክት በማስፈራቸው ማህበሩ በሌላ ደብዳቤ እንዲያስፈርማቸው መጠየቃቸውን ያሳያል፡፡
በቀን 23/01/2006 ዓ.ም ከጌሴም ኮንስትራክሽን የህብረት ሥራ ማህበር ለአቶ ፍቃዱ የተሰጠ የመጨረሻ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ከሰነዶች መካከል ይገኛል:: በደብዳቤው አቶ ፍቃዱ የማህበሩ መስራች አባል መሆናቸውንና ከዚህ ቀደም የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ
ደርሷቸው እንደነበር ያትታል፡፡ ይሁን እንጂ በተደጋጋሚ ከስብሰባና ከሥራ ከመቅረት ድርጊታቸው አለመመለሳቸውን በመጥቀስ፤ ጠቅላላ ጉባዔው ተሰብስቦ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንዲሰጣቸው መወሰኑን አስፍሯል፡፡
በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ቂርቆስ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በቀን 9/4/2006 ዓ.ም በመዝገብ ቁጥር ቂ/ክ/ከ/አግ/2/49955/06 ወጪ አድርጎ ለክፍለ ከተማው ንግድና ኢንደስትሪ ልማት ጽሕፈት ቤት የላከው ደብዳቤ ሌላው የተመለከትነው ሰነድ ነው፡፡ በዚህም በግብር ከፋይ መለያ ቁጥር 0021111945 የሚታወቀው ማህበሩ ለንግድ ፈቃድ ዕድሳት የግብር አከፋፈል የምስክር ወረቀት እንደተሰጠው ያመለክታል፡፡ በዚህም የ2006 ዓ.ም የግብር ዘመን ፈቃዳቸው እንዲታደስ ሲል ይገልፃል፡፡
ማህበሩ በቀን 7/01/2007 ዓ.ም የጻፈው ደብዳቤ ደግሞ ለአቶ ፍቃዱ ስንብት መሰጠቱን ያሳያል፡፡ ግለሰቡ አመጽ በመፍጠር፣ የተጭበረበረ ሰነድ በማምጣት ማህበሩን ለማታለል በመሞከር፣ ለማህበሩ ሕገደንብ ባለመገዛትና የተሰጣቸውን የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ አልቀበልም በማለታቸው የማህበሩ ጠቅላላ ጉባዔ ግለሰቡን በመምከርና በመቅጣት መቆየቱን ያወሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የማህበሩን አባላት በተናጠል በመሰብሰብ ሴራ በመጠንሰስ ማህበሩን ለማፍረስ ከሕግና ደንብ ውጪ 70 በመቶ ድርሻ ክፍፍል እንዲደረግ 30 በመቶ ደግሞ እንዲቀመጥ ይህ ካልሆነ ግን ለቅቀው እንደሚወጡ አመጽ ለማንሳት ማስተባበራቸው በመረጃ እንደተደረሰበት ያብራራል፡፡
የወረዳ አራት አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ባሉበት ከማህበሩ የወጡ አባላቶችም የምስክር ቃላቸውን መስጠታቸውንም ደብዳቤው ያሳያል፡፡ በመሆኑም ግለሰቡ ከማህበሩ እንዲሰናበቱ ጠቅላላ ጉባዔው በቃለ ጉባዔ መወሰኑን በመግለጽ፤ በማህበሩ ያላቸውን የአክስዮን ድርሻ ለመካፈል የመጨረሻ ትርፍ ክፍፍል ከኦዲት ሪፖርት በኋላ ስለሚፈፀም በውጪ ሆነው እንዲከታተሉ ሲል አስቀምጧል፡፡
የወረዳው ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽሕፈት ቤት ለክፍለ ከተማው ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽሕፈት ቤት በቁጥር ቂ/ክ/ከ/ጥ/አ/ኢ/ል/ጽ/ቤት00352288/2007 በቀን 7/01/2007 ዓ.ም የላከው የትብብር ደብዳቤ ሌላው ማህበሩን አስመልክቶ ከተመለከትናቸው ሰነዶች መካከል ነው፡፡ ደብዳቤው ከማህበሩ ከተሰናበቱት አባላት መካከል የአቶ ሺበሺ ጉዳይ ወደ ትግል ለፍሬ የልማት ቡድን ቀርቦ ለሁለት ቀናት ስብሰባ ተደርጎበት እንዲሰናበቱ መደረጉን ያብራራል፡፡ ይህን ተከትሎ ሁለቱ አባላት ለኅብረት ሥራ ማህበራት ማደራጃ ጽሕፈት ቤት በመሰረቱት ክስ መሠረት የክፍለ ከተማው ኅብረት ሥራ ማህበራት ማደራጃ ጽሕፈት ቤት በቀን 9/04/2007 ዓ.ም በቁጥር ቂ/ክ/ከ/ህስማ/አስ/1000/2007 ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፊንፊኔ ቅርንጫፍ በተፃፈ ደብዳቤ የማህበሩ የባንክ ሒሳብ እንዳይንቀሳቀስ መደረጉን ጽፏል፡፡
ጽሕፈት ቤቱ ለወረዳው ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽሕፈት ቤት ሳያሳውቅ ብሎም የማህበሩን መተዳደሪያ ሳያገናዝብ ይህን መሰል ውሳኔ መውሰዱ ትክክለኛ አለመሆኑን ደብዳቤው በግልጽ አስፍሯል፡፡ በዚህ ውሳኔም የተለያዩ ተያያዥ ችግሮች መፈጠራቸውን ጠቅሶ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ መጠየቁ ከደብዳቤው ይነበባል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ማህበሩ የክፍለ ከተማውን ማህበራት ማደራጃ ጽሕፈት ቤት የባንክ ሒሳቡ እንዲከፈትለት መጠየቁን የሚያሳዩ ደብዳቤዎችንም ተመልክተናል፡፡
በ02/4/2007 ዓ.ም የልማት ቡድን ስብሰባ እንዳደረጉ የሚያሳይ ቃለጉባዔ ከሰነዶቹ መካከል ይገኛል፡፡ ቃለጉባዔው አቶ ሺበሺ ተሾመ ለሦስት ወራት በሥራ ላይ እንዳልተገኙ ያስረዳል፡፡ ወደ ሥራ እንዲገቡም የማህበሩን አመራር በማነጋገር የተሞከረ ቢሆንም እርሳቸው ግን በሥራ ገበታቸው ላይ ዳግም ባለመገኘታቸው ማህበሩ እርምጃ እንዲወስድ በማለት የልማት ኮሚቴው መወሰኑን ያመለክታል፡፡
የወረዳ አራት ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽህፈት ቤት በቁጥር ቂ/ክ/ከ/ወ/4/ጥ/አ/ኢ/ል/ጽ/ቤት00351079/2007 በቀን 24/04/2007 ዓ.ም ለኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት ከማህበሩ የለቀቁ አባላትን አስመልክቶ የላከው ደብዳቤ ነው፡፡አባላቱ በቃልና በጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ለማኅበሩ ሕገደንብ ተገዢ ባለመሆናቸው ከማህበሩ አባልነት ያስለቀቋቸው መሆኑን አብራርቶ ለተቀሩት አባላት አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግላቸው መጠየቁን ያመለክታል፡፡
በቁጥር ቂክከ/ህስማ/አስ/1000/2007 በቀን 9/04/2007 ዓ.ም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ንግድና ኢንደስትሪ ልማት ጽሕፈት ቤት ህብረት ሥራ ማህበራት ማደራጃ ማስፋፊያ ዋና የሥራ ሂደት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፊንፊኔ ቅርንጫፍ የላከው ደብዳቤ ከሰነዶች መካከል ይገኝበታል:: በደብዳቤው በማህበሩ አባላት መካከል አለመግባባት ስለተፈጠረ ችግሩ እስኪፈታ ድረስ ከገቢ በቀር የማህበሩ ሒሳብ ወጪ እንዳያደርጉ በጊዜያዊነት የባንክ ሒሳብ እንዲታገድ መጠየቁ ይነበባል፡፡
በቀን 30/4/2007 ዓ.ም በቁጥር 040/3/15519 በንግድ ሚኒስቴር ለንግድ ማህበራት ሥያሜ ማጣሪያና የንግድ ሥም ማሻሻያ በኢፌዴሪ የፍትሕ ሚኒስቴር ለሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት በሚል ያገኘነው ሌላው ሰነድ ነው፡፡ በዚህም የአመልካች ሥም አሰፋሽ በለጠ እና ጓደኞቻቸው ኮንስትራክሽንና ግብዓት ምርት ኅብረት ሽርክና የሚል ሲሆን፤ የንግድ ድርጅት አቋም የኅብረት ሽርክና ማሕበር እንደሆነ ያሳያል፡፡ በዚህም የማህበር ሥም ማሻሻያ ማድረጋቸውንም ያመለክታል፡፡
ጥር 5 ቀን 2008 ዓ.ም ማህበሩ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ የፃፉት ደብዳቤ ከሰነዶች መካከል ተመልክተነዋል:: በደብዳቤው ማህበሩ ከተደራጀበት 2002 ዓ.ም ጀምሮ የነበሩትን ሒደቶችና በሁለት አባላቱ ላይ የነበረውን የስንብት ሂደት ተብራርቷል፡፡ በዚህም አቶ ፍቃዱ የስንብት ደብዳቤ እንደደረሳቸውና በመቀጠል ደግሞ አቶ ሺበሺ ለሦስት ወራት በሥራ ላይ ባለመገኘታቸው የወረዳ አራት ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽሕፈት ቤት በ14/12/2006 ዓ.ም ጉዳዩን ትግል ለፍሬ ልማት ቡድን እንዲያየው አስተላልፎት እንደነበር ያስረዳል፡፡ በዚህም መሠረት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የሁለቱ አባላት ስንብት እንደተደረገ ያብራራል፡፡
ከማህበሩ የተሰናበቱት አባላት በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ግዴታቸውን ሳይወጡና ቅሬታቸውንም በየደረጃው ሳያሳውቁ ለክፍለ ከተማው ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽህፈት ቤት አቤቱታቸውን በማቅረባቸው በቀን 9/4/2007 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፊንፊኔ ቅርንጫፍ የሚገኘው የማህበሩ የባንክ ሒሳብ እንዲታገድ መደረጉን ማህበሩ ለቢሮው በፃፈው ደብዳቤ አብራርቷል፡፡ ማህበሩ ስንብት የሰጠበት ምክንያት ሳይመረመር ዕግድ መደረጉ ተገቢነት የጎደለው ተግባር መሆኑንም ኮንኖታል፡፡
በተያያዘ በዚህ ሳቢያ የመንግስት ግብር እንዳይከፈል፣ ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም የተወሰደ ብድር እንዳይከፈል፣ የቤት ኪራይ ብሎም የጥበቃና ሌሎች የውሃና መብራት ክፍያዎች መፈፀም እንዳልተቻለ ተገልጿል፡፡ ክፍለ ከተማው ቢጠየቅም ምንም ዓይነት ምላሽ አለማግኘታቸውን በመጥቀስ ቢሮው አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ደብዳቤው ያሳያል፡፡ ቢሮውም ጥያቄያቸውን ተቀብሎ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ለኅብረት ሥራ ማህበራት ዘርፍ የማህበሩን አቤቱታ በመግለጽ አስፈላጊው እገዛ እንዲደረግላቸው መጠየቁ ሰፍሯል፡፡
የወረዳ አራት ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽሕፈት ቤት ለክፍለ ከተማው ንግድ ጽሕፈት ቤት በቁጥር ቂ/ክ/ከ/ወ/4/ጥ/አ/ኢ/ል/ጽ/ቤት0586/2009 ወጪ አድርጎ በቀን 25/04/2009 ዓ.ም ለክፍለ ከተማው ንግድ ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ መላኩን ከሰነዱ ተመልክተናል፡፡ በደብዳቤው በጽሕፈት ቤቱ የተደራጀው ማህበሩ የባንክ ሒሳቡ በመታገዱ ምክንያት የግብር፣ የብድርና ቁጠባ፣ የውሃና መብራት እንዲሁም የሼድ የመንግስት ዕዳዎችን ለመክፈል እንዳልቻሉ በመግለጽ፤ የባንክ ሒሳባቸው እንዲከፈትላቸው መጠየቃቸውን ይገልፃል፡፡ በመሆኑም ወቅቱ የንግድ ፈቃድ እድሳት የሚደረግበት በመሆኑ የማህበሩን ችግር ከግንዛቤ በመክተት እንዳይቀጡና አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግላቸው ማሳወቁን ደብዳቤው ያመለክታል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ለክፍለ ከተማው ንግድ ጽሕፈት ቤት ሥራ ኦዲት፣ኢንስፔክሽንና ሕግ ዋና የሥራ ሒደት በመዝገብ ቁጥር 076/5/1/17 በቀን 09/10/2009 ዓ.ም ማህበሩ የገጠመው ችግር በሽምግልና ዳኞች ሲታይ ቆይቶ ሕዳር 5 ቀን 2009 ዓ.ም የሽምግልና ዳኞች ያስተላለፉት ውሳኔ ቅሬታ የፈጠረበት ማህበሩ አቤቱታ ማቅረቡን በመጥቀስ ቢሮው ምላሽ የሚፈልግባቸውን ዝርዝር ነጥቦች ጠቅሶ መጠየቁ ይታያል፡፡
በቀን 7/11/2009 ዓ.ም በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የማህበሩ ጠበቃ የጻፉት ደብዳቤ ይገኝበታል፡፡ ደብዳቤው በፍርድ ባለዕዳ ማህበሩና የፍርድ ባለመብት እነ አቶ ፍቃዱ መካከል ስለነበረው የሥራ ክርክር ያብራራል፡፡ በዚህም የቂርቆስ ምድብ ፍርድ አፈፃፀም ችሎት ሐምሌ 7 ቀን 2009 ዓ.ም በማህበሩ ሥም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፊንፊኔ ቅርንጫፍ የተቀመጠ ገንዘብ ለፍርድ ባለመብቶች ወጪ ሆኖ እንዲከፈል በሚል ሕገወጥ ውሳኔ መሰጠቱን ያብራራል፡፡
ውሳኔው ከገቢ ግብር አዋጅና ተጨማሪ እሴት ታክስ አንፃር ሲታይ ከግለሰብ ባለዕዳዎች በፊት የመንግስት የግብር ዕዳ እንደሚቀድም እየታወቀ የፍርድ ባባመብቶችም የመንግስት ዕዳ ያለባቸው መሆኑን እየታወቀ ግብር ዕዳ ሳይከፈል ችሎቱ በባንክ ያለው ገንዘብ ወጪ ሆኖ እንዲከፈላቸው መወሰኑ ሕግን ያልተከተለ ነው በማለትም እንደተቸው በደብዳቤው ይነበባል፡፡ ስለሆነም ጽሕፈት ቤቱ ገንዘቡ እንዳይከፈል የዕግድ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ሲሉ መጠየቃቸው ይታያል፡፡
ሐምሌ 11 ቀን 2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለማህበሩ የላከው ደብዳቤ ከተመለከትናቸው ሰነዶች መካከል ሌላው ነው፡፡ ደብዳቤው በቀን 07/11/2009 ዓ.ም በቁጥር የኮ/መ/ቁ.40569 ከፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደደረሰው አስፍሯል፡፡ በዚህም የፍርድ ባለመብት አቶ ፍቃዱ ገብረሚካኤልና አቶ ሺበሺ ተሾመ በሐምሌ 07 ቀን 2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት 159 ሺህ 135 ብር ወጪ ተደርጎ እንዲከፈላቸው በመወሰኑ ባንኩ ክፍያውን ከመፈፀሙ በፊት ማህበሩ አስተያየቱን በሦስት ቀናት ውስጥ እንዲያሳውቅ መጠየቁ ያመለክታል፡፡
ሌላኛው ወገን
ቅሬታ የቀረበባቸውን ግለሰቦች ለማነጋገር ባደረግነው ጥረት አቶ ፍቃዱን ያገኘናቸው ሲሆን፤ አቶ ሺበሺ ግን የግል ስልክ ስላሌላቸው ልናገኛቸው እንደማንችል ገልፀውልን በማህበሩ ውስጥ የነበረውን ሁኔታ ነግረውናል፡፡ በዚህም 2007 ዓ.ም ከሥራ እንዳባረሯቸው ይናገራሉ፡፡ ባልና ሚስት አለአግባብ በሥልጣናቸው በመጠቀም የማህበሩን አባላት እንዳባረሩና በድርጅቱ የነበሩ ንብረቶችንም በግላቸው ጠቅልለው ይጠቀሙም እንደነበር ነው የሚያስረዱት:: በድርጅቱ ንግድ ፈቃድ ከአዲስ አበባ ውጪ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎችም ሥራዎችን ይሠሩና ትርፋማ እንደነበሩም ይገልፃሉ፡፡ ማህበሩ ኦዲት ይደረግ በሚል በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ምላሻቸው ግን እንቢታ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
ማህበሩን በግል ጠቅልለው ለመያዝ በነበራቸው ከፍተኛ ፍላጎት ያለአግባብ ሥራ አስኪያጇ ከሥራ እንዳሰናበቷቸው ያስታውሳሉ፡፡ በዚህም በሕግ ለመጠየቅ እንደተገደዱ ይገልፃሉ፡፡ ማህበሩ ሰባት ሚሊየን ብር አካባቢ በግንባታ ሥራዎች ሠርቶ እንዳገኘና ለሥራቸው ይጠቀሙባቸው የነበሩ የተለያዩ የኮንስትራክሽን ዕቃዎችን በማከራየትና በመሸጥ ሥራ አስኪያጇና ገንዘብ ያዥ ማለትም ባልና ሚስት በግላቸው ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
ሁኔታው ያልተስማማቸው አቶ ፍቃዱ በክፍለ ከተማ ደረጃ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽሕፈት ቤት አመራሮችና ከፍተኛ የክፍለ ከተማው አመራሮች በተገኙበት በነበረው ሥብሰባ ላይ ችግራቸውን የተነፈሱት አቶ ፍቃዱ ሰኞ ዕለት ወደ ሥራ ሲመለሱ ከሥራ እንደተሰናበቱ እንደተገለፀላቸው ይናገራሉ፡፡ ትልልቅ የመንግስት ተቋማትን ጨምሮ ከፍተኛ ፕሮጀክቶችን ወስደው ይሠሩ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ፍቃዱ፤ በሥራው ላይ ጥያቄ ማንሳትም ሆነ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይፈቅዱላቸው ነው የሚናገሩት፡፡
በማህበሩ ሥም የተለያዩ በሚሊየን ብሮች የሚቆጠሩ ገቢዎች ሁለቱ ግለሰቦች ለግላቸው ማዋል እንደጀመሩ፤ በማህበሩ ጥቅም ያጡት አቶ ፍቃዱና አቶ ሺበሺ የሚጎርሱት አጥተው ያስተዳድሯቸው የነበሩት ቤተሰቦች ዳቦ መጉረስ ጀምረው በማጣታቸው ድንጋይ መሸከም እንዲሁም ጥበቃ ሥራዎችን መሥራት ጀምረው እንደነበር በሐዘን ይናገራሉ፡፡
ጉዳዩ በሕግ ከመያዙ በፊት በግልግል ዳኝነት ውሳኔ ሲሰጥ ወደ ማህበሩ እንደማይመልሷቸው እንዲሁም ኦዲት እንደማይደረግም እንዳሳወቁ ይናገራሉ፡፡ በማህበሩ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ባለመኖሩ ባልና ሚስቱ ከሥልጣናቸው ወርደው ድጋሚ የአመራር ምርጫ እንዲደረግ አስተያየት ቢሰጥም አምባገነን ሆነው ሐሳቡን ሊቀበሉ ፈቃደኛ እንዳልነበሩ ያስታውሳሉ፡፡
ወይዘሮ አሰፋሽና አቶ በለጠ በጋራ ሆነው ያለአግባብ እንዳባረሯቸው ፤ በወቅቱ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁት አቶ ሺበሺ፤ አቶ ፍቃዱ ምንም እንዳላጠፉ መናገራቸው ለእርሳቸው መባረርም የባልና ሚስቱን ከንፈር አስነክሶ እርሾ እንዳስቀመጠ ይናገራሉ፡፡ በስተመጨረሻም ጉዳዩ ወደ ሕግ ሄዶ እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደርሶ ውድቅ እንደተደረገባቸው ይናገራሉ፡፡ በፍርድ ቤቶቹ ምንም ዓይነት ገቢ ስላልነበራቸው ጠበቃ ሳያቆሙ በራሳቸው ክርክሩን ሲያደርጉ እንደነበር ይገልፃሉ፡፡
በማህበሩ ገና ሲደራጁ ሁለቱ ግለሰቦች ባልና ሚስት እንደነበር ያውቁ እንደነበርና ይህም ተማምነው እስከሰሩ ድረስ ችግር እንዳሌለው አምነው መግባታቸውን ይናገራሉ:: ሲሚንቶ እየተሸከሙ ሌት ተቀን ጥበቃ እየሠሩ ይኖሩ እንደነበር በሐዘን የሚናገሩት አቶ ፍቃዱ ሠው ሊሳሳት ይችላል፡፡ ነገር ግን ከማህበሩ ያባረሯቸው ከሥራ ቀርተው ሳይሆን በአምባገነንነት ማህበሩን ለብቻቸው ጠቅለለው ለመያዝ ከነበራቸው ፍላጎት ነው፡፡
አጥፍተው ቢሆን እንኳ አፈር ግጠው ባቋቋሙት ማህበር ላይ ድርሻቸው ተሰጥቷቸው ሊባረሩ ሲገባ ምንም ዓይነት ሣንቲም ወደ ኪሳቸው ሳይገባ እንዳባረሯቸው ይናገራሉ፡፡ ከሥራ ከማባረር በፊት ማስጠንቀቂያ ደብዳቤዎችና የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት ቢኖርበትም የእርሳቸው መባረር ዜና ግን ይህን ያላሟላና ታሳድማለህ የሚል አጥጋቢ ያልሆነ ምላሽ እንደሆነም ነው የሚጠቁሙት፡፡ ሁሉም ችግር በመነጋገር መፍታት እየተቻለ ይህን ከማድረግ ይልቅ ከሕገደንብ ውጪ በግለሰብ ፍላጎት በመባረራቸው በሕጉ መሠረት ወደሚመለከተው አካል ሄደው አቤቱታቸውን ማሰማታቸውን ይገልፃሉ፡፡
ሌሎቹ የማህበሩ አባላትም በሁለቱ ግለሰቦች ተማርረው ለመውጣት እንደተገደዱ ይገልፃሉ፡፡ ከማህበሩ በጠፋ ንብረት ሳቢያም ከማህበሩ አባላት መካከል አንዱ ለ12 ቀናት ተጠርጥሮ በእስር ቆይቶ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ነገር ግን በድርጊቱ ዋነኛ ተዋናይ የነበሩትን ጥበቃ ያመጡት የማህበሩ ገንዘብ ያዥ አቶ በለጠ እንደነበሩ ይጠቁማሉ፡፡ ንብረቱ ከጠፋ በኋላም ጥበቃውን ለማምጣት ወደ ባህር ዳር እንደሄዱ መሰማቱን ይገልፃሉ፡፡ ለዚህም ከማህበሩ 33 ሺህ ብር ወጪ መደረጉን ይናገራሉ፡፡ የሆነው ነገር ሁሉ ባለመግባባት ተቋጨ እንጂ መጀመሪያ በግልግል ዳኝነት ሁሉ ችግሩን ለመፍታት ተሞክሮ ነበር፡፡
በዳኝነቱ ወቅት እነ ወይዘሮ አሰፋሽን በመወከል የተለያየ ሽማግሌ መቀያየሩን ይጠቁማሉ፡፡ አንዱ የእነርሱ ሽማግሌ ጉዳዩን ተመልክተው አለአግባብ እንደተባረሩና በደል እንደደረሰባቸው በመገንዘባቸው እጃቸውን እንዳወጡ ይገልፃሉ፡፡ በዚህ መልኩ ለዓመታት ጉዳዩ ሲታይ ነበር፡፡ለዚህም ደግሞ አንዱ ምክንያት በድብቅ ይሠሩ የነበሩት ሥራ ስለነበር ሲቀሩና ሲገኙ በመቆየታቸው ነው ይላሉ፡፡
በማህበሩ ተጠቅመው የሠሯቸው ቤቶችም እንዳሉ የሚናገሩት አቶ ፍቃዱ፤ ማህበሩ ሲመሰረት 200ሁለት መቶ ብር ብቻ እንዳላቸው አስመዝግበው እንደተደራጁ ያስታውሳሉ፡፡ በወቅቱ ከፍ ያለ አንድ ሺህ ብር እንዳላቸው ገልፀው ያስመዘገቡት እርሳቸው ብቻ እንደነበሩ፤እነርሱን ከማህበሩ ካባረሩ በኋላ ባገኙት ገንዘብ ከአዲስ አበባ ውጪ ክፍለ ሀገር ላይ አንድ ቤት ለመሥራት እንደቻሉና በአዲስ አበባም የጋራ መኖሪያ ቤት ባለቤት መሆን እንደቻሉ ይናገራሉ፡፡
ባልታደሰ ንግድ ፈቃድ ሲሠሩ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ፍቃዱ ማህበራት ማደራጃ ሲያግደው ሌላ የባንክ ሒሳብ ከፍተው ገንዘብ ሲያወጡና ሲያስገቡ እንደነበርም ይናገራሉ፡፡ የድርጅቱ ንግድ ፈቃድ ባለመታደሱ እንዲቆም ተደርጓል፡፡ ለገቢዎችም የጋራ ዕዳ አለብን በሚልም ሥራ አስኪያጇ መጠየቃቸውን ይናገራሉ፡፡
ዕዳው የጋራ እንደሆነ ሁሉ ትርፉም የጋራ መሆኑን ግን ከግንዛቤ አለማስገባታቸውን ይገልፃሉ፡፡ ሕግም የግራ ቀኙን ክርክር አድምጦ፣ የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮና አስፈላጊውን ማጣራት አድርጎ ግለሰቦቹ በጉልበት የወሰዱትን ገንዘብ ነው እንዲመልሱ ያደረገልን ይላሉ፡፡
ጉዳዩ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በኅብረት ሥራ ማህበራት ማደራጃ በሽምግልና ዳኝነት ታይቶ ውሳኔ ከተሰጠበት በኋላ በፌዴራሉ የተለያየ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ቀርቧል፡፡ እኛም ከሽምግልና ዳኝነቱ እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያረፉ ውሳኔዎች ምን ይላሉ? በውሳኔዎቹ ላይስ የሕግ ባለሞያ አስተያየት ምንድን ነው? በሚልና የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ የሚኖረንን ዘገባ በቀጣይ ዕትማችን ይዘን እንደምንቀርብ ለክቡራን አንባቢዎቻችን እንገልፃለን፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 21/2012
ፍዮሪ ተወልደ