* ከደረጃ በታች የሆኑ 13 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ተዘግተዋል
* ከ4 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች ችግሮቻቸው እንዲስተካከሉ ተደርጓል
አዲስ አበባ ፦ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ለቅሬታ መንስኤ የሆኑ ችግሮችን በመለየት እየፈታ መሆኑን ገለፀ፡፡ ባለስልጣኑ በ440 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ላይ የአንድ ወር የሱፐርቪዥን በማካሄድ በ 13 ቱ ላይ የመዝጋት እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡ በቅድመ ምርመራ የቴክኒክ ብቃታቸው ያተረጋገጡ ከአራት ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችም እንዲያስተካክሉ አድርጌያለሁ ብሏል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ያደታ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት በአገሪቱ ያሉ 536 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ውስጥ በ440 ዎቹ ላይ የአንድ ወር የሱፐርቪዥን ስራዎችን በመስራት በ13ቱ ላይ የመዝጋት እርምጃ የተወሰደ ሲሆን በተቀሩት ላይም ከመጀመሪያ ደረጃ ማስጠንቀቂያ ጀምሮ በተለያየ ደረጃ የሚመዘን እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ይህ እርምጃ በማሽነሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ላይም እንደቀጠለና በዚህም በ29 ተቋማት ላይ ፍተሻ በማድረግ ሶስቱ ከደረጃ በታች ሆነው በመገኘታቸው የመዝጋት እርምጃ መወሰዱን አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩልም ከተቋማቱ ባሻገር አሰልጣኞችና ፈታኞች ባልተገባ የጥቅም ግንኙነት እንዳይገናኙ የተለያዩ ስራዎች አንደሚሰሩ ተናግረው ሆኖም እስከ አሁን እጅ ከፍንጅ የተያዘ አሰልጣኝም ሆነ ፈታኝ ባለመኖሩ እርምጃ ለመውሰድ አለመቻሉን ጠቁመዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ ባለስልጣኑ በመናኸሪያዎች ላይ በመገኘት 6 ሺ በሚጠጉ መኪኖች ላይ የቅድመ ስምሪት የተሽከርካሪ ምርመራ በማድረግ የቴክኒክ ብቃታቸው ያልተረጋገጡ 4 ሺ 414 የሚሆኑት ተሽከርካሪዎች የተገኙ ሲሆን እነዚህም ችግሮቻቸው እንዲስተካክሉና ስምሪት እንዲያገኙ መደረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በመላ አገሪቱ በመንገድ ላይ ድንገተኛ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ምርመራ በማድረግ 120 ሺ ተሽከርካሪዎች በድግግሞሽ የቴክኒክ ጉድለት የተለዩበትና 102ሺ የሚሆኑት በተለያየ የጉድለት ደረጃ መፈረጃቸውን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ እነዚህም በየክልሉ እንዲቀጡ ተደርገዋል ብለዋል፡፡
ከፖሊሶችና ከስነ ስርዓት አስከባሪዎች ጋር በመቀናጀትና ሰራተኞቻችንን በማነቃቃት 36 ያህል የህገ ወጥ ስምሪት ቦታዎች በመለየት 13ቱን ማስወገድ እንደቻሉም አቶ አብዲሳ ጠቁመዋል፡፡ ሙሉ ቃለ ምልልሱን በገጽ ስምንት ላይ ያገኙታል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 21 ቀን 2012
እፀገነት አክሊሉ