አዲስ አበባ፤- ክልሉን ወደ ግጭትና ሁከት እንዲገባ እየሰሩ ያሉ አካላትና ጽንፈኛ መገናኛ ብዙሃን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የአማራ ክልል የሰላምና ደህንነት ቢሮ አስጠነቀቀ።
የቢሮ ሀላፊው አቶ አገኘሁ ተሻገር፤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት የቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ ባለፉት ዓመታት ተነስቶ የክልሉ መንግስትና ምክር ቤቱ ተገቢ ምላሽ ሰጥቷል። ይሁን እንጂ በምላሹ ያልተካተቱ ቀበሌዎች አሉ በሚል ከኮሚቴዎቹ አባላት ቅሬታ ይነሳል።
ባልተስማሙበት ጉዳይ ጥያቄ ማንሳት ተገቢነት ያለው ቢሆንም ፅንፈኛ ሃይሎች ከኋላ ሆነው ሁከት እንዲፈጠር በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ጉዳዩ በተሳሳተ መንገድ እንዲሄድ እያደረጉ ነው ያሉት የቢሮ ሃላፊው፤ ልዩነቱን የሚጠቀሙበት ሀይሎች የአማራ ክልል ተረጋግቶ እንዳይቀጥል ከጽንፈኛ ሃይሎች ጋር ትስስር ፈጥረዋል ብለዋል። እነዚህ ሃይሎች ከኋላ በመሆን ስልጠና በመስጠት፣ ትጥቅ በማስታጠቅና ገንዘብ በማቅረብ የተለያዩ የሽብር ስራ እንዲሰሩ እያደረጓቸው እንደሆነና ዓላማውም ክልሉን ማተራመስ እንደሆነም ገልፀዋል።
እንደ አቶ አገኘሁ ገለፃ ከኋላ ሆነው በሚደግፏቸው ሀይሎች የክልሉ ፖሊስና ተራ የመከላከያ ወታደር የማይታጠቃቸውን እንደ ስናይፐር፣ መትረየስና ሌሎች መሳሪያዎችን ታጥቀዋል። እነዚህ ሃይሎች አማራን ለማዳከም የተፈጠሩ ናቸው። በጽንፈኛ ኮሚቴዎች በመታገዝ መንገድና ተቋማትን በመዝጋት፣ ሰው በመግደል፣ የመንግስትን ስራ በማስተጓጎል ክልሉን ወደ ችግር ለመክተት እየሰሩ ይገኛሉ።
ጽንፈኛ መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች እንዲጋጩ ለማድረግ እየሰሩ ነው ያሉት አቶ አገኘሁ፤ በአማራ ህዝብ ላይም ሁከት እየፈጠሩ ነው ብለዋል። “ይህ አገር ወደ ግጭትና ሁከት እንዲገባም እየሰሩ ነው፤ እነዚህ አካላት ከዚህ መጥፎ ተግባራቸው ቢታገሱ የተሻለ ነው፤ ይህን ተገቢ ያልሆነ ስራቸውንም ለሚመለከተው የተናገርን ሲሆን፤ የማስተካከያ እርምጃም መወሰድ እንዳለበትም አሳስበናል” ብለዋል።
የቅማንት ኮሚቴ ያነሳቸውን ጥያቄዎች የክልሉ መንግስት በወንድማማችነት መንፈስ በድርድርና በመነጋገር እንዲፈታ ይፈልጋል ያሉት አቶ አገኘሁ፤ ይህን ለማድረግም ሰሞኑን ችግሩን ለመፍታት ስንሞክር ሰላም እንዳይሆን የሚፈልጉ አካላት ጉዳዩ ወደ ግጭት እንዲገባ እንዳደረጉት አመልክተዋል።
የሰሞኑ ግጭት የተነሳው የክልሉ ፖሊስ አባላት ተጠርጣሪዎችን ከአንድ ጣቢያ ወደሌላ በመኪና ጭነው እየሄዱ ሳለ በተከፈተ ተኩስ መሆኑንና በዚህም የሰው ህይወት ማለፉን የጠቀሱት አቶ አገኘሁ ችግሩን ለመቆጣጣር የአማራ ልዩ ሀይል በቦታው ሲደርስ ከየአካባቢው መዋቅራቸውን በማንቀሳቀስ ጥቃት ለመሰንዘር እንደሞከሩ ጠቁመዋል። በዚህ ሂደትም በተፈጠረው ግጭት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን አብራርተዋል።
ከመተማ ወደ ጎንደር የሚወስደው መንገድም እስከ ትናንት መዘጋቱን ያነሱት አቶ አገኘሁ፤ በዚህም ከውጭ ወደ አገር የሚገባው ነዳጅና ሌሎች ሸቀጦች እንዳይገቡ አድርጓል ብለዋል። የሰሊጥ መሰብሰቢያ ወቅት በመሆኑ የቀን ሰራተኞች ወደዚያ እንዳይሄዱ በማድረግ ድርጊቱ የአማራ ክልልን ህዝብ ኢኮኖሚው እንዲጎዳ የማድረግ ሴራ መሆኑንም ገልጸዋል።
አቶ አገኘሁ “ጽንፈኞቹ አልፎ አልፎ መኪና ሲያልፍ አስቁመው የመግደል ቢፈጽሙም አሁን እየተረጋጋ ነው። ይህ ችግር አጠቃላይ የቅማንት ብሄረሰብ እንደፈጠረው አድርጎ የማሰብ ሁኔታ አለ፤ ነገር ግን ችግሩን የፈጠረው የቅማንት ማህበረሰብ ሳይሆን ጽንፈኛው የቅማንት ኮሚቴ እና ከኋላ ሆነው የሚደግፉት አካላት ናቸው። ይህን የቅማንት ማህበረሰብና ወጣትም አይደግፈውም። ህዝቡ ችግሩ እንዲፈታና በሰላም አብሮ መኖር ይፈልጋል። ነገር ግን ጽንፈኞቹ በተለያየ መዋቅር አፍነውታል። ይህንን በቀጣይ ተገናኝተን በመነጋገር እንፈታዋለን” ብለዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 21 ቀን 2012
አጎናፍር ገዛኽኝ