አዲስ አበባ፡- ‹‹ኢትዮጵያውያን ለአገራችን እድገት በትብብር አሻራችንን ማስቀመጥ እስከቻልን ድረስ የኢትዮጵያን ብልፅግናና ሕልውና ሊያስቆም የሚችል አንዳች ኃይል የለም›› ሲሉ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ተናገሩ፡፡ በቻይና መንግሥት ድጋፍ የሚገነባው የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ የአረንጓዴ ልማት (ሸገርን ማስዋብ) ፕሮጀክት አካል ትናንት በይፋ ተጀም ሯል።
ፕሮጀክቱን ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የፕሮጀክቱ ሥራ አዲስ አበባን እንደስሟ አበባ ከማድረግ ባሻገር ኢትዮጵያ የሁላችንም እናትና ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የምትበቃ አገር የማድረግ አካልና ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ዘመኑ የብልፅግና ዘመን በመሆኑ አቧራ ከግራና ከቀኝ ከፍ ብሎ ሊታይ ቢችልም አሻራዎች ቦታቸውን እየያዙ አዲሲቱን ኢትዮጵያን በጋራ እንፈጥራለን›› ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ፕሮጀክቱ አዲስ አበባን እንደስሟ አዲስ አበባ እናደርጋታለን ብለን ለኢትዮጵያ ሕዝብ የገባነውን ቃል እውን ለማድረግ አዲስ አበባችንን አበባ ለማስመሰልና የስሟን ልክ መሆን እንድትችል የጀመርናቸው ሰፋፊ ስራዎች አንድ አካል ተደርጎ የሚወሰድ ነው›› ብለዋል፡፡
ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት አዲስ አበባ ቱሪስቶች የሚበዙባት የኮንፈረንስ ከተማ እንድትሆን በማድረግ የግሉ ዘርፍ አስተማማኝ የሆነ ሀብት እንዲያገኝ በር የሚከፍት መሆኑንና ከዚህ ዘርፍ የሚገኘውን ሀብት በሌሎች መስኮች ከሚገኘው ሀብት ጋር በማቀናጀት እንዲሁም በግብርናና በኢንዱስትሪ ዘርፎች የሚከናወኑ ስራዎችን በማዘመን የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ለማድረግ እድል እንደሚሰጥ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳትሆን ሌሎችም የሚመኟት፣ ሊያዩዋትና ሊኖሩባት የሚፈልጓት አገር እንድትሆን እንዲሁም የሥራ እድል በመፍጠር ኢትዮጵያውያን ስራ አጥተው እንዳይሰደዱ ማድረግ የሚቻልበትን እድል እንደሚያሰፋም ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት እንዲሳካ ሥራው በሚከናወንባቸው አካባቢዎች የሚገነቡ ግንባታዎች ለቱሪስቶች ምቹና አካባቢውንም የሚመጥኑ እንዲሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኃላፊነት እንዳለበት አሳስበው፤ የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በግንቦት ወር 2012 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅና የፕሮጀክቱን እንቅስቃሴ በቅርበት
እንደሚከታተሉት ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂያን በበኩላቸው፣ አዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ዋና ከተማነቷ በተጨማሪ የአፍሪካና የዓለም የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ማዕከል መሆኗን ጠቁመው፣ ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት ቻይናውያንን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡና ለኢትዮጵያ እድገት አወንታዊ አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ስለሚያስችል የቻይና መንግስት ለፕሮጀክቱ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡
አምባሳደሩ ፕሮጀክቱ ሕዝብን ማዕከል ያደረገ፣ ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነና ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ፋይዳዎች ያሉት በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ባዘጋጁት የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት መርሃ ግብር ላይ ከተሳተፉ የውጭ አገራት ኩባንያዎች መካከል የቻይና ኩባንያዎች ቀዳሚዎቹ እንደነበሩ አስታውሰው ፤ መንግስታቸው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የለውጥ አጀንዳዎችን እንደሚደግፍ ተናግረዋል፡፡
ትናንት በይፋ የተጀመረው ስራ 56 ኪሎ ሜትር የሚረዝም፣ 29 ቢሊዮን ብር የሚያስወጣና ለግንባታ የሦስት ዓመታት ጊዜ ያስፈልገዋል የተባለው ከእንጦጦ እስከ አቃቂ ወንዝ ድረስ የሚዘልቀው ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት አንድ አካል ነው፡፡ 12 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ይህ የፕሮጀክቱ አካል፣ ግንባታው ቻይና ኮሚኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ (ሲሲሲሲ) በተባለ ኩባንያ የሚከናወን ሲሆን፤ የፕሮጀክቱ ወጪም በቻይና መንግሥት የሚሸፈን ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 21 ቀን 2012
አንተነህ ቸሬ