አገራችን በለውጥ ሂደት ላይ ናት፡፡ ለውጡ ሰላማዊ የሆነ የኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ነው፡፡ ለውጡ ከጀመረበት ካለፉት ዘጠኝ ወራት ወዲህም በተለያዩ ዘርፎች ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ በተለይ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈን የተሄደበት ርቀት ከጊዜው በላይ ረጅም ርቀት የተጓዘ ስኬት መሆኑን ብዙዎች የሚመሰክሩት ሃቅ ነው፡፡
ያም ሆኖ ግን አሁንም ቢሆን ይህንን ለውጥ የሚገዳደሩ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱና ለሁሉም ነገር መሰረት የሆነው ደግሞ የህግ የበላይነት መሸርሸር ነው፡፡ በአንድ አገር የህግ የበላይነት ካልተከበረ ወጥቶ መግባት አዳጋች ይሆናል፡፡ በሰላም የመኖር ዋስትናም አደጋ ውስጥ ይገባል፤ የመንግስት ህልውናም ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡
ሰላምን የማስከበር ዋነኛው ሃላፊነት ደግሞ በዋናነት የመንግስት ነው፡፡ ነገር ግን ህዝቡም ቢሆን ለዚህ ሂደት ተባባሪ ሊሆን ይገባል፡፡ ያለህዝብ ተሳትፎ ተግባራዊ የሚሆን ማንኛውም ሰላምን የማስከበር እንቅስቃሴ ውጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡
ያም ሆኖ ግን አሁን አሁን በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች የሚታዩ የሰላም እጦት ችግሮች መንግስትን እየተፈታተኑና ህዝብንም ለችግር እየዳረጉ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ዜጎች ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ መፈናቀል፤ የተለያዩ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውሮች እዚህም እዚያም በተደጋጋሚ መታየት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በሰላም ለመንቀሳቀስ አለመቻል፣ ወዘተ ችግሮች ዛሬም በሰፊው ይስተዋላሉ፡፡ እነዚህ ድርጊቶች ደግሞ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚፈፀሙ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም፡፡
መንግስት የጀመረውን ሰፊ የዴሞክራታይዜሽን ስራ ከማይቀለበስበት ደረጃ ለማድረስ እና ዘለቄታዊ ሰላም፤ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ብልጽግና እንዲረጋገጥ ለማድረግ እየሰራ ባለበት በዚህ ወቅት እንዲህ አይነት የህግ የበላይነትን የሚገዳደሩ ድርጊቶች በአጭሩ ካልተቀጩ የሚያስከትሉት አደጋ የከፋ ሊሆን ይችላል፡፡
ለዘመናት በመልካምም ሆነ በፈታኝ የታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ አብሮነትና መቻቻል የአገራችን ህዝቦች አይነተኛ እሴት ሆኖ ቢቆይም ሥርዓት አልበኝነትን፤ መረን የለቀቀ እና ሕግና ሥርዓትን የማያከብሩ እንቅስቃሴዎችና ድርጊቶች መበራከት ግን በህዝቡ ውስጥ የቆየውን በሰላም አብሮ የመኖር እሴት እስከመሸርሸር ደርሰዋል፡፡ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላት ይህንን ጉዳይ ልዩ ትኩረት በመስጠት የእያንዳንዱን ዜጋ ደህንነትና ነፃነት ለማስከበር አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል፡፡
በአገራችንም የሚፈለገውን የዴሞክራሲ ሥርዓት እውን ለማድረግ፣ ዜጎች የህይወት መስዋእትነት ከፍለው ያመጡትን ለውጥ አጣጥመው ባልጠገቡበት ሁኔታ አጋጣሚውን ለእኩይ አላማቸው ለማዋል በተነሱ አካላት እዚህም እዚያም በሚጫር ግጭት እየደረሰ ያለውን ጥፋት በቁጥጥር ስር ማዋል ጊዜ የሚሰጠው ተግባር አይደለም፡፡
እንደሚታወቀው በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተቀሰቀሱ ግጭቶችና በተፈጸሙ ጥቃቶች የንጹሃን ሕይወት በከንቱ ጠፍቷል፤ አካል ጎድሏል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል፤ ለፍተው ያፈሩት ሀብት ወድሟል፤ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ተስተጓጉሏል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ሰላማዊ ዜጎችን በፊንጂ እስከማጋየት የደረሰ ክፉ ተግባር በአገራችን ተመልክተናል፡፡ በነዚህ ችግሮች የተነሳም ዜጎች ስጋት ውስጥ ሆነው እንዲኖሩ ተገደዋል፡፡
በሌላ በኩል መንግስት የኢኮኖሚ ችግሮችን ለመፍታትና ልማትን ለማፋጠን ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡ ወደ ስራ እየገቡ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን የኢኮኖሚ ሽግግሩን ለማፋጠንና የስራ አጥነት ችግሮችን በመፍታት የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ያላቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡ በኢንቨስትመንት ዘርፉም እየታየ ያለው መነቃቃት መፃኢ ተስፋችን ብሩህ መሆኑን ያመላክታል፡፡ ያም ሆኖ ግን ልማትና ኢንቨስትመንት ያለ ሰላም አይታሰብም፡፡ በሀገሪቱ የሚካሄደው ልማት ዋስትና የሚኖረውም ሰላም ሲጠበቅ ስለሆነ የህግ የበላይነትን ማስከበር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት የዴሞክራሲ ሥርኣት ግንባታውን ለማፋጠን የተያያዘው ጥረትም ያለህግ የበላይነት የትም አይደርስም፡፡ ሃሳብን በነጻነት ማራመድ የሚቻለውም በህግና በህግ እየተመሩ የሌላውን ሃሳብ በማዳመጥና በውይይት እንደመሆኑ የህግ የበላይነት መከበር ፋይዳ እዚህም ላይ ከፍተኛ ነው፡፡ ከመስመር የሚወጣ ሁሉ ወደ መስመር የሚገባው በህግና በህግ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም የህግ የበላይነትን የማስከበሩ ስራ ቀይ መስመር ሆኖ ሊቀጥል ይገባል፡፡
በሌላ በኩል መንግስት የህግ የበላይትን ሲያስከብር ብቻውን ሆኖ እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በዚህ ሂደት የህዝቡ ሃላፊነትም ከፍተኛ ነው፡፡ ህዝቡ የለውጡ ባለቤት እንደመሆኑ ለውጡን የመጠበቅም ሃላፊነት አለበት፡፡ ለውጡን ገና አጣጥሞ ባልጨረሰበት ሁኔታ በለውጡ ላይ አደጋ ሲደቀን ዝም ብሎ ሊያይ አይገባም፡፡ ስለሆነም ሰላሙን በመጠበቅ የህግ የበላይነት እንዲከበር ከጸጥታ ሃይሎች ጋር አብሮ መስራት ይኖርበታል፡፡
ይህ የመንግስት አቅጣጫ ውጤታማ እንዲሆን የሃይማኖት ተቋማት ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣አባገዳዎች…ወዘተ ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡ የማንኛውም ሰው ፖለቲካዊም ሆነ ሌላ እንቅስቃሴው በህግና በህግ አግባብ ብቻ እንዲሆን ማስተማር ይጠበቅባቸዋል፡፡
ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የህግ የበላይነት መሰረታዊ ጉዳይ ነው፤ ለሰላምም ወሳኝ ነው፤ ለኢኮኖሚ እድገትም አስፈላጊ ነው፡፡ ስለሆነም መንግስት መላውን ህዝብ እና መዋቅሩን አስተባብሮ የህግ የበላይነት ለማስከበር እያደረገ ያለውን ጥረት ማጠናከር አለበት፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2011