የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የኢኮኖሚና የማህበራዊ መሰረተ ልማት አውታሮች፣ ፋብሪካዎችና መኖሪያ ቤቶችን በመገንባትና የስራ እድል በመፍጠር የአገሪቱን ኢኮኖሚ በእጅጉ እያሳደጉ ካሉ ዘርፎች ውስጥ በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ከፌዴራል መንግስት የካፒታል በጀት ውስጥ ከ55 አስከ 60 በመቶ የሚሆነው ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሚውል መሆኑም ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚው የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡
ኢንዱስትሪው ከግብርና ቀጥሎ ከፍተኛ የሰው ኃይል የያዘና ለሌሎች ዘርፎችም ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑም ይታወቃል፡፡ ለሃገሪቱ ከፍተኛ የግብር ገቢ ከሚያስገኙ መስኮች ውስጥ ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ይሁንና ዘርፉ ለሃገር ኢኮኖሚ ያለውን አስተዋፅኦ ያህል የሚጠበቅበትን ድርሻ በአግባቡ እንዳይወጣ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች እያጋጠሙት ይገኛሉ፡፡
የኢንዱስትሪውን ተግዳሮቶች በጠራ መልኩ ለመመልከት፣ ውጤታማነቱን ይበልጥ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት የልምድ ተሞክሮና ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተጨማሪ ግብአቶችን ለማግኘት በየዓመቱ ኤግዚቢሽኖች ይካሄዳሉ፡፡ የዘንድሮው 16ኛው የኢትዮጵያ አለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽንም ልዩ ልዩ ተሳታፊዎችን በማካተት ሰሞኑን በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
በፈርስት ካይሮፕራክቲክ እና ሪሃብሊቴሽን ዌልነስ ክሊኒክ የገበያና ሽያጭ ዳይሬክተር መርየም ግርማ በግንባታ ሂደት በሰራተኞች ላይ የሚያጋጥሙ የጀርባ አጥንት ህመሞች ዙሪያ በግንባታ ዘርፉ ለተሰማሩ ሰዎች የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን ለመስጠት በኤግዚቢሽኑ ላይ እንደተሳተፉ ይናገራሉ፡፡
የጀርባ አጥንት ጤንነት ከአንገት ጀምሮ እስከእግር ጥፍር ድረስ ያለውን የሰውነት ጤንነት የሚያካትትና ሁለንተናዊ የአካል ጤንነት መሆኑን የሚገልጹት ዳይሬክተሯ፣፡ ይህም የሰዎችን አቀማመጥ፣ የአንገት ማቀርቀር፣ የአስተኛኘት ሁኔታና ሌሎችንም ከጀርባ አጥንት ጋር የተያያዙ የጤንነት ጉዳዮችን እንደሚያጠቃልል ይናገራሉ፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ በግንባታ ዘርፍ ላይ የሚሰማሩ ሰዎች በየቀኑ ነገሮችን ማንሳት፣ ማጠፍ፣ መያዝ፣ መግፋት፣ መሳብ፣ መወርወር እንዲሁም ማጎንበስ፣ መውጣትና መውረድ ሳያስተውሏቸው የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ሲሆኑ እነዚህ እንቅስቃሴዎች በአብዛኛው ከጀርባ አጥንት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በመሆኑም ክሊኒኩ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽኑን በመጠቀም በግንባታ ዘርፍ ለተሰማሩ ሰራተኞች ከጀርባ አጥንት ህመም ጋር በተያያዘ ግንዛቤ ይሰጣል፡፡ ህመሙ አስቀድሞ ከመከሰቱ በፊት ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም በበራሪ ወረቀቶች አማካኝነት መልእክት ያስተላልፋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ክሊኒኩ በአከርካሪ አጥንት ማነቃቃት ላይ ያተኮረና በየቀኑ ለአስር ደቂቃ ሊተገብር የሚችል የጤና ስልጠና በኮንስትራክሽን ሳይቶችና በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ውስጥ ይሰጣል፡፡ ሰዎች የአከርካሪ አጥንት ጉዳት ከደረሰባቸውም ህክምና ይሰጣል፡፡
በግንባታ ሳይቶች ላይ ለጉልበት ሰራተኞች የተለያዩ ስልጠናዎች እየተሰጡ እንደሚገኙ የሚገልፁት ዳይሬክተሯ፤ በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ የአበባ እርሻዎች ውስጥ ለሚሰሩ ሰራተኞችም በጀርባ አጥንት ጤንነት ዙሪያ ተመሳሳይ ስልጠናዎች ተሰጥዋል ይላሉ፡፡ በቀጣይም እንዲህ አይነቱ ስልጠና በልዩ ልዩ የግንባታ ሳይቶች ላይ እንደሚሰጥም ይጠቁማሉ፡፡
በባህርዳር ከተማ የሚገኘው የማርዳ እብነበረድ ፋብሪካ የሽያጭ ባለሙያ አቶ ገበያው ወርቅነህ እንደሚሉት፤ ፋብሪካው ማምረት ከጀመረ ስድስት ወራትን አስቆጥሯል፡፡ እብነበረድን በሃገር ውስጥ ማምረት በውጪ ምንዛሬ ወደ ሃገር ውስጥ የሚገባውን ምርት ለማስቀረት እንደሚያስችል ታምኖበት ነው ፋብሪካው የተቋቋመው፡፡
ፋብሪካው በኤግዚቢሽኑ ሲሳተፍ የመጀመሪያው መሆኑን ባለሙያው ተናግረው፤ በኤግዚቢሽኑ መሳተፉ ከሌሎች የኮንስትራክሽን ዘርፎች ጋር የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያስችለው ይገልጻሉ፡፡ በተለይም ፋብሪካው የሚያመርተው የህንፃ ማጠናቀቂያ ምርት እንደመሆኑ መጠን በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ መሳተፉ ራሱን ለማስተዋወቅ ትልቅ አድል ፈጥሮለታል፡፡
እንደ ባለሙያው ገለፃ፤ በክልል ደረጃ በተለይም ባህር ዳር አካባቢ የፋብሪካው ምርት ወደ ገበያ እየገባ ቢሆንም፣ ምርቱን በማስተዋወቅ አዲስ አበባን ጨምሮ ወደተለያዩ የክልል ከተሞች ለመግባት የተለያዩ ኤግዚቢሽኖችን መጠቀም ይኖርበታል፡፡ በዚህ አለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ላይ ተሳታፊ የሆነውም በዋናነት ምርቱን ለማስተዋወቅ ነው፡፡
ፋብሪካው በቀን ለስምንት ሰዓታት ያህል እብነበረድ ውጤቶችን እያመረተ መሆኑን የሚገልፁት ባለሙያው፣ በቀጣይ ተመሳሳይ ኤግዚቢሽኖች ላይ በመሳተፍና ምርቱን በማስተዋወቅ የማምረት አቅሙን ወደ ሃያ አራት ሰዓታት የማሳደግ እቅድ አለው፡፡ ይህም ተጨማሪ የስራ አድል እንደሚፈጥርና በቀጣይም ፋብሪካው ምርቶቹን ወደ ውጪ ሀገራት ለመላክ የሚስችል ነው፡፡
የከተማ ፕላን ባለሙያው አቶ ውብሽት ተስፋዬ በበኩላቸው በአዲስ አበባ ከተማ ለመልሶ ማልማት የተወሰኑ ቦታዎችን በዘላቂነት ማልማት እንደሚቻል የሚያሳይ ሞዴል ፕሮፖዛል በኤግዚቢሽኑ ላይ ይዘው እንደቀረቡ ይናገራሉ፡፡ በዚህ ኤግዚቢሽን ለመሳተፍ የፈለጉበት ዋነኛ ምክንያትም የአዲስ አበባ ህዝብ ሳይፈናቀል ዋናው ሃብቱ በሆነው መሬቱ ላይ እንዴት በዘላቂነት መኖር እንደሚችል ለማሳየት መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ይህንንም ለማሳየት የግልና የመንግስት ይዞታዎችን አካተዋል፡፡
ባለሙያው እንደሚሉት፤ በፕሮፖዛሉ መሰረት በመልሶ ማልማቱ ሂደት የቀበሌ ቤቶችን በሚመለከት መንግስት አንደአንድ ተደራዳሪ ሆኖ ይቀርባል፡፡ በሌላ በኩል በከተማው ውስጥ በመሬት ባንክ ያልተያዘ መሬት እንዲለማ በሚደረግበት ጊዜ በመሬት መረጃ ቋት ስር የሚገባውን መሬት በመያዝ መንግስት ይደራደርና የመሬቱን ዋጋ ደግሞ ከግል አልሚ ጋር በመደራደር እንዲለማ ያደርጋል፡፡ ይህም መንግስትም ሆነ የግል ነዋሪዎች የሚፈልጉትን ቤት ማግኘት እንዲችሉ ይጠቅማል፡፡ ከዚህ ባለፈም ሊያከራዮቸውና ሊሸጧቸው የሚችሉ ተጨማሪ መኖሪያ ቤቶችንም ማግኘት ያስችላቸዋል፡፡ መንግስትም በቀበሌ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች በተሻለ ሁኔታ እዛው አካባቢ ላይ እንዲኖሩ ለማድረግ ያስችለዋል፡፡
ፕሮፖዛሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማግኘት የተመዘገቡ የከተማዋ ነዋሪዎችንም ከመሃል ከተማ ሳይርቁ እዛው ባሉበት ለመኖር የሚያስችላቸው መሆኑን የሚናገሩት ባለሙያው፤ ይህም በአዲስ አባባ ያለውን የቤት እጥረት በዘላቂነት የሚፈታና መሬትንም በአግባቡ ለመጠቀም እንደሚያስችል ይገልጻሉ:: ከዚህ ሁሉ የተረፈው መሬት ደግሞ ለአልሚው ተሰጥቶ እንዲያለማበት ይደረጋል፤ አልሚው ከዚህ በሚያገኘው ትርፍ መንደሩን በዘላቂነት ለማልማት ያስችለዋል፡፡
እንደ ባለሙያው ገለፃ፤ ፕሮፖዛሉ እንደመነሻነት የተዘጋጀው በአራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ሁለት አዋሳኝ ወረዳዎች ላይ ሲሆን ፕሮፖዛሉን በማዘጋጀት ሂደት ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል፤ ህብረተሰቡም መጠይቆችን እንዲሞላ ተደርጓል:: በቀጣይም በነባሩ ፕሮፖዛል ላይ በየመንደሩ በመውረድ ውይይት ይደረግና ከመንግስት ጋር በዋጋ በመደራደር ፕሮፖዛሉ በአዲስ መልክ በድጋሚ እንዲዘጋጅ ይደረጋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር 63 ሺ የሚሆኑ ቤቶችን በመንግስት የግል አጋርነት /private public partnership/ ለማልማት ፕሮፖዛል አቅርቧል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማህበር ፕሮጀክቱ በግለሰብ ደረጃ ብቻ የሚሰራ ባለመሆኑና በጋራ መሰራት እንዳለበት ሃሳብ በማቅረቡ ፕሮፖዛሉ ለመንግስት ቅርቦ መልስ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡ ፕሮፖዛሉ ምላሽ የሚያገኝ ከሆነም በአዲስ አበባ ከተማ በ117ቱም ወረዳዎች ላይ የመልሶ ማልማት ስራዎች ይከናወኑበታል፡፡
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንት ኢንጂነር አምሃ ስሜ እንደሚገልፁት፤ በ16ኛው የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ኤግዚቢሽን በአብዛኛው የተሳተፉት የሃገር ውስጥና የውጭ ሀገራት የግንባታ እቃዎች አምራቾች ናቸው፡፡ ይህም በኮንስትራክሽን ዘርፉ ያለውን የቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍ ከማድረግ በዘለለ በሀገር ውስጥ ኢንቨስት በማድረግ ከውጪ የሚገቡትን ምርቶች በሃገር ውስጥ እንዲመረቱ በማድረግ የውጪ ምዛሬን ለማዳን ያስችላል፡፡
በኤግዚቢሽኑ ላይ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ካሉት በተጨማሪ ከዘርፉ ጋር የማይነጣጠሉ አካላትም ተሳትፈዋል፡፡ ለአብነትም በግንባታ ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የጤና ጉዳቶችን በተመለከተ ግንዛቤና ህክምና የሚሰጡ የጤና ክሊኒኮች፣ በከተማ ፕላን ላይ የሚሰሩ ሙያተኞችና ሌሎች ዘርፉ የሚመለከታቸው ልዩ ልዩ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ይህም የኮንስትራክሽን ዘርፉ ከሌሎች ሴክተሮች ጋር ምን ያህል ተደጋጋፊ መሆኑን ያሳያል፡፡
በኤግዚቢሽኑ ከተሳተፉ የኮንስትራክሽን ዘርፍ አቅራቢዎች በተጨማሪ ወደ ሃገር ውስጥ ገብተው መዋእለ ንዋያቸውን ስራ ላይ ማዋል የሚፈልጉ የውጭ ሀገራት ባለሃብቶችም መሳተፋቸው የኮንስትራክሽን ዘርፉን ከማሳደግ አንፃር የራሱን ሚና ይጫወታል፡፡ ይህም ማህበሩ የውጭ ምንዛሬን ከማዳን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከማምጣትና የኮንስትራክሽን ግብአቶችን በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ከሚመጡ ይልቅ በሃገር ውስጥ እንዲመረቱ ከማድረግ አንፃር የበኩሉን የዲፕሎማሲ ስራ እየሰራ መሆኑን ያሳያል፡፡
ይህንንም ጉዳይ ሚኒስቴር መስራያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ ከማህበሩ ጋር አጋር ሆኖ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ እንዲህ አይነቱን አጋጣሚ ለሃገር ጥቅም ለማዋል ከማህበሩ ጋር ተቀራርቦ መስራት የሚቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል ይላሉ፡፡
ማህበሩ እያደረገ ላለው ጥረትና የውጪ ባለሃብቶችም ወደ ሃገር ውስጥ ገብተው ኢንቨስት እንዲያደረጉ ለሚደረጉ ቅስቀሳዎች እገዛ ሊያደርግ የሚችል የተመቻቸ መድረክ ቢኖር ኢንቬስተሮች ወደ ሃገር ውስጥ የመምጣት እድላቸው ከፍተኛ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ ያስገነዝባሉ፡፡ ይህም ከፍተኛ የስራ አድል ከመፍጠሩም በላይ የውጪ ምንዛሬን ከማምጣትና የሃገሪቱን እድገት ከማፋጠን አንፃር ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ይገልጻሉ፡፡
መንግስት የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለማበረታታት የአቅም ግንባታ ፕሮግራም በመቅረፅ በስልጠና፣ በማሽነሪ አቅርቦት፣ የስራ እድል በመፍጠር እንዲሁም መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ አዋጆችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን በማውጣት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ዘርፉ ለሃገር ኢኮኖሚ የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዳይወጣ እንቅፋት የሆኑ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶችን መፍታት የግሉን ዘርፍ ጨምሮ ከሁሉም የሚጠበቅ ድርሻ መሆኑ ይታመናል::
አዲስ ዘመን መስከረም 20/2012
አስናቀ ፀጋዬ