ሙስና እና በህገ-ወጥ መንገድ ገንዘብ የማሸሽ ወንጀል ዓለማችንን ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ እርቃኗን እያስቀረ ህዝቧን ለድህነት አረንቋ እያደረገ ነው፤ ሚሊዮኖችን ጦም እያሳደረ፣ የመንግስታትን ካዝና ባዶ እያስቀረ፣ ልማትን እያስተጓጎለ፣ በአይነትም ሆነ በመጠን እየጎለበተ መጥቷል።
ወንጀሉ በአፍሪካም ተመሳሳይ መልክ አለው፤ ሲነግስ እንጂ ሲቀንስ አይታይም። በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን የሚከታለው ‹‹ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ (ጂኤፍሲ) እና ሌሎችም ተቋማት የእያንዳንዱ አገር የገንዘብና የባንክ አሰራር ያለበትን ችግር፤ ሕጋዊ አሰራሮችና ሕጋዊ ያልሆነ የገንዘብ ዝውውርን ለመግታት የተዘጋጁ አሰራሮችን በመመርመር ይፋ የሚያደርጉ መረጃዎች የአህጉሪቱ ሀገሮች ለሙስና እና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ክፉኛ ስለመጋለጣቸው ይመሰክራሉ።
ከወራት በፊት ይፋ የሆነው ኤፍቲዶትኮም ድረገጽ መረጃም በአህጉሪቱ በተንሰራፋው ኢኮኖሚያዊ ወንጀል ምክንያት አፍሪካ በዓመት በተለያዩ ስርቆቶች 148 ቢሊዮን፤ በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ደግሞ ሁለት ትሪሊዮን ዶላር እንደምታጣ አመልክቷል።
ችግሩ ይህን ይህል አሳሳቢ ቢሆንም የአፍሪካ መንግስታት ችግሩን ለመፍታት ያላቸው ቁርጠኝነት ሲፈተሽ እጅጉን ደካማ ስለመሆኑ በገሃድ ከመታየት ባለፈ በኢኮኖሚ ባለሙያዎች ሳይቀር በመረጃ የተደገፈ ምስክርነት የሚሰጥበት ነው። አብዛኞቹ የአህጉሪቱ አገራት አጠቃላይ አመታዊ ሀገራዊ የምርት መጠንና የነፍስ ወከፍ ገቢን ማሳደግ ሲገባቸው በየጊዜው ከአህጉሪቱ በህገ ወጥ መንገድ የሚወጣውና ይፋ ባልሆነ የውጪ ሀገራት ባንክ ቋት የሚጠራቀመውን ረብጣ ገንዘብ በመቆጣጠር ብሎም በማስመለስ ረገድ መንግስታት የሚወስዱት እርምጃ እጅግ አዝጋሚ መሆኑም ወንጀሉን እንዳባባሰው ይታመናል። የፍትህ አካላት ሳይቀሩ በከፍተኛ ደረጃ በድርጊቱ የሚሳተፉ መሆኑ ደግሞ ቁጥጥሩ ፍሬያማ እንዳይሆን ዋነኛ ምክንያት ሲሆን እንደሚስተዋልም ጥናቶች ያመላክታሉ።
ከወር በፊት ይፋ የሆኑ መረጃዎችም ወንጀሉ ከሚስተዋልባቸው ከ125 የአለማችን አገራት ሞዛምቢክ ቀዳሚ ሆናለች። ሶማሊያ፣ ቦትስዋና እና ናይጄሪያም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በችግሩ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ሀገሮችም ጥቂት አይደሉም። ይህም አህጉሩቱ ስለምትገኝበት የሙስና ቀውስ ተጨባጭ ማስረጃ ሆኖ ይቀርባል።
ከእነዚህ አገራት በተጓዳኝ ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኬንያም ‹‹ይህን ሀገ ወጥ ተግባር ለመከላከል በቂ ቁጥጥር አታደርግም፤ ሽብርተኝነት በገንዘብ ሲደገፍ ሊያስከትል ስለሚችለው ኪሳራ የሚያስገነዘብ ጠንካራ ህግ በማውጣት ረገድም ውስንነት አለባት›› በሚል በቀይ መዝገብ ከሰፈሩት አገራት ከግንባር ቀደምቶቹ ተርታ መገኘቷም ይታወቃል።
የተንቀሳቃሽ ስልክ የክፍያ አገልግሎትን ጨምሮ አጠቃላይ የባንክ አገልግሎት በተደራሽነትም ሆነ በአቅም ጎልብቶ በሚስተዋልባት ኪንያ፣ ህገወጥ የገንዘብ መላኪያና ማስተላላፊያ መንገዶችና የህገ ወጥ ድርጊቱ ተዋናዮች መጠን ስለመበራከታቸው ይገለጻል። እነዚህ በድብቅ የሚከናወኑ የገንዘብ ዝውውሮችም ከአገሪቱ መንግስት እይታ የተሰወሩ ስለመሆናቸውም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ችግሩ እያደር አሳሳቢ መሆኑን የተረዳው የአገሪቱ መንግስትም መፍትሄ የሚላቸውን የተለያዩ ተግባራት ፈጽሟል። ዳግም ሲመረጡ ሙስናን መፋለም ቀዳሚ አጀንዳቸው እንደሚሆን በአደባባይ የተናገሩት ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታም ቃላቸውን በተግባር ለማሳየት ብዙ ደክመዋል። በተለይ አገራቸው የተብጠለጠለችበትን ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ለመከላከል ፍቱን መድሃኒት ናቸው የተባሉ ዘዴዎችን የተገበሩ ሲሆን፣ ከእነዚህም አንዱ የአገሪቱን የመገበያያ ገንዘብ በተለይም አንድ ሺ ሽልንግ ኖት የመለወጥ ውሳኔም አሳልፈዋል።
ይህ ውሳኔ ከተላለፈ አራት ወራት ተቆጥረዋል። ታዋቂው ፀሃፊ ሞሪስ ኪሩጋም አፈጻጸሙን ተከታትሎ ሰፊ ሀተታውን በአፍሪካ ሪፖርት መፅሄት ላይ አስነብቧል። በዘገባውም ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ህገ ወጥ ተግባሩን ለመከላከል ብዙ እየደከመች ስለመሆኑ አትቷል።
በአገሪቱ የመግዛት አቅሙ ከ10 ዶላር ጋር እኩል መሆኑ የሚነገርለት አንድ ሺ ሽልንግ የብር ኖትዋን የመለወጥ ውሳኔዋ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን መቆጣጠርን ታሳቢ ያደረገ መሆን ያመላከተው ፀሃፊው፣ ሙስናን ለመፋለም ዋና አላማው መሆኑን አብራርቷል።
ከቀናት በፊት የአገሪቱ ማእከላዊ ባንክ ገዢ ፓትሪክ ኒጆሮጌ ‹‹ህገ ወጥ ተግባሩን ለመከላከል እጅግ የሚበረታታ ድጋፍ ከሌሎች ተባባሪ አካላት ተቋማት አግኝተናል›› ብለዋል። በዚህም ኡጋንዳና ታንዛኒያን የመሳሰሉ አገራት ዋነኛ ተባባሪ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ሳፋሪኮም እና ቴሌኮምን የመሳሰሉት ግዙፍ ተቋማት ለሰራተኞቻቸውና ለደንበኞቻቸው የአሮጌውን ገንዘብ ማብቂያ የጊዜ ገደብ በማስገንዘብ ረገድ ጅምር ተግባራት በመፈፀም ላይ ስለመሆናቸውም ተመላከቷል።
ይሁንና አንዳንዶች ይህን ውሳኔ ተቃውመውታል። ለምን ሲባሉም ‹‹ከሶስት አመት በፊት ህንድ መሰል ህገ ወጥ ተግባርን ለመቀነስ የመገበያያ ገንዘቧ ላይ ለውጥ ማድረጓን ተከትሎ የደረሰባት የኢኮኖሚ መንገጫገጭ በምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር እንዲደገም ስለማንፈልግ ነው›› ብለዋል።
ማእከላዊ ባንኩም ይህን ስጋት የተጋራው ቢሆንም፣ ችግሩን አስቀድሞ ለመከላከል ጠንካራ ተግባራት ስለመከናወናቸው አስታውቋል። ወላጆች ልጆቻቸው አዲሱን የመገበያያ ገንዘብ እንዲጠቀሙ እንዲነግሯቸው ማስገንዘብን ጨምሮ የፋይናንስ ምህዋሩ ተዋናዮችን የማግባባት ጠንካራና ውጤታማ ተግባር መከወኑም አብራርቷል።
ሙስናን እና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመቆጣጠሩ ሂደትም ማንኛውም የአገሪቱ ዜጋም ሆነ ሌላ ግለሰብ ከ5 ሚሊየን ብር በላይ ለመለወጥ ሲፈልግ፣ የማዕከላዊ ባንኩን እውቅና ማረጋገጫ ማቅረብ ግድ እንደሚለው መደንገጉንም አስታውቋል።
ይህን ለውጥ ተከትሎም በአገሪቱ ባንክ የነበረውን የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ወደ 22 ነጥብ 3 ቢሊየን የአገሪቱ ገንዘብ ከፍ ማለቱ በተቃራኒው ከባንኩ ማእከል ውጪ ይንቀሳቀስ የነበረው ገንዘብም ወደ 25 ነጥብ አንድ ቢሊየን የሀገሪቱ ገንዘብ መቀነሱን የአፍሪካ ሪፖርቱ ዘገባ አመላክቷል።
እስከ አለፈው የፈረንጆቹ ወር መጨረሻ ድረስም የአገሪቱ ማእከላዊ ባንክ ከግማሽ በላይ ገንዘብ ከገበያ መሰብሰቡ ቢታመንም፣ በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውሩና ሙስናን በመቆጣጠሩ ጦርነት የተመዘገበው ድልና የተገኘው ስኬት የሚፈለገውን ያህል አለመሆኑም ተጠቁሟል። የማእከላዊ ባንኩ ገዢም ይህን ድክመት አምነው ተቀብለዋል።
ሙስና እና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር በመቆጣጠሩ ሂደትም በሚፈለገው ልክ ለመጋዝ ያልቻለውም የተጭበረበረ ገንዘብ መፈብረክን በገበያው ምህዋር ውስጥ በመንቀሳቀስ መሆኑን ጠቁመው፣ ይሕም ወቅታዊው የአገሪቱ ራስ ምታት መሆኑን አስምረውበታል።
አዲሱ የመገበያያ ገንዘብ ገበያውን ከተቀላቀለ ወዲህ ባሉት ወራትም ሶስት ያህል ግለሰቦች የተጭበረበረ 100,ሺ ሽልንግ ይዘው በመገኘታቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተጠቁሟል፤ በመስከረም ወርም ተጨማሪ ሶስት ግለሰቦች መያዛቸው ታውቋል።
ይህን ያስተዋሉት ሞሪስ ኪሩን የመሳሰሉት ፀሃፍትና ሌሎች የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም፣ በአሁኑ ወቅት የምስራቅ አፍሪካዊቷን አገር መንግስትና የማእከላዊ ባንካ ዋነኛ ፈተና ሙስና ብቻ እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ የተጭበረበረ የገንዘብ ኖትን ከገበያ ለማስወጣት የተግባሩ ቀማሪና ተጠቃሚ የሆኑ ህገወጦችን አድኖ በቁጥጥር ስር ማዋል ም መሆኑን አስ ምረውበታል።
አዲስ ዘመን መስከረም 20/2012 ታምራት ተስፋዬ