በኢትዮጵያ በርካታ አገር በቀል እውቀቶች ቢኖሩም እነዚህን እውቀቶች በቅጡ ተገንዝቦና ጥናት አድርጎ ለአገር ልማት፣ ሰላምና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ ጠቀሜታ እንዲሰጡ ብሎም ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ ላይ ክፍተቶች አሉ፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ማኅበራዊ፣ ስነ ልቡናና ባህላዊ ፍልስፍናና የረቀቁ አስተሳሰቦች የጋራ እሴት በማድረግና ለአዲሱ ትውልድ በማስተላለፍ ረገድም ውስንነቶች እንዳሉ ምሁራንም ይስማማሉ፡፡
‹‹በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ያሉንን አገር በቀል እውቀቶችን በዘመናዊ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ አካተን ለአገር ዕድገት የተጠቀምንበት ጊዜ አለ ብዬ አላምንም›› የሚሉት በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎት፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢንዱስትሪ ዩኒቨርሲቲ ሊንኬጅ ዳይሬክተርና በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መሪ ተመራማሪ ዶክተር ሰለሞን ቢኖር በአንጻሩ ሩቅ ምሥራቅ አገሮች አሁን ለደረሱበት የዕድገት ደረጃ የአገር በቀል እውቀቶች ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን በአብነት ያነሳሉ፡፡
የጃፓን፣የታይላድና ቻይና አብዛኛው የሳይንስና የምርምር ዕድገታቸው ከአገር በቀል እውቀቶች ጋር ተያያዥነት ያለው መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ሰለሞን፣ የአገር በቀል እውቀቶች ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገትም ያላቸው አስተዋጽኦ በጣም ከፍተኛ ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን በባህል ህክምና ከሚደረጉ ውስን እንቅስቃሴዎች በስተቀር ጥቅም ላይ ሲውሉ አይታይም ይላሉ፡፡
እንደ ዶክተር ሰለሞን ገለጻ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችን በበላይነት መምራትና ማስተዳደር ኃላፊነት የተጣለበት ነው፡፡ ከእነዚህ ስልጣንና ተግባራት በተጨማሪ በአዋጅ 1097/11 ሳይንስን በአገር አቀፍ ደረጃ ማስተባበር ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ ሌላው ቀድሞ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሲመራ የነበረውን የከፍተኛ ተቋማትና የኢንዱስትሪ ትስስር የማስተባበር ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዘመናዊ የሳይንስና የምርምር ሥራዎች ማስተባበር ብቻ ሳይሆን አገር በቀል እውቀቶችን ጭምር በጥልቀት እየሰራበት ይገኛል፡፡ ከመዋቅሩ ጀምሮ የሳይንስ ባህል ግንባታ ዳሬክቶሬት ራሱን ችሎ ተዋቅሯል፡፡ በዚህ ዳይሬክቶሬት ስርም ከአገር በቀል እውቀት በተጨማሪ ሳይንስን መሠረት ይዞ እንዲወጣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሳይወሰን በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል ድረስ እንዲስፋፋ ሕፃናት፣ ወጣቶችና አዛውንቶች ግንዛቤ እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ ይህም ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሲደርሱ የተሻለ ልምድ እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ ስለዚህ የሳይንስ ባህል ግንባታ ዳይሬክቶሬት በአገር በቀል እውቀቶች ዙሪያ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ነግረውናል፡፡
ዶክተር ሰለሞን እንደሚሉት በአሁኑ ጊዜ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ቁጥራቸው 50 ደርሷል፡፡ በ50ዎቹ ላይ የአገር በቀል እውቀት ዙሪያ ምርምር አልተደረገም፤ ለትውልድ ለማስተላለፍ ሥራ እየተሰራም አይደለም፡፡ በጥቅል ሲታይ በአገራችን ውስጥ ያለው የካበተ አገር በቀል እውቀት አድጎ ለአገር ጠቀሜታ የሚውልበት መንገድ አልተመቻቸም፡፡ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተለይ አዲስ አበባ፣ጅማ፣ጎንደር፣መቐሌ፣ሀሮማያና ባህርዳር ዩኒቨርሲቲዎች በተናጠል አገር በቀል እውቀቶች ዙሪያ ምርምሮችን ያካሄዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ በሥርዓተ ትምህርት ተቀርጸው አዲሱ ትውልድ እንዲያውቃቸው በማድረግ ረገድ ግን ብዙም ተሰርቶበታል ብሎ ደፍሮ መናገር አይቻልም፤ ሲሉም ያለውን እጥረት ይገልጻሉ፡፡
የአገር በቀል እውቀቶች በተለይ በቤተ እምነቶች በጣም ይሰራባቸዋል፡፡ ከእምነት ውጪም አሁን ድረስ የሚሰሩ በርካታ የአገር በቀል እውቀቶች አሉ፡፡ የአገር በቀል እውቀቶች እንዲያድጉና እንዲስፋፉ ከተፈለገ የተለያዩ አማራጭ መንገዶችን መከትል ያስፈልጋል:: የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም የአገር በቀል እውቀት ለአገር ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ዕድገት ጠቀሜታ እንዳላቸው የማስተዋወቅ ሥራዎች ይሰራል፡፡ ለአብነት ያህል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር አገራዊ የአገር በቀል እውቀቶች የምክክር መድረክ በመጪው ጥቅምት ወር እንደሚያካሄድ ነግረውናል፡፡
በምክክር መድረኩም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና አመራሮች፣ አገር በቀል እውቀት ላይ የካበተ ልምድ ያላቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች የሚሳተፉበት ይሆናል፡፡ ይህም ዜጎች በአገር በቀል እውቀት ተጠቅመው ራሳቸውንና አገራቸውን የሚጠቅሙበት ሁኔታ ለመፍጠር ይረዳል፡፡ በሚኒስቴሩ አማካኝነት የዚህ ዓይነት የምክክር መድረኮችና ጉባኤዎች በቀጣይም የሚካሄዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እንዲሁም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለፈው ዓመት ሥርዓተ ትምህርት ከልሷል፡፡ የአገር በቀል እውቀቶች በተገቢው የትምህርት ክፍሎች ተካተው እንዲሰጡም አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡ ወደፊት በምርምር ተደግፈው የአገር በቀል እውቀቶች ከሚዛመዱት የትምህርት ዓይነት ጋር እንዲካተቱ ተደርጎ ለመስራት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡
በቤተ እምነቶች ያሉ የአገር በቀል እውቀቶችን ከምሁራን ጋር በቅርበት ተነጋግሮ እውቀቶቹን በማዘመንና ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ረገድ ሰፊ ክፍተት ይታያል የሚል የግል አስተያየት ያላቸው ዶክተር ሰለሞን የእውቀቶቹ ባለቤቶች የባለቤትነት መብት ስለሚያገኙ እውቀቱ ቢዘመን ምንም ሊያስጨንቃቸው እንደማይገባ ማስገዘብ ተገቢ ነው የሚል ሀሳብ አላቸው፡፡
አዲሱ ትውልድ የራሱን አገር፣ባህልና አገር በቀል እውቀቶች ማወቁ ብዙ ጥቅም አለው የሚሉት ዶክተር ሰለሞን ለምሳሌ አብዛኛው መድኃኒቶች ከውጭ የሚገቡ ናቸው ይላሉ፡፡ ነገር ግን አገር በቀል እውቀቶችን ተጠቅመን መድኃኒት እዚሁ ለማምረት ለመጪው ትውልድ እውቀቱ ማስተላለፉ ጠቀሜታ አለው፡፡ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች አገር ናት፡፡ በዓለም የብዝሀ ሕይወት ሀብት ከተለዩ ስምንት አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ አዲሱ ትውልድ አገር በቀል እውቀቶችን ተጠቅሞ ምርምር ቢያደርግ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት ይቻላል ባይ ናቸው፡፡
‹‹ሁልጊዜ የውጭ ከምንመለከት አገራችንስ ምን አለ ብለን ማተኮር አለብን የሚሉት ዶክተር ሰለሞን እነዚህ እውቀቶች የአገራችንን ገፅታ ለማስተዋወቅ፣ ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለሰላም ግንባታ ጠቀሜታ እንዲውሉ ማድረግ ለነገ የማይባል ሥራ ነው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሁሉም የአካባቢውን ባህላዊ እውቀት በትምህርት ሥርዓቱ አካቶ ለተማሪዎች ከማስተማር ይልቅ እንደ አገር አቀፍ የበለጠ ጠቀሜታ ያላቸው አገር በቀል እውቀቶች ጠቅለል ተደርገው በትምህርት ሥርዓት ተካተው ለተማሪዎች ቢሰጡ መልካም ነው የሚልም ምክረ ሀሳብ አላቸው፡፡
እንደ ዶክተር ሰለሞን አገላለፅ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ወጣቱ ብዙ ስለ አገሩ አያውቅም፡፡ ስለ አገሩም አይቆረቆርም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት በሥርዓተ ትምህርቱ አገር በቀል እውቀቶችን ባካተተ መልኩ አለመሰጠቱ ነው፡፡ አሁን አዲስ በተቀረጸው የትምህርት ሥርዓት እነዚህን ችግሮች ግምት ውስጥ በማስገባት ስለ ብዝሀነት ጠቀሜታ፣ ስለ አገርና አብሮ መኖር እሴቶች እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡
ምርምር ችግርን ለመፍታት የሚደረግ ሙከራ ነው፡፡ ሙከራ ለማድረግ እውቀት ያስፈልጋል፡፡ አገር በቀልና ዘመናዊ እውቀቶችን በምርምር አዳብሮ መስራት ይገባል፡፡ በተበጣጠሰና በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰራው ምርምር አገር ይቀይራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ በኢትዮጵያ ምርምር በፖሊሲ ደረጃ ይቀመጥ እንጂ ምርምር ምሁራን እየተመራ ከመንግሥት በጀት ብቻ ሳይጠብቅ ከውጭም ገንዘብ በማሰባሰብ የሚሰራበት ወጥ የሆነ የምርምር ሥርዓት አለመኖሩን ጠቅሰዋል፡፡
ስለዚህ ለአገር በቀል እውቀቶች ሆነ ለዘመናዊ የሳይንስ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት በአገር አቀፍ ደረጃ የምርምር ሥርዓት ዝርጋታ ያስፈልጋል፡፡ ልክ እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ ጀርመን ብሔራዊ የምርምር ካውንስል በማቋቋም የተጠናከረ ምርምር ማድረግ ይገባል ሲሉ ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡
በጀርመን አገር ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ጊሰን የትምህርት ፖሊሲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ኩከመ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት እንደ ደካማ ጎን የሚወሰደው ከሕዝቡ ባህል፣ ስነልቦና ብዝሃነት ጋር የተያያዘ አገር በቀል እውቀቶችን በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ አለመካተታቸው ነው፡፡ ቀደም ሲል ከሃይማኖት የመነጨ ግብረ ገብ የሚባል ትምህርት ይሰጥ የነበረ ቢሆንም በኋላ እንዲቀር ተደርጓል፡፡ ይህም የትምህርት ሥርዓት ቀረጻው አንዱ ድክመት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡
አገር በቀል አስተሳቦችና ዕውቀቶች ማለትም የባህል ህክምናዎች፣ ፍልስፍናዎች፣ ማህበራዊና ሥነ ልቦናዊ ሁኔታዎች የተካተቱበት ሥርዓት ትምህርት መስጠቱ በጣም ትልቅ ጠቀሜታ አለው የሚሉት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ልክ እንደ ገዳ ሁሉ ሌሎችም የአገረሰብ እውቀቶች በዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ተካተው ቢሰጡ ጥቅም አላቸው::: ለምሳሌ የኮንሶ የእርከን ሥራ በአካባቢ ጥበቃና ልማት ትምህርት ውስጥ ተካቶ ቢሰጥ በአገሪቱ ተጨባጭ ማሳያ ይሆናል ይላሉ፡፡ ይህም ተማሪው የራሱን አገር በቀል እውቀት ለማሳደግ ይቀለዋል፡፡ እነዚህን አገር በቀል እውቀቶች በሌሎች አካባቢዎች ለማስፋፋትና እንዳይጠፉ ለማድረግም ይረዳል ብለዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገለጻ የዩኒቨርሲቲዎች ዋና ሥራ እውቀት ማመንጨት፣ ማስተማርና ምርምር ማድረግ ነው፡፡ አገር በቀል የሆኑ እውቀቶችና ቴክኖሎጂዎች መሰብሰብና ማደራጀት ያስፈልጋል::: በምርምር ተቋማት አገር በቀል እውቀቶችና ቴክኖሎጂዎች በበቂ ደረጃና ጥልቀት ከተደራጁ በኋላ ከዓለም አቀፍ ተጨባጭ ሁኔታ በማያያዝ ለቀጣዩ ትውልድ መተላለፍ አለበት፡፡
በተለያዩ አካባቢዎችና ብሔረሰቦች ሌሎች አገር በቀል እውቀቶችና የአስተዳደር ሥርዓቶች አሉ፡፡ እነዚህን እውቀቶች እኩል ትኩረት ተሰጥቶቸው በተደራጀ መልኩ በአገር አቀፍ ደረጃ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ተካተው ቢሰጡ መልካም ነው ሲሉ ምክረ ሀሳባቸውን ሰጥተውናል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 19/2012
ጌትነት ምህረቴ